Print this page
Saturday, 08 February 2020 15:18

ፍሬቻ ሳያሳዩ እጥፋት!

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(1 Vote)

          “እናላችሁ… በቀጥተኛ መንገድ የመጣን መስለን ድንገት ፍሬቻ ሳናሳይ የምንታጠፍ በዝተናል፡፡ ፍቅራችንም፣ ጠባችንም ፍሬቻ የሌለው መኪና እየሆነ ነው፡፡ ወደን፣ ‘በፍቅር አብደን’ ጨርቃችንን ልንጥል የደረስን ሆነን እንከርምና…ድንገት ደግሞ “መቃብሬ ላይ እንዳትቆም” የምንባባል ጠላቶች እንሆናለን፡፡--”
        
                እንዴት ሰነበታችሁሳ!
“እንዴት አይነት  ሰው መሰላችሁ! ጊዜ የማይለውጠው፣ ሰው ከሰው የማይለይ…ብቻ በአሁኑ ዘመን እንደሱ አይነት ሰው ማግኘት መታደል ነው፡፡” እንዲህ ሲባል የነበረው መቼ  መሰላችሁ… ትናንት፡፡ ደግሞላችሁ… ማነው የሚሉት ዘፋኝ “ትናንት ዛሬ አይደለም” ምናምን የሚል ዘፈን አለው አይደል…በቃ ትናንት ዛሬ አይደለም፡፡
“ሰው መሰላችሁ! የለየት ተንኮለኛ፣ ማሺንክ ነው፡፡ አንገቱን የሚደፋው እኮ ለስትራቴጂ ነው፡፡ የሆነ ምድር ለምድር የሚሳብ ሸለምጥማጥ የሆነ ጉረኛ! በእሱ አቅም ደግሞ ሰው ይንቃል፡፡… ኸረ ቀስ! ሳይቸግራችሁ “እህ!” ብላችሁ እየሰማችሁ፣ ሰውየውን በሌለበት አስቀጠቀጣችሁትሳ! ይሄ ደግሞ እየተባለ ያለው ዛሬ ነው፡፡ የምር አስቸጋሪ ነገር ነው፡፡
እዚህ ሀገር አንድ ሰሞን ሰማይ አውጥቶ፣ በእጅ ‘የሚሠራ’ የትራፊክ ቀይ መብራት እስኪመስል ማጨብጨብ፣ ሌላ ጊዜ ደግሞ ምድር አውርዶ ባጨበጨቡት እጅ፣ በጥፊ ለማጠናገር መሞከር… አለ አይደል… ከአንድ መሶብ እንዳንቋደስ እያደረገን ነው:: እና በሆነ ባልሆነው ዥዋዥዌ በዛ፤ በሆነ ባልሆነው አጥር ዝላይ በዛ! ምንም ነገር ሳይለወጥ፣ የነበረው ሁሉ እንዳለ ሆኖ፣ ጠዋት የባረኩትን ምሽት ላይ መርገም በዛ!
“ስሚ ያቺ ጓደኛሽ፣ ማን ነበር ስሟ…ያቺ እንኳን ከእህቶቼ በላይ የማምናት የምትያት…”
“እና ስለ እሷ ምን ይጠበስልህ!”
“አትቆጪ እንጂ፣ እኔ ደህና ነች ወይ፣ አይቻት አላውቅም ልልሽ እንጂ ለሌላ አይደለም፡፡”
“እኔ የእሷ ዘበኛ ነኝ! ወይ እንድጠብቃት ቀጥረኸኛል?”
“እምዬ ድረሽ!” “ኦ ማይ ጎድ!” ወይም ‘ለዘመኑ በሚስማማ ቋንቋ’ “እዚህ ወራጅ አለ!” ብሎ መጮህ ይህን ጊዜ ነው፡፡ እኔ ምለው… ምን ነክቶናል! ከስንት ቀን በፊት “የወርቅ አክሊል ካልደፋሁላት…” አይነት ልትልላት ምንም ያልቀራትን  ምን ተገኘና ነው፣ ይሄ ሁሉ ቁጣ!
“በቃ ተይው፣ ሌላ ነገር እናውራ፡፡”
“እኔ ነኝ ከእህቶቼ በላይ እሷን የማምን! የሆነች ምቀኛ! ደግሞ እሷን ሰው ብለህ ትጠይቀኛለህ?”
“በቃ ትቸዋለሁ አልኩሽ እኮ!”
