Saturday, 08 February 2020 15:48

62 የፍቅርና የቤተሰብ ዓመታት

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(1 Vote)

   “እኛ ተቻችለን ተከባብረን እዚህ ደርሰናል” - አቶ ዘገዬ ሰይፉ
            · የ88 ዓመቱ አዛውንት ‹‹የራሴን ልናገር›› መጽሐፍ ተመርቋል
          · የልጃቸው 25ኛ ዓመት የጋብቻ በዓልም አብሮ ተከብሯል
     
         አቶ ዘገዬ ሰይፉ የ26 ዓመት አፍላ ወጣት፣ ወ/ሮ አሰለፈች ደግሞ የ14 ዓመት ታዳጊ እያሉ ነው በጋብቻ የተጣመሩት፡፡ ከዚያን ጊዜ አንስቶ ከግማሽ ክ/ዘመን በላይ በዘለቀው ትዳራቻ፣ 11 ልጆችን 15 የልጅ ልጆችን እንዲሁም ሁለት የልጅ ልጅ ልጆችን አፍርተው፣ አሁንም እንዳማረባቸው ይገኛሉ፡፡
አቶ ዘገየ  ከጃንሆይ ዘመን ጀምሮ እስከ ደርግ መንግስት ድረስ አገራቸውን በተለያዩ የስራ መስኮች ለ41 ዓመታት አገልግለዋል፡፡ ወ/ሮ አሰለፈች ደግሞ የቤቱን ጉዳይ፣ የልጆቹን እንክብካቤና ሌሎች ኃላፊነቶችን ወስደው ባለቤታቸውን እየደገፉ ኖረዋል፡፡   
እኒህ ጥንዶች፤ ባለፈው ማክሰኞ ጥር 26 ቀን 2012 ዓ.ም ከሰዓት በኋላ፣ ቦሌ ወሎ ሰፈር በሚገኘው ኤደን ገነት መናፈሻ በተሰናዳ ትልቅ ድግስ፣ 62ኛ ዓመት የጋብቻ በዓላቸውን፣ ከ10ኛ ልጃቸው አዜብ ዘገዬ 25ኛ ዓመት የጋብቻ በዓል ጋር አጣምረው በድምቀት አክብረዋል፡፡
ትልቅ የሰርግ ድግስን በሚመጥነው በዚህ ሥነ ሥርዓት ላይ የትልቆቹም የትንሾቹም ጥንዶች ቤተ ዘመዶች፣ ከልጅነት እስከ እውቀት አብረዋቸው የኖሩ ጎረቤቶች፣ ጓደኞች፣ የስራ ባልደረቦች የታደሙ ሲሆን ስለ ጥንዶቹ ተምሳሌትነት ምስክርነታቸውን ሰጥተዋል:: በሥነ ሥርዓቱ ላይ የተገኘችው የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ ናፍቆት ዮሴፍ፤ ‹‹መቻቻል ቃሉ ቀላል ነው፤ ተግባሩ ግን ከባድ ነው›› ከሚሉት የ88 ዓመት የዕድሜ ባለጸጋ አቶ ዘገዬ ሰይፉ፣ ከልጃቸው ወ/ሮ አዜብ ዘገዬና ከባለቤቷ አቶ ዳንኤል መኮንን ጋር አጫጭር ቆይታ አድርጋለች፡፡ እነሆ፡-


              እንኳን ለዚህ በዓል አደረሳችሁ?
እንኳን አብሮ አደረሰን፡፡ አመሰግናለሁ፡፡
62 ዓመት ሙሉ ትዳራችሁን በጽናት ጠብቃችሁ የመኖራችሁ ምስጢር ምንድን ነው?
