Monday, 27 January 2020 00:00

አገራችን ካልተረጋጋች፣ ለዜጐችም ለመረጠው መንግስትም፣ መከራ ነው

Written by  ዮሃንስ ሰ
Rate this item
(2 votes)

    ባለፉት ዓመታት፣ በርካታ አደገኛ ቀውሶች የተደራረቡባት አገራችን፣ ለጥቂት “ብትተርፍም”፣ እስካሁን ገና ሙሉ ለሙሉ ያልተረጋጋችና ያላገገመች አገር ናት፡፡ ዘንድሮ እንደገና፤ በፖለቲካ ምርጫ ሰበብ፣ ለሌላ ዙር የጥፋት ቀውስ ከዳረግናትና ከታመሰች፣ መዘዙ ይበዛና፤ መከራችን ይከብዳል፡፡
ለወትሮውም፣ ከችጋር ጋር የተቆራኘው የዜጐች ኑሮ፣ በአምስት ዓመታት ተከታታይ ቀውሶች ሳቢያ፣ ክፉኛ እየተናጋ ምንኛ እንደተጐሳቆለ፣ ማንም ሊክደው አይችልም፡፡ በዋጋ ንረት ምክንያት ብቻ፣ የስንቱ ሰው “ቁጠባ” የቱን ያህል ዋጋ እንዳጣ፣ የስንቱ ሰው የስራ ጅምር፣ የግንባታና የኢንቨስትመንት ውጥን በእንጥልጥል እንደቀረ፣ የስንት ሚሊዮን ዜጐች የእለት ጉርስ እንደሟሸሸ አስቡት፡፡
በአምስት ዓመት ልዩነት፣ ኑሮ፣ በእጥፍ ተወዷል፡፡ አንድ ሺ ብር ስንከፍልባቸው የነበሩ ነገሮች፣ ዛሬ ሁለት ሺ ብር ይፈጃሉ እንደማለት ነው፡፡
እንደምንም ተጣጥሮና ቆጥቦ፣ “ባጃጅ እገዛለሁ” ሲል የነበረ ወጣት፣ የቆጠበው ገንዘብ፣ ከትናንት ዛሬ፣ በዋጋ ንረት ሳቢያ እየረከሰ፣ ጥረቱ ከንቱ ይሆንበታል፡፡ “ግማሽ ያህል” ነበር ያኔ የሚጐድለው፡፡ አምስት አመት ሙሉ ቆጥቦ፣ “አሁን አሟላሁ!” ሲል፤ ለካ” በዚሁ ጊዜ ውስጥ፣ “ብር” ረክሷል፡፡ የባጃጅ ዋጋ፣ ከእጥፍ በላይ ንሯል፡፡ እናም፤ የወጣቱ ቁጠባ ከንቱ ሆነ:: ዛሬም፤ “ግማሽ ያህል ይጐድለዋል” - ባጃጅ ለመግዛት፡፡
ይህም ብቻ አይደለም፡፡ በዋጋ ንረት ሳቢያ፣ በየከተማው፣ ግንባታ እየተቋረጠ፣ ኢንቨስትመንት እየተጓተተ፣ የፋብሪካ ስራ እየተስተጓጓለ፣ ብዙዎች ለኪሳራ ተዳርገዋል፡፡
ነባር ቢዝነሶች ተሰናክለው፣ ነባር የስራ እድሎች ተዘግተዋል፡፡ የግል ኢንቨስትመንቶች ተደናቅፈው፣ አዳዲስ የስራ እድሎች ከጅምር ተጨናግፈዋል፡፡
አዎ፤ የዋጋ ንረትን ለማረጋጋት፣ ባለፉት ሁለት ዓመታት፣ መንግስት ጥሯል፡፡ የመንግስትን ወጪ እንደቀድሞው አለቅጥ ከሳማበጥ፣ በጀቱንም መረን ከመልቀቅ ታቅቦ፣ አደብ ለመግዛት ሞክሯል፡፡ ገንዘብ አለመጠን ከማተምና ብድር ከማግበስበስም ቆጠብ ብሏል፡፡
