Saturday, 30 June 2012 11:57

ፍቅር ሰርክነቱን

Written by  ኪሩቤል ሳሙኤል
Rate this item
(1 Vote)

የህሊና ቡታ፤ በሻቃ ማንነት ይሰጣል፡፡ ለሰብእ የማዘን እንግልት፣ ፍቅር ሲያስነጥስ አይነት የትንታ እንጉርጉሮ አለው…፡፡

በሃሳብ ማሳ ላይ መሽቀዳደም ከድካም ክሳት እንጂ ካሸናፊነት ህብር የለውም… ጉዞው የዘላለም ፉጨት ነው፤ …ልክ ከሰማይ ላይ እንደሚበር አይነት አሞራ ከክንፉ ጫፍ እንዳለ እርግብግቢት… ልክ መነሻው እንደማይታወቅ የሰው ልጅ እንባ… ልክ መች እንደዛመን እንደማንረዳው የፍቅር ግርፊያ… ይኸው ነው፤ በሃሳብ ማሳ ላይ መሽቀዳደም ከድካም ክሳት እንደ ካሸናፊነት ህብር የለውም፡፡

ለዛም ይመስለኛል ሰለሞን በፍቅር ጦር ሜዳ ላይ ልቡ እንክት ሲል… ሲደነግጥ… ፈርቶ ሲናጥ የድካሙ ዋጋው፣ የመውደቅ እምታው ሲሰማው… ሲርር እያለ የሚሰማው የህሊናው ድምፀት እስካሁን ከውበት ገበታ ነጥሎት ባየው ነገር ሁሉ ብሽቅ የሚለው… ለዛ ነው ጨረቃ ሙሉ ልብሷን ለብሳ ስትመጣበት እሷን ላለማየት ጉሮኖ የሚፈልገው… ለዛ ነው ከፀሀይ መግቢያ ከደመና ክፍልፋይ የሰማይ ላይ እርሻ፣ ምኞቱን ላለመዝራት… ፀሀይ በመጥለቂያዋ ሰዓት እሱ አንድ ስርጉድ ፈለጐ መጥለቅ የሚያሻው፡፡

ከሁሉም በላይ ግን ጥልቀት ያለው ትካዜ ንፋስ ስሪት ስለሆነ… ሰለሞን ከንፋስ ውስጥ ይደበቅና ቀለሙን ካየር ላይ ይረጫል… አየሩም ቀለሙን ይዞ ነጉዶ… ነጉዶ… ቀለም… ከወረቀት ላይ ነፍስ ይዘራል፡፡

ሰለሞን የሚያስበው ከድታው ስለመነነች የአንዲት ግዙፍ የሴት ነፍስ ነበር፡፡ ይህች ሴት በፊት ጉሜው ነበረች፤ ዛሬ ግልቱ አርጋው ከስልቸታው ከትካዜው አቅም ጐባባ አርገዋለች፡፡ …ይህች ሴት በፊት የሰውነቱ ላይ ወዛዊ መአዛው ነበረች… ዛሬ ነፍሱ ላይ ቆንጥር ሆና፣ ለዓይነ ውሃው ከርታታ ድካም ሆነዋለች፤ ስለዚህ ያለውን አቅም ተጠቅሞ ግፏን ሊያሳጥር ከንፋስ ውስጥ ይደበቅና ቀለሙን ካየር ላይ ይረጫል…

ከወረቀት የሚያርፉትን የቃላት ንድፎች ልም በሆኑ አይኖቹ እየተረጐማቸው ይኸው የመጨረሻው የፅሁፉ ምዕራፍ ላይ ደርሷል፡፡ እኔም እኩል ታሪኩን እንድትደመድሙ አደርጋችኋለሁ፡፡ እኔን ላስተዋውቃችሁ… እኔ የፅሁፉ ዛር ነኝ፣ ለፀሃፊው ምኞት ስል የተገነባሁ የነፍሱ መንኮራኩር…፡፡

***

ፀሀፊው የነፍሱን ግንብ ተደግፎ ማሰቡን ተያያዘው፡ ፀደንያን ሊያስወጣት ከምሰጣ ተማገደ፡፡ ፍቅሩን ከአእምሮው ሊገድብ፣ ሃያሉን የፀጥታ ጉዞ ‘ሀ’ ብሎ ጀመረ፡ አዲሷ የፀደንያ ተወካይ የጠቢቡ ሰለሞንን ሱላማጢት እንስትን አስደግፎ… የሳሮን ፅጌረዳነቷን ዘርፎ ስሟን ሳሮን አለው፡፡ ሳሮንን ሳላት… ምናባዊ ውበቷ ድንገት ከተፍ አለበት… በፍጥነት መጣችበት… (አመጣጧ ስለፈጠረበትስ ድንጋጤ አላውራ…)

