Saturday, 15 February 2020 12:05

በሃሳብ መንገድ ላይ

Written by  ተመስገን
Rate this item
(3 votes)

    “ፕላቶን እወደዋለሁ፤ ከእውነት ግን አይበልጥብኝም”
                      
             ሰውየው አዲስ ከተከራየው አፓርትመንት ስር ወደሚገኘው ካፌ ጐራ ብሎ ካፌይኑ የወጣለት ቡና (decafain coffee) አዘዘ:: መጣለትና ፉት ብሏት ቤቱ ገባ፡፡ ዘወትር ምሽት የሚያደርገው ልማዱ ነው፡፡ አለበለዚያ “እንቅልፍ አይወስደኝም” ይላል፡፡ የካፌውም ደንበኛና ቤተኛ ሆነ፡፡ አንድ ቀን አዲስ አስተናጋጅ ገጠመው፡-
“ዲካፌ” አለ እንደተለመደው፡፡
“የለንም” መለሰ አስተናጋጁ፡፡
“ሁሌ የምጠጣው’ኮ ነው፤ እንዴት የለም ትለኛለህ?”
ባለቤቱ ነገሩን ሰምቶ እየሳቀ፤
“የመጀመሪያው ቀን ስለዋሸንህ እንጂ ዲካፌ አዘጋጅተን አናውቅም” አለው፡፡
ሰውየውም፤ “የዛን ቀን ሳልተኛ ነጋ” አለው ለባለቤቱ፡፡
(“ሪደርስ ዳይጀስት” ነው ምንጫችን)፡፡
***
ወዳጄ፡- ድንጋዩን “ዳቦ ነው” ብለህ አእምሮህን ለማሳመን መሞከር ትችላለህ:: “አንተ ከመሰለህ እኔ ምን ቸገረኝ” ይልሃል፡፡ ድንጋዩ ግን ዳቦ ሆኖ ሊገመጥልህ አይችልም፡፡ ማሰብ ሌላ! ዕውነታው ሌላ!
አንድ የድሮ ቀልድ እንጨምር፡-
ሰውየው የአአምሮ ሃኪም ነው፡፡ ሁለት ህመምተኞቹን ሊፈትናቸው ፈለገና፡-
“አንዳችሁ ገዥ፣ አንዳችሁ ሻጭ ሆናችሁ ተገበያዩ” አላቸው፡፡
ነጋዴው ተመቻችቶ ቁጭ አለ፣
ሌላኛው ገንዘብ ይዞ ሊሸምት መጣ፡፡
“ባለ ሱቅ”
“አቤት”
“አንድ ሊትር ሽንኩርት ስፈርልኝ”
ይሄኔ ነጋዴው በሳቅ መንከትከት ጀመረ፡፡
ሃኪሙም፤ “ምን ያስቅሃል?” ብሎ ጠየቀው፡፡
ምን ብሎ የመለሰለት ይመስልሃል? መጨረሻ ላይ እነግርሃለሁ፡፡
***
ወዳጄ፡- እያንዳንዱ ሰው ከሌላው በተለየ ሁኔታ ዕውነትን የሚገነዘብበት ወይም ነገሮችን ለማየት የሚቆምበት ማዕዘን አለው፡፡ የተመለከተው ወይም የገመተው ነገር ግን ከሱ በተቃራኒ የቆመው ሰው ከሚያስበው ጋር ልዩነት ላይኖረው ይችላል፡፡ “የፀሐይ ግብዓት (Sun set) ከትልቅ ሆቴል ሰገነት ላይ ወይም ከእስር ቤት መስኮት ለሚመለከተው ተመሳሳይ ነው፣ ልዩነቱ ዕውነታው ላይ ሳይሆን እኛ ዘንድ ነው” ይላሉ ሊቃውንት፡፡ የዝሆንን ምንነት ለመግለጽ የሞከሩት የሶስት ዓይነ ስውራንን አስተሳሰብ ልብ ይሏል፡፡
ቡናም አንዳችን ባዶውን፣ አንዳችን በጨው፣ አንዳችን በስኳር እንጠጣለን፡፡ ጤናና አቅርቦትን ጨምሮ በተለያየ ምክንያት ሃሳባችንን ቀይረን ባዶውን፣ በጨው ወይም ስኳሩን በባዶ ብንተካ የመረረን ሊጣፍጠን፣ የጣፈጠን ሊመረን ይችላል፡፡ ቡናው አንድ ዓይነት ሆኖ፣ የተዘበራረቀው የኛ አስተሳሰብ ነው፡፡
ወዳጄ፡- የሰው ልጅ በተፈጥሮ ራሱን ያስቀድማል፤ ራሱን ከሌላው ያስበልጣል:: በዕውቀት፣ ዕምነትና ባህል ረገድ የእሱና የእሱ ብቻ አንደኛ ይመስሉታል፡፡ ዕውነት ግን ለሁሉም አንድ ነው፡፡ ዕውነት የስህተት ተቃራኒ ማለት ነው፡፡ ዕውነት አይቀየርም፡፡ “ፕላቶን እወደዋለሁ፤ ከእውነት ግን አይበልጥብኝም” ይላል አርስቶትል፤ መምህሩንና ወዳጁን፡፡ ዕውነት የሃሳብ ዋጋ የሚለካበት ሚዛን ነው፡፡ ከዕውነት የሚበልጥ ምን አለ?
