Saturday, 25 January 2020 13:12

“አዲስ ወጠ ሠሪ ዝንጅብል ታበዛለች”

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(5 votes)

“…ሰባት አስርት ዓመታት በዚች ምድር ላይ ያሳለፈውንም፣ ገና ሀያውን ሊያጋምስ ወራት የቀሩትንም በእኩል “የአፄዎች ስርአት ናፋቂ” ሊል የሚችለው ወይ ‘ፍሬሽ ካድሬ’ ነው ወይ ፖለቲካ ውስጥ ሠላሳ ዓመት ቆይቶም ከፍሬሽነት ያልወጣ ነው፡፡…”
              

              እንዴት ሰነበታችሁሳ!
ስሙኝማ… እንግዲህ ጨዋታም አይደል…ከፍሬሽ አራዳ ይሰወራችሁማ! መሄጃ ነው እኮ የሚያሳጣችሁ፡፡ ከምሽቱ ሦስት ሰዓት ድቅደቅ ባለው ጨለማ፣ የጸሀይ ጨረር መከላከያ ጥቁር መነጽር አጥልቆ መወዝወዝ ምን የሚሉት አራድነት ነው!? ነው ወይስ ‘አርቲፊሻል ኢንተሊጀንስ’ መሆኑ ነው?! ማለዳ ያጠለቃትን ምግብ ላይ መቀመጥ የለ፣ መጸዳጃ መግባት የለ፣ የውጪ መብራት የሌለበት ሰፈር ብሎ ነገር የለ፤ ልክ እንደ ውስጥ  ሱሪ ማታ ማውለቅ ምን የሚሉት ፍሬሽ አራድነት ነው?!
ደግሞ ምን አይነት ፍሬሽ አራድነት አለ መሰላችሁ…‘ቡልዶዘር አራድነት፡፡’ ‘የሸለለች’… አለ አይደል እንደ ድሮ ‘ፓሪሞድ’ የሚሏት ነገር፣ ጥብቅ ብላ ስብስብ ያለች ኮትና ሱሪ ለብሶ፣ መሄጃ ባልጠበበት መንገድ፣ ፊት ለፊቱ ያገኘውን ሁሉ እየገፈታተረ ይፈጨዋል፡፡ (የፈረደበት በ‘ማልኒዩትሪሽን’ የደቀቀ ትከሻችን ምስጋና ይግባው!) ኸረ እባክህ…እሷ ጨርቅ ተፈትጋ፣ ተፈትጋ ሶስት ወር ሳይሞላት ትነትብብሀለች፡፡
“አዲስ ወጠ ሠሪ ዝንጅብል ታበዛለች” የሚባል ነገር አለ፡፡
ደግሞላችሁ… ስታስጮህ የክብር መድፍ ልታስመስለው ምንም የማይቀራት ፍሬሽ አራዳ አለችላችሁ፡፡ በዚህ ዘመን እኮ ማስቲካ እንደ ፊኛ እየነፉ ማስጮህ አራድነት ሳይሆን ከፍተኛ የሆነ የአእምሮ ብቃት ‘ዴፊሸንሲ’ ነው፡፡ ቂ…ቂ…ቂ… እኛ የከተማው የድምጽ መጠን መግቢያ መውጫ አሳጥቶናል እንደገና በማስቲካ ማጮህ የምን ‘ሳውንድ ፖሊዩሽን’ ማባበስ ነው፡፡ እሺ ይሁን፣ ፖለቲከኛውም ምኑም እየጮኸ ስለሆነ፣ በግድ መጮህ መብታችን ነው ከተባለም፣ እናንተን የምታካክሉ በአደባባይ ማስቲካ ስታስጮሁ ደስ አይልም! ደግሞ ‘ሂዩመን ሄይሩ’ ላይ የሆነ ችግር ሊያመጣም ይችላል፡፡
