Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Saturday, 30 June 2012 12:01

አማኝ የሌለበት ፕላኔት ይፈልጉ!

Written by 
Rate this item
(0 votes)

የተከበሩት ኢትዮጵያዊ ዓለሙ ከድር፤ በአዲስ አድማስ ጋዜጣ ላይ ሰኔ 9/2004 ዓ.ም “ፈጣሪ ያዳላል? ያልተፈለገ ጥያቄ” በሚል ርዕስ በነፃ አስተያየት ዓምድ ስር የፃፉት ፅሁፍ የተሣሣተ ግንዛቤ የያዘ መልዕክት ሆኖ አግኝቼዋለሁ፡፡ ስለሆነም እርስዎ በክፋት (ከጥላቻ) ሳይሆን ከየዋህነትና ከሞኝነት ተነሳስተው የፃፉት ነው ብዬ በቅንነት በመተርጎም እርስዎ ያላዩት ጽሁፍዎ የያዘው መርዝ፣ ብዙሃኑን ጨዋና ትዕግስተኛ የሆነውን የሀገሬን ሕዝብ ከመመረዙ በፊት ተማምረንበት እናመክነው ዘንድ ምላሼን እነሆ ብያለሁ፡፡ በዚሁ አጋጣሚ ይህንን ጽሁፍ የምታነቡ ሁሉ፣ እውነትን የምትወዷት ከሆነ የተሠማችሁን ትናገሩ ዘንድ አደራዬ የጠበቀ ነው፡፡

ለመግቢያ ይህንን ካልኩ ወደ ዋናው ሃሳባችን እንግባ ከላይ በተጠቀሰው ርዕስ ስር የተፃፈውን ጽሁፍ ስናነበው እና ወደ ጭብጡ (ፍሬ ነገሩ) ስንገባ ብቃትንና ስኬትን ማድነቅ እና ማወደስ ሲገባ ሃይማኖትና እግዚአብሔርን ታዋቂ ሰዎች የምንላቸው እያወደሱ፣ የአሸናፊነትንና የራስ ጥረትን ለማይገባው ሰጥተዋል የሚል መንፈስ እና ከሳሽ ጽሁፍ ነው፡፡ በጣም የሚያሳዝነው ከእኔ የተሻለ አዋቂ ሊኖር ይችላል ብሎ አለማሰብ በራሱ ትልቅ የዕውቀት ችግር ሆኖ እናገኘዋለን፤ ምክንያቱም የፀሀፊ አለሙ እኔ አውቅልሃለሁ አገላለጽ ጊዜ ያለፈበት የኢምፔሪያሊስቶች ሀሳብ ነው፡፡ ለምሳሌ የሁለተኛው የዓለም ጦርነት መነሻ ላይ የግለሰቦችን አጀንዳ ማስፈፀም ነው እኛ ያልነው ብቻ ይሁን የሌላው እውቀት አይደለም አይነት ሃሳብ ሲንፀባረቅ ነበር፡፡ አቶ አለሙ እስኪ አንድ ጥያቄ ልጠይቅዎት፡፡ የእርስዎ ተቃዋሚነት ቢያንስ 70 ሚሊዮን ሕዝብን ነው ይችሉታል? እንዴትስ ሊደረግ ይችላል፡፡ ከ3000 ዓመት በላይ የባህልና እምነት ታሪክ ያለውን ህዝብ እንዴት ነው ስለ ኑሮህ አታውራ የምንለው? ያለ ምክንያት ከእግር ኳስ እስከ ኦሎምፒክ ከግራጁዌሽን እስከ ምርጥ አርቲስት፤ ከፓይለት እስከ ዶክተር፤ ከኢንጂነር እስከ ሳይንቲስት ያለምንም ምክንያት በቃለ መጠይቅ ወቅት በእግዚአብሔር እርዳታ እዚህ ደርሰናል ሲሉ የርስዎን ያህል እውቀት ከማጣት ይመስልዎታል? አንድ ለርስዎ የሚጠቅም ተረት ልንገርዎ፡፡ በዛውም በፖለቲካና በኑሮ ውድነት የተከዘውን ወገኔንም ትንሽ ዘና በማድረግ የማፅናናት ሥራ ቢሆነኝ፤ እርስዎንም ከገቡበት የስህተት መንገድ ለመመለስ ማስተማሪያ ቢመልስልኝ፡፡

