Saturday, 08 February 2020 16:21

የልጆች ጥግ

Written by 
Rate this item
(2 votes)

 
           ውድ ልጆች፡- መኝታ ክፍል የግል ሥፍራ መሆኑን ታውቃላችሁ አይደል!? ሰው መኝታ ክፍል ውስጥ ዘው ብሎ አይገባም፡፡ በመኝታ ክፍላችሁ ውስጥ የራሳችሁን ነገሮች ታስቀምጣላችሁ፡፡ አንዳንድ ነገሮቻችሁን ሰዎች እንዲያዩባችሁ አትፈልጉ ይሆናል፡፡ ለምሳሌ የዕለት ማስታወሻ ማስፈሪያችሁን (ዲያሪያችሁን) ማንም እንዲነካባችሁ ላትፈልጉ ትችላላችሁ:: ትክክል ናችሁ፡፡ እናንተም የሌሎችን የግል ንብረት ያለ ፈቃድ መንካት የለባችሁም፡፡
የቤተሰብ አባላትን የመኝታ ክፍሎች አክብሩ፡፡ በሌሉበት መሳቢያቸውን ወይም ኮመዲናቸውን ከፍታችሁ መመልከት ወይም መበርበር የለባችሁም፡፡ ቦርሳቸውን ወይም ሞባይላቸውን መክፈት ወይም መውሰድ ትክክል አይደለም፡፡ የሰው ዕቃ የወንድም ይሁን የአባት ወይም የእናት ሳታስፈቅዱ መውሰድ የለባችሁም፡፡
የመኝታ ክፍሉ በሩ ዝግ ከሆነ፣ ከመግባታችሁ በፊት ማንኳኳት አለባችሁ፡፡ ከዚያም ‹‹እገሌ ነኝ፤ መግባት እችላለሁ?›› ብላችሁ ጠይቁ፡፡ “መግባት ትችላለህ” ወይም “ትችያለሽ” እስክትባሉ ድረስ በትዕግስት ጠብቁ፡፡ መታጠቢያ ክፍል ከሆነ ደግሞ በሩን ከመክፈታችሁ በፊት ባዶ መሆኑን ወይም ሰው አለመኖሩን አረጋግጡ፡፡
ውድ ልጆች፡- ሁሌም አባትና እናታችሁን፣ ታላላቅ ወንድምና እህቶቻችሁን ማክበርና የሚነግሯችሁን መስማት አለባችሁ፡፡ መምህራኖቻችሁንም አክብሩ፡፡ በመምህራን መሳቅና ማሾፍ ተገቢ አይደለም፡፡ ታናናሾቻችሁን ደግሞ በምትችሉት ሁሉ እርዷቸው፡፡  
እደጉ! እደጉ! እደጉ!

Read 1533 times