Print this page
Sunday, 26 January 2020 00:00

ዓለማቀፋዊቱ የኪነ ሕንጻ ንግሥት

Written by  ታደለ ገድሌ ጸጋየ (ዶ/ር)
Rate this item
(0 votes)

  «በሆንክ ኮንግ ዩኒቨርሲቲ አናት ላይ ከእነ ግርማ ሞገሱ አምሮና ተውቦ የቆመውን የጆኪ ክለብ ኢኖቬሽን ታወር ሙዚየም አሠራር ቃላት ሊገልጹት
አይቻላቸውም፡፡ በበኩሌ ስለዚህ ነገር ምንም ለመናገር አልችልም፡፡ ቀኑን ሙሉ በሕንጻው ውስጥ ስንከራተት ብውል የውስጥ ፍላጎቴን ለመግለጽ አልችልም፡፡ ለመናገር የምችለው ሕንጻው ከግምቴ በላይ መሆኑን ብቻ ነው»
           ታደለ ገድሌ ጸጋየ (ዶ/ር)


             በመላው አውሮጳና እስያ፣ የኪነ ሕንጻ ጥበብ ይበልጥ እያበበ የመጣው፣ ዘመነ እውቀት ፤ዘመነ ዳግም ልደት ወይም ሬኔሳንስ ተብሎ በሚታወቀው በ15ኛውና 16ኛው ምእት ላይ በተከሰተው ፈጣን ሥልጣኔ ነው፡፡ በዚያ የለውጥ ዘመን ታላላቅ ከተሞች የተገነቡት፣ አስገራሚ ሕንጻዎች፣ አስደማሚ ቤተ መቅደሶች፣ የባህል ማዕከላት -- የቆሙት ዘመናዊ የንድፍ ጥበብና የጥበበ እድ ሙያ እየተስፋፋ በመምጣቱ ነው:: ከዚያ ዘመን ጀምሮ እስከ ዛሬ  ድረስ ዓለማችን እንደ ፍራንክ ሊዮድ ራይት (አሜሪካዊ)፤ እንደ ፍራንክ ጌሪ (ስፓኝ)፤ እንደ ኖርማን ፎስተር (እንግሊዛዊ)፤ ሜስ ቫን ደር ሮህ (ጀርመናዊ)፤ ፊሊፕ ጆንሰን (አሜሪካዊ)፤ እንደ ዛሐዲድ (ኢራቃዊት- እንግሊዛዊት) የመሳሰሉ ታላላቅ የኪነ ሕንጻ ጠቢባንን አፍርታለች፡፡
ዳሜ  ዛሐዲድ፤ እ.ኤ.አ ኦክቶበር 31 ቀን 1950 ዓ.ም፣ የኢራቅ ዋና ከተማ በሆነቺው ባግዳድ  ሀሎዊን ውስጥ ከሀብታም ቤተሰብ ነው የተወለደቺው፡፡ አባቷ የኢራቅ ብሔራዊ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ እንዲመሠረት ሲረዳ የነበረ ፖለቲከኛ ሲሆን እናቷ ደግሞ ዕውቅ አርቲስት ነበረች፡፡ ለሙያዋ ከነበራት ክብርና ፍቅር የተነሣ ባል አግብታ ትዳር ያልመሠረተችውና ልጅም ያልነበራት ዛሐዲድ፤ በልብ ድካም ምክንያት እ.ኤ.አ  አፕሪል 1 ቀን 2016 ዓ.