Saturday, 15 February 2020 12:07

የኮሮና ቫይረስ ተጠቂዎችና ሟቾች ቁጥር በእጅጉ ጨምሯል

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

  በቻይና በተቀሰቀሰውና ወደተለያዩ የአለማችን አገራት መስፋፋቱን በቀጠለው ኮሮና ቫይረስ የተጠቁና ለህልፈተ ህይወት የተዳረጉ ሰዎች ቁጥር በተለይ ባለፈው ረቡዕ በከፍተኛ ሁኔታ ማሻቀቡን የዘገበው ሮይተርስ፣ እስከ ትናንት በስቲያ ድረስ በመላው ቻይና በቫይረሱ የሞቱ ሰዎች ቁጥር 1 ሺህ 367፣ የተጠቂዎች ቁጥር ደግሞ 59 ሺህ 805 ያህል መድረሱን ገልጧል፡፡
በቻይና ሁቤይ ግዛት ባለፈው ረቡዕ ብቻ 242 ሰዎች መሞታቸውንና 14 ሺህ 840 ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸው መረጋገጡን የጠቆመው ዘገባው፣ ዕለቱ ወረርሽኙ ከተቀሰቀሰበት ጊዜ አንስቶ በአንድ ቀን ውስጥ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ሰዎች ለሞት የተዳረጉበት እንደሆነ ተነግሯል፡፡
እስከ ትናንት በስቲያ ድረስ በአለማቀፍ ደረጃ በኮሮና ቫይረስ ለሞት የተዳረጉ ሰዎች ቁጥር 1 ሺህ 370 መድረሱንና የተጠቂዎች ቁጥር ደግሞ ከ60 ሺህ 300 ማለፉንም ዘገባው አመልክቷል::
የአለም የጤና ድርጅት ባለፈው ማክሰኞ በሰጠው መግለጫ፤ ኮሮና ቫይረስን የመከላከል ብቃት ያለው ክትባት በመጪዎቹ 18 ወራት ጊዜ ውስጥ ይገኛል ተብሎ እንደሚጠበቅ ያለውን ተስፋ የጠቆመ ሲሆን የሌሎች አገራት ተመራማሪዎችም መድሃኒትና ክትባት ለማግኘት እየተረባረቡ እንደሚገኙ ሮይተርስ ዘግቧል፡፡
በአሜሪካ በሚገኙ ታማሚዎች ላይ ተሞክሮ አበረታች ውጤት ያስገኘውን አዲስ በሙከራ ደረጃ የሚገኝ የኮሮና ቫይረስ መድሃኒት፤ የቻይና ተመራማሪዎች ወደ ዉሃን ግዛት አስገብተው፣ በ761 ታማሚዎች ላይ እየሞከሩት መሆኑን የዘገበው ብሉምበርግ፤ በቻይና የሚገኝ አንድ መድሃኒት አምራች ኩባንያም ኮሮና ቫይረስን የመከላከል አቅም ይኖረዋል ተብሎ የታመነበትን ይህን መድሃኒት በሙከራ ደረጃ በብዛት ማምረት መጀመሩን አመልክቷል፡፡
በጃፓኑ ዮኮሃማ የባህር ዳርቻ እንቅስቃሴዋን አቋርጣ በጥብቅ እየተጠበቀች በምትገኘው መርከብ ውስጥ ከነበሩት ከ3 ሺህ 700 መንገደኞች መካከል በቫይረሱ መጠቃታቸው የተረጋገጡ ሰዎች ቁጥር ከትናንት በስቲያ 219 መድረሱን የዘገበው ቢቢሲ፤ ሁሉም ተሳፋሪዎች እንዳልተመረመሩና የተጠቂዎች ቁጥር ከዚህ የበለጠ ይጨምራል ተብሎ እንደሚጠበቅም ገልጧል፡፡ 2 ሺህ ሰዎችን አሳፍራ በመጓዝ ላይ የነበረች ሌላ መርከብም የኮሮና ተጠቂዎችን ሳታሳፍር አትቀርም በሚል ጥርጣሬ ጃፓን፣ ታይላንድና ፊሊፒንስን ጨምሮ አምስት አገራት በወደባቸው እንዳታርፍ ሲከለክሏት ሰንብታ ከትናንት በስቲያ ካምቦዲያ ብታርፍም፣ አንድም ሰው በቫይረሱ አለመጠቃቱ በምርመራ መረጋገጡ ተነግሯል፡፡
አገራት ዲፕሎማቶችን ጨምሮ በርካታ ቁጥር ያላቸው ዜጎቻቸውን ከቻይና ማስወጣት መቀጠላቸውን የዘገበው ሮይተርስ፤ በሳምንቱ ዜጎቻቸውን ካስወጡት በርካታ አገራት መካከል አሜሪካ 300፣ ካናዳ 185፣ ሲንጋፖር 174፣ ፊሊፒንስ 30፣ እንግሊዝ 200፣ ኡዝቤኪስታን 251፣ ታይዋን 500፣ ብራዚል 34፣ ጣሊያን 56፣ ደቡብ ኮርያ 147 ዜጎቻቸውን ከቻይና ማስወጣታቸውን ዘገባው አመልክቷል፡፡ ባለፈው ሃሙስ ለመጀመሪያ ጊዜ አንድ ዜጋዋን በሞት የተነጠቀችው የጃፓን ጠቅላይ ሚኒስትር ሺንዞ አቤ፣ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝን ለመግታት የሚውል የ10.3 ቢሊዮን የን ለመመደብ ማቀዳቸው የተዘገበ ሲሆን፣ ከጃፓን በተጨማሪ በሆንግ ኮንግ አንድ፣ በፊሊፒንስ አንድ ሰው በቫይረሱ ምክንያት ለሞት መዳረጉም ተነግሯል::