ሰው “መቻል መቻቻል” ይላል፤ ቃሉ ትልቅም ከባድም አይደለም፡፡ ተግባሩ ግን ትልቅም ከባድም ነው፡፡ እኔ ስቆጣ እሷ ካልቻለች፣ እንደገና መልሼ እንደምቆጣ ታውቃለች፤ ስለዚህ እሷ ተወት ታደርገኛለች፡፡ እኔም በራድ ነኝ፤ ቶሎ እበርዳለሁ፡፡ እሷ ስትቆጣ ደግሞ እኔም አንዳንዴ አልፋለሁ፤ ሰከን እልና “በቃ እውነቷን ነው፤ ይሄ የራሴ ጥፋት ነው” እልና እቀበላለሁ:: አሁን ሰው የሚጎድለው ይሄ ነው፡፡ እኔና እሷ  የተለያየ ጠባይ ይዘን ነው የተጋባነው፡፡ ሴትና ወንድ በተፈጥሮም ጠባያችን የተለያየ ነው:: ያንን አንድ ለማድረግ እሷ እኔን፣ እኔ እሷን መሸከም አለብን፡፡ እኛ እንዲህ ስለምናደርግ፣ በ62 ዓመታት የትዳር ህይወት ውስጥ ሦስተኛ ሰው በሽምግልና ገብቶ አያውቅም፡፡ እኔ ሳጠፋ እሷ ለቤተሰቦቿ አትናገርም፤ እኔም ይህንን አላደርግም፡፡ እሷ ደግሞ በልጅነቷ ስለመጣች፣ እናትና አባቴ አቅፈው ነው ያሳደጓት፡፡ እኔም እዛው ግቢ ትንሽ ቤት ስለነበረኝ አብረን ነው የኖርነው፡፡ ይሄ ሁሉ ሰላምና ፍቅር ነው ለዚህ ያደረሰን፡፡
እርስዎ የት ነው ተወልደው ያደጉት? ከወ/ሮ አሰለፈችስ ጋር እንዴት ተገናኛችሁ?
ወደ ባለቤታቸው ዞር ብለው (“የት ነው ያገኘሁሽ?” አንቺ አሉና)፤ ያቺ ፊት ለፊት የምትታይሽ ታናሽ እህቴ ሰርግ ላይ እህቷን ተከትላ ትመጣለች፡፡ እህቷ ደግሞ የአጎቴ ሚስት ነች፡፡ ከዚያ እኔ አየኋትና ደነገጥኩ፤ ልቤ ቀጥ አለ፤ ግን ይሄ ነገር ዝምድና ሳይኖረን አይቀርም ብዬ ፈራሁና ላፈገፍግ ስል፣ እናታችን “እናንተ’ኮ የጋብቻ ዝምድና እንጂ የስጋ ዝምድና የላችሁም” አሉን፡፡ ልታመልጠኝ ነው ብዬ ደንግጬ ነበር:: ይሄው ሳታመልጥ 62 ዓመት አለፈ፡፡ እኔ ተክለ ሃይማኖት ነው ሰፈሬ፣ እሷ የመጣችው ፉሪ ከሚባል አካባቢ ነው፡፡
ያኔ ከ18 ዓመት በታች ያለች ልጅ ማግባት በሕግ አያስቀጣም ነበር እንዴ? እንዴት አገቡ?
ያኔ ችግር አልነበረውም፤ ዞሮ ዞሮ እዚህ ደርሰናል፡፡ እኛ ቤት ሰርግ መጣች፤ቅልውጥም እንደሆነ አላውቅም ወይም እኔን ሊጥልላት አስቦ ይሆናል --- ብቻ መጣች፡፡ ይሄው አሁን እዚህ ደርሰናል፡፡ (ሰውዬው ንቁና ተጫዋች ናቸው) 11 ልጆች 15 የልጅ ልጆች፣ ሁለት የልጅ ልጅ ልጆች አፍርተናል፡፡ ይሄ የምታይው አጃቢው ጨፋሪው ሁሉ የእኛው ነው፡፡ በቅርቡም አንድ የልጅ ልጅ ድረናል፡፡
እንደሰማሁት እርስዎ በባህሪዎ ቁጡ ነዎት፤ ወይዘሮ አሰለፈችስ ምን አይነት ባህሪ ነው ያላቸው?
