Saturday, 22 February 2020 11:51

የ90 ዓመቱ ፖለቲከኛ የሃገሬ ጉዳይ ያሳስበኛል ይላሉ

Written by  ሰላም ገረመው
Rate this item
(2 votes)

- ‹‹ዐቢይን የደገፍኩት መዝኜ አስተውዬ ነው››
 - ምርጫውን ለማካሄድ መጀመሪያ አንድ መሆን ይፈልጋል
 - ሕዝቡን ከፋፋይ ንግግር ከልሂቃኑ አይጠበቅም

              ከፖለቲካ ራሳቸውን አግለው በጡረታ ላይ የሚገኙት የቀድሞ የተቃዋሚ ፓርቲ መሪና የአዋሽ ባንክ መስራች አቶ ቡልቻ ደመቅሳ ሰሞኑን ድንገት በጠ/ሚኒስትሩ የድጋፍ ሰልፍ ላይ ተገኝተዋል፡፡ እንዴት? ለምን? ከጋዜጠኛ ሠላም ገረመው ጋር ተነጋግረዋል፡፡ እነሆ፡-



            በለገጣፎ የድጋፍ ሰልፍ ላይ የተገኙት እንዴት ነው?
እኔ በምኖርበት አካባቢ ማንም ስለ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ክፉ የሚያወራ የለም፡፡ ሁሉም ይወዷቸዋል፤ ያከብሯቸዋል፡፡ ይሄ ሁሌም ነው የሚገርመኝ፡፡
ዶ/ር ዐብይ ሀገር መምራት ከጀመሩ አንስቶ አይተናቸዋል፡፡ ብቃት አላቸው፤ እንዲመረጡም እንፈልጋለን፡፡ ለዚህ ነው የወጣነው፡፡ ሰልፉን ለማድረግ መጀመሪያ ላይ ትንሽ እንሆናለን ብዬ አስቤ ነበር፤ ነገር ግን ከመጠን ያለፈ ነው የሆነው፡፡
ይሄ ሠልፍ እንደውም ከዚህ በፊት መደረግ ነበረበት ባይ ነኝ፡፡ ዐቢይ እውነተኛ ሰው ነው፤ ይሄንን ስለማውቅ ነው ለመደገፍ የወጣሁት፡፡ እኔ በርካታ የፖለቲካ አመራሮችን አይቻለሁ፤ ለማንም የድጋፍ ሠልፍ ወጥቼ አላውቅም፤ መዝኜ አስተውዬ ነው የደገፍኩት፤ በጣም ቅን ሠው ነው፡፡
ጠ/ሚኒስትሩን አግኝተዋቸዋ ያውቃሉ?
ከዚህ ቀደም ተገናኝተን አውርተን ነበር፡፡ አንዳንድ ነገሮች ላይ ተወያይተን ምክር እፈልጋለሁ… ከእርስዎ ብለውኛል:: አንዳንድ ጊዜ የሚፈሉጓቸው ነገሮች ሲኖሩ… ይጠይቁኛል፤ መመለስ ያለብኝን እመልስላቸዋለሁ፡፡ በቅርብ ጊዜ ባይሆንም ተገናኝተን እናውቃለን፡፡
የአገሪቱን የፖለቲካ አካሄድ እንዴት ያዩታል?