ም፣ በ65 ዓመቷ ያረፈቺው፣ በሰሜን አሜሪካ ፍሎሪዳ  በምትገኘው ሚያሚ ከተማ ለሕክምና ሆስፒታል ውስጥ እንደነበረች ነው፡፡ ኢራቅ ውስጥ ተወልዳ የብሪቲሽ  ዝነኛ የኪነ ሕንጻ ባለሙያ (አርክቴክት) ለመሆን የቻለቺው ዛሐዲድ፤ በተደጋጋሚ ከደመናማው የግላስኮ ግዛት እስከ ፀሐያማው አዘርባይዣን ድረስ ለቢሮ፣ ለመዝናኛ፣ ለሆቴል፣ ለትምህርት፣  ለኢንዱስትሪና ለመኖሪያ ቤት (አፓርትመንት) አገልግሎት የሚውሉና የሰው ልጅ የሚወድዳቸውን የሕንጻዎች እንዲሁም የልዩ ልዩ ድልድዮችን ንድፍ በመቀመር ጭምር ባስመዘገበቻቸው ወጥ የግንባታ ሥራዎቿ እ.ኤ.አ በ2004  በኪነ ሕንጻ ዘርፍ «የመጀመሪያዋ ጥበበኛ ሴት» ተብላ፣ የጄይ አርተር ፕሪዘርን የአርክቴክቸር ሽልማትን አግኝታለች፡፡
የፕሪዘር ሽልማት ማኅበረሰብንና አካባቢን መሠረት አድርገው በኪነ ሕንጻ ሙያ  ለሚጠበቡ፣ የተለየ  የፈጠራ ችሎታ፤ ራዕይና ብቃት ላላቸውና በዘርፉ ጉልሕ አስተዋጽኦ ላደረጉ ባለሙያዎች  በያመቱ የሚሰጥ የሽልማት ዓይነት ነው፡፡ ጄይ አርተር ፕሪዘር፤ የታወቀ አሜሪካዊ የኪነ ሕንጻ ባለሙያ (አርክቴክት) ነው፡፡ በየጊዜው በርካታ የአድናቆት ሽልማቶችን ከጃፓንና ከመላ አውሮፓ ያገኘቺው ዛሐዲድ፤ እ.ኤ.አ በ2016 በዘርፉ የመጀመሪያዋ ሴት ተብላ የእንግሊዝን የኪነ ህንጻ  የወርቅ ሜዳሊያ ተቀብላለች፡፡ በእንግሊዝዋ ንግሥት በዳግማዊት ኤልሳቤጥ «የእንግልዝዋ ሴት ወይዘሮ» ስትባል፣ የእንግሊዝ የበላይ ጠባቂም (ጋርዲያን) ተብላ ተጠርታለች፡፡ እ.ኤ.አ ከ2005-06 የኢንሳክሎፔዲያ ብሪታኒካ ኤዲቶሪያል ቦርድ አባል ሆና ከመሥራትዋም በላይ እ.ኤ.አ በ2012 “የብሪታኒያ ግዛት እመቤቲቱ  አዛዥ” (a Dame Commander of the Order of the British Empire ) የሚል ማዕረግ ተሰጥቷታል፡፡
ጄይ አርተር ፕሪዘር
በትውልድ ኢራቃዊት፤ በዜግነት እንግሊዛዊት የነበረቺው ዛሐዲድ፤ በመጀመሪያ ትምህርቷን የተማረቺው በቤይሩት ሊባኖስ ውስጥ በሚገኝ የአሜሪካ ትምህርት ቤት ነው፡፡ በማቲማቲክስ የመጀመሪያ ዲግሪዋን እንደተቀበለች፣ የከፍተኛ ትምህርቷን ለመማር ፈልጋ እ.ኤ.አ በ1972 ወደ ስዊዘርላንድ ተጉዛለች:: ቀጥላም  ወደ ሎንዶን በመሄድ «አርክቴክቸራል አሶሲየሽን» ከተባለውና  እ.ኤ.