Monday, 03 February 2020 11:38

የ‘ፉክክር’ ነገር

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(4 votes)


                “በሞላ ሆዳቸው ውስኪ እያጋጩ በባዶ ሆዳችን እርስ በእርሳችን የሚያንገጫግጩንን እንደ ማንቼና አርሴ ፉርሽ ያድርግልንማ! ልክ ነዋ፣ አንዳንድ ጊዜ እኮ ምንም ‘ዲፕሎማቲክ ቋንቋ’ ቅብጥርስዮ ብሎ ነገር የለም፡፡ አሀ…የኮሶ አረቄ እየተወደደብን በብላክ ሌብል ‘ሮድማፕ’ ይሠራብናል እንዴ!”
         
                እንዴት ሰነበታችሁሳ!
እንትና የሚባል ነጋዴ የነበረውን መኪና ይቸበችብና በተብለጨለጨች መኪና ይለውጣል፡፡ ይወስድናም ሱቁ በር ላይ ያቆማታል፡፡ ጎኑ ያሉት ሌሎች ነጋዴዎች “መኪናዋ በመንገድ ትለቅ፣” ምናምን ብሎ ምርቃት የለም፡፡ “ይሁን ብለናል”፣ “ከራቭ ፎር ወደ ቪ.ኤይት ያሻግር” ብሎ ነገር የለም፡፡
“ስማ… እንትና መኪና ለወጠ እኮ!”
“ኦ…ምን ለወጠ?”
“ራቭ ፎር፡፡”
“ኦ…”
እናላችሁ… በሁለትና በሶስት ቀን ወይ አንዱ፣ ወይ ሁለቱ መኪና ይለውጣሉ፡፡ የእኛ ‘‘ፉክክር’ እንዲሁ ነው፡፡
“አጅሬው መኪና ለወጠ ማለት ነው! እኔም ባልለውጥ ሞቻለኋ!” አይነት ነገር ነው፡፡ እናላችሁ…ምን ይሆናል መሰላችሁ፣ በማግስቱ አካባቢው በአዳዲስ መኪኖች ያሸበርቃል:: እንደውም… አለ አይደል…ብዙ ጊዜ ከባንክ አስቸኳይ ብድር የሚወሰደው የፉክክር መኪና ለመግዛት ነው ይባል ነበር፡፡
ዘንድሮ…የፉክከሩ አይነት ኮሚክ ሆኗል:: የቀዳዳ ጂንስ ፉከከር ልብ ብላችሁልኛል! ልክ ነዋ…መጀመሪያ የብጫቂ ብዛት አለላችሁ:: መጀመሪያ ብጫቃው ጉልበት አካባቢ ነበር:: እየወጣ እየወረደ፣ እየተባዛ ዘንድ አንዳንዶች የሚለበሱት ጂንሶች ብጫቂዎች ብዛት በሰው እጅ ሳይሆን… አለ አይደል… የአይጦች ትብበር የተጠየቀበት ይመስላሉ፡፡ 
እኔ የምለው…በየመዝናኛ ስፍራው በአርሴና በማንቼ እየተሳበበ ይደረግ የነበረው ክትክት የቀረው እኛ ልብ ገዝተን ነው ወይስ...አለ አይደል… ሁለቱም ቡድኖች ዘንድሮ ከፉርሽም የለየለት ፉርሽ ስለሆኑ ነው! ግርም የሚል እኮ ነው፣ ማንቼና አርሴ በሞላ ሆዳቸው ተሸናንፈው ሲተቃቀፉ፣ እኛ ደግሞ በባዶ ሆዳችን ስንከታከት ከረምን፡፡ የምር እኮ… ሆቴሎች መስታወታቸው ‘ሿ’ ሲል ነበር፡፡ (ሁለተኛዋ ‘ሿ’ ስላልተገኘች ነው፡፡ ቂ…ቂ…ቂ… ስሙኝማ፣ ‘ሿ፣ ሿ’ የሚባለው ነገር በቃ አንደኛውን መዝገበ ቃላታችን ውስጥ ገባ ማለት ነው! እንኳንም ገባ…ስንትና ስንት በሰማናቸው ቁጥር ማራቶን “ሩጥ፣ ሩጥ” የሚያሰኙን ቃላት አሉ አይደል እንዴ!)
በሞላ ሆዳቸው ውስኪ እያጋጩ በባዶ ሆዳችን እርስ በእርሳችን የሚያንገጫግጩንን እንደ ማንቼና አርሴ ፉርሽ ያድርግልንማ! ልክ ነዋ፣ አንዳንድ ጊዜ እኮ ምንም ‘ዲፕሎማቲክ ቋንቋ’ ቅብጥርስዮ ብሎ ነገር የለም፡፡ አሀ…የኮሶ አረቄ እየተወደደብን በብላክ ሌብል ‘ሮድማፕ’ ይሠራብናል እንዴ! ቂ…ቂ…ቂ… የምር ግን መፈጠራችንን ለማያውቁት ለቬንገርና ለፈርጉሰን ከምንከታከት፣ መፈጠራችንን እያስጠሉን ይሉትን ችግሮች መጋተር አይሻልም ነበር!
