Saturday, 22 February 2020 09:51

ተቃዋሚነት የሰለቻቸው ፖለቲከኛ ምን ይላሉ? - ምናባዊ ቃለምልልስ

Written by  ኤሊያስ
Rate this item
(6 votes)

- ‹‹ለፖለቲከኞች ሥልጣን ድምፅ እንጂ ሕይወት አይሰጥም››
     - “በውጭ የታሰሩ ዜጐችን ማስፈታት የምርጫ ቅስቀሳ ነው
      
          ”ጠ/ሚኒስትሩ ባለፈው ሳምንት ወደ ተባበሩት አረብ ኢምሬትስ ተጉዘው እዚያ ለሚገኙ ዜጐች ያከናወኗቸውን በጐ ተግባራት እንዴት አገኙት?
ተጉዘው ነበር እንዴ? (እየቀለዱ!) እኔ ስልጤ ሄደው ህገወጥ የምርጫ ቅስቀሳ ማድረጋቸውን ነው የማውቀው፡፡ ለነገሩ ሁሌም ወደ ዱባይ የሚያደርጉትን ጉዞ እኔ እንደ ቫኬሽን ነው የምቆጥረው፡፡ ልዑሉ እኮ የጠ/ሚኒስትሩ ወዳጅ ናቸው፡፡ የሰላም ኖቤል የተሸለሙ ጊዜ የዱባይ ሕንጻዎች እኮ በጠ/ሚኒስትሩ ፎቶዎች አሸብርቀው ነበር:: የአረብ ኢምሬትስ ጠ/ሚኒስትር ኖቤሉን የተሸለሙ ነበር የሚመስለው:: የሁለቱ መሪዎች ግንኙነት ከፕሮቶኮል ውጭ ነው፡፡
ግን እኮ ለቫኬሽን ሳይሆን ለሥራ ነው የተጓዙት፡፡ ብዙ ለዜጐች የሚጠቅሙ ተግባራትንም አከናውነዋል…
በአውሮፕላን ያመጧቸው “ስደተኛ ኢትዮጵያውያን” እንዳሉ ሰምቼአለሁ፡፡ ይሄ ደግሞ የጠ/ሚኒስትሩ ሆቢ እንደሆነ ነው የማውቀው፡፡ እንዲያም ሆኖ ተቃውሞ የለኝም፡፡ ነገር ግን በየአገሩ እየዞሩ  ኢትዮጵያውያንን ከእስር ማስፈታት የጠ/ሚኒስትሩ ሥራ አይመስለኝም፡፡ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የማንን ጐፈሬ ያበጥራል? በዚያ ላይ የአገሪቱ አንገብጋቢ ጉዳይ… እስረኛ ማስፈታት ነው ወይ? ብለን መጠየቅም አለብን፡፡ ሰዎች በገዛ አገራቸው እየተፈናቀሉና እየታገቱ፣ ባህር ማዶ እየሄዱ የታሰሩት ዜጎችን ማስፈታት ቀልድ ነው የሚመስለኝ፡፡ ልብ በል! ለምን በባዕድ አገር የታሰሩ ዜጎች ተፈቱ እያልኩ አይደለም:: ከዚያ መቅደም የነበረበት የአገር ውስጥ የቤት ሥራ መኖሩን እየገለጽኩ ነው፡፡
ግን እኮ ጠ/ሚኒስትሩ በመካከለኛው ምሥራቅ በስደት ከሚኖሩ በ10 ሺዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን ጋር ተገናኝተው ተወያይተዋል፡፡ የመኖሪያና የሥራ ፈቃድ ለሌላቸው እንዲያገኙ አድርገዋል፡፡ በዱባይ በሚገነባው ኤክስፖ 2020 ላይ 10 ሺ ዜጎች የሥራ ዕድል የሚያገኙበትን ሁኔታ አመቻችተዋል፡፡ በቀጣይነትም 50ሺ የሚደርሱ ኢትዮጵያውያን በተባበሩት አረብ ኢምሬትስ በሹፌርነትና ሌሎች ሙያዎች ተቀጥረው እንዲሰሩ ከአገሪቱ መንግሥት ጋር ስምምነት ላይ ደርሰዋል። ይህ መቼም ትልቅ ስኬት ይመስለኛል፡፡ አይደለም እንዴ? (ከእርስዎ ባላውቅም!)
