Saturday, 08 February 2020 15:10

ኮሮና ቫይረስ በሳምንቱ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

ቻይናን ጨምሮ በመላው አለም በኮሮናቫይረስ የተጠቁ ሰዎች ቁጥር እስከ ትናንት ድረስ ከ28 ሺህ ማለፉንና በቫይረሱ ለሞት የተዳረጉት ሰዎች ቁጥርም 565  መድረሱን የተለያዩ አለማቀፍ የመገናኛ ብዙሃን ባወጧቸው ዘገባዎች ገልጸዋል፡፡
ከቻይና ውጭ በተለያዩ 31 የአለማችን አገራት በኮሮናቫይረስ የተጠቁ ሰዎች ቁጥር እስከ ትናንት ድረስ 262 ያህል መድረሱን የዘገበው ሮይተርስ፣ በሆንግ ኮንግ አንድ፣ በፊሊፒንስ አንድ ሰው ለሞት መዳረጋቸውንም አመልክቷል፡፡
ከትናንት በስቲያ በቻይናዋ ውሃን ግዛት የተወለደ ጨቅላ ከተወለደ ከ30 ሰዓታት በኋላ በኮሮናቫይረስ መጠቃቱ በምርመራ መረጋገጡን የዘገበው ሮይተርስ፣ የህጻኑ እናት ከወሊዱ በፊት በተደረገላት ምርመራ በቫይረሱ መጠቃቷ መረጋገጡንና ይህም ቫይረሱ ከእናት ወደ ልጅ የመተላለፍ ዕድል እንዳለው ፍንጭ የሚሰጥ በመሆኑ ተመራማሪዎች ትኩረት እንዲሰጡት ማድረጉን አመልክቷል፡፡
በጃፓኑ ዩኮሃማ ወደብ ዳርቻ ስትንቀሳቀስ በነበረች አንዲት ግዙፍ መርከብ ውስጥ ከነበሩ መንገደኞች መካከል 20ዎቹ በኮሮናቫይረስ እንደተጠቁ መረጋገጡን ተከትሎ፣ መርከቧ እንዳትንቀሳቀስ መደረጓንና መንገደኞች ለ14 ቀናት ያህል መርከቧ ውስጥ ይቆያሉ መባሉንም ዘገባው አመልክቷል፡፡ በሆንግ ኮንግም በተመሳሳይ ሁኔታ፣ 3 ሺህ 600 መንገደኞችን ይዛ ስትጓዝ ከነበረች መርከብ ውስጥ 3 መንገደኞች በቫይረሱ መጠቃታቸው መረጋገጡን ተከትሎ፣ ተጓዦች ከመርከቧ እንዳይወጡ ተደርገው ምርመራው መቀጠሉንና የአገሪቱ መንግስት ከቻይና የሚገቡ መንገደኞችን በሙሉ በልዩ የተገለለ ስፍራ እንደሚያቆይ ማስታወቁም ተነግሯል፡፡
የአለም የጤና ድርጅት የኮሮናቫይረስን ስርጭት ለመግታት ለሚደረገው ጥረት የተባበሩት መንግስታት ድርጅት አባል አገራት 675 ሚሊዮን ዶላር እንዲለግሱ ጥሪ ማቅረቡ የተነገረ ሲሆን፣ ቢል እና ሚሊንዳ ጌትስ ፋውንዴሽን ከትናንት በስቲያ ለኮሮና ቫይረስ ክትባት ምርምርና ህክምና የሚውል የ100 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ ማድረጉንም ፎርብስ ዘግቧል፡፡
