Wednesday, 05 February 2020 00:00

ገጣሚው ባይሮንና ዓለማቀፋዊ ተጋድሎው

Written by  ታደለ ገድሌ ጸጋ (የዶ/ር)
Rate this item
(1 Vote)

ታዋቂው እንግሊዛዊ፤ ተሳላቂው፤ ገጣሚውና ሮማንቲስቱ ጆርጅ ጎርዶን ባይሮን፤ ሎንዶን ውስጥ ጥር 22 ቀን 1788 የተወለደ ሲሆን ያረፈው ደግሞ ሚያዚያ 19 ቀን 1824 ግሪክ ውስጥ ሚሶሎንጊ በተባለው ቦታ ነው:: የዘር ሐረጉ ከእንግሊዝ የመሳፍንት ቤተሰብ ጋር የተያያዘው  የጆርጅ ጎርዶን ባይሮን ወላጅ አባት በጣም መልከኛና ቄንጠኛ ሻለቃ የነበረው ጆን ባይሮን ሲሆን እናቱ ደግሞ የቄንጠኛው ሻለቃ ሁለተኛ ሚስት የነበረቺው ስኮትላንዳዊቱ  ካትሪን ጎርዶን ትባላለች፡፡ ጆርጅ ባይሮን ሎንዶን ውስጥ እንደተወለደ እናትና አባቱ  ስኮትላንድ  ውስጥ ወደሚገኘውና አቤርዲን ተብሎ ወደሚታወቀው ቦታ ይዘውት  ሄደው እዚያ መኖር ጀመሩ፡፡
በመሃል  ወላጅ አባቱ በ1791 ለሥራ ጉዳይ ወደ ፈረንሳይ እንደ ሄደ ሲሞት እጅግ በጣም ቅብጥብጥ ባሕርይ የነበረው ባይሮን እንደ እድለ ቢስ ተደርጎ ቢታይም፣ 10 ዓመት ሲሞላው ባልተጠበቀ ሁኔታ የቅድመ አያቱን የዊልያም አምስተኛን ሀብትና ሹመት ለመውረስ እድል አገኘ፡፡ ይህንን ምክንያት አድርጋ ወላጅ እናቱ ከስኮትላንድ ወደ እንግሊዝ ሎንዶን ይዛው ሄደች፡፡ እዚያም ኒውስቲድ አቤይ የተባለውንና በእብነበረድና በልዩ ልዩ ማዕድናት አሸብርቆ የተሠራውን ከተማ  በኸንሪ ስምንተኛ አማካይነት ሲጎበኝ ልቡ በአካባቢው ውበት ተማረከ፡፡ በኒውስቲድ ለተወሰነ ጊዜ ከተቀመጠ በኋላ  ሎንዶን  ትምህርት ቤት  ገብቶ እንዲማር ተደረገ፡፡ በ1801 በእንግሊዝ እጅግ በጣም ተወዳጅ በሆነው ሐሮን ትምህርት ቤት ገብቶ ይማር ጀመር፡፡ በ1803 ከእርሱ ጋር የሩቅ ዝምድና ካላትና ሜሪ  ቻኦርዝ ከተባለች ወጣት ጋር በፍቅር ተነደፈ፡፡ እርሷ ግን ፈቃደኛ ሳትሆን ቀረችና በዚያው ዓመት አባቱ ከሌላ ሚስቱ ከወለዳት አውግስታ ባይሮን ጋር ጥብቅ ግንኙነት ፈጠረ ይባላል፡፡
በ1805 ጆርጅ ጎርዶን ባይሮን፤ ካምብሪጅ  ቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ ገብቶ ይማር ጀመር፡፡ ከዚህ ጊዜ አንሥቶ ጥብቅ ግንኙነትና ወዳጅነት ይመሠርት የነበረው ከወንዶች ጋር እንጂ ከሴቶች ጋር አልነበረም፡፡ በ1806 በካምብሪጅ ቅድስት ሥላሴ ኮሌጅ እንደነበረ  በግሉ የመጀመሪያው የሆነውን የሙከራ ግጥም  «Fugitive Pieces» ( የተጓዡ ዕጣ ፈንታ) በሚል  አሳትሟል፡፡ “Hours of Idleness””  (የሥራ ፈትነት ሰዓቶች) የሚልና