አንድ ዝንጀሮ ቁጭ ብሎ ይስቃል፡፡ ከዛም ወዳጁ የሆነ ዝንጀሮ “ምን ሆነህ ትስቃለህ?” ቢለው “ወገኖቼ ሁሉ ቂጣቸው መላጣ ነው፤ በነሱ ነው የምስቀው” አለ “ያንተስ?”  ቢለው “የኔንማ ተቀምጨበታለሁ፤ አይታይም” አለው ይባላል፡፡

ውድ አለሙ ከድር ስለምንድን ነው እየተናገሩ ያሉት? እርስዎም እኮ በሀይማኖት ፅናት ታግለው በፀሎታቸው ሀይል ልጆቻቸውን ካሣደጉ የተከበሩ ኢትዮጵያዊ አባት አቶ ከድር የተገኙ ዘር ነዎት፡፡ ይክዳሉ? ነው ወይስ ልጅ ሲባልግ ወላጁን ያማል አይነት ነው፡፡ አንገት የተፈጠረው አዙሮ ለማየት እንጂ ለሀብል ማንጠልጠያ ብቻ እንዳልሆነ ልብ ይሉ ዘንድ እመክሮታለሁ፡፡

እስኪ የርስዎን የማቴሪያሊስት ኑሮ ብቻ እንኑር እንበል፡፡ ችግርና መከራን ለዘለአለም ከምድረ ኢትዮጵያ፣ ከዚህ ቅን ሕዝብ ላይ ያርቅልንና የኢትዮጵያ ህዝብ ተስፋ ከሚያደርጋቸው የገቢ ምንጮች አንዱ የባህልና ቱሪዝም ነው፡፡ ለምን ቢሉ ላለፉት አያሌ ዓመታት የሕዝባችንን የረሀብና የሰቆቃ ህይወት ከታደጉት ነገሮች አንዱ ኢትዮጵያ በአፍሪካ ከሚገኙ የቱሪስት መስህብ ሀገሮች አንዷ መሆኑ ነው፡፡ ይህ ደግሞ እርስዎ የሚያመልኩት የሳይንስ ውጤት ብቻ አይደለም፡፡ ዝርዝሩን ለኢትዮጵያ ህዝብ ልተወው፡፡ ይህም ማለት እርስዎ እና መሰሎችዎ የምታምኑበትን ፍልስፍና ለመቃወም አይደለም፤ ጉዳቱን እና ተቀባይነት የሌለው መሆኑን ለመግለፅ ይረዳ ዘንድ ነው፡፡እርስዎ እንዳሉት የኢትዮጵያ ህዝብ ፈሪሃ እግዚአብሔር ስላለው፤ ምስኪንና ቁዘማ ላይ ያለ አድርገውታል፡፡ ነገር ግን ሕዝቡን ዝምታ ውስጥ የከተተው በርስዎ አስተሳሰብ የፍርሃትና የአቅመቢስነት ስሜት ነው፡፡ ይህንን የፈጠረው ደግሞ ሀይማኖት አይደለም፡፡ እርስዎ እንዳሉት በደፋርነት እና በማንአለብኝነት ኢትዮጵያን ሶማሊያ እናርጋት? ለመሆኑ ሀገራችንን የጎዳት ከገዢዎቻችን ብቃት ማጣት ጀርባ ያሳለፍነው የርስ በርስ የጦርነት ዘመን እንደሆነ አያውቁም? ይህንን ፍልስፍናዎን መንግስትም ተሸውዶበት የታሪክ ስህተት እየሰራ እንደሆነ ያውቃሉ? “እኔ ነኝ የህዝቡን ችግር የማውቀው” በሚል አባዜ፡፡ ሕዝቡ ስለችግሩ ሲጮህ “አንተ አታውቅም፤ እኔ ነኝ የማውቅልህ” እየተባለ፡፡ ፖለቲካ ምን እየሰራ እንዳለ አያዩም?

