Saturday, 15 February 2020 11:36

ስለ “ነፃነት” እና “እኩልነት” እናውጋ (“መብት” ወይም “ሰብአዊ መብት”ስ?)

Written by  (ከአብዱራህማን አህመዲን፤ የቀድሞ የፓርላማ አባል)
Rate this item
(10 votes)

   “ሶቅራጥስ፣ ፕሌቶና አርስቶትልን የመሳሰሉ የተፈጥሮ ህግን መሰረት ያደረጉ ንድፈ ሃሳብ አቀንቃኞች በበኩላቸው፤ የሰብአዊ መብቶች መነሻ መሰረቶች ተፈጥሯዊ የሞራል፣ የሃይማኖት፣ ወግና ልማዶች ናቸው ብለው ያስባሉ፡፡ አርስቶትል “የተፈጥሮ ህግ” አባት የሚባለውም በዚህ ምክንያት ነው፡፡--”
           
             በዚህ ሳምንት በማቀርባት በዚች መጣጥፍ ትኩረት የማደርገው በሰብአዊ መብት እኩልነትና ነፃነት ዙሪያ ነው፡፡ ጽሑፌን የምጀምረው ስለ ጽንሰ ሃሳቡ ትርጉምና ምንነት የተወሰኑ ነጥቦችን በማቅረብ ይሆናል፡፡ “ነፃነት እና እኩልነት” የሰብአዊ ፍጡራን ቀዳሚ መብቶች ናቸው፡፡ ስለ “ነፃነት” እና ስለ “እኩልነት” ከመነጋገራችን በፊት ስለ “መብት” ወይም ስለ “ሰብአዊ መብት” ምንነት የጋራ ግንዛቤ መያዝ አስፈላጊ ነው፡፡ በመሆኑም በዚህ ርእስ ስር “መብት፣ ነፃነት እና እኩልነት” የተሰኙት ጽንሰ-ሃሳቦችን በተመለከተ በቅድሚያ በአጭር በአጭሩ ሃሳብ ለማቅረብ ጥረት ይደረጋል፡፡
መብት ምንድነው?
“መብት” የሚለው ጽንሰ ሃሳብ እጅግ ሰፊና ላቅ ያለ ደረጃ ያለው መሆኑን በመስኩ ጥናት ያደረጉ የመብት ተሟጋቾች ይናገራሉ:: እዚህ ላይ ልብ ሊባል የሚገባው መሰረታዊ ነገር “መብት” እና “ሰብአዊ መብት” የሚሉት አገላለፆች እየተቀያየሩ ሥራ ላይ ሲውሉ የሚስተዋል መሆኑ ነው፡፡ “መብት” የሚለው አጠቃቀም በአጠቃላይ ለተፈጥሮ “ሰው” እና በህግ የሰውነት ደረጃ የተሰጣቸው “ተቋማት” ያላቸውን መብት የሚያመለክት ነው፡፡ “ሰብአዊ መብት” የሚለው አጠቃቀም ግን ለተፈጥሮ ሰው ማለትም ለሰብአዊ ፍጡራን ብቻ የተሰጡ መብቶችን የሚያመለክት ነው፡፡
“መብት” በሚለው ጽንሰ ሃሳብ ዙሪያ ሁሉም ሰው የሚስማማበት፣ ወጥነት ያለው ትርጉም ማግኘት አስቸጋሪ ነው፡፡ አንዳንድ የህግ ምሁራን “መብት ማለት ሰዎች የሚኖራቸው፣ ማንም የማይነካባቸው ነገር ነው” ይላሉ፡፡ ሌሎች ደግሞ “መብት ማለት ሰዎች እንዲፈጽሙት የተፈቀደላቸው ድንጋጌ ነው” የሚል ትርጉም ይሰጡታል፡፡ ሌሎች ወገኖች በበኩላቸው፤ “መብት በመፈጠር የምንቀዳጀው፣ በህግ ጥበቃ የሚደረግለት ነገር ነው” በማለት ይተረጉሙታል:: በአጠቃላይ፤ ሰብአዊ መብት አንድ ሰው “ሰው በመሆኑ” የሚቀዳጀው፣ ከልደቱ እስከ ህልፈቱ የሚጎናጸፈው መብት ነው፡፡ ማንኛውም ሰው ይህንን መብት ለማግኘት በየትኛውም ስፍራ፣ ምንም ዓይነት መገለልም ሆነ መድሎ አይደረግበትም፡፡
