Saturday, 29 February 2020 10:46

ኢትዮ ቴሌኮም በብሮድባንድ ኢንተርኔት ላይ ማሻሻያ አደረገ

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(0 votes)

 - ማሻሻያው በፍጥነት ጭማሪ እና በታሪፍ ቅናሽ ቀርቧል
      - ለዚህ ፕሮጀክት 748 ሚሊዮን ከብድር ነፃ በጀት ወጥቷል
              
             ኢትዮ ቴሌኮም ብሮድባንድ ኢንተርኔት አገልግሎት ላይ የዋጋና የፍጥነት ማሻሻያ ማድረጉን ይፋ አደረገ፡፡ ተቋሙ ሀሙስ የካቲት 19 ቀን 2012 ዓ.ም ረፋድ ላይ በሸራተን ሆቴል ላሊበላ አዳራሽ አገልግሎት ሰጪዎች፣ ሆቴሎች፣ ባንኮች ሌሎች የፋይናንስ ተቋማት ተወካዮች በተገኙበት ይፋ ያደረገው ይሄው ማሻሻያ የብሮድ ባንድ ኢንተርኔትን ፍጥነት በሶስት በአራትና በስድስት እጥፍ ከማሳደጉም በተጨማሪ ከፍተኛ የታሪፍ ቅናሽ ማድረጉንም የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ሥራ አስፈጻሚ ወ/ሪት ፍሬ ሕይወት አድማሱ ገልፀዋል፡፡ ሶስት አመት የፈጀው ይሄው የማሻሻያ ትግበራ 748 ሚ.ብር በጀት የወጣበት ሲሆን ከዚህም ውስጥ 12.4 ሚ ዶላር በውጭ ምንዛሬ መክፈሉንና ገንዘቡ ከብድር ነፃ የሆነና ተቋሙ ራሱ ያመነጨው ስለመሆኑም ጨምረው ገልጸዋል፡፡
የፍጥነትና የታሪፍ ማሻሻያው ለንግድ ድርጅቶች፣ ለመኖሪያ ቤቶችና ለVPN ተጠቃሚዎች የቀረበ ሲሆን ለቪፒኤን 72 በመቶ፣ ለመኖሪያ ቤቶች 69 በመቶ እንዲሁም ለድርጅቶች 65 በመቶ የታሪፍ ቅናሽ መደረጉን ተናግረዋል፡፡
ቀደም ሲል ለመኖሪያ ቤቶች 512 KB በሰከንድ ይጠቀሙና 546 ብር ይከፍሉ ለነበሩ ተጠቃሚዎች በማሻሻያው ከ512 KB ወደ 1 ሜጋ ባይት በሰከንድ ሆኖ ክፍያውም ከ546 ወደ 499 ዝቅ ማለቱ ተገልጻል፡፡ ለVPN  ደግሞ አራት እጥፍ የፍጥነት ማሻሻያ የተደረገ ሲሆን ቀደም ሲል 6 ሜጋ ባይት በሰንድ ለመጠቀም 6 ሺህ 552 ክፍያ ይጠየቅ እንደነበረና አዲስ በተሻሻለው አሰራር ከ6 ሜጋ ባይት ወደ 27 ሜጋ ባይት በሰከንድ አድጎ ክፍያውም ቀደሞ ለ6 ሜጋ ባይት ይከፍሉ ከነበሩት 6 ሺህ 552 ብር ወደ 5 ሺህ 880 ብር ዝቅ ማለቱን የኢትዮ ቴሌኮም ዋና የገበያ መኮንን ለታዳሚው አስረድተዋል፡፡
ማሻሻያው በአዲስ አበባ፣ በክልልና በውጭ አገር የንግድ ቅርንጫፍ ለመክፈትና ስራን ለማሳለጥ ወሳኝ በመሆኑ እንዲሁም ደረጃውን የጠበቀ የኢንተርኔት አገልግሎት በአንድ አገር ኢኮኖሚ ላይ የሚሳርፈውን በጎ ተፅዕኖ በመገንዘብ ይህንን ኢንተርቬንሽን መውሰዳቸውን ዋና ሥራ አስፈጻሚዋ ተናግረዋል፡፡ ይህን የማሻሻያ ሥራ ‹‹ZTE›› ከተባለው የቻይና ኩባንያ ጋር ሲሰራ መቆየቱን የተናገሩት ወ/ሪት ፍሬ ሕይወት እስከ ዛሬ ሲያገለግሉ የነበሩ አሮጌ ዕቃዎችን ሙሉ በሙሉ በአዲስ በመተካት፣ በፍጥነት ማሻሻል፣ በታሪፍ ትመና ስራ ላይ ተቋማቸው ተጠምዶ መቆየቱንና ለዚህ ፍሬ መብቃቱን ተናግረው ለአገልግሎቱ ተጠቃሚዎችና አዲስ አገልግሎት እየጠየቁ ላሉ ደንበኞች እንኳን ደስ አላችሁ ብለዋል፡፡
