Monday, 03 February 2020 12:07

“ኮሮና ቫይረስ” እና ዓለማችን በመሰንበቻው

Written by 
Rate this item
(6 votes)

   ከእስያ እስከ አሜሪካ፣ ከአውሮፓ እስከ መካከለኛው ምስራቅና አፍሪካ መላውን አለም በስጋት ማራዱን፣ ብዙዎችን ለህልፈተ ህይወት መዳረጉን፣ ከጤና ችግርነት አልፎ የኢኮኖሚና የፖለቲካ ቀውስ ማስከተሉን ተያይዞታል - በቻይና ተቀስቅሶ በፍጥነት በርካታ አገራትን ማዳረሱን የቀጠለው አደገኛው የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ፡፡
ባለፈው ወር በቻይናዋ ዉሃን ግዛት ለመጀመሪያ የታየውና እያደር እየተስፋፋና በወረርሽኝ መልክ በመከሰት አህጉር ተሻግሮ ወደተለያዩ የአለማችን አገራትን በመዛመት ብዙዎችን ማጥቃቱን የቀጠለው ኮሮና ቫይረስ የአለማችን መገናኛ ብዙሃን የሳምንቱ ዋነኛ ርዕሰ ጉዳይ ሆኖ ዘልቋል፡፡ የተለያዩ መገናኛ ብዙሃን ጉዳዩን በተመለከተ በሳምንቱ ካወጧቸው ዘገባዎች የቀነጫጨብናቸውንና የኮሮና ቫይረስን ወቅታዊ ሁኔታ ያስቃኛሉ ያልናቸውን መረጃዎች እንዲህ ይዘን ቀርበናል፡፡

እያሻቀበ የመጣው የተጠቂዎችና የሟቾች ቁጥር
የቫይረሱ ወረርሽኝ በተቀሰቀሰባት ቻይና እስካ ትናንት ተሲያት ድረስ ከ213 በላይ ሰዎች ለሞት መዳረጋቸውንና በድምሩ ወደ 10 ሺህ የሚጠጉ ሰዎች በኮሮና ቫይረስ መጠቃታቸውን የአገሪቱ መንግስት ይፋ ባደረገው መረጃ ያስታወቀ ሲሆን፣ ከቻይና ውጭ በቫይረሱ የሚጠቁ ሰዎች ቁጥር መጨመሩ ከፍተኛ ስጋት መፍጠሩ ተነግሯል፡፡
ዘጋርዲያን እንደዘገበው እስከትናንት ረቡዕ ድረስ ታይላንድ 14፣ ሆንግ ኮንግ 8፣ ጃፓን 7፣ አሜሪካ፣ ታይዋንና አውስትራሊያ እያንዳንዳቸው 5፣ ሲንጋፖር፣ ደቡብ ኮርያ፣ ፈረንሳይና ማሌዢያ እያንዳንዳቸው አራት፣ ካናዳ 3፣ ቬትናም እና እንግሊዝ 2፣ ኔፓል፣ ካምቦዲያ፣ ጣሊያን፣ ጀርመንና የተባበሩት አረብ ኤሜሬቶች እያንዳንዳቸው 1 ዜጎቻቸው በኮሮና ቫይረስ መጠቃታቸውን በይፋ አስታውቀዋል፡፡