የሳሮን አይኖች በኢየሩሳሌም ውስጥ ከኢትዮጵያ ገዳም አጠገብ እንዳሉ የውሃ ኩሬዎች ናቸው… አቤት ሲያስደነግጡ፡፡ ጥርሶቿ የፀሀይ ብርሃን ብትናት በምሉእ እንደፈሰሰባቸው የጉም ፈሊጣዊ ጥረቶች ናቸው… አቤት ሲያስደነግጡ፡፡ የአገጯ ውርደት እንደዋሻ ሚካኤል ፍልፍል ቤተመቅደስ የሂደቱ ጥልቀት ነገን የሚያስረሳ ነው፡ጉሮሮዋ የወፍ ንዴት ይመስላል…፡፡ ፀሃፊው እየደነገጠ ሳሮንን ይቀርፃታል… ይፈጥራታል፡፡ አንገቷ ድንገት ታየው…  ቅርፁ ከህሊና ለመፋቅ የዘላለም ጥረትን ይጋብዛል፡ ደረቷ ያንቀሸርራል… ጡቶቿ የሁለንታን ቅርፅ ይዘው የአርማጌዴዎንን መምጣት እያስታወሱ በስስት ያሳዝናሉ፡ የወገቦቿ ቅርንጫፎች የሆኑት እግሮቿ ለፀሀፊውም ለኔም ያልገቡን አላማ አላቸው… ሳሮን ውጫዊ ቅርፊቷ አለቀ፤ ውስጧ ያለችው ነፍስ… ግዙፏ ነፍስ የፀደንያ ናት… ልትፋቅ በምናብ ቀጠሮ የታጠረችው ጨካኟ ነፍስ… ከሀዲ ውልታ፡፡

ሰለሞን ሳሮን አሳዘነችው፡፡ ላይቀጣት ያቅማማ ጀመር፡ ምክንያት ሊፈጥር ማጠ… የስሟ መነሻ ለምን እንደኔ ሆነ?... የ’ሰ’ ዝርያ… አይኖቿ ለምን እንደኔ ፅድቅ ሆኑ? ጉንጮቿ ለምን ቀድሞ እንደተወረወረ የዝናብ እንክብል ሆኑ?... ንፁህና የተዳፈነ ፀጥታ፡፡ ለምን እንድራራላት ሆና ተፈጠረች?

ከጠቀሱ ሰማይ ላይ ሁለቱም አርምመው ይተያያሉ፤ የህይወት እስትንፋስ እፍ አለባት… ፀደንያን አስታወሳት… ፀደንያን እንዳስታወሳት ሳሮን ነፍስ ዘራች፡፡ የአይኖቿ ሽፋሽፍቶች ተጋጥመው ተላቀቁ… ውበቱ ሆነችለት… በሸቀ፡፡ ያይኖቿ ሽፋሽፍቶች እንደመርግ ሆኑበት… በሸቀ፤ ሊሸሻት ፈለገ፡፡ እንደፈለገ አወቀችበት፤ ቅንድቦቿ እርስ በርስ ተጠጋጉ… በሸቀ… ተናደደ… ነደደ ታምራለች፡፡ …ጭራሽ ሳቀች፤ እድሉን ሊጠቀም አይኖቹን አስፍቶ በጥርሷ ገባ፣ እንከን ሊፈልግ… ምንም ነገር አጣ፣ ዞሮ አመለጣት፣ ሸሻት፡፡ የምናብ ሙሽራው ተከተለችው፣ ከሰማያት ሰማያት አወጣት… ትንፋሿን ሊያዳክም፡፡

የምናብ ሙሽራው… ሳሮን ትከተለዋለች፡፡ በብልሃት እያቆራረጠ ከኦሪዮን ኮከብ ጠርዛት ጋር አላተማት… ጊዜያቸው ሳይደርስ በምናብ መብቱ የማዛሮት ከዋክብትን በላይዋ ላይ አዘነበባት፡፡ ሳሮን እየተደሰቀችም ቢሆን ትከተለዋለች… እንድታፈቅረው አድርጐ ስለሰራት ትከተለዋለች፡፡ ከካኒየን ጥልፍልፍ ተራሮች ጋር ወስዶ አላተማት፡፡ አሁን ድንገት ህመም ተሰማው… ሀዘን ቢጤ አመመው፤ እንደው… እንደ ድንገት ቃረማት፣ በሀይል በሸቀ… አሁንም ታምራለች፡፡ ወደ ፅእረ አርያም ሊበር ፈለገ… ሊነፍስ፡፡ ያይነጥላዋን የከበበው ኩነኔዋ ከፈጣሪ ደጃፍ እንደማያደርሳት ቢገባው… ከወደዛ ሊያደክማት ወሰነ፡፡ ሳሮን ትከተለዋለች…