በዓለም ላይ ያሉ መንግስታት ሰብአዊ መብትን የማክበር፣ የመጠበቅና የማሟላት ግዴታዎች እንዳሉባቸው ይናገራሉ፤የሰብአዊ መብት ተሟጋቾች፡፡ ሰብአዊ መብት የሚለው ጽንሰ ሃሳብ እንዲመነጭ ካደረጉት ምክንያቶች አንዱ፣ ዜጎችን ከመንግስታቸው ህገ ወጥ የመብት ረገጣ ለመጠበቅ ነው፡፡ ሰብአዊ መብት ከሌሎች መብቶች በሁለት ነገሮች እንደሚለይም ይነገራል፡፡ ይኸውም፤ አንደኛ፡- ሰዎች “ሰው” በመሆናቸው የሚቀዳጁት እንጂ ማንም የሚሰጣቸው ወይም የሚገዙት አለመሆኑ፣ ሁሉም ሰው ዳር ድንበር ሳይወስነው፣ በየትኛውም ስፍራ፣ እኩል የሚቀዳጀው መሆኑ ሲሆን፤ ሁለተኛ፡- እነዚህን መብቶች የማስከበር ኃላፊነት የተሰጠው ለግለሰቦች ሳይሆን በየትኛውም ሀገር ለሚገኝ መንግስትና ባለስልጣናት መሆኑ ነው፡፡
ሰብአዊ መብቶች በህግ ጥበቃ ሊደረግላቸው ይገባል፡፡ ዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብት ድንጋጌ እ.ኤ.አ በ1948 የወጣውና በዓለም ላይ የሚገኙ ሀገሮች መንግስታት ተቀብለው ተግባራዊ እንዲያደርጉት የተደረገው በዚሁ ምክንያት ነው፡፡ ከሰብአዊ መብት አኳያ “መንግስት እና ግለሰብ” እንዲሁም “ግለሰብ እና ግለሰብ” የጠበቀ ግንኙነት አላቸው፡፡ በዚህም መሰረት፤ መንግስት ሰብአዊ መብትን ማክበር ብቻ ሳይሆን ዜጎች እርስ በርሳቸው የመብት መድፈቅ እንዳይፈጽሙ ህግና ስርዓትን የማስከበር ኃላፊነትም አለበት፡፡
መብት ህጋዊ፣ ማህበራዊ ወይም የነፃነት ስነ ምግባራዊ መርሆዎችን ያጠቃልላል፡፡ መብት ለሰዎች በህግ የተፈቀዱና የተከለከሉ መሰረታዊ ድንጋጌዎችን ያመለክታል፡፡ መብት ከህግ፣ ከስነ ምግባር፣ ከፍትህና ከሞራል ንድፈ-ሃሳቦች ጋር የተያያዘ ነው፡፡ መብት መሰረታዊ የስልጣኔ ምልክት ተደርጎም ይወሰዳል፡፡ የአንድ ማህበረሰብ ባህል የመሰረት ድንጋይ በመሆኑ፣ የማህበረሰብ የግጭት ታሪክ፣ በመብት እድገት ታሪክ ውስጥ ይገኛል፡፡ ከዚሁ ጋር በተያያዘ መልኩ፣ የሣንፎርድ የፍልስፍና ኢንሳይክሎፔዲያ፤ “መብት የአንድን መንግስት መዋቅራዊ ምንነት፣ የህጉን ይዘትና የሞራል ቅርጽ ያሳያል” ይላል፡፡
የሰብአዊ መብት ዘርፎች
“ሰብአዊ መብት” ለሚለው ጽንሰ-ሃሳብ የተለያዩ ሰዎች የተለያየ ትርጉም መስጠት ብቻ ሳይሆን በልዩ ልዩ ዘርፎች ሲከፋፍሉትም ይስተዋላል፡፡ የተለያዩ ምሁራንም ከየራሳቸው ሙያ አኳያ የተለያዩ ትርጓሜዎችን ሲሰጡ ይታያሉ፡፡ ለምሣሌ፡- አንዳንዶች “ሃሳብን የመግለጽ፣ በህይወት የመኖር፣ የመምረጥ፣ ሰላማዊ ሰልፍ የማድረግ፣ በህግ ፊት እኩል የመሆን፣ ጥገኝነት የማግኘት፣ የመስራት፣ የጦር መሣሪያ የመያዝ፣… መብት” እያሉ ይዘረዝሯቸዋል፡፡ ሌሎች ደግሞ፤ “የህፃናት መብት፣ የእንስሳት መብት፣ የሰራተኞች መብት፣ የሴቶች መብት…” በማለት ይከፋፍሏቸዋል:: የግለሰብ መብት እና የቡድን መብት የሚል አከፋፈልም አለ፡፡ አንዳንዶች “የሲቪል፣ የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚ፣ የማህበራዊና የባህል መብቶች” ብለው ሲከፍሏቸው፤ ሌሎች ወገኖች ደግሞ “አንደኛ፣ ሁለተኛና ሦስተኛ ትውልድ ሰብአዊ መብቶች” በማለት ይከፋፍሏቸዋል፡፡