ነገር ግን፣ የገንዘብ ህትመት በአግባቡ ተመጥኖ፣ ከኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ጋር ተስተካክሏል ማለት አይደለም፡፡ የብር ህትመት ከቀድሞው ባይብስበትም፤ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ በሰላም እጦት ጭምር በመዳከሙ፤ በገንዘብ ህትመት ሳቢያ የሚፈጠረው የዋጋ ንረት ከፍተኛ ሆኗል፡፡ በአጠቃላይ፣ በዋጋ ንረት ምክንያት ብቻ፣ በአገር ኢኮኖሚና በዜጐች ኑሮ ላይ የሚደርሰው ጉዳት፣ እጅግ ከባድ እንደሆነ ለመግለጽ ፈልጌ ነው፡፡ በዚህ ላይ፣ በመንግስት የቢዝነስ ተቋማት አማካኝነት የሚመጣው ጥፋትም አለብን፡፡
የመንግስት የቢዝነስ ድርጅቶችና ፕሮጀክቶች፣ በጥቂት አመታት ውስጥ የፈጠሩት ችግር፣ በዓይነትም በመጠንም፣ አገሪቱን ከዳር ዳር አዳርሶ ኢኮኖሚውን አብረክርኳል:: ያባከኑት ሃብት፣ በቢሊዮን በቢሊዮን ብር እየዘገኑ እንደዘበት የመበተን ያህል ነው:: በማግስቱ ከዚህም ከዚያም እየተበደሩ እንደገና ያባክናሉ፡፡ ይሄውና አገሪቱ የእዳ ክምር ተጭኗታል፡፡ ይህንን ግዙፍ ችግር፣ ለማቃለል እየተሞከረ መሆኑ ጥሩ ነው፡፡
ግን ከባድ ስራ ነው፡፡ በግዙፍ የመንግስት ፕሮጀክቶችና በመንግስት የቢዝነስ ድርጅቶች በኩል የሚከሰተውን የሃብት ብክነት፣ ሙሉ ለሙሉ ለማስወገድ ይቅርና፤ በግማሽ ያህል ለመቀነስ እንኳ፣ አመታትን ይፈጃል፡፡ የተወሰኑ የስኳር ፕሮጀክቶችን ለግል ኩባንያዎች የመሸጥ እቅድ፣ በወር በሁለት ወር የሚያልቅ ቀላል ስራ እንዳልሆነ እያየነው ነው፡፡
አላማን ሳይስቱ፣ አባካኝ የመንግስት ቢዝነሶችን የመሸጥ እቅድ እንዳይጓተት እየተጉ፣ ግን ደግሞ በጥድፊያ ለመገላገል “ከህግና ስርዓት” ሳይወጡ፣ ለበርካታ ዓመታት በጽናት መጓዝን ይጠይቃል - የሃብት ብክነትን የመቀነስ አላማ:: ለዚህም ሰላም ያስፈልጋል፡፡ ሕግና ሥርዓትን ማደላደል ያስፈልጋል፡፡
ታዲያ፤ “የስኳር ፕሮጀክቶችን የመሳሰሉ የመንግስት የቢዝነስ ተቋማት፣ በሽያጭ ለግል ኩባንያዎች መተላለፍ ይኖርባቸዋል”፣… ሲባል፤ ሽያጭን በቁንጽል ማየት ማለት አይደለም፡፡ የመንግስት የሃብት ብክነትንና ኪሳራን ለመቀነስ ያህል ብቻ አይደለም፤ የመንግስት ቢዝነሶችን መሸጥ አስፈላጊ የሚሆነው፡፡
የቢዝነስ ፕሮጀክቶችና ተቋማት፣ በግል ይዞታና በነፃ የገበያ ስርዓት ውስጥ፣ ምርታማ፣ ስኬታማና ትርፋማ የሚሆኑበት እድልም መፈጠር አለበት፡፡ አለበለዚያ፣ የመንግስት ቢዝነሶችን ለግል መሸጥ፣ ብቻውን፣ ከንቱ ድካም ይሆናል፡፡ ጥያቄው ምንድነው?
አንዱ የስኳር እርሻና ፋብሪካ፣ ለግል ኩባንያ ከተሸጠ በኋላ፣ ምርታማና ትርፋማ የመሆን እድል ይኖረዋል ወይ?
