Saturday, 22 February 2020 09:51

28ኛው የESOG አመታዊ ጉባኤ

Written by  ፀሐይ ተፈረደኝ ከኢሶግ
Rate this item
(2 votes)

  የኢትዮጵያ የማህጸንና ጽንስ ሐኪሞች ማህበር ESOG ከተመሰረተ እነሆ የ28ኛ አመቱን ጉባኤ ከየካቲት 9-10/ 2012/ እ.ኤ.አ Feb 17-18/2020 በአዲስ አበባ አካሄደ፡፡ ጉባኤው ከመካሄ ዱም በፊት ለሶስት ቀናት ያህል ለማህጸንና ጽንስ ሕክምና ባለሙያዎች የሙያ ማዳበሪያ ስልጠናዎች በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል በቅዱስ ጳውሎስ ሚሊኒየም ሜዲካል ኮሌጅ እንዲሁም በኢት ዮጵያ የህብረ ተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ተሰጥቶአል፡፡ በጉባኤው ላይ ከተለያዩ ሀገራት የተወከሉ የህክምና ባለሙያዎች የተሳተፉ ሲሆን ምርምር የተደረገባቸው የስነተዋልዶ ጤና ርእሶችም ቀርበዋል፡፡ በጉባኤው ላይ ከቀረቡት የተለያዩ ርእሰ ጉዳዮች በዚህ እትም ለንባብ ያልነው በግል ሆስፒታሎች በቀዶ ሕክምና ልጅን የመውለድ ጉዳይ ይገኝበታል፡፡
ይህንን ርእሰ ጉዳይ በኢትዮጵያ የማህጸንና ጽንስ ሐኪሞች ማህበር የሚዘጋጀው የኢትዮጵያ የስነተዋልዶ ጤና ጆርናል (EJRH) January, 2020 በVolume 12, No. 1 በተለይም በግል የህክምና ተቋማት በቀዶ ሕክምና ልጅ የሚወልዱ እናቶችን ምን ያህል እንደሆኑና ተያያዥ የሆኑ የተለያዩ አለምአቀፍ ገጽታዎችን ዳስሶአል፡፡ ጽሁፉን ጥናት አድርገው ለጆርናሉ ያደረሱት የማህጸንና ጽንስ ሐኪሞች ሲሆኑ በጥናቱ የተካተቱትና ይህንን ርእሰ ጉዳይ በጉባኤው ላይ ያቀረቡት ዶ/ር ደረጀ ንጉሴ የማህጸንና ጽንስ ሕክምና እስፔሻሊስት ናቸው፡፡
በአንዳንድ አጋጣሚዎች በሚከሰት የጤና ሁኔታ በሐኪሞች ሲታዘዝ በቀዶ ሕክምና ልጅን መገላገል ለእናትየውም ሆነ ለሕጻኑ ሕይወትን ለማዳን እንደሚያገለግል አያጠያይቅም፡፡ ሆኖም ግን በአሁኑ ወቅት በአለም አቀፍ ደረጃ የህክምና ትእዛዝ ሳይኖር በግል ፈቃደኝነት ብቻ በቀዶ ሕክምና ልጃቸውን የሚገላገሉ እናቶች ቁጥር እየጨመረ መሄዱ ትኩረትን የሚሻ ሆኖአል፡፡  
በቀዶ ሕክምና ልጅን ማዋለድ ከሚያስፈልገው ወጪ እና ከሚያስከትለው ጉዳት አንጻር ቀላል የማይባል ሲሆን በተጨማሪም በማዋለድ ወቅት የሚገጥመው የደም መፍሰስ፤ ኢንፌክሽን፤ እና የማደንዘዣ ችግር በቀጥታ ለእናቶች ሞት ምክንያት ሊሆን እንደሚችል መረጃው ይጠቁማል፡፡
የአለም የጤና ድርጅት በቀዶ ሕክምና የሚወልዱ ሴቶች ከ10-15 በመቶ ሊደርሱ እንደሚችሉ የሚገልጽ ሲሆን መጠኑ ከ10 ከመቶ በታች ከሆነ ግን እናቶች ሕይወታቸው እንዲድን አገልግሎት ሊያገኙ የሚችሉበትን አቅም ውስንነት ያመላክታል:: ከዚህም በተጨማሪ የእናቶችንና ከወሊድ በሁዋላ ያለውን የጤና ሁኔታ በ24 አገሮች ውስጥ በ373 ጤና ተቋማት ከ289‚636 ወላዶች አንጻር ሲገመገም ከፍተኛ የሆነው በቀዶ ሕክምና መውለድ ለእናቶች ሞት እና ጤና መጉዋደል ምክንያት እንደሆነ ታምኖአል፡፡  
