Monday, 03 February 2020 11:32

‹‹እሺ ጌታዬ›› የሚወዱት ፓርቲዎች

Written by  አያሌው አስረስ
Rate this item
(3 votes)

       ዛሬ በአገራችን የብሔር የፖለቲካ ድርጅቶች አቋቁመው እየሠሩ የሚገኙት ፕሮፌሰር መረራ ጉዲና፣ ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ፣ ዶ/ር አረጋዊ በርሔ ወዘተ የቀድሞው ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ፣ የአሁኑ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ነበሩ:: የዩኒቨርሲቲው ተማሪ በነበሩበት ጊዜ ንቁ ተሳትፎም ነበራቸው፡፡ በዚያን ጊዜ የተማሩ የሚያውቁት ሰልፍ ጠርተው አደባባይ የሚወጡት በአገራቸው ጉዳይ ብቻ ሳይሆን በአፍሪካና በሰው ልጆች ጉዳይ ሁሉ ነበር:: በደቡብ አፍሪካ የተፈፀመውን ሻርፕ ቪል እልቂትን የተቃወሙት የዩኒቨርስቲው ተማሪዎች ነበሩ፡፡ ለቬትናምና ለፍልስጤም ሕዝብ ያልጮኸ፣ አሜሪካና ጀርመን ኤምባሲ በር ቆሞ ያላወገዘ፣ የተቃውሞ ደብዳቤውን ለየኤምባሲው ያላደረሰ የዚያ ዘመን የዩኒቨርሲቲ ተማሪ አልነበረም፡፡  
ለወገንና፣ ለአገር ብቻ ሳይሆን ለሰው ልጅ የሚቆረቆር መንፈስ የነበራቸው የትናንት ተማሪዎች፤ በላያቸው ላይ ባሰለጠኑት ክልላዊነት ስሜት ተውጠው፣ ከእኔ ሰው በቀር የሌላው ምን ግዴ በሚል መንፈስ ተሸብበው፣ ምንም ይደረግ ምን፣ በጎም ሆነ ክፉ ጉዳይ ፍለጋ የሚገቡት፣ ፈልገውም የሚያገኙት የአካባቢያቸውን ብቻ ነው:: በኅብረ ብሔር የተደራጁት የፖለቲካ ፓርቲዎችም ቢሆኑ የሚያሳዩት እንቅስቃሴ፤ ከብሔር ድርጅቶች የተለየ አይደለም፡፡
በምሥራቅ ወለጋ እየተዋጉ ያሉት አቶ ኩምሳ ድሪባ፣ የ‹‹ኦነጋዊያን›› ችግር እንጂ የሌላው የፖለቲካ ድርጅት ችግር የአገር ችግር ሆኖ አይታያቸውም፡፡ እዚያ የሚፈፀም የሰብዓዊ መብት ጥሰት በእነሱ አካባቢ እስካልተደገመ ድረስ ‹‹ለምን?›› ማለት አያስፈልጋቸውም፡፡ የሌላው ቁስል የእነሱ ቁስል ስላልሆነ አያማቸውም፡፡ እንዲያውም አንዳንድ ጊዜ በሌላው ቁስል ላይ ጨው ሲነሰንሱ የሚገኝበት ጊዜም እንዳለ መገንዘብ አይገድም፡፡  
በየጉዳዩ ራሳቸውን የዳር ተመልካች የሚያደርጉት የፖለቲካ ድርጅቶች ዛሬም ካለፈ ስህተታቸው ለመማር ፍላጎት ያላቸው አይመስልም፡፡
የእነሱን ሚና ምን ሊሆን ይችል እንደነበር ለማየት በቅርቡ የሱዳኑን ፕሬዚዳንት አልበሽርን ከሥልጣን ያስወገደውን የሱዳንን ሕዝብ አመጽ ማየት ይገባል፡፡ ሳይታሰብ ገንፍሎ ፕሬዚዳንት አልበሽርን ያንበረከከውን የሕዝቡን አመጽ ወደ ሥልጣን ያመጣው የሱዳን ወታደራዊ መንግሥት ነበር፡፡ የፖለቲካ ፓርቲዎች ከሕዝብ ወግነው የወታደሩን መንግሥት ወጥረው በመያዛቸው፣ የወታደሩ መንግሥት ከሲቪሎች ጋር ለመደራደር፣ ሥልጣን ለማጋራት ተገደደ፡፡  የእኛ የፖለቲካ ድርጅቶች አንድነት ፈጥረው፣ ማስተባበርና ሕዝብን ከጎናቸው ማሰለፍ ችለው ቢሆን ኖሮ፣ ያን ጊዜ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ሥልጣን ለመልቀቅ ሲወስኑ ሊያቀርቡት የሚገባው ጥያቄ ‹‹መንግሥታችሁ ፈርሷል፤ አገር የመምራት አቅም የላችሁም፤ የሽግግር መንግሥት መመሥረት አለበት›› የሚል ነበር፡፡ እነሱ ግን አላደረጉትም፡፡