ስሙኝማ …አምራች ፋብሪካዎች እንደመገንባት በፉክክር ስታዲየም ስንገነባ ነው እኮ የከረምነው! ለዚያውም “በሌለ ነገር፡፡” (የእኔ ሳይሆን ከሞላ ጎደል እንደ ‘ኮቴሽን’ ይወሰድማ::) ልክ እኮ አንዱ ቡቲክ ሲከፍት በማግስቱ እዛው አካባቢ ሌሎች አምስት ቡቲኮች እንደሚከፈቱት ነው፡፡ የምር እኮ ፉክክራችን… አለ አይደል… አንዳንዴ “ሰዉ ይሄን ያህል ግራ ተጋብቷል!” የሚያሰኝ ነው፡፡ አንድ ሰሞን የትኛው ከፍተኛ የትምህርት ተቋም ይጀምረው እንጃ እንጂ የሆነ ቦታ የክብር ዶክትሬት መስጠት ይጀመራል፡፡
ወዲያው ሁሉም ሰጪ ሆነና ከመደበኛ ተመራቂዎች ይልቅ ዋነኛው ዜና የክብር ዶክትሬት የሚሰጠው ለእነማን እንደሆነ የሚወራው ሆኖ ነበር፡፡ ደግሞም ለዛውም ነገርዬው ዘንድ ብዙ ነገሮች እየሆኑ እንዳለው ‘የሀገር ልጅ፣ ለሀገር ልጅ’ ሆኖ ነበር፡፡
እኔ የምለው…አንግዲህ ጨዋታም አይደል፣ እነኚህ ከባድ ሚዛኖቹ ይገቡባቸዋል የሚባሉት ‘ፉት’ ቤቶች ያለው ፉክክር የጉድ ነው አሉ:: አንድ ጠርሙስ ውስኪ አውርዶ ሁለት ሺህ ምናምንና ሦስት ሺ ምናምን ቆጥሮ መስጠት ብሎ ነገር የለም አሉ፡፡ የታሰረችውን አስሯን መዘዝ አድርጎ ለአስተናጋጆቹ “ቆጥረሽ ውሰጂና መልሺ” አይነት ነገር ነው ይላሉ፡፡ እንግዲህ ይሄም ‘ፉክክር’ ነው አሉ፡፡
የምር ግን ‘በዲታዎቹ’ ሰፈር ያለው ፉክከር ይህች አቅም አንሷት ‘የግሉኮስ ያለህ’’ ለማለት ምንም የማይቀራት ብራችን የሚደርስባት መንገላታት ፍራሽ አንጥፎ የሚያስቀምጥ ነው አሉ፡፡ እናላችሁ… ብዛቱ ምንም ይሁን ምን ‘የተበተነ’ ብር ማውጣት ዓይን ያስገባል አሉ፡፡ እኔ የምለው…ቺቺንያ እንደ ቀድሞ ‘እንደደመቀች’ ነው? መለስ ቀለስ ይሉ ነበሩ እኮ ቤርሙዳ፡፡
እኔ የምለው…እንግዲህ ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ…የፒያሳው አዲስ አበባ ማዘጋጃ ቤት ህንጻ የከተማዋ ‘ላንድማርክ’ መሆኑ ቀረ ማለት ነው? በፊት እኮ ውጪ ሀገር የሚሄድ ሰው ከተማችን ውስጥ ፎቅ መኖሩን ለማሳመን የማዘጋጃ ቤትን ፎቶ ነበር ይዞ የሚሄደው:: ለዚያውም “እሱን እንኳን ተወው፡፡ ወይ ጆሀንስበርግ፣ ወይ ካይሮ ነው” እየተባለ ነበር፡፡
አሁን ሰንጋ ተራ ‘ዎል ስትሪት’ን ሊመስል! ምን ያደርጋል፣ ኑሮ ‘ዎል’ ሆነና እንደዛ አይነት ህንጻዎች ውስጥ የምንገባባቸው ምክንያቶች አሳጣን እንጂ! (ስኳርና ዘይት እንትን ባንክ አዲሱ ህንጻ አስራ ሶስተኛ ፎቅ ላይ ይከፋፈልልንማ! ቢያንስ የጥበቃዎች ከእግር እስከ ራስ ግልምጫ ይቀርልናል፡፡) ስሙኝማ…የህንጻውም ነገር እኮ ፉክክር አይነት ነበር፡፡ ለዚህ እኮ ነው የይድረስ፣ ይድረስ ‘ሳጥን’ ህንጻዎች የበዙብን፡፡