አገራት ዜጎቻቸውን እያወጡና ድንበር እየዘጉ፣ አየር መንገዶች በረራ እያቋረጡ ነው
አሜሪካ እና ጃፓን ባለፈው ረቡዕ ብቻ በቻይናዋ ውሃን ግዛት ውስጥ የሚገኙ በመቶዎች የሚቆጠሩ ዜጎቻቸውን ያስወጡ ሲሆን፣ እንግሊዝም በርካታ ዜጎቿን ወደ ግዛቷ መልሳለች ተብሏል፡፡
የእንግሊዙ ብሪቲሽ ኤርዌይስ ወደ ቻይና የሚያደርጋቸውን በረራዎች በሙሉ መሰረዙን ባለፈው ረቡዕ ያስታወቀ ሲሆን፣ የአሜሪካው ዩናይትድ ኤርላይንስም ወደ ቻይና ያደርጋቸው የነበሩ 24 በረራዎችን መሰረዙን ገልጧል፡፡
ወደ ቻይና ያደርጉት የነበረውን በረራ በእጅጉ ከቀነሱ ሌሎች የአለማችን አየር መንገዶች መካከልም ኤር ካናዳ፣ ካቲ ፓሲፊክ፣ ኤር ሴኡልና ላዮን ኤር አንደሚገኙበትም ዴይሊ ሜይል ዘግቧል፡፡
የፊት ጭምብል እጥረት ተከስቷል
ቫይረሱ በትንፋሽ የሚተላለፍ እንደመሆኑ ቻይናውያን አፍንጫ እና አፋቸውን በጭምብል ሸፍነው እንዲንቀሳቀሱ በመንግስት አካላት መመሪያ እንደተሰጣቸው የዘገበው ኒውዮርክ ታይምስ፣ ይህን ተከትሎም በአገሪቱ የጭምብል እጥረት መከሰቱን አመልክቷል፡፡
ይህን የአቅርቦት ችግር እንደመልካም አጋጣሚ በመጠቀም በመዲናዋ ቤጂንግ ጭምብሎችን ከመደበኛው ዋጋቸው በ6 እጥፍ ያህል ጨምሮ ሲሸጥ የተገኘ አንድ መድሃኒት ቤት 400 ሺህ ዶላር እንደተቀጣም ዘገባው ገልጧል፡፡
የተባበሩት መንግስታት የህጻናት መርጃ ድርጅት ዩኔሴፍ የቫይረሱን መስፋፋት ለመግታት የሚያገለግሉ ቁሳቁሶችን እጥረት ለመቅረፍ በማሰብ ጭንብልን ጨምሮ 6 ሜትሪክ ቶን የሚመዝኑ ቁሳቁሶችን ባለፈው ረቡዕ ወደ ቻይና መላኩን አስታውቋል፡፡
 
ክትባት ፍለጋ ደፋ ቀና
የኮሮና ቫይረስ ያጠቃቸው ሰዎች ቁጥር ከ17 አመታት በፊት በአገሪቱ ተከስቶ የነበው ሳርስ የተሰኘ የመተንፈሻ አካላት በሽታ ካጠቃቸው ሰዎች መብለጡን የዘገበው ዘጋርዲያን፣ ይህን ተከትሎም አገሪቱ ከአለም የጤና ድርጅትና ከሌሎች አገራት መንግስታት ጋር በመተባበር ወረርሽኙን ለመግታት ጠንክራ መስራት መጀመሯን አመልክቷል፡፡
ኮሮና እያደር ወደ በርካታ አገራት መስፋፋቱንና አለማቀፍ ስጋት መሆኑን ተከትሎ፣ ቻይናውያንን ጨምሮ የተለያዩ የአለማችን አገራት ስመጥር የህክምና ሊቃውንትና የዘርፉ ተመራማሪዎች ለዚህ አደገኛ ቫይረስ ክትባት ለማግኘት ሌት ተቀን ደፋ ቀና በማለት ላይ እንደሚገኙ ተነግሯል፡፡
ከቻይና ተመራማሪዎች በተጨማሪ የአሜሪካ እና የአውስትራሊያ የምርምር ተቋማትና ሳይንቲስቶች ወረርሽኙን ለመግታት የሚያስችል አንዳች መላ ለማግኘት ጥረት በማድረግ ላይ እንደሚገኙ የዘገበው ሮይተርስ፣ የሚልቦርን ተመራማሪዎች ከአንድ ታማሚ ደም በመውሰድ ለምርምር የሚውል ቫይረስ እየፈጠሩ መሆኑን አመልክቷል፡፡
ጉዳዩ አለማቀፍ ስጋት መሆኑን ተከትሎ የዓለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ቴድሮስ አድሃኖም ባለፈው ረቡዕ ወደ ቻይና አቅንተው ከአገሪቱ ፕሬዚዳንት ሺ ጂንፒንግ ጋር በቤጂንግ ውይይት ያደረጉ ሲሆን፣ ድርጅታቸው የቫይረሱን ስርጭት ከቻይና ጋር በትብብር እንደሚሰራ እና አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግም አስታውቀዋል፡፡
 
