Print this page
Saturday, 08 February 2020 14:53

ኢትዮጵያ የራሷን የነዳጅ ምርት መጠቀም ጀመረች

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(15 votes)

  1650 በርሜል ድፍድፍ ነዳጅ ለአገር ውስጥ ገበያ ቀርቧል

             ኢትዮጵያ የራሷን የነዳጅ ምርት ለአገር ውስጥ ፍጆታ መጠቀም የጀመረች ሲሆን፤ የማዕድንና ነዳጅ ሚኒስቴር ባለፉት 6 ወራት 1650 በርሜል ድፍድፍ ነዳጅ ለሀገር ውስጥ ገበያ መቅረቡን አስታውቋል፡፡
በመጪው ሣምንት ለህዝብ ተወካዮች ም/ቤት ሊቀርብ በተዘጋጀው የማዕድንና ነዳጅ ሚኒስቴር የ6 ወራት የስራ አፈፃፀም ሪፖርት፤ በሶማሌ ክልል ኦጋዴን ከአንድ አመት ተኩል በፊት በሙከራ ደረጃ መመረት የጀመረው ነዳጅ፤ ባለፉት 6 ወራት ለሀገር ውስጥ ገበያ ሲቀርብ መቆየቱን ያመለክታል፡፡
‹‹ኒው ቢዝነስ ኢትዮጵያ›› የተሰኘው ድረ ገጽ፣ ማዕድንና ነዳጅ ሚኒስቴርን ጠቅሶ ባወጣው መረጃ፤ በሙከራ ደረጃ ካለፈው ሐምሌ 2011 ጀምሮ ላለፉት 6 ወራት 1650 በርሜል ድፍድፍ ነዳጅ ለሀገር ውስጥ ገበያ መቅረቡንና በዚህም ሀገሪቱ ከውጭ ተገዝቶ ለሚገባ ነዳጅ ታወጣ ከነበረው የውጭ ምንዛሪ፣ 55ሺህ 994 ዶላር ማዳን መቻሏን ጠቁሟል፡፡
በኦጋዴን ያለውን የነዳጅ ምርት ከሀገር ውስጥ ገበያ ባሻገር ወደ ውጪ ለመላክ፣ ከኦጋዴን እስከ ጅቡቲ የውስጥ ለውስጥ ነዳጅ ማስተላለፊያ መስመር ግንባታ በቅርቡ እንደሚጀመርም ታውቋል፡፡ የኢትዮጵያን ነዳጅ ከሚረከቡ 3 የውጭ ሀገር ኩባንያዎች ጋር ስምምነት መፈረሙም በሥራ አፈፃፀም ሪፖርቱ ላይ ተገልጿል፡፡ በአጠቃላይ በኢትዮጵያ የማዕድን ዘርፍ በአመቱ ከ60ሺህ በላይ ለሚሆኑ ዜጐች የስራ እድል መፈጠሩንም ለማወቅ ተችሏል፡፡

Read 14946 times