ኮሮና ቫይረስ የአለም ስጋት መሆኑ እንደቀጠለ ቢሆንም፣ ባሳለፍነው ሳምንት፣ በቻይና በየዕለቱ በኮሮና ቫይረስ አዲስ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር በ48 ነጥብ 2 በመቶ ቀንሶ፣ ከሆስፒታል አገግመው የሚወጡ የቫይረሱ ተጠቂዎች ቁጥርም ከፍተኛ ጭማሪ አሳይቶ የነበረ ቢሆንም፣ ባለፈው ረቡዕ ግን የተጠቂዎችና የሟቾች ቁጥር ድንገት በከፍተኛ ሁኔታ ማሻቀቡን የሃገሪቱ ጤና ኮሚሽን አስታውቋል፡፡
በቻይና ከቫይረሱ የማገገም እድል ከሁለት ሳምንት በፊት ከነበረበት 1 ነጥብ 3 በመቶ ወደ 10 ነጥብ 6 በመቶ ከፍ ብሎ እንደነበር ያስታወሰው ኮሚሽኑ፤ እስካለፈው ማክሰኞ ድረስም 4 ሺህ 740 ሰዎች ከቫይረሱ ሙሉ በሙሉ አገግመው ከሆስፒታል መውጣታቸውንም አክሎ ገልጧል::             የኮሮና ቫይረስ አለማቀፍ ስርጭት - እስከ ትናንት በስቲያ
ተ.ቁ         የአገር ስም        የተጠቂዎች ቁጥር     የሟቾችቁጥር
1       ቻይና               59,822                1,367
2        ጃፓን                 247*                    1
3       ሆንግ ኮንግ            51                        1
4       ሲንጋፖር               50
5       ታይላንድ                33
6       ደቡብ ኮርያ             28
7       ታይዋን                   18
8       ማሌዢያ                 18
9      ቬትናም                   16
10    ጀርመን                    16
11    አውስትራሊያ             15
12    አሜሪካ                    14
13    ፈረንሳይ                   11
14    ማካኡ                     10
15    እንግሊዝ                   9
16   የተባበሩት አረብ
ኤሜሬትስ                         8
17 ካናዳ                          7
18 ህንድ                          3
19 ፊሊፒንስ                     3                             1
20 ጣሊያን                       3
21 ሩስያ                           2
22 ስፔን                           2
23 ቤልጂየም                     1
24 ስዊድን                         1
25 ፊላንድ                         1
26 ኔፓል                          1
27 ሲሪላንካ                       1
28 ካምቦዲያ                      1
የጃፓን ተጠቂዎች ቁጥር የመርከብ ተጠቂዎችን ይጨምራል
ድምር                               60,381               1,370

Read 3330 times