Saturday, 22 February 2020 10:54

ምርጫ 2012 190 ቀናት ቀረው

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(1 Vote)

   በሥራ ውጥረትና በጊዜ እጥረት የተከበበው ምርጫ ቦርድ

           - የምርጫ አስፈፃሚ ኤክስፐርቶችን ማግኘት አስቸጋሪ ነው
           - ህዝብን ለብጥብጥና ግጭት የሚዳርጉ የምርጫ ቅስቀሳዎች እንዴት ይታያሉ?
           - የምርጫ ቦርድ የምርጫ ማስፈፀሚያ ባጀት ምን ያህል ነው?
 
 ስም፡- ሶሊያና ሽመልስ ገ/ሚካኤል
የትውልድ ቦታ፡- አዲስ አበባ
ዕድሜ፡- 33
የጋብቻ ሁኔታ፡- ያላገባች
የትምህርት ዝግጅት፡- በሕግና ፖሊሲ ትምህርት 2ኛ ዲግሪና 3ኛ ዲግሪ ጀምረው ያቋረጡ
የሥራ ኃላፊነት፡- በኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ የኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር

        6ኛው አገር አቀፍና ጠቅላላ ምርጫ ሊካሄድ ወራት ብቻ ቀርተውታል፡፡ በአጭር ጊዜ ዝግጅት ሊካሄድ እንቅስቃሴ የተጀመረው የዘንድሮ ምርጫ ነሐሴ 23 ቀን 2012 ዓ.ም እንደሚደረግ የምርጫ ቦርድ የጊዜ ሰሌዳ ይጠቁማል፡፡ ምርጫው በአጭር ጊዜ ዝግጅት የሚካሄድ እንደመሆኑ ምን ተግዳሮቶች ሊገጥሙት ይችላል? የወጣው የጊዜ ሰሌዳ ጊዜያዊ ነው ወይስ የመጨረሻው የፖለቲካ ፓርቲዎች የቅስቀሳ ሁኔታ ምን ይመስላል? የቦርዱ የምርጫ ማስፈፀሚያ በጀት ምን ያህል ነው? ለፓርቲዎች የምርጫ ማስፈጸሚያ ምን ያህል በጅቷል? በሚሉትና ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ ናፍቆት ዮሴፍ፤ ከኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ የኮሚኒኬሽን ዳይሬክተር ከወይዘሪት ሶሊያና ሽመልስ ጋር ተከታዩን ቃለምልልስ አድርጋለች፡፡


              ለምርጫው እየተደረገ ያለው ዝግጅት ምን ይመስላል?
እንግዲህ ለምርጫው አቅም በፈቀደ መጠን እንቅስቃሴ እያደረግን ነው ቀኑም እየቀረበ ከመምጣቱ አንጻር የሚቻለው ሁሉ እየተደረገ ነው፡፡
ባለፈው ሳምንት ዝርዝር የጊዜ ሰሌዳ አውጥታችኋል፡፡ የጊዜ ሰሌዳው ጊዜያዊ ነው ወይስ የመጨረሻው?
የጊዜ ሰሌዳው የመጨረሻው ነው፡፡ ምክንያቱም ውይይትና ምክክር አድርገን፣ ግብአት ሰብስበን ያወጣነው የጊዜ ሰሌዳ ነው፤ የሚቀየር ሳይሆን የመጨረሻው ነው፡፡
ቦርዱ ካወጣው የጊዜ ሰሌዳ በፊት የምርጫ ቅስቀሳ የጀመሩ ፓርቲዎች እንዳሉ ይነገራል፡፡ ቦርዱ በዚህ ላይ ምን ይላል?