በአፍሪካ በየጊዜው ቁጥሩ እየጨመረ የመጣው በቀዶ ሕክምና ልጅን መውለድ ምክንያቱ ጽንሱ በእናቱ ማህጸን ውስጥ ሳለ መሞቱ፤ የጽንሱ አስቀድሞውኑ መቋረጥ፤ወይንም ለሚወለደው ልጅ ሕይወት አስጊ የሚሆን ነገር ከታየ፤ እናትየውም የገጠማት የጤና ችግር ጊዜ የማይሰጣት ከሆነ …ወዘተ የመሳሰሉት ችግሮች ሲከሰቱ በሕክምና ባለሙያዎች በሚሰጥ ውሳኔ መሰራት ያለበት ነው፡፡ ስለዚህም ግልጽ በሆነ መንገድ የህክምና ባለሙያው ውሳኔ እና ምክንያቱ ለወላ ድዋ ሊነገራት ይገባል፡፡ ወላድዋ ወይንም ቤተሰቡ በቀዶ ሕክምና መገላገልዋ ለእራስዋም ይሁን ለልጅዋ የሚኖረውን ጥቅም አስቀድመው ከተረዱ በሁዋላ ፈቃደኝነታቸውን ገልጸው ስራው ሙያዊ በሆነ መንገድ ሊካሄድ ይገባል፡፡
የኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዲሞክራሲያው ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር እ.ኤ.አ በ2010 ባቀረበው አመታዊ ሪፖርት  በቀዶ ሕክምና የሚወልዱ ሴቶች በአዲስ አበባ 36 ከመቶ ነበሩ፡፡ የህክምና ትምህርት በሚሰጥባቸው ዩኒቨርሲቲዎች፤ መንግስታዊ ባልሆኑ ድርጅቶች እና በግል ሆስፒታሎች በአዲስ አበባ 31.1 ከመቶ የሚሆኑ በቀዶ ሕክምና የወለዱ ሲሆን በግል የህክምና ተቋማትና መንግስ ታዊ ባልሆኑ የሕክምና ተቋማት በቀዶ ጥገና የሚወልዱ ሴቶች ቁጥር 48.3 ከመቶ ነበሩ፡፡
ከላይ ከተጠቀሰው መረጃ በመነሳት በአገር አቀፍ ደረጃ ያለው በቀዶ ሕክምና ልጅን መገላገል 3.79 ከመቶ ሲሆን ይህ ደግሞ ከአለም የጤና ድርጅት ግምት ያነሰ እና በአገሪቱ ከአንዱ አካባቢ ሌላው ከፍ የሚልበትን ሁኔታ ይጠቁማል፡፡ ለምሳሌም በሶማሊያ 0.76 ከመቶ ሲሆን በአዲስ አበባ ደግሞ 41 ከመቶ መሆኑ እ.ኤ.አ በ2011 ተመዝግቦአል፡፡ ይህ የሚያሳየውም ከቦታ ቦታ እኩል የሆነ አገልግሎት ሊሰጥ የማይችል መሆኑን ነው የኢትዮጵያ ማህጸንና ጽንስ ሐኪሞች ማህበር የሚያወጣው ጆርናል የሚያሳየው፡፡
በአገሪቱ የሚሰጠው የቀዶ ሕክምና አገልግሎት በተመሳሳይ አለመሆኑ የሚያሳየው አዲስ አበባ ላይ ብዙ የግል ሆስፒታሎች ከፍ ያለ ገንዘብ እያስከፈሉ ሕክምናውን የሚሰጡ መሆናቸውንና ባለሙያዎችም በበቂ የሚገኙበት መሆኑን የሚያመላክት ሲሆን ይህ ደግሞ ትክክለኛውን የማዋለድ አገልግሎት በአገሪቱ በእኩልነት መስጠት የማይቻልባቸው ሁኔታዎች መኖራቸውን የሚያመላክት ነው፡፡ የፌደራል ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር እንደሚገልጸው፡-
በኢትዮጵያ ማንኛዋም እርጉዝ ሴት ትክክለኛውን መረጃ ማግኘት፤
የምትፈልገውን ነገር ሕክምናውን ከሚሰጣት ባለሙያ ጋር መወያየት፤
