Monday, 24 February 2020 00:00

ኮሮና ቫይረስ በሳምንቱ

Written by 
Rate this item
(3 votes)

   ከዕለት ወደ ዕለት መስፋፋቱንና ብዙዎችን ተጠቂ ማድረጉን የቀጠለው ኮሮና ቫይረስ እስከ ትናንት በስቲያ ድረስ በመላው አለም ከ75 ሺህ በላይ ሰዎችን ማጥቃቱንና ለሞት መዳረጉን አለማቀፍ መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል፡፡
ወረርሽኙ በተቀሰቀሰባት ቻይና እስከ ትናንት በስቲያ ድረስ 74 ሺህ 185 ሰዎች በቫይረሱ ሲጠቁ፤ የሟቾች ቁጥር ደግሞ 2004 መድረሱ ተነግሯል፡፡ ኢራንና ግብጽ በሳምንቱ አዳዲስ የኮሮና ቫይረስ ተጠቂዎች የተገኙባቸው ሁለቱ የአለማችን አገራት ሲሆኑ በኢራን 2፣ በግብጽ ደግሞ 1 ሰው በቫይረሱ መያዙ ተረጋግጧል ሲል ሮይተርስ ዘግቧል፡፡ በደቡብ ኮርያ ባለፈው ረቡዕ ብቻ 20 አዳዲስ የቫይረሱ ተጠቂዎች መገኘታቸውን የጠቆመው ዘገባው፤ የተጠቂዎች ቁጥር ወደ 51 ከፍ ማለቱንም አመልክቷል፡፡ በሺህዎች የሚቆጠሩ መንገደኞችን አሳፍራ በጃፓን የባህር ዳርቻ ለቀናት ታፍና በቆየችው መርከብ ውስጥ የነበሩት 542 ሰዎች ቫይረሱ እንዳለባቸው የተረጋገጠ ሲሆን የሩስያ መንግስት ከትናንት በስቲያ ጀምሮ ቻይናውያን ወደ ግዛቱ እንዳይገቡ እገዳ መጣሉን የዘገበው ዘ ጋርዲያን፤ እገዳው እስከ መቼ እንደሚቆይ የታወቀ ነገር የለም ብሏል፡፡
የአሜሪካ የንግድ ምክር ቤት ሰራሁት ያለውን ጥናት ጠቅሶ ዘ ኢንዲፔንደንት እንደዘገበው ደግሞ፣ በቻይና ከሚገኙት የአሜሪካ ኩባንያዎች መካከል ግማሹ በኮሮና ቫይረስ ሳቢያ እንቅስቃሴያቸው በከፍተኛ ሁኔታ መገታቱን መግለጻቸውና 78 በመቶ የሚሆኑት ደግሞ የሰው ሃይል እጥረት እንደገጠማቸው መናገራቸው ተወስቷል፡፡

Read 23041 times