ኮሮና እና የአለም ኢኮኖሚ
በቻይና የሚንቀሳቀሱ የአሜሪካ ኩባንያዎች የኮሮና ቫይረስ መስፋፋቱን ተከትሎ ስራቸውን በከፊል ወይም ሙሉ ለሙሉ እያቋረጡ መውጣት መጀመራቸውን የተለያዩ አለማቀፍ መገናኛ ብዙሃን በመዘገብ ላይ ይገኛሉ፡፡
ስታርባክስ በቻይና ከሚገኙት መደብሮቹ ግማሹን ወይም ከ2ሺህ በላይ የሚሆኑትን መዝጋቱን ባለፈው ማክሰኞ ያስታወቀ ሲሆን፣ የአሜሪካው ማክዶናልድ፣ የጃፓኑ ኒፖንና የደቡብ ኮርያው ኤልጂ ኤሌክትሮኒክስም በቻይና የነበራቸውን ቢሮ በመዝጋት ስራ ማቋረጣቸውን አመልክቷል፡፡
ፌስቡክ፣ ማይክሮሶፍትና አፕል ሰራተኞቻቸው ወደ ቻይና እንዳይጓዙ እገዳ መጣላቸውን የዘገበው ዘ ጋርዲያን፣ በቻይና የሚገኙትም ለጊዜው ከቤት እንዳይወጡ ማስጠንቀቂያ መስጠታቸውን አስረድቷል፡፡
በሳምንቱ መጀመሪያ አራት ሰራተኞቹ በኮሮና ቫይረስ የተጠቁበት የጀርመኑ መኪና አምራች ኩባንያ ዌባስቶ በቻይና የሚገኘውን ፋብሪካውን ላልተወሰነ ጊዜ መዝጋቱን ያስታወቀ ሲሆን፣ የጃፓኑ ቶዮታ ኩባንያም እስከ መጪው የካቲት ወር አጋማሽ በቻይና ያለውን ፋብሪካውን እንደሚዘጋ አስታውቋል፡፡
የጃፓኑ ሆንዳ ሞተርስ ሰራተኞቹ ወደ ቻይና እንዳይሄዱ ማገዱንና ስታንዳርድ ቻርተርድ ባንክና የአውስትራሊያ ኮመንዌልዝ ባንክን ጨምሮ ታላላቅ አለማቀፍ ባንኮች ሰራተኞቻቸውን ወደ ቻይና እንዳይሄዱ ማገዳቸውንም አክሎ ገልጧል፡፡
በቻይና እየተዘጉ ያሉ ፋብሪካዎችና ኢንዱስትሪዎች እየተበራከቱ መምጣታቸው፣ አየር መንገዶችና አገራት ወደ ቻይና የሚያደርጉትን በረራ ማቋረጣቸውና በአውሮፕላን ጣቢያዎች የሚደረገው ምርመራ ጉዞን በማስተጓጎል ቢዝነስን መጉዳቱ አይቀሬ ነው እየተባለ ነው፡፡
በቻይና ሂልተንና ማሪዮትን የመሳሰሉ ሆቴሎች ስራቸውን ማቆማቸውን፣ ታላላቅ ሆቴሎችና የቱሪዝም መዳረሻዎች ኦና ውለው ማደር መጀመራቸውን የዘገበው ኒውዮርክ ታይምስ፣ የንግድ እንቅስቃሴ መገታቱንና ወረርሽኙ የቻይናን የአዲሱ አመት የመጀመሪያ ሩብ አመት ዕድገት ከ5 በመቶ በታች ሊያደርገው እንደሚችልም የኢኮኖሚ ባለሙያዎች በመናገር ላይ መሆናቸውን አመልክቷል፡፡

አፍሪካ
ባለፈው ረቡዕ ወደ መካከለኛው ምስራቅ መሻገሩና በተባበሩት አረብ ኤሜሬቶች አንድን ሰው ማጥቃቱ የተነገረለት ኮሮና፣ በዚህ አያያዙ በፍጥነት ወደ አፍሪካ መግባቱ እንደማይቀር የሚናገሩ ብዙዎች ናቸው፡፡
ደቡብ አፍሪካ፣ ኢትዮጵና ግብጽን የመሳሰሉ በርካታ የአፍሪካ አገራት በአውሮፕላን ማረፊያ ጣቢያዎቻቸው የምርመራ ማዕከላትን በመክፈት ቫይረሱ ወደ ግዛታቸው እንዳይገባ በተጠንቀቅ ሌት ተቀን እየሰሩ ይገኛሉ፡፡
የአፍሪካ ህብረት የጤናው ዘርፍ ሃላፊ የሰጡትን መግለጫ ጠቅሶ አናዶሉ ኤጀንሲ እንደዘገበው፣ በተለያዩ አገራት በወሬ ደረጃ የታመሙ ሰዎች ስለመኖራቸው ቢነገርም እስካለፈው ረቡዕ ድረስ በየትኛውም የአፍሪካ አገር በህክምና ምርመራ የተረጋገጠ በቫይረሱ የተጠቃ ሰው አልተገኘም፡፡