ሥላቃዊ ኂስ የሆነ  የግጥም ስብስቡን ለኅትመት ያበቃው በ19 ዓመቱ ነው፡፡ የዘመኑን ገጣሚዎችና የሥነ ጽሑፍ ሰዎችን  የተቸበት የዚህ ግጥም ይዘት «ኢድንበርግ ሪቪው» በተሰኘ ጋዜጣ ላይ በወጣበት ወቅት የእንግሊዝንና የስኮትላንድ ገጣሚዎችን በበለጠ እንዲሠሩ አነሣሣቸው፡፡ በዚህም የሥነ ግጥም ሥራው የሥላቃዊ እውቀት ባለቤት መሆኑን አሥመስክሮ፣ ለመጀመሪያ ጊዜ  በዓለም አቀፍ ደረጃ እውቅናን አትርፎበታል::
ወዲያው የእንግሊዝ ፓርላማ  አባል ሆነ:: በዚህ ምክንያት በ1809 ከሌሎች የእንግሊዝ ፓርላማ አባላት ጋር የውጭ አገር  ጉብኝት ለማድረግ  ወደ ፖርቱጋል፤ እስፓኝ ሊዝቦን፤ ወደ ጅብላርተር፤ ማልታ፤ ግሪክና አልባኒያ ተጓዘ፡፡ በውጭ አገር የሁለት ዓመት ቆይታው የእስፓኝ ሕዝብ በናፖሊዮን ቦናፓርት የሚታዘዘውን  የፈረንሳይ ወራሪ ጦር በጀግንነት መክቶ፣ ወደመጣበት ሲመልሰው ከመመልከቱ ባሻገር በዘመኑ ኃይለኛና ወራሪ የነበረው የናፖሊዮን ጦር ብትንትኑ እንደሚወጣና እንደተነቃነቀ ጥርስ መርገፉ እንደማይቀር ተንብዮ ጻፈ:: ባይሮን ወደ መካከለኛው ኤስያ ወደ ግሪክ በመርከብ ተጉዞ ጠረፍ ላይ ከወረደ በኋላ አስከ አቴንስ ድረስ በእግሩ ተጉዞ ደረሰ፡፡ ቀጥሎ  በእግሩ ወደ ቁስጥንጥንያ (ቱርክ) ሄዶ ትሮይንና ሔሌስፖንትን (አሁን ዳንዳኔለስ የተባለቀውን ቦታ) ጎበኘ፡፡ በዚያም የቱርኮችን የበላይነትና ጨቋኝነት፤የግሪኮችን ተዋራጅነት  አጤነ፡፡
በሐምሌ 1811 ወደ ሎንዶን ሲመለስ ኒውስቲድ ውስጥ ትኖር የነበረቺው ወላጅ እናቱ እንደሞተች ተረዳ፡፡ ለሕዝብ ነጻነት ስሱ የሆነው፤ ፀረ መሳፍንት አቋም የነበረው፤ ተራማጅ አስተሳሰብ በማራመድ የሚታወቀውና ዘመኑን ሁሉ የዝቅተኛውን ማኅበረሰብ ጥቅም ለማስከበር ሲታገል የኖረው ጆርጅ ጎርደን ባይሮን በ1812  «የቺልድ  ሐሮልድ  ጉዞ»  (Childe Harold’s Pligrimage) በሚል የግጥም ሥራውን ጆን ሙራይ በተባለ ሰው አሳታሚነት ለንባብ አበቃ:: በዚህ ግጥሙ ዋና ገጸ ባሕርይ ሆኖ የተሣለው ቺልድ ሐሮልድ፤ በጭቁኖች ፍቅር እየተመሰጠ፣ በብርቱ የአገዛዝ ቀንበር ሥር የወደቁ የተለያዩ ሕዝቦችን ነጻ ለማውጣት፣ በአውሮፓና በእስያ ሀገሮች ሌት ተቀን ሲጓዝና ሲባዝን ይታያል፡፡   
