Saturday, 08 February 2020 14:49

በቻይና የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ተማሪዎች ተማፅኖአችን ሰሚ አላገኘም ሲሉ አማረሩ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(2 votes)


             በኮሮናቫይረስ በከፍተኛ ደረጃ በተጠቃችው የቻይና ውሃን ግዛት የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ተማሪዎች፣ መንግስት ወደ ሀገራቸው እንዲመልሳቸው ቢማፀኑም ምላሽ የሚሠጣቸው አካል ማጣታቸውን አስታወቁ፡፡ ተማሪዎቹ በተለያዩ የማህበራዊ መገናኛ መድረኮችና በመገናኛ ብዙኃን ባስተላለፏቸው መልዕክቶች፣ በየዩኒቨርስቲያቸው ማደሪያ ክፍሎች ተዘግቶባቸው ላለፉት 15 ቀናት መውጣትና መንቀሳቀስ እንዳልቻሉ ጠቁመዋል::
‹‹ሁኔታው እጅግ አስጨናቂ ነው፤ በየቀኑ ሰው በቫይረሱ ይያዛል፣ ይሞታል” ስትል ለመገናኛ ብዙሃን ያስረዳችው አንዲት ኢትዮጵያዊ ተማሪ፤ መንግስት ከዚህ ስጋት ሊታደገን ይገባል›› ብላለች፡፡ ‹‹እስካሁን በቻይና የሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ አንዳችንንም አግኝቶ ሊያነጋግረን ሙከራ አላደረገም›› የሚሉት ተማሪዎቹ፤ ‹‹በተለያየ አግባብ ያደረግነው ጥሪም በቸልታ ታልፏል›› ብለዋል፡፡ ‹‹የሌሎች ሀገራት ዜጐች የሆኑ ተማሪዎች በየመንግስቶቻቸው ወደየሀገራቸው ተወስደዋል፤ በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያውያን ብቻ ናቸው በየማደሪያ ክፍሎቻቸው የቀሩት›› ብለዋል - ተማሪዎቹ፡፡ በተማሪዎቹ አቤቱታ ዙሪያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ የሆኑትን አቶ ነቢያት ጌታቸው በስልክ አግኝተን ለማነጋገር ያደረግነው ሙከራ አልተሳካም፡፡በሌላ በኩል፣ የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር፣ 29 የጥርጣሬ ጥቆማዎች እንደደረሱትና ከእነዚህ ውስጥ 14ቱ በበሽታው የሚያስጠረጥሩ ምልክቶች በማሳየታቸው በምርመራ ተለይቶ እስኪታወቅ በማግለያ ውስጥ ክትትል ሲደረግላቸው መቆየቱን፣ ከእነዚህ ውስጥ ስምንቱ በምርመራ ነጻ መሆናቸው መረጋገጡንና የቀሪዎቹ ውጤት እየተጠበቀ መሆኑንም አስታውቋል፡፡ በተመሳሳይ፣ ከቻይና ሁዋን ግዛት ወደ ኢትዮጵያ የሚገቡ ማናቸውንም መንገደኞች በለይቶ ማቆያ ማዕከላት ውስጥ እንዲቆዩ ተወስኗል ተብሏል፡፡

Read 11508 times