በጣም አሳሳቢ ነው፡፡ እንደሚሰበር ዕቃ በጥንቃቄ መያዝ አለበት፡፡ ዋናው ያለመተዋወቅ ነው፡፡ አፄ ኃይለስላሴ ከልጅነታቸው ጀምሮ ይታወቃሉ፡፡ በእሳቸው ጊዜ ማን ማንን እንደሚክድ፣ ማን ማንን እንደሚያምን ይታወቃል፡፡ ከልጅ እያሱ ጋር ተናንቀው ግልፅ በሆነ የፖለቲካ ታክቲክ አሸንፈዋል፡፡ አፄ ኃይለስላሴ በብልጠት… በዕውቀት… ነገርን በመረዳት መውጫውን ቀድሞ በማወቅ ነበር ስልጣንን የያዙት፡፡ አሁን ያለው አካሄድ በጣም አደገኛ ነው፡፡ ወጣቱ በሚያውቀው ፖለቲካ ውስጥ እስካሁን ጠቢብ የሆነ፣ ሁሉንም የሚፈታ መሪ አልነበረም፡፡ ‹‹ይሄንን አደረኩ፤ አግባብቼ አስታረቅኩ፤ ይቅርታ አደረግሁ፤ ይሄንን ለአገር አበረከትኩ›› የሚል እንደ አፄ ኃለስላሴ አልነበረም፤ ስለዚህ  ሁሉም ይናናቃል፤መከባበር የለውም፤ ሌላው ቀርቶ “መንግስቱ እንኳን” ይላሉ ሰዎች  “መንግስቱ እንኳን ቆራጥ ሆኖ አገሩን አረጋጋ፤  በብዙዎች ተፈራ…” እያሉ ያወራሉ፡፡ ይሄ ማለት መግደል ጀግና ያስብላል፤ መግደል አገርን መምራት ቀላል ያደርጋል ማለት ነው፡፡ በርግጥ መንግስቱ አይፈሩም፤ ቆራጥ ነበሩ፡፡ በዚህ ምክንያት ግን መንግስቱን ፈርተው ብዙ ምሁራን ሸሽተው አገር ለቀው ተሰደዱ፤ ይሄ አገሪቱ የተማረ ሰው እንድታጣ አድርጓታል፡፡
ኢህአዴግ ደግሞ እውቀት የጎደለው አረማመድ ነበር የሚሄደው፡፡ የአፈና ፖለቲካ ውስጥ ገባ፡፡ ህዝቡም ምንም ተስፋ የሚሆን ነገር አጣ፡፡ ምኞት መመኘት ብቻ ሆነ፡፡ ዋጋ የተከፈለበት ነገር ሁሉ ሲጠፉ ህዝቡ ተስፋ እየቆረጠ መጣ፡፡ ለውጥ መጣልን ብለው በደርግ ጊዜ እንደተሰደዱት ሁሉ በኢህአዴግም ጊዜ መሰደድ ጀመሩ፡፡ ኢህአዴግም በገባው ቃል መሰረት መፈፀም ሲያቅተው ህዝቡን በመጫን በሃይል ማሳመን ፈለገ፡፡ ጫናው እየበዛ ሲመጣ ህዝቡም ተቃውሞውን መግለፅ ጀመረ፡፡ ይሄ ህዝብ ያየው በጭቆና መገዛትን ነው፤ በተለይ ወጣቱ፡፡ ስለዚህ አሁን የመጡት ጠ/ሚኒስትር “አልገልም፤ በመነጋገር ችግር እንፍታ” በማለት ከመግደል ይልቅ ይቅርታን፣ ከማሰር ይልቅ መፍታትን ሲያሳዩ ሃሳቡ በጣም ጥሩ ነበር፤ ግን አንዳንድ አመፅን የሚፈልጉ አካላት የሚያስነሱትን ብጥብጥ በፍቅር ሲያልፉና በይቅርታ ሲያሳልፉት ህዝቡ ያለመደው ነገር ስለሆነ ሊቃወም ይችላል፡፡ ዶ/ር ዐቢይ የውጪ ሃገር አመራርን ነው እያሳዩ ያሉት፡፡ ትክክለኛ ዲሞክራሲ የምንለው ማለት ነው፡፡ በርግጥ ለምን እንደማይገድሉ አውቃለሁ፤ ቢሆንም ዲሞክራሲን ሲናፍቅ የነበረ ህዝብ በአንድ ጊዜ ሲያየው ግራ ሊገባው ይችላል፡፡
ከውጪ ሃገራት ገንዘብ ለምኖ ሃገርን የሚታደግ መሪ እኛ ሃገር አልነበረም፡፡ ይሄንን ሁሉ አሁን እያየን ነው፡፡ ስለዚህ ዶ/ር ዐቢይ ሰው እንደሚወዳቸው ያወቁ አይመስለኝም፤ ሊያውቁ ይገባል፡፡ ይሄንን ማወቃቸው ምናአልባት ትንሽም ቢሆን ቆንጠጥ ያለ እርምጃ እንዲወስዱ ያደርጋቸዋል፡፡ እሳቸው የኃይል እርምጃ መውሰድ እንደማይፈልጉ አውቃለሁ ግን ማድረግ አለባቸው፡፡
ሌሎች አገራት ያሉት ወጣት አመራሮች ዴሞክራሲያዊ ፖለቲካ የሚያራምዱት ህዝቡ የለመደው ስለሆነ ነው፤ እሳቸው ያንን ለማምጣት መጀመሪያ ማስተማር ይጠበቅባቸዋል፡፡
የጠ/ሚኒስትሩ ድክመቶች የሚሉት ነገር አለ?