በአበባና በፍራፍሬ እርሻዎች ላይ የተፈፀመው አይነት የስርዓት አልበኝነት ጥቃትና ውድመት፣ በስኳር እርሻዎች ላይም የሚደርስ ከሆነ፣ ምርታማም ትርፋማም ሊሆኑ አይችሉም፡፡ በተቃራኒው፣ የስኳር እርሻዎች፣ ለእልፍ ወጣቶች፣ እልፍ የስራ እድሎችን የሚፈጥሩ፣ የአገር ኢኮኖሚን ለማሳደግ የሚረዱ ከመሆን ይልቅ፣ የጥቃት ኢላማ፣ የውድቀት ማረጋገጫ ሆነው ያርፉታል፡፡
የሲሚንቶ ፋብሪካዎችን ሲያጉላሉ፣ እስካሁንም የወርቅ ማዕድን ተቋም ላይ ዘምተው ስራ ሲያስተጓጉሉ የምናያቸው፣…ነገሮችን አስቧቸው፡፡ የፖለቲከኞች አጥፊ ዲስኩርና ቅስቀሳ፣ የመንግስት ባለስልጣናት ስህተትም ሆነ የጥፋት ተባባሪነት፣ የጥቂት ወጣቶች አላዋቂነት ወይም የደርዘን ወጣቶች ስርዓት አልበኝነት፣… በየቦታው ሞልተዋል፡፡
እነዚህ የጥፋትና የክፋት ዘመቻዎች ወደፊትም እንዲቀጥሉ፣ ለምሳሌ የስኳር ፋብሪካዎችንም አላማ እንዲያደርጉ ይፈቀድላቸዋል ወይ? ውሎ ሳያድር የወጣቶችን የስራ እድል ሲዘጋ የምናየው የእስካሁኑ የጥፋትና የክፋት መንገድ፣ ወደፊትም ፋብሪካዎችንና እርሻዎችን የሚያወድምና የሚያከስር ከሆነ፣ ሌሎች ጥረቶች ሁሉ መክነው ይቀራሉ፡፡ የመንግስት የቢዝነስ ተቋማትን ለግል መሸጥ እጅጉን ጠቃሚ የሚሆነው፣ ሰላምና እርጋታ፣ የህግ የበላይነትና ነፃ የገበያ ኢኮኖሚ ስርዓት እየተስፋፋ የሚሄድ ከሆነ ብቻ ነው፡፡
በየእለቱ፣ እዚህም ግርግር፣ እዚያም ሁከት የሚፈጠር ከሆነ፤ በየቀኑ፣ በዚህ በኩል ከተማው ተረበሸ፣ በዚያ በኩል መንገድ ተዘጋ እየተባለ፣ ሰርቶ መግባትና አምርቶ ገበያ መላክ፣ “ፈተና” ከሆነብን፣ ኑሮና ስራ፣ ነጋ ጠባ የሚስተጓጐል ከሆነ፣ ሌላው ሌላው ምን ይረባል?
ምን ለማለት ፈልጌ ነው?
የዘንድሮው ምርጫ በሰላም ካልተጠናቀቀ፣… አገሪቱ ወደለየለት ትርምስ ባትገባም እንኳ፣ ከድጡ ወደ ማጡ የሚያስገባ አደገኛ ቀውስ ይሆንባታል፡፡
በምርጫ ሰበብ አገር ከተበጠበጠ፣ እዚያው በዚያው፣ በሰው ህይወትና በኑሮ ላይ የሚደርሰው ጥፋት ቀላል አይደለም፡፡ ነገር ግን፣ መዘዙ ከዚህ በላይ የረዘመና የበዛ ይሆናል፡፡
እንደገና ለመረጋጋት፣ ወደ ሰላም ለመመለስ፣ ጊዜ ይፈጃል፡፡ አመት ሁለት ዓመት፣ ከዚያም በላይ፡፡ የአገርንና የዜጐችን ህልውና ለተጨማሪ አደጋ፣ ኢኮኖሚንና የዜጐች ኑሮን ለተጨማሪ መከራ የሚዳርጉ አመታት ይሆኑብናል - በዘንድሮው ምርጫ የአገሪቱ ሰላም ለይቶለት ከተናጋ፡፡
ነገር ግን፣ የፖለቲካ ምርጫ፣ ከሰላምና ከአገር ህልውና ከኑሮና ከሕይወት በታች እንጂ በላይ መሆን አልነበረበትም፤ መሆንም የለበትም፡፡Read 11532 times