የተከበሩ ፀሀፊ አለሙ፤ በእውነት ደፍረው ሃይማኖት የኢትዮጵያን ሕዝብ ፈሪና አቅመ ቢስ አድርጎታል ሲሉ አያፍሩም? የአድዋን ድል ሲቀዳጅ የኢትዮጵያ ሕዝብ ሀይማኖት አልነበረውም ነው ወይስ የኢትዮጵያ አርበኞች ማህበርን አያውቁትም? በማንም ይመን በምንም የኢትዮጵያ ህዝብ ዓለም የሚያውቀው ሀይማኖታዊና ባህላዊ ታሪክ አለው፡፡

ይሄንን እኔና እርስዎ አናስጥለውም? የት ጋ ነው የኢትዮጵያ ህዝብ በሀማይኖት የተነሳ ኋላ ቀር የሆነው? ላሊበላ ላይ፣ አክሱም ላይ፣ ሶፍ ኡመር ላይ፣ ጐንደር ላይ፣ ጣና ላይ፣ ሐረር ላይ፣ የት? ልብ ይበሉ! እርስዎ በጥረቷና በእውቀቷ ልዕለ ሀያል ሆነች ብለው የሚያምኑባት አሜሪካ፤ የመገበያያ ገንዘቧ ላይ ምን ብላ እንደጻፈች ያውቃሉ? We Trust in God! (በእግዚአብሔር እናምናለን) በዚህ አባባሏ አሜሪካ ተጎዳች? ያልገባንን መጠየቅ ስህተት አይደለም፡፡ የማናውቀውን መዘባረቅ ግን ያስጠይቃል፡፡ ለዚህ ነው አባቶቻችን ሲናገሩ “ከመናገርህ በፊት አስብ፤ የአፍ ስብራት ወጌሻ የለውምና” የሚሉት፡፡ እንደርስዎ አባባል እኮ አንድ ሰው ከአራት ኪሎ ተነስቶ ለሥራ በታክሲ ወይም በአውቶቡስ መርካቶ ቢሄድ፣ መርካቶ የደረሰው በገንዘቡ እና በጥረቱ ብቻ እንጂ ታክሲ እና አውቶቡስ አላገዙትም ማለት ነው፡፡ አይከብድም? አውቶቡስ እና ታክሲ ሊመሰገኑ አይገባም? ባዶ ግብዝነት በእውነት የት ያደርሳል?

ስለዚህ የእኔ ሀሳብ ብቻ ይጠቅማል የሚል ፍልስፍና ይጎዳል፡፡ እኔ የገባኝ ውጤቱም የሚያምረው እርስዎ ያሉትን በጥረቴ በስኬቴ ደረስኩ ብሎ የሚያምን ካለ፣ ጥሩ እንሰማዋለን፡፡ ሌላውም በእግዚአብሔር እርዳታ በሃይማኖቴ እገዛ ወ.ዘ.ተ ይበል፤ እኛ የምንፈልገው ማንኛውም ሰው ለውጤት መብቃቱ ላይ ነው፡፡ “የትም ፍጪው ዱቄቱን አምጭው” እንደሚባለው፡፡ በመሰረቱ አንድ ሰው በሃይማኖቱም ሆነ በማንም እገዛ ለውጤት በቃሁ ብሎ መናገር መብቱ ነው ለምን ቢባል እንዴት ሆኖ ለአሸናፊነት እንደበቃ የሚያውቀው እሱ ብቻ ነው፡፡ ስለዚህ በተጠየቀበት መድረክ ሁሉ የራሱን የህይወት ተሞክሮ መናገር የዛ ሰው መብት ነው፡፡ ከጠንካራ እና ከስኬታማ አሸናፊ ሰዎች ጀርባ ጠንካራ ሴት፣ ሀይማኖት፣ ቤተሰብ ወ.ዘ.ተ ሊኖር እንደሚችል ደግሞ የተጠኑ ማስረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ በዚህ ዙሪያ ስለ ታዋቂ እና ስኬታማ ሰዎች የተጻፉ ብዙ መፅሐፎችን መጥቀስ ይቻላል፡፡