እሱማ ለሚቃወማቸው አሳልፎ መስጠት ማለት ነው:: መምከር ካለብኝም በግሌ እመክራቸዋለሁ፡፡
የአገሪቱን አለመረጋጋት እንዴት ያዩታል?
በጣም ያሳስበኛል፡፡ በተለይ እኔ ባደኩበት ወለጋ በጣም ከባድ ነገር ነው ያለው፡፡ እኔ ያልገባኝ ‹‹በእንደዚህ አይነት አካሄድ የት ይደረሳል? ብለው ነው አኩርፈው ቤታቸውን ዘግተው የተቀመጡት?›› ብዬ ወለጋዎቹን እጠይቃለሁ፡፡ መተባበር ከሌለ፣ ህዝብ ካልተባበረ ምንም ነገር አይረጋጋም፡፡
እኔን ብዙ ሰዎች ‹‹ያለመጠን በዲሞክራሲ ታምናለህ፤ ትደግፋለህ›› የሚሉኝ አሉ:: ጠ/ሚኒስትሩ እያሳዩ ያሉት ዲሞክራሲ ግን በእኔ ሃሳብ የበዛ ይመስለኛል፡፡  አፄ ቴዎድሮስ አንድ ልብ ነበራቸው፤ ወደ ኋላ የማይመለሱ ነበሩ፤ አፄ ኃይስላሴም በጣም ተወደው ነበር፤ ሁሉም ለጥ ብለው ነበር የተገዙላቸው፡፡ ቀስ ብለው ግን ኃይለኛ እየሆኑ መጡ፡፡ ከዛ ቀጥሎ የመጡትም መንግስቱ ይለውጣል ተብሎ ሲጠበቅ ሃይለኛ ሆኑ፡፡ ኢህአዴግም አትተንፍሱ እያለ ሃይሉን ያሳይ ነበር፡፡ እነዚህን ሁሉ አይተን አሁን በነፃነት ስንለቀቅ ይከብዳል፤ እሱን ማሰብ ያስፈልጋል፡፡
እኔ ግን በዋናነት የሚያሳስበኝ የአንድነት ጉዳይ ነው፡፡ የአማራና የኦሮሞ የቆየ ታሪክን ሊያበላሹ የሚፈልጉት ወገኖችን መስማት የለባቸውም፡፡ ከኦሮሞም ከአማራም የተማሩና ልምድ ያላቸው ሰዎች አሉ፤ እነሱን አነጋግሮ መፍትሄ ማበጀት በጣም ቀላል ነው፡፡ የእኛ ሃገር ጥል ብዙ ውስጥ የዘለቀ አይደለም፡፡ ምክንያቱም አማራ ላይ አንድ ችግር ቢከሰት ኦሮሞው ዝም ብሎ አይተኛም ይተባበራል፡፡ አማራውም እንደዛው፡፡ መቅደም ያለበት ሰላም ነው፤ ኩርፊያቸው ቀላል በመሆኑ በሚደመጡ ሰዎች ማስመከርና መመለስ ይቻላል፡፡
ሌላው የትግራይ ጉዳይ ነው፡፡ ትግራይ ስንል ህዝቡን ነው  እኔ የምለው፡፡ በስልጣን ላይ በነበሩ ጊዜ የነበራቸውን ሃይለኝነት ማውራት አይጠቅምም፤ እራስን ለይቶ ማየት የትም አያደርስም፡፡ ስለዚህ ማንም ማንንም ጥሎ ዝቅ አድርጎ አይቶ መኖር አይቻልም፡፡ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ አንዱን እራሱን ለይቶ መጓዝ አይቻልም:: እኔ ቀድሜ ስለ ፖለቲካ አውቃለሁና ብሎ መሄዱ አያዋጣውም፡፡ ምክንያቱም ሌሎቹም ዝም ብለው እንጂ የተሻሉ ብዙዎች አሉ፡፡ ለምሳሌ አማራ ውስጥ በጣም ቆራጦች አቅም ያላቸው ሰዎችን እያየን ነው:: እነዚህ ሰዎች ቀድመው ለምን አልወጡም? ለምን ለሃገራቸው አልተቆረቆሩም? ልንል አንችልም፤ ምክንያቱም ቀደም ሲል በነበረው ስርዓት ታፍነው ነበር፡፡ አሁን አንዱ አንዱን እያስተማረ፣ አብረው ነው መጓዝ ያለባቸው::
በአገሪቱ እየታየ የመጣው ዘረኝነት መነሻው ምንድነው ይላሉ?