አ በ1970ዎቹ ላይ በዘመናዊ ኪነ ሕንጻ  ትምህርት ዋነኛ ማዕከል  ተደርጎ ይታይ ወደነበረው ተቋም ውስጥ ገባች:: በቆይታዋም  ኢሊያ ዜንግሊስና ሬም ኮልሐስ ከተባሉ ሁለት የኪነ ሕንጻ ባለሙያ ሴቶች ጋር ተዋወቀች፡፡ የኪነ ሕንጻ ሥራንም አብራቸው ለመሥራት ከመስማማት አልፋ ሥራዎቿን እ.ኤ.አ በ1978 በሎንዶን ማኅበራዊና ተፈጥሯዊ  ሕይወት ላይ መሠረት አድርጋ ትንቀሳቀስ ጀመር፡፡
እ.ኤ.አ በ1983 ዛሐዲድ በሙያዋ በዓለም አቀፍ የኪነ ሕንጻ ሥራዎች የውድድር መድረክ ላይ ጠንካራ ተወዳዳሪና አሸናፊ እየሆነች የመጣች ሲሆን ዕውቅናዋም በመላው ዓለም ተናኘ፡፡ የበለጠ እንድትታወቅ ያደረጋትም በተለይ ሆንግ ኮንግ ውስጥ በማራኪነቱና በምቾት ሰጭነቱ የሚታወቀውን የዘመናዊ ሕንጻ ንድፍ ሠርታ ከተገነባ በኋላ ነው፡፡ የዚህ ሕንጻ ንድፍ በጎን በኩል የተሰደሩና በርካታ ንብርብር ሕንጻዎችና ማማዎች ያሉት፤በተራራው በኩል ወደ ታች የዘመመና የሚንቀሳቀስ በሚመስል መልኩ አስገራሚ መተላለፊያዎች እንዲኖሩት ሆኖ የተገነባና በካዝሚር ማሌይቪችና በሌሎች እውቅ የንድፍ ሥራ ጠቢባን  አነሣሽነት የተለየ ሥነ ውበት ተጎናጽፎና ክንፍ ያለው አውሮፕላንን ወይም የምትበር ወፍን ተመስሎ  እንዲጠናቀቅ ተደርጓል፡፡
ጋላክሲ ሶሎ
 እ.ኤ.አ በ2012 ቻይና ቤጂንግ ከተማ የተገነባውና ጋላክሲ ሶሎ በመባል የሚታወቀው ንድፈ ሕንጻ የተቀመረው በዛሐዲድ ነው:: ሕንጻው የዐራት ቤቶች ቅርጽ ሲኖረው፣ በድልድዮችና በልዩ ልዩ ደረጃዎች የተያያዘ ነው:: 18  ክፍሎች፣ የተለያዩ የመዝናኛ ቦታዎች ያሉት ሕንጻው፤ የቻይና ባህላዊ የኪነ ሕንጻ  ጥበብ እንዲያንጸባርቅ ሆኖ ተገንብቷል፡፡ በተጨማሪም ንድፉ በቻይና የኪነ ሕንጻ ባለሙያዎች ጭምር አስተያየት ተሰጥቶበትና በሐሳብ ዳብሮ ስለተዘጋጀ፣ በአዲስነቱና በወጥነቱ ተወዳዳሪ የሌለው ሕንጻ ሆኗል፡፡ በተመሳሳይ  በጉዋንጆው ከተማ የትእይንት ማሳያ ቦታ (ኦፔራ ሐውስ) ንድፍ የተሠራው በዚህችው ባለሙያ ነው:: አስገራሚና በራሪ ወፍ የሚመስል የሕንጻ ንድፍም ሠርታለች፡፡
አስገራሚና በራሪ ወፍ የሚመስለው  ሕንጻ