እናላችሁ… ትናንት ሰማይ ላይ ስላደረሱላችሁ ሰው፣ ሰንበት ብላችሁ የሆነ ነገር ስትጠይቁ ጠንቀቅ ነው፡፡ ትናንት ዛሬ አይደለማ!
ይኸው ምድረ ፖለቲከኛ አንዴ መንከባለል ጀምራ የሚያቆማት ሰው እንዳጣች ኳስ “አዙረኝ አታዙረኛ” ምናምን ጨዋታ የሚጫወተው ትናንት “የቁርጥ ቀን አጋሬ” ያለውን ሰው መሽቶ ሲነጋ “ደመኛ ጠላቴ፣” እያለ አይደል እንዴ! ፖለቲከኞች፤ ስደብ የሚያምረው በእናንተ ሳይሆን በትረምፕ ነው! ቂ…ቂ…ቂ…
እኔ የምለው… እግረ መንገድ የሆነ ነገር ትዝ ብሎኝ ነው፣ ይሄ ተሳፋሪዎች ቀበቶ እሰሩ ምናምን የተባልነው ነገር አለ አይደል… ነገርየው አሪፍ ነው፡፡ እንደውም እዚህ ሀገር አብዛኛው ‘ስልጣኔያችን’ ሰውነታቸው ላይ ‘መሀረብ ቢጤ ጣል አድርገው’ የሚደንሱ ወጣቶች በበዙባቸው የዘፈን ክሊፖችና፣ “ከእንትን ሀገር የወሰድነው…” በሚሉ የንግግር ማሳመሪያዎች ታጥሮ ቀረና ነው እንጂ ቀበቶ ማሰር ከአስርት ዓመታት በፊት መጀመር የነበረበት ነው::
እናላችሁ አሁን “ቀበቶ እሰሩ” ስንባል እኛን ለመከላከል ሳይሆን እኛን ለመቅጣት የተደረገ እያሰመሰልነው ነው:: አንዱ “ቀበቶ እሰር” የተባለና በአለባበሱ ዘመናዊ ለመምሰል ለሽልማት የሚያበቃ ጥረት ያደረገ (ቂ…ቂ…ቂ…) ዘመነኛ ቢጤ ተሳፋሪ ምን አለ መሰላችሁ… “በገመድ የጠፈሩኝ ነው የሚመስለኝ፡፡” እንግዲህ በእሱ ቤት ማጣጣሉ ነው፡፡ እናላችሁ…በዚህ በቀበቶ ጉዳይ፣ በተለይም ሚኒባስ ታክሲዎች ላይ እኛም ገራሚዎች፣ አንዳንድ ሾፌሮችም ገራሚዎች ሆነናል፡፡
ምን መሰላችሁ…መአት ታክሲዎች ላይ ቀበቶውንና የቀበቶውን ዘለበት ብታገኙት እንኳን መጀመሪያ ነገር ሙሉ ለሙሉ አይሳብላችሁም፤ ሙሉ ለመሉ ከተሳበላችሁም የዘለበቷ ማስገቢያ በቀላሉ አትገኝም፡፡ (ብቻዋን እየተነቀለች ትቸበቸባለች እንዴ! ያልተቸበቸበ፣ በመቸብቸብ ላይ ያልሆነና ወደፊት የማይቸበቸብ ነገር የለም በሚል ነው፡፡)
ታዲያላችሁ ማስገቢያዋ በሌለችበት ምን ቢሆን ጥሩ ነው…ሾፌር ሆዬ “ያዝ አድርገው” ይላችኋል፡፡ እናማ…አለ አይደል…ሦስት፣ አራት ሳምንት የቀረው ጽንስ እንደ ጄት ሊ ‘እየተራገጠ’ ያስቸገራት ነፍሰጡር ሆዷን ደገፍ አንደምታደርገው፣ እናንተም ቀበቶዋን ሆዳችሁ ላይ ለጠፍ አደርጋችሁ ይዛችሁ ትሄዳላችሁ:: እናማ…በፊት ጋቢና ለመግባት የምንሯሯጥ ሰዎች አሁን ‘ከሰፊው ህዝብ’ ጋር ወደ ኋላ መቀመጥ እየጀመርን ነው ለማለት ያህል ነው፡፡
ሰዓቱ ከምሽቱ አስራ ሁለት ሰዓት፡፡ እሷዬዋ ከሥራ ወጥታ የአዲስ አበባን ምክንያታዊና ምክንያተ-ቢስ ግርግርና ትርምስ ተቋቁማ እንደተለመደው ቤቷ ሳይመሽ ገብታለች:: ባሌ ሆዬ ደግሞ ያለወትሮው ቀድሞ ገብቶ ተኮፍሷል::
“ሥራ የምትወጪው አስራ አንድ ሰዓት፣ እስካሁን የት ነበርሽ?”
