Saturday, 15 February 2020 11:57

የጨረታ ቀን

Written by  ደረጀ በላይነህ
Rate this item
(13 votes)

  እዚያ ሰፈር ብዙ ነጋዴዎች ነበሩ:: ብዙ ኃይለኞች፣ ብዙ ደጎች፣ ብዙ ጨካኞች፤ ብዙ ርሁሩሆች፡፡ ሰላሳ ዐመት ያለፈው ልጅነቴ ትዝ ያለኝ ከብዙ ጊዜ በኋላ ወላይታ ሶዶን በማየቴ ነው:: በተለይ የድሮው ሕብረት ቡና ቤት አካባቢ ስደርስ፣ አንጀቴ ተላወሰ:: የጋሽ ላቁ ቡና ቤት፣የእትዬ ቦጋለች ጠጅ ቤት፣ የጋሽ ወልደትንሳይ ስጋ ቤት፣ ብቻ ምኑ ቅጡ!ጋሽ ወልደተንሳይ ሲጋራቸውን በአፍንጫቸው ቡንን ሲያደርጉ አስታወስኩና እንባዬ አነቀኝ:: ጃንጥላቸውን በግራ እጃቸው ይዘው፣የኩባ ወታደሮች መለዮ አድርገው ትዝ አሉኝ፡፡
የጥጥ ፋብሪካው ዘበኛ ጫምቡራ ጫኬ ሲመሻሽ ስለ ጦር ሜዳ ውሎው በትዝታ ዘራፍ የሚለው ሳይቀር በጆሮዬ ተንቆረቆረ:: የእትዬ ወርቄ ቡና ቤት፣ አለባበስዋ፣ ቁመትዋ፣ የትግሬ ሽሩባዋ፣ ወርቆችዋ…ዘለግ ያለው ቁመትዋ!! ሁሉ ነገርዋ፡፡ የጌታቸው ቡና ቤት፣ የአብዮት ጥበቃ ልብሱና መለዮው፣አጭር ቁመቱ….
ብቻ ምኑ ቅጡ! ሁሉም ነገር ተለውጧል:: “ተራማጅ ሉካንዳ ቤት” ይባል የነበረውን ስጋ ቤት ሳይ ያኔ እዚያ ቤት የሚመጡት መምህራን፣የቀበሌ ሹሞች፣ የኢሠፓ አባላት ሁሉ ከፊቴ ድቅን አሉ፡፡ አሁን የሁሉም ንግድ ቤቶች ባለቤቶቻቸው የሉም፡፡ ቤቶቹም አካባቢውም ተቀይሯል፡፡ ቤቶቹ በአብዛኛው አምረዋል፡፡
በሊጋባ በየነ ትምህርት ቤት በኩል ሳልፍ፣ የነአቦነሽን ቤት ሳልፍ ርዕሰ መምህራችን ጋሽ ዘብዴዎስ ጨማ፣የእርሻ መምህራችን ጋሽ ተስፋዬ ገብሬ ፊቴ ድቅን አሉ፡፡
የአኢወማ አባል ካልሆንክ ብለው የተከራከሩኝ ሊቀመንበሩ አለማየሁና ሌሎቹም ትዝ መጡብኝ፡፡ በትዝታ ውስጥ ጥላቻ ይኖር ይሆን! አይመስለኝም፡፡
ማን ነበረች ሃይለኛዋ ባለመጠጥ ቤት? እትዬ ፅጌ የት ደርሳ ይሆን? ዘፋኙ ነዋይ ደበበ በየሰርግ ቤቱ እስክስታ የሚመታበት ጊዜ ሁላችን ከቤት ተደብቀን ትከሻችንን ስንነቀንቅ፡፡ እነውሮ፣ እነእመቤት እነ ጋሽ ሃይሉ፡፡
መኪናዬን አቁሜ እንባዬን ወደ ውስጥ ጠባሁት፡፡ከማን ጋር ላውራ!ዓለሙ ዴኣ የቴሌ ሰራተኛ ነበር፡፡ ተማሪ ሆኜ ሻይ ቡና የሚለኝ ትዝ አለኝ፡፡ ጋርጠው፣ ገመቹ ጀቤሳ የሂሳቡ ሊቅ፣አለማየሁ አውቶሜካኒክ፣ አለማየሁ፣ ፈራ ጎዶ እምምም አለኝ:: የሰው ልጅና ዘመኑ ጥላ ነው፡፡ ጠቢቡ ሰለሞን እውነቱን ነው:: ሁሉም ነገር ከንቱ የከንቱ ከንቱ ነው …ነፋስንም እንደመከተል ነው:: አሁን የሉካንዳ ነጋዴው የጋሽ ቦረና ጡንቻ የታለ! የላቁ ሰው መውደድ የት አደረሰው! ጋሽ ላቁ አማርኛው የተንገዳገደ ነው፡፡ግን ሰው ሲወድደው ለብቻ ነው፡፡ቅን ነው ይሉታል፡፡
አዲስ አበባ ደወልኩ፤እዚያው የሰቀቀን ኩሬ ውስጥ ነበርኩ፡፡ጓደኛዬ ገረመው ‹‹ምን ተገኘ ዛሬ!››አለኝ፡፡
 ‹‹ናፍቆት ነው…ሆም ሲክነስ››
‹‹ተዐምር ነው፡፡››