ከዘመነኞቿ የኪነ ሕንጻ ባለሙያዎች የላቀ ችሎታ የተቸራት በመሆኗ  «የ20ኛው ክፍለ ዘመን ኪነ ሕንጻ መሪ» ተብላ የምትወደሰው ዛሐዲድ፤ እ.ኤ.አ ከ1997---2000 ባሉት ጊዜያት በ8.500 ስኩየር ሜትር ላይ ያረፈውን የአሜሪካ የኪነ ጥበብ ሙዚየም ሕንጻ ፕሮጀክት አቅርባ በማሸነፏ «በንድፈ ሕንጻ  ጥበብ የመጀመሪያዋ ሴት” ተብላ ተደንቃለች፡፡ ዛሐዲድ  የጂኦሜትሪ ችሎታዋን በሚገባ ተጠቅማ ሕንጻውን ተደናቂና ውጤታማ አድርጋዋለች፡፡ በተለየ ስልትና በተከፋፈለ መንገድ የምታቀርበው ረቂቅ የሆነ የሕንጻ ንድፍ በተለይ እ.ኤ.አ በ1988 በኒው ዮርክ ከተማ በሚገኘውና «ሞደርን አርት ሙዚየም” ተብሎ በሚታወቀው ማእከል፤ በኤግዚቢሽን መልክ ቀርቦ ከፍተኛ ዝናን አትርፎላታል፡፡  የሥራዋ የመጀመሪያ ፕሮጀክት አድርጋ የሠራችው እ.ኤ.አ በ1989-93 ጀርመን ውስጥ ተግባራዊ ያደረገቺው«ፉትራ የእሳት አደጋ ጣቢያ” (ፉትራ ፋየር ስቴሽን) የተባለው ነው፡፡ ከሥራዎቿ ውስጥ እ.ኤ.አ በ2008 የነደፈቺውና ሎንዶን ውስጥ የተሠራው ኢቢሲያን ግሬስ አካዳሚ፤ በ2011 ተግባራዊ ያደረገቺው የግላስኮ ወንዝ ዳር ሙዚየም፤ የሮም ኪነ ጥበብ ሙዚየም ሌሎች ተጠቃሽ ሥራዎቿ ናቸው፡፡ ይህች ድንቅየዋና ብርቅየዋ የኪነ ሕንጻ ጠቢብት ሮም ውስጥ በሠራችው የሙዚየም ንድፈ ሕንጻ «የ21ኛውን ክፍለ ዘመን ሥልጣኔ  የምታመለክት  ጥበበኛ» እስከመባል ደርሳለች፡፡
የሮም ኪነ ጥበብ ሙዚየም
ማንበብና መመራመር የምትወድደውና አዳዲስ ጥናታዊ ግኝቶችን በማቅረብ የምትታወቀው  ዛሐዲድ፤  በኪነ ሕንጻ ንድፍ በተወዳደረቺባቸው ዓለማት ሁሉ አሸናፊና ተመራጭ ከመሆኗ የተነሳ  ሁሉም ሀገሮች  ሥራዎቿን ያለ ውድድር እስከመቀበል ደርሰው ነበር፡፡ በዚህ ረገድ እኤአ በ1992-93 የበርሊንን የኪነ ጥበብና ብዙኃን መገናኛ ማእከልን፤ እ.ኤ.አ  በ1994 በዋልስ  የካርዲፍ ቤይ ኦፔራ ተቋምን አዲስነትና ወጥነት ባለው መንገድ ሠርታለች:: አብዛኛውን ጊዜ የምትጠቀምበት የንድፍ  ፍልስፍና የተመሠረተው በ«ፓራሜትሪክ ንድፈ ሐሳብ» ላይ ነው፡፡ በአንድ ሕንጻ የውስጥና የውጭ ንድፍ ረገድ የተለያየ ፍልስፍና አለ:: ለአብነትም ክላሲካል፤ ሞደርኒዝም፤ ፖስት ሞደርኒዝምና ፓራሜትሪክ የሚሉት ተጠቃሾች ሲሆኑ  ፓራሜትሪክ  የሚባለው  ቀደም ሲል ፍራንክ ኤል ራይት የተባለው የኪነ ሕንጻ ባለሙያ ይጠቀምበት የነበረና ከተፈጥሮ ክሥተቶችና ከማኅበረሰብ አስተሳሰብ ጋር የሚዛመዱ መስመሮችን መሠረት አድርጎ የሚሠራ የንድፍ ዓይነት ነው፡፡ ለዚህ የፓራሜትሪክ  ንድፍ ምሳሌ የሚሆነውም እ.ኤ.አ በ2014 አቅዳ የነደፈቺውና በአዘርባይዣን፣ ባኩ ከተማ «ሀይዳር አሊየቭ  ማዕከል» በሚል ስያሜ አምሮና ተውቦ  የሚገኘው የሙዚየም ሕንጻ ነው፡፡