እሷ ከእኔ በጣም ትሻላለች፡፡ ቻይ ናት:: ባጠፋም ብቆጣም ፀባዬን ስለምታውቅ ትችላለች፡፡ እንደነገርኩሽም ምልስ ነኝ፤ ቶሎ እበርዳለሁ፤ ተቆጥቼ አልቆይም፤ አኩራፊም አይደለሁም፡፡
ተጣልታችሁ ጎሸም ጎሸም አድርገዋቸው ያውቃሉ?
የለም የለም፤ ተደባድበን አናውቅም፤ እኔ አልደባደብም፤ ይሄን አድርጌ አላውቅም፡፡ ያው ቁጣ ነው እንዳልኩሽ፤ ቶሎ እበርዳለሁ፡፡
ስራን በተመለከተ እንግዲህ ከጃንሆይ ጊዜ ጀምሮ ነው ሲያገለግሉ የነበሩት፡፡ እስኪ ስለሱ ያውጉኝ?
አዎ፤ በጃንሆይ ጊዜ ‹‹ቤተ ርስት›› በተባለ ግምጃ ቤት ነው ሥራ የጀመርኩት፡፡ እንዴት እዛ ጀመርኩ መሰለሽ፤ አባቴም እዛ በዳኝነት ይሰሩ ነበር::
ያን ጊዜ ልጅ ነኝ፤ አባቴ 700 ጋሻ መሬት ስልጤ ውስጥ የነበረውን የመንግስ ይዞታ ግለሰቦች ሲጠቀሙበት ስለነበር አባቴ በሞያቸው ሲከራከሩ ቆይተው በመርታታቸው ያንን የፍርድ አፈጻጸም ለማስፈፀም ሄደው ነው በተከራካሪዎች የተገደሉት፡፡ ያን ጊዜ እንግዲህ ጉዳዩን ጃንሆይ ሰምተው ነው፣ እዛ ስራ የጀመርኩት፡፡ በወቅቱ የ16 ዓመት ልጅ ነበርኩኝ፡፡ ከዚያም በፅህፈት ሚኒስቴር እና በደርግ ደግሞ በሚኒስትሮች ምክር ቤት፣ በድምሩ ለ41 ዓመታት አገልግያለሁ፡፡ ከዚያም በግል ድርጅት ውስጥ ለጥቂት አመታት ሰርቻለሁ፡፡
አሁንስ ምንም አይሰሩም?
አሁን ምንም አልሰራም፡፡ ያው በጡረታ ላይ ነኝ፤ እየተጦርኩ ነው፤ ለቁም ነገር የበቁ ጥሩ ጥሩ ልጆች  አድርሻለሁ፤ ቅድመ አያት ሆነናል፡፡
‹‹የራሴን ልናገር›› የተሰኘ መጽሐፍዎም በዚህ ሥነ ሥርዓት ላይ ተመርቋል፡፡ የመጽሐፉ ጭብጥ ምንድን ነው?
እንግዲህ እኛ ተቻችለን ተከባብረን እዚህ ደርሰናል፡፡ ዛሬም ትንሿ ልጃችን በጽናትና በፍቅር 25 የትዳር አመታትን ዘልቃለች። ይህ ምሳሌነት ከእኛ ቤተሰብ ወጥቶ ለወጣቱ ትውልድ መማሪያ ይሆን ዘንድ፣ እንዴት በጽናት በትዳር እንደሚዘለቅ፣ ከራሴ የሕይወት ተሞክሮ እያዛመድኩ ነው የጻፍኩት፡፡
ይሄ ጥቂት አበርክቶ ለትውልዱ ይጠቅማል በሚል፣ የ62 ዓመት የትዳር ጉዞዬን፣ የስራዬን ሁኔታ፣ በሥራና በትዳር ሊያጋጥሙ የሚችሉ ፈተናዎችንና እነዚያን ፈተናዎች እንዴት ማለፍ እንደሚቻል፣ የራሴን ልምድ ለማካፈል ሞክሬአለሁ፡፡
እስቲ ለወጣቱ ትውልድ፣ ሕይወትንና ትዳርን በተመለከተ አጭር መልዕክት ያስተላልፉ?
