Friday, 14 February 2020 09:28

‹‹ከመንግሥት ይልቅ ጋዜጣ ቢኖር እመርጣለሁ››

Written by  ተፈሪ መኮንን
Rate this item
(1 Vote)

     የአድማስ ትውስታ

                      ‹‹ከመንግሥት ይልቅ ጋዜጣ ቢኖር እመርጣለሁ››
                              
             አንዳንድ ሀሳቦች ‹‹የብብትና የቆጥ›› ችግር አለባቸው፡፡ የቆጡን ልናወርድ ስንል የብብቱን ላለመጣል መጠንቀቅ ይገባናል፡፡ ‹‹የሁለት ፊት እውቅና የሚጠይቁ ጉዳዮች አሉ››፡፡ ለማለት ነው፡፡ እንዲህ ባሉ ነገሮች ውስጥ አንደኛውን ገጽ በአዎንታ ስንይዘው ሌላኛው አሉታዊ ይሆናል:: ይህን የምለው ተቸግሬ እንጂ መጠማዘዝ ፈልጌ አይደለም፡፡ እንዲህ ሀሳቤን ያጠማዘዘው ጉዳይ ‹‹መብቶች ሰው ከመሆን ይመነጫሉ›› የሚሉትና የምለው የዘወትር ፀሎት ያደረግነው ሀሳብ ነው፡፡
እርግጥ ነው ‹‹በማንም ሊጣሱ የማይችሉ፣ ሰው በመሆን የያዝናቸው መብቶች አሉ›› ግን ‹‹የማይጣሱ መብቶች›› መባላቸው ብቻ እኒህን መብቶች የማይጣሱ አያደርጋቸውም፡፡ በሌላ ረገድ፤ በተፈጥሮ የያዝናቸው መሆኑ ብቻ እንደ ንብረት እንድናውቃቸውና እንድንጠብቃቸው ያደርገናል ማለት አይሆንም፡፡ መብትና ነፃነት ያሉና የነበሩ ቢሆኑም ሀብት ያደረግናቸው በእውቀት ነው፡፡ ግኝት ወይም Discovery ናቸው፡፡ እንደ መብት ለመጠየቅና ለማስከበር፤ እውቀት እንዲሁም ብርታት ይጠይቁናል:: “ሰው በመሆን ያገኘናቸው” ሲባል ይህን እውነት ሊያስረሳን አይገባም፡፡ መብትና ነፃነት፤ በእውቀት በጥረትና በትግል የምንጐናፀፋቸው ሰብአዊ  ሀብቶች ናቸው፡፡
‹‹በችሮታ የሚሰጡን አይደሉም›› ሲባሉም ይህን የሰውን ልጅ ተፈጥሮ አውቆ እንዲከበር የሚጣጣር መንግስትን ለመፍጠር መድከም አያስፈልገንም ማለት አይደለም፡፡ እነኝህ ሰው በመሆን ብቻ ንብረታችን የሚሆኑ ‹‹ሰብአዊ አለባዎች›› ከተፈጥሮ እንዴት እንደመነጩ ማወቅ፣ አውቆም ማህበራዊ ስርዓቱን ለመቀየር መታገል አስፈላጊ ነው፡፡ እንደዚሁ ዕውቀቱን ወይም እውነቱን ዘወትር በንቃት ለመጠበቅ የሚታትር ዜጋ ያስፈልጋል፡፡ መብትና ነፃነት መቼም ቢሆን የማይዘናጉና የንቁ ዜጐች ሀብት ናቸው፡፡
ወደ ኋላ ዘወር እንበል፡፡ እንዲህ ወደ ኋላ ዘወር እንበልና ከእነዚህ መብትና ነፃነቶች አንዱን እንምረጥ፡፡ የፕሬስ  ነፃነት፡፡
ለፕሬስ ነፃነት የተደረገውን ጥረት፣ በታሪክ መዝገብ ስንመለከት፣ የሰውን ተፈጥሮ በመመርመር ሰብዓዊ አላባዎችን ለይተው፣ እውነቱን ያገኙ ሰዎች፣ ሀሳቡን በተግባር ለማዋል የተጣጣሩ ትጉሃን መሪዎች እና ንቁ ዜጎች የፈፀሙትን ገድል እናስተውላለን፡፡