ከተፈቀደው ጊዜ በፊት ቅስቀሳ መጀመር ትክክል አይደለም፡፡ ነገር ግን አሁን ላይ ችግሩ ምንድን ነው? አንዳንድ ቦታዎች ላይ በምርጫ ቅስቀሳዎችና በውይይቶች መካከል ያለውን ልዩነት በመሀል ማስመር አስቸጋሪ ይሆናል:: ለምሳሌ የፖለቲካ ፓርቲዎች በማንኛውም ሁኔታ ከሕብረተሰቡ ጋር መገናኘት፣ ውይይት ማድረግ፣ ፖሊሲዎቻቸውን ማስተዋወቅና መነጋገር አለባቸው፡፡ ስለዚህ ይህን በሚያደርጉና የምርጫ ቅስቀሳ በሚያደርጉ ፓርቲዎች መካከል ያለው ልዩነት ምንድን ነው? የሚለውን ለመለየት መጤን ያለባቸው ጉዳዮች ምንድን ናቸው? የሚሉት መስፈርቶች በእኛ በኩል እየተሰራ ነው፡፡ ያ መመሪያ ከወጣ በኋላ ፓርቲዎቹ የሚያደርጉትን እየተከታተልን፣ የትኛው ነው ያችን መስመር ያለፈው? የሚለውን ለይተን እናውቃለን፡፡ ያንን ለይተን ካወቅን በኋላ በተለያየ ደረጃ ከነዚህ ፓርቲዎች ጋር ግንኙነት እናደርጋለን፡፡ ጠርተን የምንነጋገርበት ጊዜ ይኖራል፣ አንዳንድ ጊዜ እንዲህ አይነት ነገር ትክክል አይደለም ብለን የመመሪያ አቅጣጫ የምንሰጥበት ጊዜ አለ:: አስፈላጊ ሲሆን በጽሑፍ የምናሳውቅበት ሁኔታ ይኖራል፡፡ በጣም አስፈላጊ ሲሆን መግለጫ እናወጣለን፡፡ ይህ እንግዲህ በየደረጃው ግንኙነቱን እንደየ ሁኔታው እየፈጠርን እናስኬደዋለን ብለን ነው የምናስበው፡፡ ይህ እንግዲህ በማህበረሰቡ ውስጥ የሚፈጥረው ውዥንብር ካለ ማለቴ ነው፡፡ እኛ ግን ከዚያ በፊት እያደረግነው ያለነው ዝግጅት ምንድን ነው… የምረጡኝ ዘመቻን የሚመለከተውን መመሪያችንን ስንሰራ፣ የምረጡኝ ዘመቻ በአጠቃላይ በሕጉ ውስጥ በጉልህ እንደሚታየው ጊዜው ሲደርስ ነው መደረግ ያለበት:: ነገር ግን የምረጡኝ ቅስቀሳና የፖለቲካ ፓርቲዎች ከሕዝብ ጋር የሚያደርጓቸው ሌሎች ውይይቶች ልዩነታቸው ምንድን ነው? አንዳንድ ፓርቲዎች በየትኛውስ ጊዜ የምረጡኝ ዘመቻ ብንጀምር ብለው ሊከራከሩ ይችላሉ፡፡ ለምን ከተፈቀደው ጊዜ በፊት መጀመር እንደማይቻልና ስለ አላማው፣ ስለ ምረጡኝ ቅስቀሳና ከሕዝቡ ጋር ስለ ሚደረግ ውይይት የልዩነቱን መስመር ለየት አድርገን ካስቀመጥን በኋላ በቅርቡ የምናሳውቅበት ሁኔታ ይኖራል:: ቅድም እንዳልኩሽ፤ በተለያየ ደረጃ ከፖለቲካ ፓርቲዎቹ ጋር ንግግር እያደረግን በአጠቃላይ የመጫወቻ ሜዳው እንዳይዛነፍ ለማድረግ እንጥራለን፡፡
የፖለቲካ ፓርቲዎች በሕዝባዊ ስብሰባዎችና በቅስቀሳ ወቅት ሕዝቡን የሚያጋጭ፣ ብሄርን ከብሄር የሚያቃርን የጥላቻ ንግግርና ረብሻ የሚያስነሱ ቅስቀሳዎችን እንዳያደርጉ ቦርዱ ምን ዓይነት ቅድመ ጥንቃቄና ማስጠንቀቂያ አስቀምጧል?
በነገራችን ላይ በሕግም ክልክል ነው:: በወንጀል ሕጉ ላይ በግልጽ ተቀምጧል፡፡ የምርጫ ሕጉንም ብንመለከት፣ ማንኛውም የፖለቲካ ፓርቲ ቅስቀሳ በሚያደርግበት ወቅት ጥቃትን፣ የሀይል እርምጃን እንዳይጠቀም፣ ግጭት የሚያስነሱ ነገሮችን እንዳያደርግ፣ በማህበራዊ አመጣጥ፣ በብሄር፣ በፆታና በመሳሰሉት ጉዳዮች ግጭት የሚፈጥር ሁኔታ ውስጥ እንዳይገባ ክልከላ አለ፡፡ ይሄ በምርጫ ሕጉም ብቻ ሳይሆን በወንጀለኛ መቅጫውም በግልጽ የተቀመጠ ጉዳይ ነው፡፡ የፖለቲካ ፓርቲዎች ስለሆኑና በምርጫ ሕጉ ስለሚገዙም ብቻ ሳይሆን እንደ ማንኛውም ሰው በወንጀል ሕጉም ስለሚገዙ በሁለቱም በኩል ይመለከታቸዋል፤ ስለዚህ በዚህ በኩል ከፍተኛ ጥንቃቄ እንዲያደርጉ እኛም ከወዲሁ እናስገነዝባለን:: ግዴታቸውም ነው፡፡ በእርግጥ ቦርዱ የፖለቲካ ፓርቲዎች ላይ በሕጉ መሰረት አይቶና ገምግሞ በትክክልም ተረድቶ እነዚህ ጉዳዮች ወደ ግጭት የሚያመሩ ከሆነ የሚወስደው እርምጃ አለ፡፡ ከዚያ ውጭም ደግሞ ይመለከተኛል የሚል ማንኛውም የማህበረሰብ አካል ወደ ሕግ ሊወስደው የሚችለው ጉዳይ ነው፡፡ በአጠቃላይ ጉዳዩ ከቦርዱና ከፓርቲዎቹ ጋር ብቻ የተገናኘ ጉዳይ አይደለም ለማለት ነው፡፡ ጉዳዩ ከተፈፀመ እንደ ማንኛውም የሕግ ጥሰት በግለሰቦቹ፣  ባስተባበሩትና በተሳተፉት ላይ እርምጃ ይወሰዳል። ነገር ግን ቦርዱ በተጨማሪ ሊያደርገው የሚችለው የፖለቲካ ፓርቲዎችን ስለሚያስተዳድር በፓርቲዎች በኩል እንዲህ አይነት ችግሮች ከተመለከተ የማስተካከያ እርምጃ ያደርጋል፡፡
ምርጫ በተፈጥሮውም መካረርና ውድድር ስላለው በውድድሩ የተነሳ ምናልባት እንዲህ አይነት ነገሮች ከተፈጠሩ የማስተካከያ እርምጃ እንወስዳለን፡፡ በተለይ የምርጫ ዘመቻው ሲጀመር የአቅም ዝግጅት ያስፈልጋል፣ ሚዲያውን ሞኒተር ማድረግ የግድ ነው። እያንዳንዳቸውን ንግግሮች መከታተል ወሳኝ ነው፡፡ በህግ ባለሙያና በስነ ሥርዓት በደንብ አይቶ ጉዳዩን ማጤን ያስፈልጋል ምክንያቱም እንደ ማፈኛ መንገድም እንዳይሆን ማለቴ ነው፡፡ አንድ የፖለቲካ ፓርቲ ቅስቀሳ ባደረገ ቁጥር  “በህገወጥ መንገድ ቅስቀሳ አድርገሃል” የሚል አፈናና ጫና እንዳይደርስበት በህግ ባለሙያም በኩል እየፈተሽን፣ ሚዲያውን እየተከታተልን ግብአት የምንሰጠው ነገር ይኖራል፡፡ በአጠቃላይ ቀደም ብዬ እንደገለጽኩት፤ ለግጭት የሚዳርጉ ሁኔታዎችን የሚፈጥሩ የፖለቲካ ፓርቲዎችና አመራሮቻቸው የሚቀጡት በምርጫ ህጉ ብቻ ሳይሆን በወንጀል ህጉም መሆኑን ልብ ሊሉት ይገባል፡፡
የምርጫው የዝግጅት ጊዜ በጣም አጭር መሆኑ ግልጽ ነው፡፡ ቦርዱም የሲዳማን የክልልነት ጥያቄ መመለስን ጨምሮ በበርካታ ስራዎች ተጠምዶ ቆይቷል፡፡ የጊዜ ሰሌዳውን እስካወጣችሁበት የገጠማችሁ ተግዳሮቶች ምንድን ናቸው? እስከ ምርጫው ፍፃሜ ይገጥመናል የምትሏቸው ተግዳሮቶችስ ምን ሊሆኑ ይችላሉ?