ፈጣሪ ያዳላል ላሉት አንድ ሰው ስለ አንድ ነገር ለመናገር መጀመሪያ ማወቅ አለበት፡፡  ፀሐፊው ግን፤ የሃይማኖቶችን ታሪክና አስተምህሮ አያውቁትም ማወቅም አይፈልጉም፤ አያምኑበትም፡፡ ስለዚህ ወደ ስህተት ገብተዋል፡፡ ይህንንም ማሳየት ከተፈለገ ፈጣሪ ማለት  በየትኛውም ሀይማኖቶች እምነት (ዶክትሪን) “የሚሳነው ነገር የሌለ፤ ዘለአለማዊና አሸናፊ ነው፡፡” ስለዚህ ከፈጣሪ ጋር የሆኑ ሰዎች ሁሉ አሸናፊዎች ናቸው፡፡ ንጉስ ከሠራዊቱ ብዛት፣ ባለፀጋ ከሀብቱ ብዛት፣ ጠቢብም ከጥበቡ ብዛት ከሞት አያመልጥም፤ ፈጣሪ ግን ለዘለዓለም ይኖራል፡፡ ይህ ማስረጃ ፈጣሪ አሸናፊ ለመሆኑ በቂ ይመስለኛል፡፡ ባናምንም መቼም አንካካድም፡፡ በቴክኖሎጂና በሰው ልጅ ጥበብ የሚወጣ ፀሀይ፣ የሚዘንብ ዝናብ፣ የምንተነፍሰው አየር የለም፡፡ “አሳ ጎርጓሪ ዘንዶ ያወጣል” አቶ አለሙ ጠንቀቅ ማለት ጥሩ ነው፡፡ አንዳንዴም ራስን ተማሪ አላዋቂ ማድረግ ይጠቅማል፡፡ ሌላው ሀይማኖት ያለቦታው ጣልቃ እየገባ ያሉት ነው፡፡ የሀይማኖት ነገር መስማት አልፈልግም ካሉ አማኝ ሕዝብ የሌለበት ፕላኔት ማፈላለግ ግድ ይልዎታል፡፡ የዚህ ምድር ሕዝብ የሚኖርባት ዓለም ውስጥ እስካለን ድረስ ፖለቲካም፣ ሃይማኖትም፣ ሳይንስም፣ ወ.ዘ.ተ መስማታችን አይቀሬ ነው፡፡ ማንኛችንም በምንኖረው ኑሮ ውስጥ እስከጠቀመን ድረስ ከፖለቲካውም ከሃይማኖቱም ከሳይንሱም እንጋራለን፡፡

በአሁኑ ሰዓት ሰው ከገዢው ፓርቲ ጭቆናና “እኔ ነኝ አዋቂ፤ ከኔ ሌላ ለኢትዮጵያ የሚበጅ ፓርቲ አልተወለደም አይወለድም” በሚል ዲስኩር በመጐዳቱ ከፖለቲካ ብሶት የተነሳ ዝምታና ትዕግስትን መምረጡ የኢትዮጵያ ህዝብ እሚያወራው ስላጣ ሀይማኖት ማውራት ጀመረ አያስብልም፡፡ ኧረ በህግ! የኢትዮጵያ ታሪክ በሚል ርዕስ የተፃፉ ብዙ መጽሀፍቶች አሉና ያንብቡ፡፡ ከኢህአዴግ መፈጠር በፊትም የኢትዮጵያ ሕዝብ የብዙ ሀይማኖቶች ባለቤት ሆኖ ኖሯል፡፡