እዚያው ቆሜ ብዙ ደቂቃዎች አወራን:: አስተማሪዎቻችንን፣ ጓደኞቻችንን፣ በዐይን ያፈቀርናቸውን ልጆች ሁሉ አሰብን፡፡ያ ሁሉ ግን ደስ ይላል፡፡ ቲቸር ወይንሼት አስተማሪዬ! ማርክ ስቀንስ ምን ሆነሃል! እያለች የምትወጥረኝ ትዝ ብሎኝ እንባ አይኔ ላይ ተንጠለጠለ፡፡
ድሮ አስር ሳንቲም ብርቅ ነበር፡፡ ግን ፍቅር የትናየት! እንደዛሬ እገሌ ዘሩ ማነው፣ ምንድነው የለም፡፡ የጓደኛ አባት መጥፎ ቦታ ካገኘህ ይዠልጥሃል፡፤ልጄ ለምን ተነካ! የሚል ወንድ የለም፡፡ ‹‹ደግ አደረገልህ!ምን ስታደርግ አገኘህ ይባላል::
መኪናዬን ያቆምኩት ጋሽ ላቆ ቡና ቤት ፊትለፊት ነበር፡፡ በተለምዶ “ጋሽ ላቆ” እየተባለ ይጠራ ነበር፡፡ አንገቴን መሪ ላይ ደፍቼ ሳላስበው እንባዬ ፈሰሰ፡፡
ሚስቴ ስትደውልልኝ ድምጼ  ጥሩ አልነበረም፡፡ “ምን ሆነሃል!” ብላ ነገሩን ስነግራት ሳቀች፡፡ ለስንቱ አልቅሰህ ትችላለህ›› ብላ አፅናናችኝ፡፡
ለሰው ልጅ ግን ከሰው በላይ ሀብት አለው!?
እትዬ ወርቄ በዚህ መሃል ገዝፋ መጣችብኝ፡፡ ትግሪኛ ተናጋሪ ስለሆነች አማርኛ እምብዛም ናት፡፡ አንዳንዴ እንዲያውም ረስታ በአማርኛ የጀመረችውን በትግርኛ ትቀጥላለች:: በኋላ ትዝ ሲላት ‹፣ዋይ! ረሳሁት አደል››ትልና ተመለሳለች፡፡
ጋሽ ላቆ ቡና ቤት የባንክ ጨረታ የወጣ ቀን ሁሉም ሰው በናፍቆትና በሃዘን ይከታተል ነበር፡፡ ስጋ ቤቱም ቡናቤቱም አላዋጣውም፡፡ ስለዚህ የባንክ ዕዳውን መክፈል ስላቃተው ጨረታ ወጣበት፡፡
ሰዐቱ ደረሰ፡፡ ጋሽ ፋንታ፣ጌታቸው፣ እትዬ ወርቄና ሌሎቹም ተጫረቱ፡፡ ጋሽ ላቆና ባለቤቱ እንባ አንቋቸዋል፡፡ ልጆቹም ውጭ ላይ አቀርቅረዋል፡፡
ጨረታው ተጀመረ፡፡
በኋላ ጨረታው አሸናፊ ሲታወቅ እትዬ ወርቄ ሆና ተገኘች፡፡ታዲያ ሕዝቡ በተሰበበበት እትዬ ወርቄ አንድ ነገር ልናገር አለች፡፡ ሁሉም ሰው በፈገግታ ያያታል፡፡ ጋሽ ላቆ ግን በሰቀቀን፡፡
‹‹ስሙ ››አለች፡፡
‹‹ዛሬ የመጣነው የላቆን ቡና ቤት ለመጫረት ነው፣ላቆ አልተሳካለትም››
ጋሽ ላቆ ስቅስቅ አለ ‹‹አታልቅስ ላቆ!ፈጣሪ ያውቃል፡፡››
አንገቱን ነቀነቀ፡፡ ካለቀ በኋላ ምን ያውቃል የሚል ይመስላል፡፡
‹‹አብረን በልተናል፣ አብረን ጠጥተናል:: ልጆቹ የልጆቻችን ጓደኞች ናቸው፡፡ ዛሬ እርሱ ተሸንፎ እኔ ርሱን ቤት አሸንፌያለሁ፡፡ ዕድል እንደዚህ ናት::››
ብዙ ሰዎች ቅሬታ ታየባቸው፡፡
‹‹የዛሬው ጨረታ አሸናፊ ላቆ ራሱ ነው፡፡››
ሰው ሁሉ ግር አለው፤እኔ ልጫረት የመጣሁት ለላቆ እንጂ የላቆን ቤት ወስጄ፣ የራሴ ላደርግ አይደለም፡፡ ወደፊት ካገኘ ይከፍለኛል፤ ካልሆነለትም ፈጣሪ ይከፍለኛል፡፡
እልልል አለች የጋሽ ላቆ ሚስት፡፡
የዘር ጉዳይ የታል! እትዬ ወርቄ ትግራይ፣ ጋሽ ላቆ ወላይታ፡፡
ትዝታዬ ከእንባ ጋር ፈሰሰ፡፡ ሰው የነበርነው ያኔ ነበር፡፡ ያኔ ዘርና ሃይማኖት ጭንቅላታችን ላይ ሳይወጣ፡፡ ሳላስበው ወደ ቀድሞው ዳምጤ ሆቴል መኪናዬን አከነፍኩ፡፡
ወይ ሃገሬ…ወይ ትዝታ!!


Read 2970 times