ከፍተኛ ዝናን ባተረፈለት በዚህ ግጥሙ፤ ንጉሣዊ ሞናርኪዝምና የቡርዧ ወግ አጥባቂ ሥርዓት አላስፈላጊ ስለሆነ እንዴት መደምሰስ እንዳለበትና በየአገሩ በተለያየ የአገዛዝ ቀንበር ሥር ወድቀው በባርነት የሚማቅቁ ሕዝቦች ነጻ መውጣት እንዳለባቸው አስተምሯል:: ጅላጅልና ሆዳም የመሳፍንት ገጣሚዎችና ጸሐፊዎች የማይረቡ በመሆናቸው አውግዞ ተሣልቆባቸዋል፡፡ በእነርሱ ሥራ የእንግሊዝ ሥነ ጽሑፍ እንደሚቀጭጭ እንጂ እንደማያድግ ያለውን እምነት አስቀምጧል፡፡ እናም «የእንግሊዝ ተራማጅና ወጣት ገጣሚዎች ለአዳዲስ የሥነ ጽሑፍ ፈጠራ ተነሣሥተው ሕዝባዊነታቸውንና ጀግንነታቸውን በአደባባይ ማሳየት አለባቸው» ሲል ጥሪ አቅርቧል፡፡                      
ጆርጅ ባይሮን በዐረቦች አለባበስ
በዚህ የግጥም ሥራው (Childe Harold’s Pligrimage)  በተለይም የግሪክ ፖለቲከኞች፣ የግሪክን ሕዝብ ፍላጎት ማስጠበቅ ሲኖርባቸው፣ የቤተ ክርስቲያን ንዋየ ቅድሳትንና ቅርሳቅርሶችንና የኪነ ጥበብ ውጤቶችን መዝረፋቸው አግባብ አይደለም፤ ሌብነት ነው እያለ አውግዟቸዋል:: በልዩ ድፍረት ተሞልቶና ልምድ አዳብሮ ወደ ሀገሩ እንግሊዝ የተመለሰው ባይሮን፤ ሕዝብን ለማሳመን በሚችለው የንግግር ተሰጥዖውመ የእያንዳንዱ እንግሊዛዊ ኑሮ እንዲሻሻል፤ የምግብ፤ የመጠለያና ልብስ ፍላጎቱ ሙሉ በሙሉ እንዲሟላለት ከፍተኛ ትግል አድርጓል::  በ1813 «ምሥራቃዊ ግጥሞች» በሚል ርእስ ያሳተመው መድበል፤ የመካከለኛው ምሥራቅ ሕዝብ የአውሮፓን ተስፋፊነትና ግፈኝነት የማይፈልግ፤ለዐርነቱ ተሟጋችና ነጻነት አፍቃሪ መሆኑን ያብራራል፡፡
ሎርድ ባይሮን በ1817 «ማንፍሬድ»የተሰኘ  ድራማዊ ግጥሙን ለእይታ ካቀረበ በኋላ  በፖለቲካ ጠላቶቹ አቀንቃኝነት የተዘረጋበትን ጽልመታዊ ሕይወት ተቋቁሞ ማለፍ ስላስጠላው ሀገሩን እንግሊዝን እስከ መጠረሻው ለቅቆ ወደ ስዊዘርላንድ ተሰደደ፡፡ እዚያም «የቺልድ  ሐሮልድ  ጉዞ»  የተሰኘ ሥራውን  እያስፋፋ ማሳተም ጀመረ፡፡ በስዊዘርላንድ ውስጥ እንደ እርሱ ስደተኞች ከሆኑት ታላላቅ የእንግሊዝ ደራሲዎችና ገጣሚዎች ጋር ከመተዋወቁም ባሻገር በተለይ ታዋቂው እንግሊዛዊ ደራሲ ፔርሲና ሺሌይ  የባይሮን የክፉቀን ወዳጅ በመሆን እንዲረጋጋና መንፈሱ እንዲሰክን እየመከረ በብዙ አግዞታል፡፡ በዚሁ ዓመት (1817) ባይሮን ወደ ጣሊያን አገር ሄዶ መኖር ሲጀምር የአውሮፓ ማኅበረሰብ በታላቅ ለውጥ ላይ ይገኝ ነበርና የቀሳውስት አንድነትና ውግዘት የሕዝቡን የለውጥ እንቅስቃሴ ሊገታው እንዳልቻለ ተገነዘበ፡፡ ኢጣሊያ ውስጥ እያለ «የጎስቋሎች ዘፈን» በሚል የደረሰው ግጥም፤ የእንግሊዝ የሰራተኛ መደብ ብረት አንሥቶ በመፋለም ነጻነቱን እንዲቀዳጅ እንዲህ ሲል ያነሣሣል፡-
«---ለራሱ ነጻነት መታገል ያልቻለ፤
  የሞተ ካልሆነ ማንም ፍጡር የለ፡፡
ግሪካዊም ሆነ ወይም ሮማዊ፤
አፍሪካዊም ሆነ ወይም ዐረባዊ፤
እኔ የማላውቀው የሆነው ለባዊ፤
ጦር ሜዳ ላይ ወጥቶ ጦር ሜዳ ላይ ወርዶ፤