ለዚህም 200 ዓመት እና ከዛም በላይ ዕድሜ ያስቆጠሩ ቤተ አምልኮቶች ምስክሮች ናቸው፡፡ ከዚህ በተረፈ ግን የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ሲመረቁም ይሁን አትሌቶች ሲያሸንፉ ታዋቂ አርቲስቶችም ይሁን ምሁራኑ ወይም ባለስልጣኑ በግል ህይወቱ ተሞክሮ ላይ ቃለ መጠይቅ ሲደረጉ በሀይማኖቴ እገዛ፣ በፀሎቴ ሀይል፣ በእግዚአብሔር ዕርዳታ፣ በአላህ ሀይል፣ በወላዲተ አምላክ ፀሎት እያሉ ሲናገሩ ልንረዳቸው የሚገባን ለውጤት የበቁበት የህይወት ተሞክሯቸው መሆኑን መቀበል ብቻ ነው፡፡ እነዚህ ሰዎች በእርግጠኝነት ሁሉም ጋዜጠኛ ይመሰክራል ብዬ አምናለሁ “በኔ ሀይማኖት ካላመናችሁ እኔ የደረስኩበት አትደርሱም” ብለው አያውቁም፡፡ ስለዚህ ከላይ የተጠቀሰውን ንግግር መናገራቸው ስብከት አያሰኝም፡፡ ስለዚህ የለም በጥረታችሁ እና በስኬታችሁ እንጂ እናንተ በምትሉት አላሸነፋችሁም ማለት የጤነኛ አስተሳሰብ መገለጫ አይደለም፡፡

በመጨረሻም አንድ ገጠመኜን ላጋራና እንሰነባበት፡፡ በአንድ ወቅት በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል የታመመ ሰው ለማሳከም ሄጄ ወረፋ በመጠባበቅ ላይ እያለሁ፣ በርከት ያሉ ሰዎች እንኳን ደስ አለሽ እያሉ የሚስሟት አንዲት ቆንጆ ወጣት ትኩረቴን ሳበችውና ጠጋ ብዬ የደስታቸውን ምክንያት ጠየቅሁ፡፡ ከዚህ በፊት በዚህ ሆስፒታል ለህክምና መጥታ የኤች አይ ቪ ታማሚ መሆንዋ ተነግሯት፣ ኤች አይ ቪ ፖዘቲቭ ሰርተፊኬት የነበራት ሲሆን ለሶስት ወር በቤተ-እምነቷ በፀሎት ቆይታ ሙሉ ለሙሉ ጤነኛ መሆንዋን ስላወቀች (ስለተፈወሰች) የቀድሞ ዶክተሯ ጋ መጥታ ምርመራ ስታደርግ የኤች አይ ቪ ኔጌቲቭ (ነፃ) ሰርተፍኬት ተሰጥቷት በፌሽታ ወደ ቤትዋ ሄዳለች፡፡

አሁን እንግዲህ እርስዎ እንዳሉት ይህች ልጅ በቃለ መጠይቅ ሰዓት በጥረቴ እና በስኬቴ ዳንኩ ትበል? እኔ እመክርዎታለሁ፤ ሶስተኛ ዓይን ያፈላልጉ - ስህተትዎትን አይተው የሚታረሙበት፡፡ መልካም እናስብ ቅን እንሁን፣ ሌሎችን እንረዳ፣ የሌሎችንም ሃሳብ በበጎ እንይ፡፡ ወደ አንድነታችን የሚወስደንን መንገድ እንያዝ፤ መለያየት ወደ ሞት እንጂ ወደ ህይወት አያደርስምና፡፡ ቸር እንሰንብት

 

 

Read 3305 times Last modified on Saturday, 30 June 2012 12:09