ሚዲያዎች መቼም ለመጣው ሁሉ ማጨብጨብ ትወዳላችሁ፡፡ ለዚህ ነው እንጂ ይሄ ትልቅ ስኬት ተብሎ የሚንቆለጳጰስ አይደለም፡፡ እኔ እንደ ፖለቲከኛ ጉዳዩን በጥያቄና በጥርጣሬ ነው የምመለከተው፡፡ አረቦቹ ይህን ሁሉ ውለታ የሚያደርጉልን በምን ምክንያት ነው? ብዬ እጠይቃለሁ:: እነሱም ቃል የተገባላቸው ነገር ለምሳሌ በኛ መንግሥት በኩል ማለቴ ነው፡፡ በነገራችን ላይ ጠ/ሚኒስትሩ በየሄዱበት አገር የታሰሩ ኢትዮጵያውያንን በአንዲት ቀን  እያስፈቱ በራሳቸው አውሮፕላን አሳፍረው መምጣታቸው አጃኢብ የሚያሰኝ ነው:: አገራቱ ወንጀለኛ ብለው ያሰሯቸውን እንደዘበት እየፈቱ የሚሰጧቸው ጠ/ሚኒስትሩ ማጂክ ይሰራሉ እንዴ? ይሄን ጉዳይ ኢንቨስቲጌት ለማድረግ ስፖንሰር እያፈላለግሁ ነው፡፡ በምን ስምምነት ታሳሪዎችን እያስፈቱ እንደሚያመጡ ማን ያውቃል? ሰውየው እኮ ኢሕአዴግ ናቸው፡፡
ኢሕአዴግ እኮ አሁን የለም፡፡ በምርጫ ቦርድ ህጋዊ ሰውነቱን አጥቷል፡፡ አሁን ያለው ብልፅግና ፓርቲና ጠ/ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አህመድ ናቸው…ተሳሳትኩ?
ምን ትላለህ?!  እሳቸውም ፓርቲውም የኢሕአዴግ ውላጆች አይደሉም እንዴ?! ፓርቲው ስሙን ስለቀየረ ብቻ ባህርይውንም ይቀይራል ማለት አይደለም፡፡ ስሙ ብልጽግና ይሁን እንጂ ባህርይው አሁንም የኢሕአዴግ ነው፡፡
ይሁንልዎት…ፓርቲያችሁ በጠ/ሚኒስትሩ የደቡብ አፍሪካ ጉብኝትም ላይ ተመሳሳይ አቋም ነው ያለው?
በትክክል! እኔ እንደውም በግሌ የማምነው፤ ጠ/ሚኒስትሩ በቅርቡ ያደረጓቸው የባህር ማዶ ጉብኝቶች ሁሉ፣ ብልጽግና ፓርቲን ለማስተዋወቅና ደጋፊን ለማበራከት የታለሙ ናቸው፡፡ በሌላ አነጋገር፤ እኛ እዚህ አገር በምርጫ ቦርድ የተከለከለውን የምርጫ ቅስቀሳ፣ እሳቸው በአፍሪካና መካከለኛው ምሥራቅ ሳይቀር ሲያጧጡፉት ነው የከረሙት፡፡ ባለፈው ሳምንት ደግሞ በስልጤ ዞን ከ60ሺ ነዋሪዎች ጋር ተወያይተዋል፡፡ የምርጫ ቅስቀሳ ነው፡፡ አልቀበለውም፡፡
የምርጫ ቅስቀሳ ገደቡ በኢትዮጵያ ብቻ አይደለም እንዴ የሚሰራው?
ኢትዮጵያውያን ባሉበት ሁሉ ይሰራል!
እንዴት? የምርጫ ቦርድ ሕግ እንደዚያ ይላል?
ሕጉ ባይልም… በባህር ማዶ የሚደረገው ቅስቀሳ፣ በዚህ አገር መራጮች ላይ ጉልህ ተጽዕኖ የማሳረፍ አቅም አለው ብዬ አምናለሁ፡፡ ጠ/ሚኒስትሩም ይሄ ገብቷቸዋል:: ውጤትም እያመጣላቸው ነው:: እሳቸው በመካከለኛው ምስራቅ ሲቀሰቅሱ፣ እዚህ ከተለያዩ የኦሮምያ አካባቢዎች “ዐቢይ ዓይናችን ነው፤ አትንኩብን!” የሚል ህዝባዊ ድጋፍ ሲደረግላቸው ነው የሰነበተው፡፡ ሰውየው የዋዛ አይደሉም፡፡
ፓርቲያችሁ በምርጫ አሸንፎ ሥልጣን ቢይዝ ምን ዓይነት የኢኮኖሚ ፖሊሲ ነው የምታራምዱት?