አንዳንድ ሊቃውንት እንደሚያስተምሩት፤ የሰብአዊ መብት ድንጋጌዎች በሦስት ትውልዶች (Generations) ቅብብሎሽ እየተሻሻሉ እስከዚህ ዘመን እንደደረሱ ይነገራል:: የመጀመሪያው ትውልድ የሰብአዊ መብት ድንጋጌዎች የሚባሉት አንዳንድ ጊዜ “ሰማያዊ መብቶች” (Blue Rights) የሚል ስያሜ ሲሰጣቸው ይስተዋላል፡፡ እነዚህም መብቶች፤ ነጻነትንና የፖለቲካ ተሳትፎን የሚያመለክቱ እንደ “በህይወት የመኖር መብት፣ በህግ ፊት እኩል የመሆን መብት፣ የመናገር ነፃነት፣ ፍትህ የማግኘት መብት፣ የሃይማኖት ነፃነትና የመምረጥ መብት” የመሳሰሉትን ያጠቃልላል፡፡
የሁለተኛው ትውልድ የሰብአዊ መብት ድንጋጌዎች በዋናነት እኩልነትን ብቻ ሳይሆን ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊና ባህላዊ ሁኔታዎችን የሚመለከቱ መብቶች ናቸው፡፡ ከነዚህ በተጨማሪ ሥራ የማግኘትና ምቹ የስራ ቦታ፣ መጠለያ ምግብና ጤና… የመሳሰሉትም መብቶች በዚሁ ትውልድ ውስጥ የሚካተቱ ናቸው፡፡ ሦስተኛው ትውልድ የሰብአዊ መብት ድንጋጌዎች የሚያካትታቸው ጉዳዮች በርካታ ናቸው፡፡ አንዳንዶች “አረንጓዴ መብቶች” የሚል ስያሜ ሰጥተዋቸዋል፡፡
ከፍልስፍና እይታ አኳያ የሰብአዊ መብት ድንጋጌዎች የተገኙት ከተፈጥሮ ህግ ነው:: የተፈጥሮ ህጎች የመነጩት ደግሞ ከተለያዩ የፍልስፍናና የሃይማኖት መሰረቶች ነው፡፡ እንደ ዴቪድ ሁም ያሉ አንዳንድ የንድፈ ሃሳብ ሊቃውንት ደግሞ የሰብአዊ መብት ድንጋጌዎች የመነጩት እያደገ ከመጣ የሰዎች የሞራል ባህሪ ነው ይላሉ፡፡ “ተፈጥሯዊ መብቶች” የሚባሉት ሰው ሰራሽ ያልሆኑ፣ ሰዎች በተፈጥሮ የተቀዳጇቸው መብቶች ናቸው፡፡ እነዚህ መብቶች ሁሉም ሰብአዊ ፍጡራን ሊኖራቸው የሚገቡ፣ አብረውን የሚወለዱ፣ ማንም ሊቀማን የማይችላቸው መብቶች ናቸው፡፡ ለምሳሌ፡- በህይወት የመኖር መብት ተፈጥሯዊ መብት ነው:: ይህ መብት አንዳንድ ጊዜ “የሞራል መብት” ወይም “ሰዎች ሊያጡት የማይገባ መብት” በመባል ይታወቃል፡፡ ሶቅራጥስ፣ ፕሌቶና አርስቶትልን የመሳሰሉ የተፈጥሮ ህግን መሰረት ያደረጉ ንድፈ ሃሳብ አቀንቃኞች በበኩላቸው፤ የሰብአዊ መብቶች መነሻ መሰረቶች ተፈጥሯዊ የሞራል፣ የሃይማኖት፣ ወግና ልማዶች ናቸው ብለው ያስባሉ፡፡ አርስቶትል “የተፈጥሮ ህግ” አባት የሚባለውም በዚህ ምክንያት ነው፡፡
በሚቀጥለው ሳምንት ስለ ሰብአዊ መብት ታሪካዊ አጀማመር፣ ስለ መብትና ግዴታ፣ ስለ መብትና ትግል እንዲሁም መብት በዴሞክራሲ ስርዓት ውስጥ እንዲኖር ለምን እንዳስፈለገ ለማቅረብ ጥረት ይደረጋል፡፡
 ጸሐፊውን Email: This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it. ማግኘት ይቻላል፡፡

Read 4872 times