የጠላቱን አንገት ይጥላል ቀርድዶ፡፡---»
በዘመኑ የአውሮፓን አስተሳሰብ ጠልቆ የተረዳ ገጣሚ ነው ተብሎ ይደነቅ የነበረው መልከ መልካሙ ጆርጅ ባይሮን፤ የእንግሊዝ ተሣላቂ ደራስያንን ፈለግ ተከትሎ፣ ችሎታውን ያዳበረ ገጣሚ ሲሆን ሥራዎቹ የ19ኛው ክፍለ ዘመን ተሣላቅያን ለነበሩት ለእነ ቻርለስ ዲከንስና ቴከሬይ የፈጠራ መነሻ ሆኗቸዋል፡፡ «ዓለም ከዐረመኔዎች መዳፍ ልትላቀቅ የምትችለው በአብዮታዊ ትግል ነው» የሚል እምነት የነበረው ባይሮን፤ በሥራዎቹ  የሚፈጥራቸው ገጸ ባሕርያት ሁሉ አብዮታውያን ናቸው፡፡ ገጸ ባሕርያቱ ልክ እንደ ቼ ጉቬራ አብዮታዊ እንቅስቃሴ ባለበት የዓለም ዳርቻ ሁሉ ሲዘዋወሩና በተጨቋኞች ረድፍ ሆነው ሲታገሉ ይስተዋላሉ፡፡ በትግል ሜዳ ላይ ቢወድቁ ሞታቸው ጊዜያዊ እንጂ ዘለዓለማዊ እንዳልሆነ ይሰብካሉ፡፡ ለዚህም  በ1819 ጀምሮ በ1824 አጠናቅቆ ያሳተመውና ዶን ዡዋን ብሎ በሰየመው ረጅም የሥነ ግጥም መድበል የምናገኘው ዶን ዡዋን ተጠቃሽ ነው፡፡
«ዶን ዡዋን » በሪያሊዝምና በምርምር  ላይ የተመሠረተና ጥልቀት ያለው  ሥላቃዊ ግጥም ነው፡፡ የመጽሐፉ ዋና ገጸ ባሕርይ ዶን ዡዋን ነጻነት ወዳድና የተግባር ሰው   ሲሆን በሡልጣናዊቱት ቱርክ፤ በዛራይቱ ሩሲያ፤ በንጉሣዊቱ እንግሊዝ እየተዘዋወረ ያየውንና ተመሳሳይ መልክ ያለውን ዓለማቀፋዊ ጭቆና ያወግዛል፡፡ ይህንን ሁሉ እኩይ ድርጊት የተረዳው  ዶን ዡዋን፣ በባርነት ለቁስጥንጥንያ( ቱርክ) ተሸጦ በነበረበት ወቅት ነው፡፡ በኋላ  ከቁስጥንጥንያ አምልጦ የሩሲያ ግዛት  ወደ ሆነውና በአስማኤሎቭስክ ጠረፍ  ለጥበቃ ተሰማርቶ ለነበረው ለሩሲያ ጦር እጅ ይሰጣል ፡፡ የሩሲያ ጦርም ታላቋ ንግሥት ዳግማዊት ካትሪን ወዳለችበት ወደ ፒተርስበርግ ይልከዋል፡፡ ንግሥቲቱም የዶን ዡዋንን ብልኅነት ተመልክታ ታቀርበዋለች፡፡ በሩሲያ የእንግሊዝ አምባሳደር ሆኖ እንዲሠራም ሹመት ትሰጠዋለች፡፡ ታላቁ ሩሲያዊ ባለቅኔ አሌክሳንደር ሰርጌይቪች ፑሽኪን ከሚያከብራቸውና ሥራዎቹን በጥልቀት አንብቦና መርምሮ  ታላቅ ተጽዕኖ ከፈጠሩበት ገጣሚዎች ውስጥ በአንደኛ ደረጃ ባይሮን መሆኑን እየደጋገመ ከመናገሩም በላይ «ነጻነት ወዳድ ሥራዎቼ የባይሮን መንፈስ የተጠናወታቸው ናቸው» ብሏል፡፡