ወዳጄ፡- ወደ ሰሞኑ ጉዳይ ስንመጣ፣ አፍሪካ የአስተሳሰብ ለውጥ አምጥታለች፡፡ ለድህነቷ፣ ለኋላ ቀርነቷ፣ ለፍትህና ዴሞክራሲ ጥሟ እንቅፋት የሆነውን የእርስበርስ ግጭት ለማስቆም የሚያስችላትን አጀንዳ ቀርፃለች፡- “Silencing the gun!” በሚል፡፡
ወዳጄ፡- ፕሌቶን  ያለ ምክንያት አላነሳነውም:: ከ2500 ዓመት በፊት፡- “የአንድን አገር ፖለቲካ ለመረዳት የህዝቡን ስነልቦና ማወቅ ግድ ነው፣ መንግሥታትም እንደ ሰው ተፈጥሯቸው ይለያያል፡፡ የፖለቲካ ስርዓት የሚገነባው በግዛታቸው በሚኖረው ህዝብ ፍላጐት ላይ ተመስርቶ ነው፡፡ መንግሥት ማለት ህዝብ፤ ህዝብ ማለት መንግሥት ነው የሚባለው ለዚህ ነው፡፡ መልካምና የሰለጠኑ ዜጐች እስኪበዙ ድረስ መልካምና የሰለጠነ መንግሥት መገንባት ያስቸግራል፡፡ ስር ነቀል ለውጥ በቀላሉ የሚታለም አይደለም” ብሎ ነበር፡፡ ጥያቄው፤ ከዚህ ሁሉ ዘመን በኋላ አፍሪካ ምን ያህል ተራምዳለች? የሚል ሲሆን ታላቁ አርማህም በመጽሐፉ፡- “ምስኪን አፍሪካ፤ እስከ መቼ ይሆን መሪ እንዳይወጣልሽ የተረገምሽው?” በማለት ያጠናክረዋል፡፡ በውስጠ “ዘ” የምናውቃቸውን ጨምሮ፣ ኔሬሬ፣ ሴንጐር፣ ናስርና ማንዴላን የመሳሰሉ “የገባቸው” መሪዎች እንዳላፈራች ሁሉ ቦካሳ፣ ኢዲ አሚንና ሳሙኤል ዶን ዓይነት አምባገነኖች ገነውባታል፡፡ በዘመነ ቅኝ አገዛዝ በተፈፀሙ ኢ-ፍትሃዊነት ሲወገዙ ከነበሩ አውሮፓውያን በላይ አፍሪካውያን በዘር በጐሳና በሃይማኖት ተከፋፍለው፣ የተጠፋፉበት የእርስበርስ ግጭት፣ ባዕዳኑ ፈፀሙት ከተባለው አንድ ሺ ዕጥፍ የከፋ ነው፡፡ ሩዋንዳ፣ ደቡብ ሱዳንና ሶማሊያ ጥቂት ምሳሌዎች ናቸው፡፡
“Why is Africa burning in my mind?
If nat the leaders; it must be “I” getting mad” ብሎን ነበር ገጣሚው፡፡ ዕውነቱን ነው፡፡ ከዕውነት የሚበልጥ ምን አለ?
ወዳጄ፡- አንድ ነገር ግን ልብ በል፡- አርማህ እንደሚለው …”ህዝቦች የሀገራቸውን ስም እየጠሩ “እንደዚህ ነኝ” ማለት እስከ መታገድ በተደረሰበት አገር፣ አፍሪካዊ መባል ጥቅሙ ምንድን ነው?..ጋናዊ ሆኖ “ጋናዊ ነኝ” ማለት የሚኮራባት ሳይሆን እንደ ወንጀለኛ ካስቆጠረ፣ አፍሪካዊነት ምን ይፈይዳል? “ፅድቁ ቀርቶብኝ በቅጡ በኮነነኝ” ይላል አበሻ! ይኸን ዕውነት እኛም አገር አስተውለናል፡፡ ከዕውነት የሚበልጥ ምን አለ?
ወዳጄ፡- አሁን አሁን ግን አዲስ አፍሪካ ብቅ እያለች ነው፡፡ ወደ አንድነትና ወደ ስልጣኔ ፊቷን የመለሰች አፍሪካ! የጐሳ ግጭትና የጦር መሳሪያዎቿን አደብ ለማስገዛት ቃል የገባች አፍሪካ! (“Silencing the gun” is the century’s best Motto!!)
Hurrah! Mother land!
The key, you have found
The key of your hidden guts,
And we are proud…
No more to be old fashioned!!...የተባለላት አፍሪካ!
***
አማኑኤል ወደሚገኙት ጓደኞቻችን ስንመለስ፡-
ሸማቹ…” አንድ ሊትር ሽንኩርት ስፈርልኝ” ሲል ነጋዴው ከት ብሎ መሳቁን አውስተናል፡፡
ሃኪሙ፡-
“ምን ያስቅሃል?” ሲለው
“ጠርሙስ አልያዘም’ኮ” ሲል ነበር የመለሰለት፡፡
በነገራችን ላይ “Madness and genius are neighbours” መባሉ ዐውነት አይመስልህም ወዳጄ?... ከዕውነት የሚበልጥ ምን አለ?
ሠላም!!

Read 1922 times