በመግቢያችን እንዳልኩት ‹‹መቻቻል›› የሚለው ቃል ቀላል ነው፡፡ ተግባሩ ግን ከባድ ነው፡፡ ስለዚህ  ወጣቱ ተተኪ ትውልድ እንደመሆኑ፣ እሱንም የሚተካው መልካም ሰብዕና ያለው ትውልድ ለማፍራት፣ ከታላላቆቹ መቻቻልና መከባበርን ማዳበር፣ መማር አለበት ባይ ነኝ፡፡



___________________________



           ‹‹ባለቤቴ ከእንቁም ከወርቅም በላይ ናት›› ‹‹ለዚህ ሁሉ ክብርና ስኬት፣ ክብሩን
           አቶ ዳንኤል መኮንን (የወ/ሮ አዜብ ባለቤት) እግዚአብሄር ይውሰድ›› - ወ/ሮ አዜብ ዘገዬ


             ከባለቤትዎ ከወ/ሮ አዜብ ጋር እንዴት ተዋወቃችሁ?
የትውውቃችን ጉዳይ ረጅም ታሪክ አለው:: በአጭር ለማስቀመጥ፣ የተዋወቅንበት መነሻ፣ ዛሬ 62ኛ ዓመት የጋብቻ በአላቸውን እያከበሩ ያሉት የባለቤቴ አባት አቶ ዘገየ ሰይፉ፣ ቅድም እንደመሰከሩት፣ እግዚአብሄር ጥሩ ትዳር እንዲሰጠኝ ፀልዬ ነበር፡፡ የእግዚአብሔርን መልስም እየጠበቅሁ ነበር፡፡ ከዚያ አንድ ቀን፣ የቤተሰብ የንግድ ድርጅት በተሳተፈበት ባዛር ላይ ተገኝቼ፣ ባዛር ስናሳይ ነው ለመጀመሪያ ጊዜ ያየኋት፡፡ ይሄ እንግዲህ በፈረንጆቹ አቆጣጠር፣ በ1994 ዓ.ም ይመስለኛል፡፡ እናም እዛ ባዛር ላይ እቃ ይዘን ስንሳተፍ፣ ሱቃችንን ለመሙላት ተጨማሪ እቃ ያስፈልገን ስለነበር፣ ዞር ዞር እያልኩ እቃ ስመለከት ነው ያየኋት፡፡
ልክ እንዳይዋት ምን ተሰማዎት?
ልክ እንዳየኋት ደንግጬ መንቀሳቀስ አልቻልኩም፡፡ ይህ የሆነው ፀሎት በፀለይኩ በአመት ከ6 ወር ጊዜ ውስጥ ነው፡፡ ግን ለመጀመሪያ ጊዜ ሳያት የፀሎቴ መልስ እንደሆነች፣ እግዚአብሄር የሰጠኝ ስጦታ እንደሆነች አምኜአለሁ፡፡ ያ ደግሞ ትክክል ነበር:: አንደኛ ደነገጥኩ፤ ከዚያ ከእግዚአብሄር ጋር ነው ንግግር የጀመርኩት፤ ”እሷ ናት ማለት ነው የሰጠኸኝ” እያልኩኝ፡፡ ገብቼም አነጋገርኳት፤ ይኸው ለዚህ ደርሰናል፡፡
መጀመርያ ምን ብለው ነው ያነጋገሯት?