ስሙኝማ…እኔ የምለው ይሄ የመኪናዎች ነገር:: ፊት ወንበር ያለ ተሳፋሪም ቀበቶ ይሠር ስለተባለ ማጉረምረም ምንድነው! ደግሞላችሁ፣ አንዳንዴ መንገድ ላይ ያሉት ነጫጭ መስመራ መስመሮች ምን ያደርጋሉ ያሰኛል፡፡ አለ አይደል…ከአየር ላይ የተነሱ የከተሞች ፊልሞችን ብናይ አዲስ አበባን ለመለየት ብሄራዊ ቲያትርን “የወጣበት ወጪ አንበሳ ያደርገዋል፣” የተባለለትን አንበሳ ማየት አያስፈለግም፡፡ የመኪኖችን አቋቋም ማየት ይበቃል፡፡ እኛም ከተማ መሆን አቅቶናል፣ ከተማዋም በመስታወት ተብለጨለጨች እንጂ ዘመናዊ ከተማ መሆን እያቃታት ነው፡፡  
እንዳለመታደል ሆነና እዚህ ሀገር የቆመውን መጣል እንጂ የወደቀ ማንሳት ላይ ለወሬ የምንበቃ አልሆንንም፡፡ እናላችሁ… በተቻለ መጠን አለመውደቅ ነው፡፡ በፖለቲካ በሉት፣ በኤኮኖሚ በሉት በምን በሉት ብቻ ቀደም ሲል ደህና የሚባለው ስፍራ ቆይታችሁ ድንገት ዘጭ ካላችሁ እናንተን አያድርገኝ ማለት ነው:: ስሙኝማ…ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ…ምን አይነት ነገር አለ መሰላችሁ፡፡ ያኔ ሰዉን ሁሉ ረስቶ በነበረበት ጊዜ፣ ዓለምን ረስቶ በነበረበት ጊዜ፣ ማንነቱንም የረሳ ይመስል በነበረበት ጊዜ ያላፈራውን ወዳጅ አሁን ዘጭ ብሎ ሲንደባለል ከየት ያምጣው!
እግረ መንገድ የሆነ ነገር ትዝ ብሎኝ ነው፡፡ እኔ የምለው… ዘንድሮ መፎከርም በፉክክር ሆነ እንዴ፡፡ (መቼም ዘንድሮ ከውስጥም፣ ከውጪም እኛ ላይ የማይፎክር የለም! ይሄን ያህል ‘ከስተናል’ እንዴ! አንዱ ተነስቶ የሆነ መድረክ ላይ ይፎክርብንና “በዚሁ ያስቀርልን” ስንል፣ ብዙም ሳይቆይ ሌላኛው ደግሞ ይነሳና “ግነን በሉኝ” ይለናል፡፡ እዚህም ፉከራ፣ እዛም ፉከራ፡፡ “ዝም ብለህ ከምትፎክር እስቲ ምን እንደምታደርግ እንይህ!” አይባል ነገር ሆነና የእኛም ጫንቃ ለመደው መሰለኝ፡፡ ኸረ እባካችሁ…
የማን ቤት ፈርሶ የማን ሊበጅ
የአውሬ መፈንጫ ይሆናል እንጂ
የምትሉትን ለቀቅ አድርጉን!
ስሙኝማ…ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ፣ ይሄ ቻይና ውስጥ ተፈጠረ የተባለው ወረርሽኝን …አለ አይደል…በዛው ያስቀርልን ማለት ነው:: ግን ምን መሰላችሁ…እስቲ የታላላቅ የዓለም ሚዲያዎችን አዘጋገብ ልብ በሉልኝማ፡፡ ይህ ነገር የተፈጠረው በሆነ የአፍሪካ ሀገር ቢሆን ኖሮ በአጭሩ “አያድርስ!” ማለት ነው፡፡ ይሄኔ ስንትና ስንት የእርግማን ናዳ በወረደብን ነበር:: ይሄኔ አለመሰልጠናችን፣ ከዘመኑ ጋር ‘እኩል መራመድ’ አለመቻላችን… ብቻ ምን አለፋችሁ ቁም ስቅላችንን ባሳዩን ነበር፡፡ እውነትም “የዲያብሎስ ጆሮ ይደፈን፣” የሚያሰኝ ነው፡፡
እናማ…አለ አይደል… መፎካከር የግድ ከሆነ ዘጠኝ ሺህ ዘጠኝ መቶ ችግሮች አሉብን አይደል… እስቲ በቂ ጤና ጣቢያና ትምህርት ቤት በሌለበት ስታዲየምና ሀውልት ብቻ ከማቆም ሆስፒታልና የትምህርት ማእከላትን ጨምሩትማ! ይቺ ‘ኤጎ’ የሚሏት ነገር እኮ የሚበላው ሳይጠፋ ጦም ታሳድራለች!
ደህና ሰንብቱልኝማ!


Read 2013 times