ባለፈው ሳምንት በመቶዎች የሚቆጠሩ ዜጎቿን ከቻይናዋ ውሃን ግዛት ያስወጣችው አሜሪካ፤ ባለፉት ቀናትም ተጨማሪ 350 ዜጎቿን ማስወጣቷንና ሰዎቹ ካሊፎርኒያ ውስጥ በሚገኙ ወታደራዊ ማዕከላት ከሰው ተገልለው እንዲቀመጡ መደረጋቸው ተነግሯል:: የታይዋን መንግስት ከሃሙስ ጀምሮ ከቻይና ለሚመጡ ሰዎች ድንበሯን ዝግ ማድረጉን በይፋ ያስታወቀ ሲሆን፣ አውስትራሊያና ኒውዚላንድን ጨምሮ በርካታ የአለማችን አገራት ዜጎቻቸውን ማውጣት መቀጠላቸውም ተዘግቧል፡፡
ከአውሮፓ አገራት መካከል ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ዜጎቿ በቫይረሱ የተጠቁባት አገር ጀርመን መሆኗን የዘገበው አሶሼትድ ፕሬስ፣ እስከ ትናንት ድረስ 12 ጀርመናውያን በቫይረሱ መጠቃታቸውንም አመልክቷል፡፡ በአሜሪካም በተመሳሳይ የኮሮና ቫይረስ ተጠቂዎች ቁጥር 12 መድረሱን ዘገባው አስታውቋል፡፡
በቻይናዋ የፋይናንስ ከተማ ሻንጋይ የሚገኙ ትምህርት ቤቶች በሙሉ ለአንድ ወር ያህል እንዲዘጉ መወሰኑን የዘገበው ሮይተርስ፣ ኤር ካናዳ፣ ኤር ፍራንስ፣ ኤር ኢንዲያ፣ ኤር ታንዛኒያና ኳታር ኤርዌይስን ጨምሮ ወደ ቻይና የሚያደርጉትን በረራ ሙሉ ለሙሉና በከፊል ለማቋረጥ የወሰኑ አየር መንገዶች መበራከታቸውን ጠቁሟል፡፡ ኮሮና ቫይረስ በአለማቀፍ ደረጃ እያሳደረ የሚገኘው ኢኮኖሚያዊ ተጽዕኖ ተባብሶ መቀጠሉን የዘገበው ዘ ጋርዲያን በበኩሉ፣ በታላላቅ አየር መንገዶች፣ በመኪና አምራችና የቴክኖሎጂ ኩባንያዎች፣ በቱሪዝም ተቋማት፣ በአክሲዮን ገበያዎች ወዘተ ላይ እጅግ ከፍተኛ ተጽዕኖ ማድረሱን አመልክቷል፡፡
ከ170 ቀናት በኋላ የሚጀመረው የ2020 የቶኪዮ ኦሎምፒክ በኮሮና ቫይረስ ምክንያት ሊስተጓጎል እንደሚችል ከፍተኛ ስጋት መፈጠሩን የአዘጋጅ ኮሚቴው ሃላፊ ከትናንት በስቲያ በሰጡት መግለጫ መናገራቸውንም ዘገባው አክሎ ገልጧል፡፡
በሌላ ዜና ደግሞ፣ ከቻይና የኮሮና ቫይረስ ስርጭት መባባስ ጋር ተያይዞ የአፍ መሸፈኛ ጭንብል እጥረት ገጥሟት በሰነበተችው ሆንግ ኮንግ ከሰሞኑ ደግሞ የመጸዳጃ ቤት ወረቀትና የኮንዶም እጥረት መከሰቱን ብሉምበርግ ዘግቧል፡፡
ማህበራዊ ድረገጾች ባለፉት ቀናት ያሰራጩት የምርቶች እጥረት ማስጠንቀቂያ መልዕክት በርካታ ዜጎችን እንዳስጨነቃቸውና ምርቶችን በብዛት መግዛት እንዳስጀመራቸው የጠቆመው ዘገባው፤ ካለፈው ረቡዕ አንስቶ በአገሪቱ በሚገኙት መደብሮች የመጸዳጃ ቤት ወረቀትና ኮንዶምን ጨምሮ በርካታ ሸቀጦች መጥፋታቸውን አስታውቋል፡፡

Read 2042 times