አሁን፤ ‹‹ሀሳብን በነፃነት የመግለፅ መብት››  እንዲከበር ጥረት ካደረጉ ሰዎች መካከል ጆን ፒተር ዚንገር አንዱ ነው። የእሱንም፣ እንደ አብነት የሚጠቀስ አንድ ድርጊት መጥቀስ እፈልጋለሁ፡፡ ሀሳብን ከመግለጽ ነፃነት ጋር ተያይዞ፣ እንደ ድንቅ የሚጠቀስ አንድ ታሪካዊ ትግል ያደረገው ጀርመናዊው ጆን ፒተር ዜንገር ነበር፡፡ ዜንገር ይህን ድንቅ የተባለ ታሪክ በፈፀመበት ጊዜ አሜሪካ በእንግሊዝ የቅኝ አገዛዝ ስር ነበረች፡፡ በዚህ ጊዜ የአሜሪካ ጋዜጦች ላይ ይወጡ የነበሩት ጽሑፎች ከእንግሊዝ ጋዜጦች እየተቀነጨቡ የሚወሰዱ ሀሳቦች ብቻ ናቸው:: እንጂ፣ ነፃ የዘገባ ሥራ ማቅረቡ ችግር ነበር፡፡ ዜንገር በ1735 እ.ኤ.አ ዓ.ም አንድ የአፈና ገመድ እንዲበጠስ አደረገ፡፡ ለነፃ የዘገባ ሥራ በር ከፈተ::
ይኸው ጀርመናዊ አሳታሚ፣ ‹‹የእንግሊዝ ንጉሳዊ መስተዳድርን ስም የሚያጎድፍ ጽሑፍ አትመሃል›› በሚል በስም ማጥፋት ወንጀል ተከሰሰ፡፡ የዜንገር ደጋፊዎች (ንቁ ዜጎች) አንድ ጠበቃ ገዝተው አቆሙለት፡፡ ጠበቃው እንድሪዊ ሀሚልተን ይግባኝ ጠየቀ፡፡ ሀሚልተን፣ በወቅቱ ለስም ማጥፋት ወንጀል ከተሰጠው ትርጉም ለየት ያለ ፍቺ ይዞ መጣ፡፡ በዚሁ ሀሳብ ላይ ተመስርቶ አቤት አለ፡፡ የዳኞቹ ትኩረት፤ ዜንገር የገዢዎቹን ቁጣ ሊቀሰቅስ የሚችል ጽሑፍ እንዲታተም ማድረጉን ማረጋገጥ ብቻ ነበር፡፡ የሀሚልተን መከራከሪያ ግን፣ ቁጣን የሚቀሰቅስ ወይም ሊያስቀይም የሚችል ነገር መጻፉ ሳይሆን፤ የተፃፈው ነገር እውነት መሆን አለመሆኑ ነበር፡፡  
በወቅቱ በነበረው ትርጓሜ፤ አንድ ጽሑፍ በስም ማጥፋት የሚያስቀጣው፤ እውነትም ሆነ ሀሰት፤ የቀረበው ሀሳብ ንጉሳዊ መስተዳድሩን ሊያስቀይም የሚችል ይዘት ማቅረቡን በማረጋገጥ ነው፡፡ በጽሑፉ የቀረበው ነገር፣ እውነት መሆኑ ነፃ አያወጣም ማለት ነው። ሀሚልተን ግን፣ ‹‹እውነት ከሆነ እንደ ስም ማጥፋት ተቆጥሮ ሊያስቀጣ አይገባም›› የሚል ትርጉም ይዞ ቀረበ፡። ዳኞቹ ተቀበሉት፡፡ ስለዚህ፣ ‹‹በጽሑፉ የቀረበው ነገር እውነት በመሆኑ፣ ጆን ፒተር ዜንገር በስም ማጥፋት ሊከሰስ አይገባም›› ብለው ብይን ሰጡ፡፡
በአሜሪካ የጋዜጠኝነት ሥራ ታሪክ እንደ ድንቅና ወሳኝ ነጥብ የሚቆጠረው ይኸው ነው:: ይህም ጋዜጠኛው፤ ንቁ ዜጎችና ነፃ ህሊናቸውን ተከትለው ለመስራት የደፈሩ ዳኞች ያስገኙት ውጤት ነው፡፡ እናም ‹‹… እውነትን የተመረኮዘ ነገር በስም ማጥፋት ሊያስከስስ አይችልም›› የሚል መርህ እንዲፀና ተደረገ፡፡ በጆን ዜንገር ድፍረት፣ የፕሬስ ተቋማት በፖለቲካዊ ጉዳዮች ላይ ቆፍጣና አስተያየት ለመስጠት ተደፋፈሩ፡፡ የፕሬስ ነፃነት በዚህ መሰል ትግል እየዳበረ ነው፣ ከዛሬ የደረሰው።
በዚህ በእኛ ሀገር ለፕሬስ ነፃነት መጠናከር አብነት የሚደረጉ ድርጊቶች ካሉ፣ ገና በወጉ የምናውቃቸው አይመስለኝም፡፡ ይሁንና፣ አጭር በሆነው የዴሞክራሲያዊ ሂደት የኢትዮጵያ ፕሬስ (በተለይ የግሉ) ጉልህ ድርሻ ሊኖረው እንደሚችል እገምታለሁ፡፡