የኢኮኖሚ ፖሊሲያችንን የምንገልጸው የምርጫ ቅስቀሳው ሲጀመር ነው:: የኛ ፖሊሲ የዚህችን አገር የኢኮኖሚ ችግር ለመፍታት ብቸኛ አማራጭ ነው፡፡ “ማባዛት” የሚል ስያሜ ሰጥተነዋል፡፡ በማንም ያልተሞከረ ኦሪጂናል የኢኮኖሚ ፖሊሲ ነው የቀረፅነው፡፡ ግን ልንሰረቅ እንችላለን የሚል ፍራቻ አለን:: ስለዚህ አሁን ልንገርህ አልችልም። በአንድ ነገር ግን ከድሮው ኢሕአዴግም ሆነ ከአዲሱ ብልጽግና ፓርቲ እንለያለን፡፡ እኛትላልቅ የመንግሥት የልማት ድርጅቶችን ለውጭ ኢንቨስተሮች ፈጽሞ አንሸጥም፡፡ በተለይ አየር መንገዳችንን ከአድዋ ድል ለይተን አናየውም፡፡ የነፃነታችን አርማ አድርገን ነው የምንቆጥረው። አየር መንገድን በከፊልም ቢሆን ፕራይቬታይዝ ማድረግ፣ ነፃነታችንን ፕራይቬታይዝ እንደማድረግ ነው የምንቆጥረው፡፡
በምርጫው ማን የሚያሸንፍ ይመስልዎታል?
ይሄን ጥያቄ ከእኔ ይልቅ ለሕዝባችን ብታቀርብለት እቅጯን ይነግርህ ነበር፡፡
የትኛው ሕዝባችሁ? ደጋፊዎቻችሁን ማለትዎ ነው?
ላለፉት 28 ዓመታት የታገልንለትና የተሰዋንለት ሕዝባችንን ነዋ! ከሰሜን እስከ ምዕራብ፤ ከምስራቅ እስከ ደቡብ ያለውን ህዝባችንን ማለቴ ነው፡፡
የጠ/ሚኒስትሩ ብልጽግና ፓርቲ በምርጫው ያሸንፋል ብላችሁ አትሰጉም?
ብልጽግና እኮ የራሱን ዕድሜ ጨርሶ በሌሎቻችን ዕድሜ እየኖረ የሚገኝ ይሉኝታ ቢስ ፓርቲ ነው፡፡ 28 ዓመት ሙሉ በኢሕአዴግ ስም በስልጣን ላይ ከቆየ በኋላ አሁን ስሙን ቀይሮ ደግሞ ለሌላ የስልጣን ዘመን እየተዘጋጀ ነው፡፡ እንደኔ ቢሆን ከምርጫው መገለል ያለበት ፓርቲ ነው፡፡
ለምን? በየትኛው ሕግ ነው የሚገለለው?
ኢሕአዴግ እኮ በሕግ አይደለም ሥልጣን ላይ የቆየው፡፡ በሀይል ነው፤ በጠብመንጃ፡፡
እናንተም ያንኑ ልትደግሙት ነው ታዲያ…? ለምን ውሳኔውን ለሕዝብ አትተውለትም?… ሕዝብ ያሻውን ይምረጥ…
ለነገሩ ነፃ፣ ፍትሃዊና  ዴሞክራሲያዊ ምርጫ ከተካሄደ… ብልጽግና ሊያሸንፍ አይችልም፡፡ እስከ ዛሬም ኮሮጆ እየሰረቀ ነው 100 ፐርሰንት አሸነፍኩ ሲለን የነበረው:: ሕዝባችን እኛን ለመምረጥ  ከአሁኑ የምርጫውን ዕለት በጉጉት እየተጠባበቀ ነው፡፡ እኛ ካሸነፍን ደግሞ እንደ ኢሕአዴግ ሥልጣን ለብቻችን የሙጥኝ ብለን አንይዝም:: ለሌሎች ፓርቲዎችም እናጋራለን:: በአገራችን ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ Power Sharing የሚባለውን የሥልጣን ማጋራት አሰራር ተግባራዊ እናደርጋለን፡፡  
ሥልጣን የምታጋሩት ለማነው? በምርጫ ለተሸነፉ ፓርቲዎች ነው?