በዚህ ረገድ በ1820ዎቹ ላይ የእስፓኝ ሕዝብ ፀረ ፊውዳልና ጸረ አሜሪካ ትግሉን ሲያፋፍምና  በ1821 በኢጣሊያ የካራቢኔሪዎች ዐመፅ ሲቀጣጠል፤በግሪክ የቱርክን የበላይነት ለመቋቋም ሕዝቡ ሲታገል፤ ከሩሲያ የገባርነትን ሥርዓት ለማስወገድ የአርሶ አደሮች ዐመፅ በእነ ኢሜሊያ ፑጋቾቭ መሪነት ድብልቅልቁ ሲወጣ ባይሮን የሕዝብ ዐመፅ ደጋፊና በአካል በተገኘበት ቦታ ሁሉ የትግሉ ተሳታፊ ነበር:: በተለይም በኢጣሊያ ካራቢኔሪዎች (ለውጥ  አራማጅና ዐመፀኛ ወታደሮች) በአድኃሪው መንግሥታቸው ሰልፍ ሲያደርጉና ጦር ሲመዝዙ፣ የባይሮንን ቤት የጦር መሣሪያ ማስቀመጫ  ግምጃ ቤት አድርገውት ነበር:: ትግሉንም ፍትሐዊና ትክክለኛም ነው እያለ ባይሮን ያስተጋባ ነበር፡፡ ይሁን እንጂ የካራቢኔሪዎች ዐመፅ ሳይንሳዊ አመራር በማጣቱና ብዙ ተከታይ ሕዝብ ባለማፍራቱ በእንጭጩ ከሸፈ፤ ዐመፀኞችም እየተያዙ ተገደሉ፤ታሠሩ፡፡ በዚህ ወቅት ለውጥ አራማጁ ባይሮንም የስዊዘርላንድ ፖሊሶች በአደረጉት ስለላና ክትትል ሊያዝ ችሏል፡፡ ቢሆንም ጀግናውና አብዮተኛው  ባይሮን ከፖሊሶች እጅ በዘዴ አመለጠ፡፡ በዚህ ወቅት እንግሊዝን ከኢጣሊያ ጋር የሚያነጻጽርና «ቢፖ» የተሰኘ ግጥም አሳትሟል፡፡
ከፖሊሶች እጅ ከአመለጠ በኋላም ፈርቶና ትግል በቃኝ ብሎ ብዕሩንም፤ መሣሪያውንም አላስቀመጠም፡፡ ይልቁንም ነጻነት ወዳድ የሆኑ ብዙ የግጥምና ሌሎች የምርምርና ታሪክ ቀመስ  ሥራዎቹን ያበረከተው ከዚህ በኋላ ነው፡፡ በ1823  «የዘቀጠ ዘመን » በሚል ሌላ ፖለቲካዊና ሥላቃዊ የግጥም ሥራውን አበርክቷል፡፡ ይህ ግጥም የአውሮፓ መንግሥታት በኢጣሊያ ቬሮና ከተማ ተሰባስበው ያሳለፉት  አምባገነናዊ ውሳኔ  የአውሮጳ  ተራማጅ ኃይሎችን የሚያዳክም የወንጀል ድርጊት መሆኑን ያስረዳል:: በ1823 ወደ ግሪክ የተሰደደው ጆርጅ ጎርዶን ባይሮን፤ የኢትዮጵያ ሕዝብ ደመኛ ጠላቶች የነበሩት  ቱርኮች በግሪኮች ላይ የሚያደርሱትን በደልና ጭካኔ የተመላበት ርምጃ ተመልክቶ ረኀብና ጥም ሳይበግረው፣ መንፈሳዊ ኃይሉንና ጉልበቱን ለግሪኮች የነጻነት ትግል አውሎታል:: በገንዘቡ የጦር መሣሪያ፤ምግብና ልብስ እየገዛ ለግሪክ ነጻ አውጭዎችና ለውጭ አገር  ወድዶ ዘማች ተዋጊዎች ያድልና  ግሪኮች ከቱርክ ጋር የሚያደርጉት  ፍትሐዊ ጦርነት በድል እንዲደመደም ያበረታታ ነበር፡፡
ለሰው ልጅ የተለየ ፍቅር የነበረው ጆርጅ ጎርዶን ባይሮን፤ የሚቀርጸው ገጸ ባሕርይ ሁሉ ሰውንና ነጻነትን የሚወድድ ነው፡፡ ከጥንታዊው ሰው ታሪካዊ ጉዞ በመነሣት ነጻ፤ ዘመናዊና ተራማጅ ማኅበረሰብ በዓለም ላይ ተፈጥሮ ለማየት ብርቱ ምኞት የነበረው ጆርጅ  ባይሮን፤ በሰው አገር በስደት ላይ እያለ ቢሞትም ታማኝ የሕዝብ ጓደኛ መሆኑን በኢጣሊያ ካራቢኔሪዎች፤ በፈረንሳይ ሪፐብሊካኖች፤ በስፓኝ አብዮተኞች፤ በግሪክ ዐርበኞች፤ በጀርመን ተማሪዎች፤ በሩሲያ ሶሻል ዲሞክራቶች፤ በእንግሊዝ  ሠራተኞች ታሪክ ለዘለዓለም ሲወሳ ይኖራል፡፡



Read 1120 times