48 ሰዓት የፈጀው ሆስፒታል
የቫይረሱን ስርጭት ለመግታት ሌት ተቀን ታጥቃ የምትሰራው ቻይና 1 ሺህ አልጋዎች ያሉትን የኮሮና ቫይረስ ህክምና ሆስፒታል በ48 ሰዓታት ጊዜ ውስጥ ሙሉ ለሙሉ በማደራጀት ለአገልግሎት ክፍት ማድረጓ ተዘግቧል፡፡
5000 ያህል የቻይና የግንባታ ሰራተኞች፣ ኤሌክትሪሻኖችና ሌሎች ባልደረቦቻቸው በውሃን ግዛት አቅራቢያ የሚገኝን አንድ ባዶ ህንጻ በ40 ሰዓታት ውስጥ ተረባርበው ለሆስፒታልነት እንዲበቃ ማድረጋቸው ነው የተነገረው፡፡
ቻይና ሌሎች ሁለት አዳዲስ ሆስፒታሎችን በቀናት እድሜ ውስጥ ገንብታ ለማጠናቀቅ ተፍ ተፍ እያለች እንደምትገኝም ተዘግቧል፡፡
ቻይና ውሃንን ጨምሮ ቫይረሱ ከተስፋፋባቸውና 20 ሚሊዮን ያህል ህዝብ ከሚኖርባቸው ሶስት ግዛቶች መንገደኞች እንዳይወጡና ቫይረሱን እንዳያሰራጩ ለማድረግ ሲባል ሁሉም የትራንስፖርት አገልግሎቶች ባለፈው ሳምንት ሃሙስ ዝግ ያደረገች ሲሆን፣ በሌሎች ግዛቶች የሚንቀሳቀሱ ዜጎችም ጥብቅ የጤና ምርመራ እየተደረገባቸው እንደሚገኝና የአዲስ አመት በዓልን ጨምሮ ሌሎች ዝግጅቶች እንዲሰረዙ መወሰኑም ይታወሳል፡፡
የቻይና መንግስት ባለፈው የፈረንጆች አመት የመጨረሻ ዕለት ከአለም የጤና ድርጅት ጋር በጋራ በሰጠው የማስጠንቀቂያ መግለጫ ቫይረሱ መቀስቀሱን ያስታወሰው ዘገባው፣ ከአስር ቀናት በኋላ በቫይረሱ የተያዘው የመጀመሪያው ሰው መሞቱንና በቀጣይ ሳምንታትም በስፋት በመሰራጨት በርካቶችን ማጥቃቱንም አክሎ ገልጧል፡፡
ኮሮና ምንድን ነው?
ከቻይና ተነስቶ አለምን በፍጥነት በማዳረስ ላይ የሚገኘው አዲስ በሽታ ኮሮና በተባለ ቫይረስ ምክንያት የሚመጣ ሲሆን፣ ቀደም ሲል ሰዎችን የሚያጠቁ ከዚህ ቫይረስ ጋር ዝምድና ያላቸው ስድስት አይነት የቫይረሱ እንደነበሩ ተነግሯል፡፡
የሰሞኑ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ በቻይናዋ ዉሃን ግዛት ውስጥ ከሚገኝ የደቡብ ቻይና ባሕር አካባቢ የአሳ መሸጫ ገበያ መነሳቱን የሚጠቁሙ መረጃዎች የተገኙ ሲሆን፣ በበሽታው የተያዘ ሰው ቫይረሱን እስከ ሦስት ለሚደርሱ ሰዎች ሊያስተላልፍ እንደሚችል ተነግሯል፡፡
የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን ለመግታት የሚደረገውን ጥረት አዳጋች ካደረጉት ጉዳዮች አንዱ በበሽታው የተያዙ ሰዎች የበሽታው ምልክቶችን ከማሳየታቸው በፊት ቫይረሱን ወደ ሌሎች ሰዎች ማስተላለፍ መቻላቸው እንደሚገኝበት የቻይና የህክምና ባለሙያዎችን ጠቅሶ ቢቢሲ ዘግቧል፡፡

Read 12189 times