ማንም ህፃን የለም፡፡ ሁሉም አዋቂ ነው:: ለምሳሌ ኦሮሞዎች ወደ ስልጣን ሲመጡ ለምን እንደ ህወሃቶች ይሆናሉ? ዘረኛ በመሆን ህወሃት ምን ተጠቀመ? ለብቻ መሆን ለማን ጠቀመ? ማንን አሳደገ? ይሄ በአገራችን ብዙ ውድቀቶች ሲያመጣ አይተናል፡፡ ዘረኝነት ከፍ አያደርግም፤ መነሻውን ሁሉም ያውቀዋል፡፡
ስለ ቀጣዩ ምርጫ ምን ያስባሉ?
ምርጫው ምንም  ትርፍ አያመጣም፤ መጀመሪያ መደረግ ያለበት የትግራይ ህዝብና አሁን ያለውን አመራር ማቀራረብ ነው፡፡ ሰዎች ናቸው፤ መልዐክ አይደሉም ያጠፋሉ፤ ይህንን ሊያምኑ ይገባል፡፡ አንድ የትግራይ አመራር አጠፋ ማለት ሁሉም የትግራይ ተወላጅ ጥፋተኛ ነው ማለት አይደለም፡፡ እራሳቸውን አሳምነው ለህዝቡ ሲሉ ወደ አንድ መምጣት መቻል አለባቸው፡፡ የሚጎዳው ህዝቡ ነው፤ ለህዝቡ ሊታዘንለት ይገባል፡፡ እኔ ሳስበው የትግራይ ማህበረሰብ አንድ መሆን ይፈልጋል፤ ገፍቶ የጠየቀው ስለሌለ እንጂ፡፡ ስለዚህ ይህንን ምርጫ ለማካሄድ መጀመሪያ አንድ መሆን ያስፈልጋል፤ የሚረብሹ ነገሮች መጥራት አለባቸው፡፡
የሀገሪቱ የፖለቲካ ልሂቃን ሲዘላለፉ ይታያሉ፡፡ እርስዎ ምን ይመክራሉ?
ሁሉም ቢመከሩ ይሰማሉ፤ አዋቂዎች ናቸው፡፡ ለተፈጠረው ችግር ምክንያቱ… ኦሮሞን ከፋፍለው፣ አማራን ከፋፍለው ማየታቸው ነው፡፡
የእኛ እኮ ችግር እንደ ሊቢያ እንደ ሶሪያ አይደለም፤ በጣም ቀላል ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ ዋናው ነገር ለህዝቦች የሚነገረው ጥሩ ሊሆን ይገባል፡፡ ለምሳሌ እኔ በጣም ካዘንኩባቸው ንግግሮች አንዱ፣ የጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ ንግግር ነው:: ‹‹አማራ የበላይነቱን ያድሳል›› ሲል ምን ማለት እንደሆነ አይገባኝም፡፡ አማራን እኮ በርካታ ጀግኖች አስተዳድረዋታል፡፡ ግን የማንንም ክብር አልነኩም፡፡

Read 2981 times