Saturday, 22 February 2020 11:30

በእስር ላይ የሚገኙት አቶ በረከት ስምኦን በጠና ታመዋል ተባለ

Written by  ሠላም ገረመው
Rate this item
(13 votes)

       “በፍጥነት ህክምና ካላገኘ ለህይወቱ ያሰጋዋል” - ባለቤታቸው
                               
            ላለፉት 27 ዓመታት በተለያዩ ከፍተኛ የመንግስት ሃላፊነቶች ላይ ያገለገሉትና በቅርቡ በሙስና ተከስሰው  የታሠሩት አቶ በረከት ስምኦን በጠና መታመማቸውን የተናገሩት ባለቤታቸው፤ አስፈላጊውን ህክምና ባለማግኘታቸው ቤተሰቡ በስጋት ላይ መሆኑን ገልጸል፡፡
ከዚህ ቀደም ከፍተኛ ህመም ገጥሟቸው ህክምናቸውን በደቡብ አፍሪካ መከታተል የጀመሩ ቢሆንም፤ ከጥረት ኮርፖሬት ጋር ተያይዞ በተጠረጠሩበት የሙስና ወንጀል በባህርዳር በመታሰራቸው ለቀዶ ህክምና የተሰጣቸው ቀጠሮ ማለፉን የጠቆሙት ባለቤታቸው ወ/ሮ አሲ ፈንቴ፤ጤንነታቸው በአሳሳቢ ደረጃ ላይ እንደሚገኝ ለአዲስ አድማስ ተናግረዋል፡፡
ከአንድ ዓመት በላይ በእስር የቆዩት አቶ በረከት መታመማቸውን የሰሙት ከሰው መሆኑን የገለፁት ወ/ሮ አሲ “ቤተሰቦቼን አላስጨንቅም” በሚል እንዳልነገራቸው ይገልፃሉ፡፡
ከአቶ በረከት ጉዳይ ጋር በተያያዘ ለጠ/ሚኒስትሩ ደብዳቤ ማስገባታቸውን ያስታወሱት ባለቤታቸው፤  “ጉዳዩ የክልል በመሆኑ ክልሉን አናግሩ፤ እኔ በሌላ የግል ጉዳያችሁ ላይ ችግር ከገጠማችሁ አግዛችኋለሁ” የሚል ምላሽ ከጠ/ሚኒስትሩ እንደተሰጣቸው ጠቁመዋል፡፡
ይሄን ተከትሎም ለአማራ ክልል ከፍተኛ አመራሮች አቶ በረከትን ጨምሮ ሌሎች አብረዋቸው የተከሰሱ ግለሰቦች በነፃ እንዲሰናበቱ  መጠየቃቸውን የሚናገሩት ወ/ሮ አሲ፤ የአመራሮቹ ውሳኔ ምን ሊሆን እንደሚችል መገመት አስቸጋሪ መሆኑን በጭንቀት ተሞልተው አስረድተዋል፡፡  
አቶ በረከት በፍጥነት አስቸኳይ ህክምና ካላገኙ ለህይወታቸው እንደሚያሰጋቸው የተናገሩት ወ/ሮ አሲ፤ ይህንን ጉዳይ ሁሉም በትኩረት ሊያየው የሚገባ ነው ብለዋል፡፡
አቶ በረከት ስምኦን ከጥረት ኮርፖሬት ጋር በተያያዘ “ምዝበራ ፈጽመዋል፣ ስልጣናቸውን አለአግባብ ተጠቅመዋል” በሚል በአማራ ክልል ክስ ተመስርቶባቸው ከታሰሩ ከአንድ ዓመት በላይ አልፏቸዋል፡፡

Read 16082 times