እኔ እንደምገምተው፣ የኢትዮጵያ ፕሬስ ከነእንከኑ ትልቅ ታሪክ ሰርቷል፡፡ አሁን  አሁን ሁነኛ ጥረት እያደረጉ ከሚታዩት ሲቪክ ተቋማትና ጠንካራ ግለሰቦች ሁሉ ቀድሞ ነፃነት ስጋ ለብሶ የታየው በግል ፕሬስ ተቋም ይመስለኛል፡፡ ታሪካዊና ወቅታዊ የሥነ ልቦና አጥርን ነቅለው ለመሄድ የሞከሩት እነሱ ናቸው:: ብዙዎች ፍርሃት ባጀበው ሁኔታ የሚያነቡትን እነርሱ ጽፈዋል፡፡ የሚጽፉት ነገር ትክክል ሆነ አልሆነ በዚህ ሚዛን ለውጥ አያመጣም:: ሀሳባቸው ዘለፋና እልህ እንዲሁም የልምድ እጥረት ያጠላበት ይሆናል፡፡ ግን ከፍርሃት አጥር ቀድመው የወጡት ያው የግል ፕሬስ ተቋማት ናቸው፡፡
ስለዚህ፤ በኢትዮጵያ የዴሞክራሲያዊ ስርዓት ሂደት ታሪክ ትልቅ ድርሻ እንደሚይዙ አልጠራጠርም፡፡ እንዲህ ያለ ድርሻ ከሚጠበቅባቸው ዜጎች፣ ከዳኞች፣ ከማህበራዊ ሳይንስ ምሁራን፣ አንዳንዴም ከተቀናቃኝ የፖለቲካ ድርጅቶች በላይ ለነፃነት መረጋገጥ ብዙ የተንገላቱ ናቸው ማለት ይቻላል፡፡ ይህንም እንተወው፡፡ ቢያንስ፣ ለንባብ ባህል መዳበር ሊንቁት የማይቻል ትልቅ ድርሻ ስላደረጉ፤ ማህበራዊ ልማቱን አግዘዋል፡፡ ከፋም ለማም ከየትኛውም የህትመት ውጤቶች ሁሉ ለመጀመሪያ ጊዜ ሰፊ አድማጭ ለመያዝ የበቁ ናቸው፡፡ ዜጎች በሆነ መንገድ ተሳትፎ እንዲያደርጉ በር የከፈቱ ናቸው፡፡ ብስለት የጎደለው ጥረት ነው ሊሉት ይችላሉ፡፡ ቢሆንም፣ ፍትህን ለማስፈንና መልካም አስተዳደርን ለመፍጠር ድርሻቸው ከፍተኛ ነው፡፡ እስኪ ጥቅል ወሬ እናውራ፡፡
ፕሬስ፤ ሀሳብን በነፃ ከመግለጽ መብት ጋር የተያያዘ ተቋም ነው፡፡ ሀሳብን የመግለጽ መብት የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት መጀመሪያና መጨረሻ ነው፡፡ ሀሳብን በነፃ የመግለጽ መብት ሲጣስ የማይጣስ መብት የለም፡፡ የማይነካ የማህበረሰብ ክፍል አይኖርም፡፡ ውጤቱም አምባገነንነት ነው፡፡ ፍላጎቶቻችንን ለማሳወቅ፣ ፍላጎቶቻችንን የተከተለ ሁነኛ ስርዓት ለመፍጠር፣ ይህም ስርዓት እንዳይታጎል ለመከላከል፣ ሲታጎልም ቁጣን ለመግለጽ፣ የሚሻሻልበትንም መንገድ ለማመላከት፣ አፈፃፀሙን ለመከታተል፣ የምንችለው በፕሬስ ተቋማት ነው ይበልጡን:: እንዲያም ሲል፣ ‹‹በማህበራዊ ውል›› (Social contract) የፀናው፤ መንግስት የሚሉት ተቋም፣ እንዲፈርስና እንዲቀየር ለማድረግ ፕሬስ አስፈላጊ ነው፡፡
እናም፤ ከመንግሥት ምስረታ እስከ ክንውንና ውጤት ድረስ የፕሬስ ተቋማት ድርሻ ብዙ ነው:: መንግሥት ወደ አገዛዝ የሚሄደው የዕለት ክንውኑን የምንከታተልበት መንገድ ሲጠፋ ነው፡፡ የእኛን እውነተኛ ፍላጎት ተከትለውና አክብረው እንዲመሩን የምንመርጣቸው ሰዎች፣ ገዢዎቻችን መሆን የሚጀምሩት የሚሰሩትን ማወቅ ባልቻልን ጊዜ ነው፡፡ እሚሰሩትን እንዳናውቅ ሲፈልጉ ገዢዎች ለመሆንና ለብዝበዛ እየተሰናዱ ነው፡፡ ስለዚህ፣ ከሁሉ አስቀድመው የፕሬስ ነፃነትን ወይም መረጃን ይነፍጉናል፡፡ እንዲያ ፍላጎት ከሌለ ግን መብትና ነፃነትን ጥሶ ለመሄድ የሚሻ ቡድንና ግለሰብ እንዳይቀናጣ የሚከላከለው ዋና መንግስት ነው:: የእስካሁን አካሄዴን ስትመለከቱ፣ ነፃነትንና መብትን ሊነፍገን የሚችለው መንግስት ነው:: ልክ ነው፡፡ ግን ቀዳዳ እንዳይፈጠር ወይም የቆጡን ስናወርድ የብብቱን እንዳንጥል እሰጋለሁ፡፡
መንግሥት ነፃነትን ሊነፍግ የሚችል ተቋም የሚሆነው አምባገነን ባህርይ የያዘ ከሆነ ብቻ ነው፡፡ ካልሆነ ግን የነፃነት ጠባቂያችን እርሱ ነው፡፡ እርሱ ሳይኖር ነፃነት አደጋ ላይ ትወድቃለች፡፡ ‹‹ከፍላጎትህ እና ከጥቅምህ ፍላጎቴ እና ጥቅሜ ይበልጣል›› የሚል አሊያም እሚመካውን ተመክቶ ‹‹እኔ ልግነን›› ባይ ሲመጣ ጋሻችን የሚሆነው፤ ያው መንግስት የምንለው ድርጅት ነው፡፡ የምናጥላላው አምባገነን መንግስትን እንጂ መንግስትን አይደለም፡፡ አምባገነን እንዳይሆንም፤ በፈቃዳችን አምሳል የሚቀረጽ መንግስት መፍጠር ይገባናል፡፡ ይህን ለማድረግ ታዲያ፤ ፍላጎታችን ምን እንደሆነ አስቀድመን መግለጽ አለብን፡፡ በፍላጎታችን አምሳል ካቋቋምን በኋላም፤ የሚሰራውን ለማወቅ መረጃ የማግኘት መብት እንዲከበርልን እናደርጋለን፡፡ ባገኘነው መረጃ ከመንገድ ወጥቶ መሄዱን ስናውቅ እናወግዛለን፡፡ ለፍርድ እናቀርባለን፤ አጥፊው ተገቢውን ቅጣት ማግኘቱን እንከታተላለን፡፡
ተመልከቱ፤ ፈቃዳችንን ለመግለጽ ወይም ሀሳብን በነፃ የመግለጽ መብት እንዲከበር - ነፃ ጋዜጣ፡፡ መንግስት እንደ ፈቃዳችን መሄዱን ለመከታተል - ጋዜጣ፡፡ ከመንገድ የወጣውን የሚቀጣው ወገን (ፍ/ቤት) ያለ ጭንቀት በተገቢው መንገድ መስራቱን ለማወቅ - ጋዜጣ:: በደልና ሕገወጥ ድርጊት ከተፈፀመ፣ ያንን ለመቃወም - ጋዜጣ፡፡ በደል ደርሶብን እንደሆነ ያነ ለመግለጽ - ጋዜጣ፡፡ ነገሮች ሁሉ በፈለግነው አቅጣጫ መሄዳቸውን ለማረጋገጥ - ጋዜጣ:: ካልሆነም ስልጣን የያዘው ቡድን እንዲነሳልን ለመመካከርና ለመወሰን - ጋዜጣ፡፡ እናም፤ ጋዜጣ ሲጠፋ፣ ሁሉንም እናጣለን፡፡ አስተውሉ! ጋዜጣ ብቻ አይደለም፤ ከተጽዕኖ የራቀ ነፃ ጋዜጣ፡፡ ስለዚህ፤ በፕሬስ ነፃነት ላይ የሚፈፀም በደል፣ የጋዜጠኞች ችግር ብቻ ተደርጎ መታየት የለበትም፡፡ የጠቅላላው ህብረተሰብ ችግር ነው፡፡
ለዚህ ይመስለኛል፣ ‹‹መንግስት ኖሮ ጋዜጣ ባይኖር ይሻልሃል፤ ወይስ ጋዜጣ ኖሮ መንግስት ባይኖር ትመርጣለህ?›› ብትሉኝ ምንም ሳላመነታ፤ ጋዜጣ ኖሮ መንግስት ባይኖር ይሻለኛል እላችኋለሁ›› ሲባል የሰማነው፡፡ ለምን ቢባል፣ ጋዜጣ የሌለበት የመንግስት አስተዳደር አምባገነን መሆኑ አይቀርም፡፡ ‹‹ነፃነቴን ወይም ሞቴን ስጡኝ›› እንደ ማለት ነው፡፡
(አዲስ አድማስ፤ የካቲት 24,1993)           


Read 2084 times