ለጊዜው እቃ እንደሚፈልግ ሰው ገብቼ ነው ያነጋገርኳት፡፡ እኛም ሱቅ እንዳለንና መጥታ እቃ ማየት እንደምትችል ገለጽኩላት፤ መጥታ እቃ አየች፤ ባዛሩ የ10 ቀን ነበር፤ ተዘጋ፡፡
ከዚያስ ምን ሆነ? ስልክ ተቀያየራችሁ ወይስ?---
አልተቀያየርንም፤ ሌላ የባዛር ትርኢት እስኪከፈት እጠብቅ ነበር፤ ከ15 ቀን በኋላ ተመሳሳይ ባዛር ተከፈተ፡፡ ይህን ጊዜ በናፍቆትና በጉጉት ነበር የምጠብቀው:: በዚህ ባዛር ላይ ፈልጌ ፈልጌ አገኘኋት፡፡ ይሄ ጊዜ እንዳያልፈኝ ስለፈለግሁ፣ በግድ ምሳ እንድትጋበዘኝ ጠየቅኋት፡፡ ምሳ እየበላን የተሰማኝን ገለጽኩላት:: ‹‹ሳይሽ ደንግጫለሁ፤ ያላንቺ እንደማልኖር ልቤ አውቋል፤ ግን ካንቺ ፈቃድ አላልፍም፤ የሚሆን ከሆነ ንገሪኝ፤ ካልሆነም ቁርጤን አውቄ ልቀመጥ፤ ምክንያቱም ታምሜያለሁ›› ብዬ መውደዴን ነገርኳት፡፡ ወዲያው አልመለሰችልኝም፡፡ ‹‹እስኪ እናየዋለን›› አለች:: ነገር ግን ሁሉንም በትዕግስት ጠበቅኩኝ:: የእግዚአብሄርም ፈቃድ ስለታከለበት፣ ሂደቶችን አልፈን፣ በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ለጋብቻ በቃን፡፡ እኛ ባናቅደውም አጋጣሚዎች ተፈጠሩ፤ አሜሪካ መሄድ ነበረብን፤ ተጋብተን ወደ አሜሪካ አመራን፡፡ ይኸው 25ኛ ዓመት የጋብቻ በዓላችንን እያከበርን ነው፡፡
አሁን ኑሯችሁ በአሜሪካ ነው?
አዎ! አሜሪካ ፊላደልፊያ፣ ቴንሶቬኒያ ስቴት ነው የምንኖረው፡፡
በምን ሥራ ላይ ነው የተሰማሩት?  
የሚገርምሽ እንደ አጋጣሚ ሆኖ፣ ብዙ ቦታ አብረን ነው የሰራነው፡፡ አሁንም በተለያየ ዲፓርትመንት ቢሆንም፣ ‹ITW›› በሚባል ግዙፍ ዓለም አቀፍ ኩባንያ ውስጥ ነው የምንሰራው፤ እኔ በጥራት ምህንድስና፣ እሷ ደግሞ በጥራት ቴክኒካል ድጋፍ፡፡   
ስንት ልጆች አፍርታችኋል?
ሦስት ልጆች አፍርተናል፡፡ የመጀመሪያ ልጃችን አዛሪያ ዳንኤል ይባላል፤ የ20 ዓመት የዩኒቨርሲቲ ተማሪ ነው፡፡ ሁለተኛ ልጃችን ፌቨን ዳንኤል፣ 18 ዓመቷ ነው፤ ሦስተኛውና የመጨረሻው ጆሹዋ ዳንኤል፣ የ16 ዓመት ልጅ ነው፡፡
ባለቤትዎን ወ/ሮ አዜብን በአጭሩ ይግለጽዋት ቢባሉ--?