የታሪፍ ቅናሹም ሆነ የፍጥነት ማሻሻያው ብዙ ጥናት የተደረገበትና ከሌሎች አገራት ተሞክሮ የተወሰደ ሲሆን ታሪፉም ቢሆን የአገራችንን ኢኮኖሚ፣ የዜጎችን የመክፈል አቅም፣ ኢኮኖሚውን ደግፈው የያዙ የንግድ ተቋማትን ሁኔታና ሌሎች ተዛማጅ ሁኔታዎችን ግምት ውስጥ ያስገባ መሆኑን የገለፁት ሥራ አስፈጻሚዋ፣ ይህ አገልግሎት ንግድን በማቀላጠፍ ግንኙነት በመፍጠር ኢኮኖሚውን እንደሚያሳድግና የአገራችን ዋነኛ ችግር የሆነውን ሥራ አጥነትም እንደሚቀንስ ጨምረው ገልጸዋል፡፡
ኢትዮ ቴሌኮም በተጨማሪም ‹‹Fiber to the home›› የተሰኘ በኮፐር ሲሰጥ የነበረውን አገልግሎት በፋይበር የማቅረብ ስራ፣ ‹‹Combo Offer›› የተሰኘ ድምፅና ኢንተርኔትን በአንድ ጊዜ አገልግሎት ላይ የሚያውል የ2 በ1 አገልግሎት እንዲሁም ‹‹Try and Buy ›› የተሰኘ ደንበኞች አገልግሎቱን አይተው ሞክረውና ተረድተው እንዲገዙ የሚያደርጉ አሰራሮችን ያቀረበ ሲሆን ሰርቪስ ሌቭል አግሪመንት (SLA) የተሰኘውም አገልግሎት ከሚያቀርባቸው አማራጮች አንዱ መሆኑ ተገልጿል፡፡
ቀደም ሲል ደንበኞች አገልግሎቱን ለመጠቀም ሲመጡ አገልግሎቱን ለማስጀመር ይከፈል የነበረው 280 ብር ክፍያ ቀርቶ ደንበኞች በነፃ ወደ አገልግሎቱ እንዲገቡ ከመደረጉም በተጨማሪ ለአገልግሎቱ ደንበኞች የግድ ወደ ሽያጭ ማዕከል መሄድ የነበረባቸው ሲሆን በአሁኑ ወቅት ተቋሙ በዘረጋው የኦን ላይን አገልግሎት ቢሯቸው ወይም መኖሪያ ቤታቸው ሆነው በተከፈተው ድረ ገፅ ኦንላይን አገልግሎቱን ማግኘት የሚያስችል አሰራር መዘርጋቱም ይፋ ሆኗል፡፡ ኢትዮ ቴሌኮም አሁን ባለበት ቁመና ከጎረቤት አጋራት አንጻር ደንበኞቹን ዝቅተኛ በማስከፈል ሰፊ አገልግሎት የሚሰጥ ተቋም መሆኑ የተገለፀ ሲሆን ውድ እያስከፈሉ ጥቂት ተጠቃሚ ከመያዝ ታሪፍን ቀነስ አድርጎ ብዙዎች የቴክኖሎጂው ተጠቃሚ እንዲሆኑ ማድረግ የማህበረሰቡን ኑሮ ከማሻሻልና ከማዘመን ባለፈ በአገር ኢኮኖሚ ላይ ለውጥ ማምጣት እንደሚቻል በማመን ታሪፍ መቀነሱን ወ/ሪት ፍሬ ሕይወት አብራርተዋል፡፡
ኢትዮ ቴሌኮም በቅርቡ ከፍተኛ የታሪፍ ቅናሽ ማድረጉ የሚታወስ ሲሆን የ4G እና የአድቫንስድ LTE የቴሌኮም አገልግሎት ለተጠቃሚ ማቅረቡንና በቀጣይ ወደ 5G እና ከዚያ በላይ ያሉ አገልግሎቶች ጊዜያቸውን ጠብቀው ለአገልግሎት እንደሚቀርቡም ተገልጿል። በዕለቱ ለታዳሚዎች የእጣ ኩፖን ተሰጥቶ ለ10 ባለ ዕድሎች ዘመናዊ ላፕቶፕ ለ10 እጣው ለወጣላቸው ደግሞ የኢንተርኔት ሞደም ሽልማት ተበርክቷል፡፡      

Read 1767 times