ዘማሪው የቅዳሴ ባለቤት መዋሲት ፅሁፉን ሊያሰፍር በሚዘጋጅበት የነፍስ በረራው እለት ላይ የሰለሞን ነፍስ የሳሮንን ነፍስ አስከትሎ ስድስተኛው ሰማይ ላይ ከተመ፡፡ ዞሮ ተመለከታት፣ አይኖቿ ጠበው ያለበሳት ነጭ ጥለት ለብቻው ከሰውነቷ ላይ ሲዋልል አያት… በሸቀ… አሁንም ታምራለች፡፡ ፀደንያ ብትሆን እንደዚህ አታምርም አለ… (እራሱን እየዋሸው ነበር፡፡)

ሳሮንን እንዳታወራ አድርጐ ስለፈጠራት አታወራም… እንድታለቅስ ስለፈለገ ግን ታለቅሳለች፡፡ ቆም ብሎ ተመለከታት፣ አሳዘነችው፡፡ ይዟት ወደ ኢትዮጵያ ቶጳዚዮን ተራራ ላይ አወጣት፡፡ ከፊቱ አስቀምጧት እንደገና ሊያስባት ሞከረ፡፡

አይኖቿን እያየ የበፊት ውድቀቱን ያስተውል ጀመረ… ባይኑ ውስጥ ሳሮንን እየሰገሰገ የበፊት ምንነቱን መደጋገም ጀመረ፤ የፀደንያ መርገምት የፍቅር አሜሄላ ጠረቋቆሰው፡፡ሳሮን የአይበሉባው ፈሳሽ ሆነች፡፡ ፀደንያ የመቅኔው ድርቀት ሆነች፡፡ አብሯት ሊሞት አይገባውም… ቀድሞ ራሱን ፈራጅ ማድረግ ያስፈልገዋል፤ ስለዚህ አርቆ ንፋሱን የሚጋልበውን ትቢያ ተመለከተ… ይሄ ቅዠታም ትቢያ…

ስለዚህ አሁን ያለውን ሃይል አጠረቃቅሞ ሙሉው እሱነቱን በገደለችው የፍቅር አምድ ላይ የፀደንያን ዛር አምጥቶ ሊኮልፋት ወሰነ፤ ቀጥሎም ሊጨረንቃት በመጨረሻም የመጨረሻውን ወዷት ከአየር ጋላቢው ትቢያ ላይ ሊቀብራት…ሳሮን ሁሉም የገባት ይመስል ከንፋሱ እትም ላይ ፈዛ ለመጥፋት ትግል አደረገች፤ የሰለሞን ስሪት ስለሆነች ሳሮን ፀደንያን ሆና ትሞታለች፣ ያኔ ሰለሞን ሰላሙን ከምናቡ ውበት ተበድሮ ይገዛል፡፡ እናም ለመጨረሻ ጊዜ እስከ ማራኪው ውድቀት ሌሊት ድረስ አይኖቿን ባይኖቹ እየማሰነ አፈቀራት… ትንታ እስክትሆነው ድረስ ወዳፍንጫው ማጋት… ማቅለሽለሽ እስክትሆነው ድረስ በያንዳንዱ የሰውነቱ ክፍል ውስጥ ሰገሰጋት፤ እንዳትጠጋው ጥርኝ ሆነባት፣ በፍቃዱ የሷን መአዛ ተመገበው፡፡

ሰአተ ቀጠሮው ደርሶ በጠፍ ጨረቃዋ ምሪት ያላማውን ጥግ ሊፈፅም የጀመረውን ምዕራፍ ሊዘጋ ወሰነ፡፡ በስስት ከተቀመጠችበት አነሳት… ሳሮንን… ፀደንያን፡፡ በዛ የጨረቃ አቧራ ቅይጥ ከሆነው የምድር ትቢያ ላይ አወጣት… በምሬት ስትመለከተው አያት… አሁንም ታምራለች፡፡ በመብቱ ሙሉ ሰውነቱን ይለያየው ጀመር፤ አየር ላይ አርቆ ቀበራቸው፤ አይኗን ብቻ እየቋመጠ ተመለከተው… የሳሮንን አይን… የፀደንያን አይን፡፡ በመጨረሻ አይኗን አርቆ ድብ ወደተባለው የከዋክብት ቤተሰብ ላከው… ደግሞ ላያየው፡ እፎይታ ተሰማው… ሀዘን ተሰማው… በሸቀ፡፡ እየሞተች የምታምር ነፍስ…