ባለቤቴ ከወርቅም፣ ከብርም፣ ከእንቁም በላይ የተለየች፤ ከፈጣሪ የተሰጠችኝ ድንቅ ሚስት ናት፤ የምሬን ነው እጅግ ሲበዛ መልካም ሰው ናት፡፡ እኔ ከዚህ በላይ እሷን የምገልጽበት ቃል የለኝም፡፡


         እንኳን ለዚህ ቀን አበቃሽ --
አሜን፤ አመሰግናለሁ፡፡
ገና ዛሬ ያገባሽ አዲስ ሙሽራ እኮ ነው የምትመስይው--!
እውነት ለመናገር፣ ሁሉም አዲስ ሙሽራ ነው የምትመስይው እያለኝ ነበር፤ አንቺም ደገምሽው፤ ለዚህ ሁሉ ክብርና ስኬት ያበቃኝ፣ እግዚአብሄር ክብሩን ይውሰድ፡፡
ለአቶ ዘገዬና ለወ/ሮ እልፍነሽ ስንተኛ ልጅ ነሽ?
አሥረኛ  ነኝ፤ ከኔ በላይ ዘጠኝ አሉ፡፡
የመጨረሻ ልጅ ሆነሽ መጀመሪያ ያገባሽ ይመስለኛል፤ እንዴት ሊሆን ቻለ?
 በጣም በልጅነቴ ቀድሜ ነው ያገባሁት:: ባለቤቴ እጮኛዬ ሳለ፣ አሜሪካ የመሄድ አጋጣሚ ሲፈጠር፣ አብረን መሄድ ነበረብን፤ ስለዚህ ቶሎ ወደ ጋብቻ ገባን፡፡
ከባለቤትሽ ጋር የተገናኘሽበት ቀንና  የ25 ዓመት የትዳር ጉዞሽን እንዴት ታስታውሽዋለሽ?
ከዳኒ ጋር እንዴት እንደተገናኘን አስታውሳለሁ፡፡ ከዚህ በፊት ጥሩ ክርስቲያን የሆነ፣ እግዚአብሄርን የሚፈራ ባልና የማልፈታው ትዳር ስጠኝ ብዬ እፀልይ ነበር፡፡ እውነትም እግዚአብሄር ፀሎትን ይሰማልና የሰጠኝ እንደ ፀሎቴ ነው፡፡ ስለዚህ 25 አመታትን በጥሩ ፍቅር አሳልፈናል፡፡ እንዳልኩሽ የተጋባነውም በጊዜ ነው፤ ሃኒሙናችን አሜሪካ ነበር፡፡ እግዚአብሄር ከእኛ ጋር በከፍታም በዝቅታም፣ በመውረድም በመውጣትም አብሮን ስለነበር፣ እየረዳን እዚህ ደርሰናል፡፡ እግዚአብሄርን ከመፍራታችን የተነሳ ቆመናል፡፡ ባሌም ደግሞ እኔን በልጅነቴ ስላገባኝ፣ እንደ አባት ሆኖ ተቻችለን አልፈናል፡፡ እኔም ያኔ ባህሪዬ ሁሉ እንደ ልጅ ስለነበረ፣ በትዕግስት ነው ያቆየኝ፡፡ እሱም አባቱ በልጅነቱ ስለሞቱ፣ የመጀመሪያ ልጅ ሆኖ ቤተሰቡን በኃላፊነት ሲያግዝ ስለነበር፣ ለእኔም እንደ አባት ነበር:: የእሱ ትዕግስትና ጥንካሬ ብዙ ስላስተማረኝ፣ ዕድለኛ ነኝ ማለት እችላለሁ፡፡
ከአቶ ዳንኤል ጋር ተጣልታችሁ ታውቃላችሁ?
አዎ፤ በደንብ ነዋ የምንጣላው!
ለምሳሌ በምን ጉዳዮች ላይ ትጣላላችሁ?