የሌሎችን ባላስታውስም የኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዴሞክራሲያዊ መድረክ (መድረክ)፤ ገዥው ፓርቲ ኢሕአዴግ አንደ አንድ የፖለቲካ ድርጅት የሚሳተፍበት ብሔራዊ የአንድነት መንግሥት እንዲመሠረት ያቀረበውን ጥያቄ ደግፎ የቆመ ሌላ የፖለቲካ ድርጅት አላስታውስም፡፡ የመድረክን ሀሳብ የሚያዳብርና የሚያጠናክር ሌላ ፓርቲም አላየሁም፡፡ ይህን ያላደረጉት የራሳቸውን ጥንካሬ  የሚለኩት ሌላውን  በማጠናከርና በማሳተፍ ሳይሆን በሌላው መደክም በመሆኑ ነው፡፡ በሌላ አገላለጽ እንናገረው ከተባለ፤ አንድን ሀሳብ ደግፈው መቆማቸው ‹‹ራሳችንን ያሳንስብናል›› ብለው ስለሚፈሩም ነው፡፡
በዶ/ር ዐቢይ አሕመድ የሚመራው የኢሕአዴግ መንግሥት፤ ሥልጣኑን ከያዘና ሥልጣኑንም ካደላደለ በኋላ የሚታየው የተቀናቃኝ የፖለቲካ ፓርቲዎች ሚና ‹‹ከእሺ ጌታዩ›› ፈቀቅ ያለ አይደለም፡፡ መንግሥቱን ለመፈታተንና ተጠያቂ ለማድረግ ሲነሱ አይታዩም፡፡
የተሻሻለውን የምርጫ ሕግ እንደ ምሳሌ እንውሰድ፡፡ ሁሉም ባይሆን ብዙዎቹ የፖለቲካ ድርጅቶች በቀረበው ረቂቅ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባና የምርጫ ሕግ ላይ ተወያይተዋል፡፡ እንዲካተት የፈለጉትን ሀሳብ አቅርበዋል፡፡ የምርጫ ሕጉ በምክር ቤቱ ሕግ ሆኖ በወጣ ጊዜ ግን አቀረብናቸው ያሏቸው ሀሳቦች እንዳልተካተቱ በተግባር አይተዋል። አንዳንዶቹ ተቃውሟቸውን እንዳሰሙ፣ የረሃብ አድማ ለማድረግ እንደተዘጋጁ መግለጫ እስከ መስጠት ተራምደዋል፡፡
መጨረሻ ላይ የታየው ግን አንድም ፓርቲ በአቋሙ አለመግፋቱና በመንግሥት ላይ ጫና ለማድረግ አለመቻሉ ነው፡፡ ይህ ደግሞ ለመንግሥት የልብ ልብ መስጠቱ አያጠራጥርም፡፡
በአሁኑ ወቅት የኢትዮጵያ ፖለቲካዊ ሁኔታ ሁለት ጥያቄዎች እየተነሱበት ነው:: አንደኛው፤ ‹‹አሁን ያለው መንግሥት ሕገ መንግሥታዊ ሥልጣኑ እያበቃ ነውና አገር አቀፍ ምርጫ ተካሂዶ አዲስ መንግሥት መሰየም አለበት›› የሚለው ሲሆን ሌላው ‹‹ምርጫ ለማካሄድ የሚያስችል ሰላማዊ ሁኔታ ስለሌለ መረጋጋት እስኪፈጠር ድረስ ምርጫው መዘግየት አለበት›› የሚለው ነው::
ሌላውም ሀሳብ ይነሳል፡፡ በዶክተር ዐቢይ የሚመራው መንግሥት ወደ ሥልጣን ያመጣው በሕዝብ ግፊት ነው፡፡ ይህ መንግሥት ለውጡን ማስቀጠል አልቻለም:: ለውጡን ማስቀጠል የሚችል አዲስ ‹‹የሽግግር መንግሥት›› መቋቋም አለበት የሚል ነው፡፡
አንድ ነገር እውነት ነው፡፡ በየቦታው የሚፈፀሙ ወንጀሎች ሲታዩ፣ ሕግ እየተከበረ፤ አገር በሕግና በሥርዓት እየተመራ ነው ለማለት የሚያስችል ነገር የለም፡፡ በየቦታው ጉልበተኛ እየተነሳ የአካባቢውን ሰላም እያደፈረሰ ነው፡፡ የሰሞኑ የሐረር ሁኔታ ለዚህ ጥሩ ማስረጃ ነው፡፡
‹‹እሺ  ጌታዬ›› ማለት የሚወዱት የአገራችን የፖለቲካ ፓርቲዎች፤ መንግሥት ላይ ጫና አድርገው ለውጡ መንገዱን አቃንቶ እንዲራመድ ማድረግ ይችላሉ? ወይስ ዛሬም መንግሥት በራሱ ጊዜ በማን አለብኝ ወደ ፊት ይገሰግሳል? ጊዜ ይፍታው!

Read 629 times