በጣም ብዙ ተግዳሮቶች ናቸው ያሉብን:: ይሄ ምንም ጥያቄ የለውም፡፡ አንዱና ዋነኛው ችግራችን፤ የድርጅታዊ አቅም ማነስ ነው:: እኛ አሁን ላይ ያለን አቅምና ልንሰራ የምንፈልገው የጥራት ደረጃ ክፍተት አለው:: በድርጅታዊ አቅም የሰው ሃይል እጥረት ያስቸግረናል፡፡
እርግጥ ድርጅታዊ አቅም በአንዴ አይደለም የሚገነባው፡፡ እኛ እናከናውናለን ብለን ባሰብነው የምርጫ ጥራትና ድርጅታችን ባለው የሰራተኞቻችን አቅምና መሰል ጉዳዮች ችግር አለብን፡፡ ይህ እስካሁን የነበረብን ችግር ነው፡፡ ወደፊትም ከፍተኛ ችግር ሆኖ ሊቀጥል ይችላል፡፡ ምርጫው ክረምት ላይ መካሄዱ ሌላው ተግዳሮት ይሆናል፡፡ ምክንያቱም የምርጫ ማስፈፀሚያ እቃዎችን ከቦታ ቦታ ማንቀሳቀስና በሰዓቱ የሚፈለገው ቦታ ላይ ማድረስ ይኖርብናል:: ይህን ለማድረግ መንገዶች አስቸጋሪ ይሆናሉ:: በአጠቃላይ ከመራጩ ይልቅ ጫናው እኛ ላይ ይወድቃል፡፡ ይሄ ሁለተኛው ዋና ችግራችን ነው፡፡
በሰው ሃይልና በባለሙያ እጥረት ያለባችሁን ድርጅታዊ ክፍተት ለመሙላት እስከ ምርጫው ድረስ ምን ያህል ዝግጅት ታደርጋላችሁ? በጀትን በተመለከተ ከአሜሪካና ከሌሎች ዓለም አቀፍ ተቋማት ድጋፍ እያገኛችሁ እንደሆነ እየሰማን ነው፡፡ ይህን በተመለከተ ቢያብራሩልኝ?
የገንዘብ ድጋፎች መኖራቸው እውነት ነው አሉ፡፡ ዋና ዋናዎቹ የታወቁ ናቸው፡፡ ከአሜሪካ መንግስትና ከአውሮፓ ህብረት የምናገኘው የገንዘብ ድጋፍ አለ፡፡ ከተባበሩት መንግስታት የልማት ድርጅትም (UNDP) እንዲሁ እናገኛለን፡፡ ከዩኤስ አይዲም የምናገኘው አለ፡፡ የልማት ፕሮግራሙ ከተለያዩ አገራት የሚገኘውን ገንዘብ ሰብስቦ የሚያስተዳድረው አለ፡፡ አገራት በተናጠል ለቦርዱ ገንዘብ እንዳይሰጡ፣ አንድ ቋት ውስጥ ከትቶ ያስተዳድራል፡፡ ለምሳሌ እነ ስውዲን፣ ጃፓን፣ ኖርዌይ የመሳሰሉት አገራት በተናጠል እየመጡ ከሚሰጡ አንድ ቦታ ላይ ወስደው ድጋፉን ይሰጡና ዩኤንዲፒ ያሰባጥረዋል ማለት ነው፡፡
በአጠቃላይ የአሜሪካ መንግስት፣ የአሜሪካ የልማት ድርጅት/ዩኤስኤይድ/ እና አውሮፓ ህብረት ግን ዋና ዋና የገንዘብ ድጋፍ ሰጪዎች ናቸው፡፡ አንዳንዴ የቴክኒክ ድጋፍም ይሰጣሉ፡፡ ዞሮ ዞሮ ገንዘብም ቢመጣ፣ የማስፈፀም አቅምን ማጐልበትና የሰው ሃይል ማሰልጠን ያስፈልጋል፡፡ ከምርጫው ጋር በተገናኘ ኤክስፐርቶችን ኢትዮጵያ ውስጥ ማግኘት አስቸጋሪ ነው:: ቦርዱ ውስጥ ቆይተው የሰሩት ጥቂቶች ናቸው፡፡ ቦታው ብዙ ሰራተኛ ቶሎ ቶሎ የሚለቅበት ስለሆነ እዚህ የቆዩትም ሰራተኞቻችን የአቅም ችግር አለባቸው፡፡ ስለዚህ ይህ ሁሉ ክፍተት ባለበት ሁኔታ፣ የገንዘብ ድጋፉ ቢኖርም ማስፈፀሙ ላይ ችግሮች ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ ድርጅታዊ ለውጥ እየተሰራ የሚቀየር ነገርም አለ፡፡
