Monday, 17 February 2020 00:00

ዳንጎቴ ለ9ኛ ተከታታይ አመት ቀዳሚው የአፍሪካ ቢሊየነር ሆነዋል

Written by 
Rate this item
(0 votes)

  ባለፉት ስምንት ተከታታይ አመታት የአፍሪካ ቁጥር አንድ ቢሊየነር ሆነው የዘለቁት ናይጀሪያዊው ባለጸጋ አሊኮ ዳንጎቴ፤ ዘንድሮም በ10.1 ቢሊዮን ዶላር የተጣራ ሃብት የአህጉሪቱ ቀዳሚ ባለጸጋ መሆናቸውን ፎርብስ መጽሄት ዘግቧል፡፡
ፎርብስ መጽሄት ሰሙኑን ይፋ ባደረገው የ2020 የፈረንጆች አመት አፍሪካውያን ቢሊየነሮች ዝርዝር ውስጥ የሁለተኛነት ደረጃን የያዙት በግንባታና በኬሚካል ምርቶች ኢንዱስትሪ ዘርፎች የተሰማሩት ግብጻዊው ቢሊየነር ናሴፍ ሳዋሪስ ሲሆኑ፣ የባለሃብቱ የተጣራ ሃብት 8 ቢሊዮን ዶላር ያህል መድረሱ ተነግሯል፡፡
በቴሌኮምና በነዳጅ ዘርፎች የተሰማሩትና 7.7 ቢሊዮን ዶላር የተጣራ ሃብት ያፈሩት ሌላኛው ናይጀሪያዊ ቢሊየነር ማይክ አዴኑጋ በሶስተኛ ደረጃ ላይ ሲቀመጡ፣ በአልማዝ ማዕድን ዘርፍ የተሰማሩት ደቡብ አፍሪካዊው ኒኪ ኦፕኔመርና ቤተሰቦቹ በ7.6 ቢሊዮን ዶላር ሃብት አራተኛ ደረጃን ይዘዋል፡፡
ከአፍሪካ ምርጥ 20 ቢሊየነሮች መካከል ሁለቱ ሴቶች መሆናቸውንና አንደኛዋ የአንጎላ የቀድሞ ፕሬዚዳንት ጆሴ ኤዱዋርዶ ዶስ ሳንቶስ ልጅ የሆነችውና በሙስና ከሰሞኑ ክስ የተመሰረተባት ኤሳቤል ዶስ ሳንቶስ መሆኗን የጠቆመው ፎርብስ መጽሄት፤ የሃያዎቹ አፍሪካውያን ቢሊየነሮች አጠቃላይ የሃብት መጠን 73.4 ቢሊዮን ዶላር መድረሱንም አክሎ ገልጧል፡፡
ከ54 የአፍሪካ አገራት መካከል የስምንቱ አገራት ቢሊየነሮች ብቻ በተካተቱበት በዘንድሮው የአፍሪካውያን ቢሊየነሮች ዝርዝር ውስጥ ግብጽና ደቡብ አፍሪካ በተመሳሳይ አምስት ቢሊየነሮችን፣ ናይጀሪያ አራት ቢሊየነሮችን፣ ሞሮኮ ሁለት ቢሊየነሮችን በማስመዝገብ፣ ከአንደኛ እስከ ሶስተኛ ያለውን ደረጃ መያዛቸውንም ዘገባው አመልክቷል፡፡

Read 3016 times