የባኩ ከተማ ሙዚየም
በዚህም ሥራዋ የተነሣ «ዛሐዲድ፤  የብሪቲሽ ሮያል አርክቴክት ማእከልና የከርቭ ንግሥት ናት» እስከመባል ደርሳለች፡፡ እ.ኤ.አ በ2004 «ጆኪ ክለብ ኢኖቬሽን ታወር» በሚል ለሆንግ ኮንግ ፖሊቴክኒክ ዩኒቨርሲቲ የሠራቺው  የሙዚየም ንድፍም ተጠቃሽ ነው፡፡
የሆንግ ኮንግ ዩኒቨርሲቲ ኢኖቬሽን ታወር
የዛሐዲድን ሥራዎች በተመለከተ በርካታ የዓለም ብዙኃን መገናኛ እየተቀባበሉ ሲዘግቡ ኖረዋል፡፡ እኛም ዘግይቶም ቢሆን ይኸው ሥራዎቿን አስተዋወቅንላት፡፡ የሆንግኮንግ ዩኒቨርሲቲ ሙዚየምን ከጎበኙ የብዙኃን መገናኛ ባለሙያዎች  ውስጥ አንዱ ጋዜጠኛ በጻፈላት አስተያየት፤ «በሆንክ ኮንግ ዩኒቨርሲቲ አናት ላይ ከእነ ግርማ ሞገሱ  አምሮና ተውቦ የቆመውን የጆኪ ክለብ ኢኖቬሽን ታወር ሙዚየም  አሠራር ቃላት ሊገልጹት አይቻላቸውም፡፡ በበኩሌ ስለዚህ ነገር ምንም ለመናገር አልችልም፡፡ ቀኑን ሙሉ በሕንጻው ውስጥ ስንከራተት ብውል የውስጥ ፍላጎቴን  ለመግለጽ  አልችልም:: ለመናገር የምችለው ሕንጻው ከግምቴ በላይ መሆኑን ብቻ ነው» ብሏል፡፡ ዛሐዲድ  ከፍታ ያለው የሕንጻ ንድፍ በመሥራት አቻ ስላልተገኘላትና ተወዳድራም የሚያሸንፋት ባለመገኘቱ ዓለም አቀፍ እውቅናን ፤ፍቅርንና አክብሮትን አግኝታለች፡፡ ለዚህ ያበቃትም እ.ኤ.አ በ1993  በተለይ በውበቱና በቁመቱ እጅግ ከፍተኛ የሆነውን የሆንክ ኮንግ የመዝናኛ ሕንጻ ንድፍ ሠርታ ከተገነባ በኋላ ነው፡፡
ከምርጥ ሥራዎቿ ውስጥ የሚመደቡ የሥራ ውጤቶቿ፡- በቤልጅግ፤ በቻይና፤ በጀርመን፤ በእንግሊዝ፤ በስኮትላንድ፤ በዐረብ ሀገራት፤ በሳዉዲ ዐረቢያ ሪያድ፤ በደቡብ ኮርያ፤ በሞስኮ፤ በፈረንሳይ፤ በሻንጋይ ቻይና፤ በሲንጋፑር፤ በደቡብና በሰሜን ኮርያ፤ በጃፓን፤ በኢጣሊያ፤ በአሜሪካና በሌሎች በርካታ ዓለማት ውስጥ  ይገኛሉ፡፡
አብረቅራቂው የቢሮ ሕንጻ በቻይና