እንዴታ! የትግል አጋሮቻችን አይደሉ እንዴ!
እርስዎ እንዳሉት… ነፃ፣ ፍትሃዊና ዴሞክራሲያዊ ምርጫ ተካሂዶ… ብልጽግና ፓርቲ ቢያሸንፍስ…?
አይደረግም! አይደረግም! ብልጽግና ካሸነፈ… ከናንተ ከሚዲያዎች ጋር አብሮ… ምርጫውን በጠራራ ፀሐይ አጭበርብሯል ማለት ነው፡፡ ሕዝባችን ደግሞ ይህን ሁኔታ በዝምታ አይመለከተውም፡፡ አደባባይ ወጥቶ የተሰረቀ ድምፁን ያስመልሳል፡፡
ግን እኮ የሰሞኑን የድጋፍ ሰልፍ ስናይ…ጠ/ሚኒስትሩ ወይም ፓርቲያቸው ማጭበርበር ሳያስፈልጋቸው ምርጫውን በቀላሉ ማሸነፍ ይችላሉ…አይመስልዎትም?
እንግዲህ ምን ይታወቃል…ጠ/ሚኒስትሩ እንዳልኩህ የሆነ ማጂክ አላቸው፡፡ ባለፈው ሳምንት የተቀናቃኛቸው ህዝባዊ መሰረት እንደሆነ ከሚታወቅ የአገሪቱ ክፍል እሳቸውን ለመደገፍ ግልብጥ ብሎ የወጣው ነዋሪ አስደንግጠኛል፡፡ ተቀናቃኛቸውም ባዩት ነገር አቅላቸውን ስተው ሆስፒታል እንደገቡ ሰምቻለሁ፡፡ ያለዚያ ሁኔታውን አይቼ ብልፅግናን መቀላቀሌ አይቀርም! ከ2013 በኋላ በተቃዋሚነት የመቀጠል ዓላማ የለኝም ሥልጣን ጠምቶኛል፡፡ Log in
ውድ አንባቢያን፡-  በዚህ ምናባዊ ቃለ ምልልስ ላይ ሥልጣን የተጠሙት ፖለቲከኛ፤ በዘንድሮ ምርጫ ቤተ መንግሥት እንደሚገቡ አልመዋል (ደምድመዋል ማለት ይሻላል!) የእኚህ ፖለቲከኛ ችግር በምርጫው እሳቸውና ፓርቲያቸው ብቻ እንደሚያሸንፍ መደምደማቸው ነው፡፡ ከተሸነፉስ? አገር ይቀወጣል ባይ ናቸው፡፡ ‹‹ምርጫው ተጭበርብሯል›› ማለት ነው ይላሉ፡፡ የጎዳና ላይ ነውጥ ለመቀስቀስም ተዘጋጅተዋል - ‹‹የተሰረቀ ድምፅ›› ለማስመለስ፡፡ ‹‹ሕዝባችን አደባባይ ወጥቶ ድምፁን ያስመልሳል›› ብለዋል፡፡ (“ለእኛ ሥልጣን ደሙን ያፈሳል›› ማለታቸው ነው!)
ወዳጆቼ፤ የቀድሞው አምባገነኑ የሊቢያ መሪ ሙአመር ጋዳፊ በCNN ጋዜጠኛ ከስልጣን መቼ እንደሚወርዱ ሲጠየቁ፤ ‹‹ሕዝቡ እኮ ይወደኛል፤ ለእኔ ሊሞት - ለእኔ ሊሰዋ ሁሌም ዝግጁ ነው›› ብለው ነበር፡፡ (እንደኛ ፖለቲከኞች አንዘነጋውም፡፡)
እኛ መራጮች ደግሞ ‹‹ለሥልጣን ድምፅ እንጂ ደም አንሰጥም!›› የሚለውን መፈክር አንዘነጋውም፡፡    

Read 5068 times