ብዙ ጊዜ የምንጋጨው በልጆች አስተዳደግ ላይ ነው፡፡ በልጆች አስተዳደግ ላይ እንዳልኩሽ፣ እኔም እሱም ከየቤተሰቦቻችን ያመጣናቸው ልምዶች አሉን፡፡ እኔ እንዲህ ነው ልጅ የሚያድገው፤ ለምን እንዲያ ታደርጋለህ ስለው፣ እሱ ደግሞ ልጅ በዚህ መልኩ ማሳደግ አይቻልም፤ ለምንድነው ጠንከር የማትይው የሚለው ነው የሚያጣላን፡፡
አንቺ ልጅ ታሞላቅቂያለሽ፤ እሱ እንደ ኢትዮጵያዊ አባት ኮስተር ብሎ ማሳደግ ይፈልጋል?
ትክክል ነሽ፡፡ በዚህ ነው የምንጋጨው፡፡ ፈረንጅ አገር ብንኖርም ልጆች በሥርዓት ማደግ አለባቸው ይላል፡፡
አሁን ላይ ሆነሽ ስታስቢው ባለቤትሽ ትክክል ነው?
ምንም ጥያቄ የለውም፡፡ በጣም የሚገርመው ልጆቼ አድገዋል፡፡ ልጆቼ በሙሉ “እናንተ እኛን እንዳሳደጋችሁን ነው ልጆቻችንን የምናሳድገው” ይላሉ፡፡ ትልቁ ዩኒቨርሲቲ ያለው ልጄ ደግሞ ‹‹ማሚ እንዳንቺ ያለች ጠንካራና ጥሩ ሚስት ማግባት ነው የምፈልገው›› ይለኛል፡፡ አሁን ዞር ብዬ ሳየው፣ ለሌላው ወላጅም የምመክረው፣ ከብሩም ከሩጫውም ከምኑም ቀንሶ፣ ከሁሉም በላይ ለልጆች ትኩረት እንዲሰጥ ነው፡፡ ምክንያቱም ልጆቻችን ቢጠፉ የያዝነው ሁሉ ከንቱ ነው የሚሆነው፡፡ በዚህ በኩል ባለቤቴ ጠንካራና ለልጆቹ ትኩረት የሚሰጥ በመሆኑ፣ ዛሬ ልጆቻችን መልካሞች፣ ሥርዓት ያላቸው፣ እግዚአብሄርን የሚፈሩና ወላጆቻቸውን የሚያከብሩ ናቸው፡፡ ክብሩ ለእግዚአብሄር ይሁን፡፡
የወላጆችሽ 62ኛ ዓመት የጋብቻ በዓል ላይ፣ የ25ኛ ዓመት የጋብቻ በዓልሽን አብረሽ ማክበርሽ ምን ዓይነት  ስሜት ፈጠረብሽ?
የሚገርምሽ ቅድም ለባለቤቴ ‹‹ይሄን ነገር በህልሜ ነው ወይስ በእውኔ ነው?›› እያልኩት ነበር፡፡ ከእናቴና ከአባቴ ጋር በጋራ ሳከብር ማመን ሁሉ ነው ያቃተኝ፡፡ ብዙ ጊዜ ሰዎች የጋብቻ በዓል ሲያከብሩ አውቃለሁ፡፡ ግን ልጅ ከእናትና አባቱ ጋር የጋብቻ በዓል ሲያከብር አላየሁም ወይም አልሰማሁ ይሆናል፡፡ ይሄ ለእኛ በጣም መታደል ነው፡፡ አንደኛ፤ ለብዙ ሰው ምሳሌ የሚሆኑት እናትና አባቴ በሕይወት እያሉ መከናወኑ፣ ሁለተኛ፤ አብረን ማክበራችን ያስደንቃል ያስደስታልም፡፡ ተንከባክበው፣ በሥነ ምግባር አንፀው አሳድገው፣ ለዚህ አደረሱኝ፤ እኔም ለወግ ለማዕረግ በቅቼ፣ የእነሱን አርአያነት ተከትዬ፣ 25 ዓመት በትዳር ፀንቼ ከእነሱ ጋር ሳከብር ትልቅ መታደል ነው፡፡ በዚህ አጋጣሚ እጅግ አከብራቸዋለሁ፤ እወዳቸዋለሁ፤ ከዚህ በላይ ረጅም እድሜ እንዲሰጣቸውም እመኛለሁ፡፡
ከእናትና አባትሽ ጋር በድጋሚ የስንተኛ ዓመት በዓልሽን ማክበር ትፈልጊያለሽ?   