ዛሐዲድ ቻይና ቤጂንግ  ከተማ ውስጥ የሚቆም አስደናቂ ንድፈ ሕንጻ አቅርባ ለውጤት አብቅታለች፡፡ በተመሳሳይ እ.ኤ.አ በ2012 ሎንዶን ውስጥ የኦሎምፒክ ማዕከልን ንድፍ በልዩ ጥበብ ነድፋ ተግባራዊ አድርጋለች፡፡ እንደዚሁም  እ.ኤ.አ በ2013 አዲሱን የጃፓን ቶኪዮ  የኦሎምፒክ ብሔራዊ ስታዲየም ንድፍ በክለሳ መልክ ሠርታ ለውጤት አብቅታለች፡፡ እ.ኤ.አ በሴፕቴምበር 2010 ከአሜሪካ የቦምብ ውርጅብኝ በኋላ በኢራቅ አዲሱን የብሔራዊ ባንክ ዋና መሥሪያ ቤት ንድፈ ሕንጻ አዘጋጅታና ከመንግሥት ጋር  ሕጋዊ ውል ፈጽማ ለውጤት አብቅታለች፡፡ በእርስዋ አማካይነት የንድፉ  ፕሮጀክት ተሠርቶና በቻይና ቤጂንግ ከተማ አስደናቂና አብረቅራቂ  ሆኖ የቆመ  ሕንጻ ይገኛል፡፡ የሕንጻው ንድፍ ክብ ሆኖ እንደ ተራራ የተያያዙና የተሳሰሩ ሦስት ቅርፅ ያላቸው ግንቦች ይታያሉ፡፡ የሕንጻው ስም «ዋንጊነግ ሶሆ» ይባላል:: ሐይዲድ የሎንዶንን ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት፤ በ2014 የተሠራውን የሎንዶንን ሙዚየም፤ የሚቺጋን መንግሥት ዩኒቨርሲቲን፤ በሳውዲ ዐረቢያ የንጉሥ አብደላህ የፔትሮሊየም ጥናትና ምርምር ማዕከልን፤ የበልጅግን የባሕር ኃይል ወደብ፤ የሞስኮንና የፈረንሳይን  የመንግሥት መሥሪያ ቤት ቢሮዎች፤ በቻይና የሞርፈስ ሆቴልን ንድፎች የሠራች፤ በልዩ ልዩ ፋሽን ፤በፈርኒቸር፤ በግራፊክና በሌሎች ቅርጻቅርጽ ዘርፎች ችሎታዋን ያስመሰከረችና ልዩ ልዩ ዓለም አቀፍ ሽልማቶችን ያገኘች ጥበበኛ ናት፡፡
በሞስኮ የመንግሥት ቢሮ ሕንጻ
የሳውዲ ዐረቢያ የንጉሥ አብደላህ የፔትሮሊየም ጥናትና ምርምር ማዕከል
የበልጅግ የባሕር ኃይል ወደብ
ዛሐዲድ የከርቭ ንግሥት
 የዛሐዲድ ሥራዎች በዓለም ወጣት የኪነ ሕንጻ ጠቢባን ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ በመፍጠሩ በአሁኑ ዘመን ያለው የኪነ ሕንጻ ንድፍ በእጅጉ እየተራቀቀ በመሄድ ላይ ይገኛል፡፡ ምክንያቱም የዛሐዲድ የኪነ ሕንጻ ፕሮጀክት ከዘመን አይሽሬው የአነዳደፍ ጥበብ ወጥቶ፣ በአዲስ አስተሳሰብ፣ በወጥነትና በዘመናዊነት ላይ የተመሠረተ በመሆኑ ነው፡፡                             



Read 1273 times