ይሄ በአንድ በኩል ክፍተት ይፈጥራል፡፡ ለምሳሌ የምርጫ ቦርድ አባላት ዘግይተው ነው የተመረጡት፡፡ የምርጫው ወደ ክረምት መገፋትም አንዱ ምክንያት የነዚህ የቦርድ አባላት በጊዜ አለመመረጥ ነው፡፡ ከነሱ ቀጥሎ ሌሎች ሰራተኞችን ማደራጀት ጀምሯል:: ነገር ግን ከዚሁ ጐን ለጐን የምርጫ ዝግጅቱንም አብሮ ማስኬድ ያስፈልጋል:: ሁለቱን በአጭር ጊዜ ጐን ለጐን ማስኬድ ደግሞ አስቸጋሪ ነው የሚሆነው፡፡  
ከተቋማቱ የሚገኘው ገንዘብ የሰው ሃይል እጥረቱን ፣የኤክስፐርቶችን ስልጠናና ሌሎች ክፍተቶችን ለመሙላት አያግዝም?
ያግዛል እንጂ ምንም ጥያቄ የለውም:: እንደነዚህ አይነት ድጋፎች ባይኖሩ ኖሮ፣ የምንፈልገውን የጥራት ደረጃ እንኳን ላናሟላ እንችላለን፡፡ ነገር ግን ድጋፉ አለ ማለት መቶ በመቶ እንከን የለሽ ይሆናል ማለት አይደለም፡፡ የገንዘብም የቴክኒክም ድጋፍ ኖሮ እንኳን ተግዳሮችም አይቀሩም ለማለት ነው፡፡
የቀድሞውን የምርጫ ቦርድና የአሁኑን አነፃፅረው ይንገሩኝ…
ይሄንን በተደጋጋሚ ገልፀነዋል፡፡ በጥናት ልታሟሉት ትችላላችሁ፡፡ በህግ መዋቅሩ፣ በቦርድ አደረጃጀቱ፣ ሌላው ቀርቶ በበጀቱ መጠን የተለየ ነው፡፡ ያ ሁሉ በጀት ለምን ተጨመረ የሚለውንም ገልፀናል፡፡ ስለዚህ መለስ ብላችሁ የገለጽነውን ነገር ብታጠኑ መልሱን ልታገኙት ትችላላችሁ፡፡
ለፓለቲካ ፓርቲዎች የምርጫ ማስፈፀሚያ የተመደበውን በጀት ማወቅ ይቻላል?
በጀቱን አሁን አላውቀውም፡፡ ወደፊት አረጋግጬ ብነግርሽ የተሻለ ነው በተጨባጭ አምና ምንም የገንዘብ ድጋፍ አልሰጠንም:: ለድጋፍ ተብሎ የተሰጠውንም ገንዘብ መልሰናል፡፡ ምክንያቱም ፓርቲዎቹም ጋ የነበረው መስፈርት ትክክል አልነበረም፤ የቀደመውም አሰራር ችግር ስለነበረበት ምንም አይነት ድጋፍ አናደርግም ብለን በጀቱን ለገንዘብ ሚኒስቴር መልሰናል:: ዘንድሮ ገንዘቡ ለፓርቲዎች ይሰጣል አይሰጥም? የሚገኘው ድጋፍ ምን ያህል ነው? በምን መስፈርት ነው የሚሰጠው? የሚለው ጉዳይ የራሱ መመሪያ እየተሰራለት ነው፡፡ በዚያ ላይ ደግሞ ገንዘቡን በተጨባጭ ከመንግሥት አግኝተናል ወይ የሚለውን ነገር እርግጠኛ አይደለሁምና ማረጋገጥ ይኖግብኛል፡፡ አሁን መግለጽ አልችልም፡፡

Read 1299 times Last modified on Saturday, 22 February 2020 13:15