***

ምዕራፉን እንደዘጋ እኔም ከሀዘኔ ባነንኩኝ… ሳሮንን ተባብረን ገደልናት፡፡ ፀሀፊው ሰለሞን የፀደንያን ሞት ሲያሰላስል ድንገት እነዛ ጥርሶቿ መጡበት… ደነገጠ፡፡

ድንገት እነዛ ከንፈሮች ሲተነፍሱ ተመለከታቸው… እነዛ አይኖች… ጆሮዎች… ፀጉሮች… እግሮች…፡፡ ፀደንያ አልሞተችም… የሞተችው ሳሮን ብቻ ነበረች፤ ምዕራፉ የተዘጋው የሳሮን ብቻ ነበር፡፡ ለካ ፀደንያ ያን ሁሉ ጊዜ በትዝታ መንበርዋ ላይ ተንሰራፍታ እያስካካች የዛችን ነፍስ እልቂት እየተመለከተች ነበር… ለካ ፀደንያ አልሞተችም… የሞተችው ሳሮን ነበረች፡፡ሰለሞን በፀደንያ ሳቅ ሙሉ ሰውነቱ ተረበሸ፡፡ የያዘውን ወረቀት በአየር ላይ በተነው፡፡ ብዙ ዘመናት አልፈው ነበረ ሳሮንን ለማጥፋት ያሰበው… ፀደንያ ግን ዘላለማዊ ነበረች፡፡ የዘላለም ቀንዲል… የአርምሞ ደረጣ… የሰው ዘመን ደርዘኛ… ይህች የማትናብል የነፍስ አጥቅ… ይህች ፀደንያ…

ሰለሞን በድንጋጤ ሀዘን እጁን አፉ ላይ ጫነው፡፡ ነፍሰ ገዳይ ሊባል ነው… ጨካኝ ሊባል ነው… አረመኔ ሊባል ነው… በራሱ ሊወቀስ ነው፡፡አይነውሃውን ሰብስቦ ወደ መሬት ላከ፤ ሁለንታ ደግሞ እንባውን ልታጣጥም ነው፣ እኔም የፅሁፍ ዛሩ ተከትዬው ከእንባው ጋር ወደ መሬት ተወረወርኩ፡፡ ደግሞ እንደማልመለስ አውቀዋለሁ… ካሁን በኋላ ህመሙን ልታመምለት ዘንድ አቅመቢስ መሆኔን አምኜ ማንም ሊድጠኝ ያይኑ ላይ ትዝብቱ ሆኜ ከመሬት ልጠለስ ነው፡፡

***

ስለዚህም መጀመሪያው ተመልሶ መጀመሪያ ይሆናል… ፍልሚያው የፍቅር ስለሆነ፡፡ በመሆኑም መጀመሪያ ያልኩትን ደግሜ፣ ትዝታ ብቻ ልሁናችሁ…

***

የህሊና ቡታ በሻቃ ማንነት ይሰጣል፡፡ ለሰብእ የማዘን እንግልት ፍቅር ሲያስነጥስ አይነት የትንታ እንጉርጉሮ አለው…፡፡ በሃሳብ ማሳ ላይ መሽቀዳደም ከድካም ክሳት እንጂ ካሸናፊነት ህብር የለውም… ጉዞው የዘላለም ፉጨት ነው፣… ልክ ከሰማይ ላይ እንደሚበር አይነት አሞራ ከክንፉ ጫፍ እንዳለ እርግብግቢት… ልክ መነሻው እንደማይታወቅ የሰው ልጅ እንባ… ልክ መች እንደዛመን እንደማንረዳው የፍቅር ግርፊያ… ይኸው ነው፣ በሃሳብ ማሳ ላይ መሽቀዳደም ከድካም ክሳት እንጂ ካሸናፊነት ህብር የለውም፡፡

ቃላት መፍቻ

የህሊና ቡታ - እሪታ፣ የሰው ያለህ ማለት

እንደዛመነ - ተኮሰ፣ ተቃጠለ

ጉሜው - ቤተሰብ፣ ሚስት

ጐባባ - ጐባጣ

በደጅ - የቄሶች በራፍ ስር የሚበቅል ለመድሃኒትነት የሚጠቅም ቅጠል

ያንቀሸርራል - ሰውነት ያደርቃል

እንደመርግ - የድንጋይ ናዳ

ልማም - በጥርስና በድድ ላይ የሚታይ ከምግብ ቅሬታ የመጣ ነጭ እድፍ

ሊኮልፋት - ሊያቆሽሻት

ሊጨረንቃት - ሊጨቁናት

ደረጣ - ሁከት

ደርዘኛ - ብጥበጣ

የማትናብል - የማትወረወር

አጥቅ - ሽመል፣ መቃ ቀርከሃ

 

 

 

Read 4833 times Last modified on Saturday, 30 June 2012 13:16