“ዛሬ ምን ነክቶሀል! ሰዓቱ ገና አይደለም እንዴ!”
“አስራ ሁለት ሰዓት ነው ገና? ስንት ሰዓት ልትመጪ አስበሽ ነበር? አራት ሰዓት!”
“ሰውየው ዛሬ ምን ነክቶታል! እና አስራ አንድ ሰዓት ከሥራ ወጥቼ ሁለት ታክሲ ይዤ፣ አስራ አንድ ሰዓት ከአምስት እንድደርስልህ ነው!”
“እሱን እንጃልሽ! ብቻ ከዛሬ ጀምሮ አስተካክይ::”
“ምኑን ነው የማስተካክለው! ምነው እስከዛሬ አስራ ሁለት ሰዓት ቤት የምትደርሺው ትራንስፖርቱንስ፣ ግፊያውንስ እንዴት ችለሽው እንደሆነ ይገርመኛል ስትለኝ አልነበር እንዴ! ዛሬ ምን ተግኝቶ ነው ትንፋሼን እንኳን ሳልሰበሰብ የምትነጅሰኝ!”
“ብቻ ተናግሬያለሁ…”
እሱ ጂኑን መገልበጫ ፈራንካ አጥቶ በጊዜ ገብቷልና እሷ ምን እዳ አለባት!
የምር…ሰውየው እኮ ትናንት ከትናንት ወዲያ ባለቤቱ ሁልጊዜም ቤት የምትገባው ሳይመሽ እንደሆነ እየደሰኮረ ደረቱን ይነፋ ነበር፡፡ የጂን ወዳጆቹ…“የደበቃችሁት መኪና ቢኖራችሁ ነው እንጂ፣ እንዴት ከጫፍ ጫፍ በአንድ ሰዓት ውስጥ ትደርሳለች” እያሉ ሲያዳንቁት ነው እኮ የከረሙት፡፡  እሱም… “የእኔ ባለቤት እግዜር በሁሉም ነገር እጁን ታጥቦ የሠራት ነች” እያለ መሸለያው ነች እኮ! (እኔ የምለው… እንግዲህ ጨዋታም አይደል…እግዜር እጁን ታጥቦ የሠራቸው ካሉ እኛ ምንድነን ማለት ነው? አሀ ልክ ነዋ…‘የቁመት ሞክሼዎቼ’ እንደዚህ የሰፋ የሴንቲ ሜትር ልዩነት የመጣበት ምክንያት ይጣራልናማ!
ስሙኝማ…ድሮ አንድ የብሶት መግለጫ ዜማ ነበረች…
እኔን ለቸገረኝ ለበላሁ ሽምብራ
ጓደኛዬ ጠላኝ እንደባላጋራ
የምትል፡፡ የምር ግን…አለ አይደል… ይቺ ስንኝ እንደ ታሪካዊ ማስረጃነትም ልታገለግል ትችላለች፡፡ ልከ ነዋ…በዛን ጊዜ የቸገረው ሰው ሽምብራ ይበላል እንጂ ጦሙን አያድርማ! ደግሞ ሽምብራ እኮ የምግብ ይዘቷ የጉድ ነው፡፡ አሁን “ለተሟላ ጤንነት ከወርችና ከቅልጥም ጋር መታገላችሁን ተዉና አረንጓዴ አብዝታችሁ ተመገቡ የምንባልበት ዘመን ሊመጣ… “ሆድን በጎመን ቢደልሉት፣ ጉልበት በዳገት ይለግማል” እያልን እንዘባበትባት ነበር እኮ! ደግነቱ የቲማቲምና የሽንኩርትን ያህል አልተቀየመችንም፡፡ ቂ…ቂ…ቂ…
እናላችሁ… በቀጥተኛ መንገድ የመጣን መስለን ድንገት ፍሬቻ ሳናሳይ የምንታጠፍ በዝተናል፡፡ ፍቅራችንም፣ ጠባችንም ፍሬቻ የሌለው መኪና እየሆነ ነው፡፡ ወደን፣ ‘በፍቅር አብደን’ ጨርቃችንን ልንጥል የደረስን ሆነን እንከርምና…ድንገት ደግሞ “መቃብሬ ላይ እንዳትቆም” የምንባባል ጠላቶች እንሆናለን:: (ስሙኝማ…ለጠቅላላ እውቀት ያህል፣  ሰውየው መቃብሩ ላይ ባለመቆሙ ቅዠት ይቀርለት እንደሆነ እንጂ፣ ምን እንዳያጣ ነው!) ፍሬቻ ሳያሳዩ የመታጠፍን ዘመን ያሳጥርልንማ!   
ደህና ሰንብቱልኝማ!

Read 1612 times