እሱ የእግዚአብሄር ፈቃድ ነው። አሁን ሲናገሩ እንደሰማሁት፤ ወላጆቼ ከዚህ ቀጥሎ የሚያከብሩት 75ኛ የአልማዝ ኢዮቤልዩ በዓል ነው፤ ያኔ የኛ ወደ 35 ዓመት ይሆናል፤ ብቻ አላውቅም፡፡ ካልሆነም ለሌሎች እህት ወንድሞቼ እድል ብሰጣቸው ደስ ይለኛል፡።
የተደገሰው የትልቅ ሰርግ ድግስ ነው፤ አንቺም እንደ ሙሽራ ቬሎ ለብሰሽ ነበር፡፡  ይህን በዓል ከወላጆችሽ ጋር እንድታከብሪ ሀሳቡን ያፈለቀው ማን ነው?
በጣም ጥሩ ሀሳብ አስታወስሽኝ፡፡ በዚህ አጋጣሚ የታላቅ ወንድሜ ሚስት ቤተልሄም ብርሃነ ትባላለች፡፡ ቤቴልሄምና ወንድሜ ሳሙኤል ዘገዬ በጣም የተለዩ፣ ቤተሰቦቻቸውን የሚወዱና የሚያከብሩ ናቸው፡፡ እግዚአብሄር በምድርም ፀጋ የሰጣቸውና የባረካቸው ናቸው:: ሀብት ንብረት አለን ብለው የማይኩራሩ፣ ለቤተሰቦቻቸው ቅርብና ተንከባካቢ ስለሆኑ እጅግ አመሰግናቸዋለሁ፡፡ እኔ ቤቲን እንደ አማች አላያትም፤ ወንድሜ ሳሚ ዕንቁ የሆነች እህት ነው፣ ወደ ቤተሰቡ አምጥቶ የሰጠን፡፡ ይህን ሁሉ ሀሳብ አንስተው ለዚህ ያበቁን ቤቲና ሳሚ ናቸው፤ ፈጣሪ ሕይወታችሁን ልጆቻችሁን ይባርክ፡፡ እናቴና አባቴ ለደረሱበት ክብር እንድትበቁ ምኞቴ ነው፡፡
ሌላው ማስተላለፍ የምፈልገው፣ እናትና አባቶቼ ልጆቻቸውን የዳሩት ለጉራጌ፣ ለኤርትራዊ፣ ለኦሮሞ፣ ለአማራ፣ ለትግሬ ነው፤ ብቻ ሁሉም ብሔር ብሔረሰብ እኛ ቤት አለ:: ይሄ ሁሉ ሰው ዘር ሳይቆጥር፣ በሰውነቱ ብቻ ተፋቅሮ ነው የሚኖረው፡፡ ምክንያቱም ፍቅር፤ ዘር ቋንቋና ብሔር አይመርጥም፡፡ ስለዚህ የእኔ ቤተሰብ፣ ኢትዮጵያን በሙሉ የሚወክል፣ ተዋዶ ተፋቅሮና ተከባብሮ የሚኖር ስለሆነ ኢትዮጵያዊያን እባካችሁ፣ ዘር ጎሳና ቋንቋ አይለያየን፤ ተከባብረን ተዋደን፣ እንደ ቀድሟችን እንኑር እላለሁ፡፡   

Read 1801 times