የሚሰጣትን ሕክምና በሚመለከት አስቀድማ ማወቅ፤
የግል የጤንነት ሁኔታዋ መከበር፤
ምስጢርዋ የመጠበቅ መብት እና ፤    
አገልግሎቱን በሚመለከት የሚሰማትን አስተያየት መስጠት መብት አላት፡፡
ከላይ የተዘረዘሩትን መብቶች ለማሟላት እ.ኤ.አ በ2010 የፌደራል ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር በአ ለም የጤና ድርጅት መመሪያ ላይ በመመስረት በአገልግሎቱ ላይ ትኩረት ያደረገ መመሪያና ግብ ያስቀመጠ ሲሆን ይህም ከመውለድ በፊት፤ በወሊድ ጊዜ፤ ከወሊድ በሁዋላ፤ እና አዲስ የሚወለዱ ሕጻናትን አገልግሎት የሚመለከት ነው፡፡
በዚህ መመሪያም እንደተጠቀሰው የቀዶ ሕክምና አገልግሎት የሚሰጠው እናትየውን በጤናማ ሁኔታ በተፈጥሮአዊው መንገድ ማዋለድ የማይቻልበት የአካል መጥበብ ወይንም አለመፍታታ ትን ጨምሮ ሌሎች ችግሮችም ሲገጥሙ ወይንም እናትየው ልጁን በመውለድ ምክንያት ችግር የሚገጥማት ሲሆን አለዚያም ከሚወለደው ልጅ ጋር በተያያዘ ችግር ከተፈጠረ ነው፡፡
መመሪያው እንደሚገልጸው አገልግሎቱን ለመስጠት የሰለጠነ ባለሙያ እና የተሟላ መሳሪያ ሊኖር ይገባል፡፡ መመሪያው በተጨማሪ እንደሚገልጸውም በቀዶ ሕክምና ልጅን በመውለድ ምክንያት የሚከሰተው የእናቶች ሞት በጤናማ መንገድ ከሚወልዱ ይልቅ የበዛ ነው፡፡ ከመውለድ በፊት በክትትል ጊዜ ለእናቶች የሚሰጠው የመረጃ አሰጣጥ ድክመት እንዲሁም ተቋማቱ ለስራው ዝግጁ መሆን የሚገባቸው ሲሆን ግን የመፈጠረው ድክመት፤ ወይንም አገልግሎቱን ለመስጠት የሚያስችሉ አካሄዶች በትክክል አለመፈጸማቸው ችግሩን የሚያባብሱት መሆናቸው ተጠቁሞአል፡፡
በስተመጨረሻም በጥናቱ እንደተጠቀሰው እ.ኤ.አ በእናቶችና ሕጻናት ሆስፒታሎች ከApril 2017 –Dec. 2018 ከ 25% ወደ 47% ማለትም በእጥፍ የጨመረ ሲሆን ይህም በአዲስ አበባም በተመሳሳይ ወቅት 44 ከመቶ ደርሶአል፡፡ ይህም አገልግሎቱ በከፍተኛ ደረጃ እያደገ  መሆኑን ያሳያል፡፡
የጥናት ወረቀቱ በመደምደሚያው እንዳስነበበው በቀዶ ሕክምና መውለድ በየጊዜው ቁጥሩ እያደገ መጥቶአል፡፡ በብዛት ቁጥሩ እየጨመረ የመጣውም ወጣት በሆኑ ወላዶች ቨፈቃደኝነት በቀዶ ሕክምና ለመውለድ ጥያቄ መቅረብ ጭምር ነው፡፡ በሌላም በኩል ለአገልግሎቱ እንደ ምክንያት ከሚ ቆጠሩት ውስጥ የጽንሱ የልብ ምት መዛባትና የወላድዋ አገልግሎቱን መጠየቅ ይገኝበታል፡፡ አልፎ አልፎም አገልግሎቱን ከሚሰጠው ባለሙያ ባህርይና የገቢ ማግኛ ተደርጎ መወሰዱም ተጠቃሽ ይሆናል፡፡ ማህበራዊና ባህላዊ ሁኔታዎችም የእናቶችን ውሳኔ መስጠት እንደሚፈታተኑ እሙን ነው፡፡ ለዚህም መፍትሔው በአገልግሎቱ ዙሪያ ተገቢው ጥናት መደረግ እንደሚገባውና የቀዶ ሕክምናው አገልግሎት በትክክል ለማን ይገባል የሚለውን በባለሙያዎች አማካኝነት መወሰን አስፈላጊ ነው ሲል ጥናቱ ይፋ አድርጎአል፡፡

Read 12005 times