ከ‘ፍሬሽ ካድሬ’ ይሰውራችሁ፡፡ የገዥም፣ የ‘ተገዥም’ ካድሬዎች ማለት ነው፡፡ አለ አይደል… ‘ፍሬሽ ካድሬ’ የሚያውቀው ሀሳብ ማፍለቅ ሳይሆን መፈክር ማጮህ ነው፡፡ የራስን ‘ጥንካሬ’ ከመግለጽ ይልቅ ያኛውን ወገን ለማጣጣል ወይ “የምናምን ናፋቂ” ወይ “የምናምን ተላላኪ” ምናምን ይላል፡፡ ሰባት አስርት ዓመታት በዚች ምድር ላይ ያሳለፈውንም፣ ገና ሀያውን ሊያጋምስ ወራት የቀሩትንም በእኩል “የአፄዎች ስርአት ናፋቂ” ሊል የሚችለው ወይ ‘ፍሬሽ ካድሬ’ ነው ወይ ፖለቲካ ውስጥ ሠላሳ ዓመት ቆይቶም ከፍሬሽነት ያልወጣ ነው፡፡ እባካችሁ… ካድሬዎቻችሁን አደባባይ ከማውጣታችሁ በፊት ማብሰሉ ቢያቅታችሁ እንኳን፣ (ብዙዎቻችሁን ለ‘አብሳይነት’ ደረጃ መድረስ ስለምንጠራጠር ነው፣) ለብ፣ ለብ አድርጓቸውማ!
“አዲስ ወጠ ሠሪ ዝንጅብል ታበዛለች፡፡”
እናማ…በ‘ፍሬሽነት’ ወዲያውኑ ለአገልግሎት  መዋል ያለበት፣ የእንትን ቡድን ፖለቲካ ካድሬ ሳይሆን የአትክልት ተራ ቆስጣ ነው፡፡ ቂ…ቂ…ቂ…
ከ‘ፍሬሽ’ ባለስልጣን ይሰውራችሁ:: በተለይም በአንድ ጊዜ ከምድር ቤት ወደ አምስተኛ ፎቅ የሚወረወር ፍሬሽ አለቃ… ልክ እኮ ሲኮሳተር ሁሉም የሰውነት ክፍሎቹ ተጨረማምቶ የተኮሳተረ ሳይሆን የሆነ የ‘ነርቭ ፕሮብሌም’ ያለበት ነው የሚመስለው፡፡ ፍሬሽ አለቆች፣ ስሙኝማ… መኮሳተር የአለቅነት መለኪያ አይደለም፡፡
ስሙኝማ… እንግዲህ ጨዋታም አይደል፣ ግራ ግብት የሚል ነገር አለ፡፡ ውጭ ሀገር በተለይ አሜሪካ ከርመው ለጉብኝትም ለምንም  ከሚመጡት ሰዎች አንዳንዶቹ ምንድነው እንዲህ “አልበርት አይንስታይን” ካላላችሁን አይነት ነገር የሚሞክራቸው?! አለ አይደል… የእኛይቱ ዓለም ብቻ ሳይሆን በቀደም ተገኘች የተባለችውና ለኑሮም ሳትመች አትቀርም የተባለላት ፕላኔት እውቀት ሳይቀር የሰፈረባቸው ነው የሚመስሉት፡፡ አሀ...ተዉና! “አት ሊስት” እና “ወሃሳፕ”ን እኮ እኛም እንሞክራቸዋለን፡፡
“ስማ እከሌ እኮ አሜሪካ ከገባ አምስት ዓመት ነው ምናምን ሆነው አሉ!”
“አትለኝም!”
“አትለኝም!” የምትለዋ አባባል… አለ አይደል… ዋናው የሲ.ኤን.ኤን. ተንታኝ ሆኗላ! እንደማለት ልትመስል ትችላለች፡፡  እናላችሁ… እከሌ በምናምን ዓመቱ ‘አይቶን ሊመለስ’ ይመጣል:: አንዳንዶቻችን ከእሱ የምንጠብቀው በ‘ብላኩ’ ሰፈር አንዷ የእኛን ፊፍቲ ገደማ ደርሳለች የምትባለዋን ዶላሯን ብቻ አይደለም:: እንደ ውሀ ጠጥቶት የመጣ የሚመስለንን ‘እውቀትም’ ነው:: እሱም ቢሆን ‘አያሳፍረንም’፡፡ ገና ሲጀምር… “በቃ፣ ይቺ ሀገር ከእንግዲህ ተስፋ የላትም” ይልና የምድር ለምድር ተምዘግዛጊ ሚሳይል ይለቅብናል፡፡ እኛም  እንቀበላለን፡፡ ለምን ቢሉ… የመጣው ‘ካማሪካን’ ነዋ! ኮሚክ እኮ ነው… በሰባት ዓመት ቆይታው ከዲሲ ምናምነኛ ስትሪት መኖሪያ አካባቢው የወጣው፣ የዛሬ ሶስት ዓመት ዘመድ ሊቀበል ኤይርፖት የሄደ ጊዜ ነው! ቂ…ቂ…ቂ…
እኔ የምለው…የዶላሯን ነገር ካነሳን አይቀር፣ ይቺ መቶ ብራችን እንዲሁም አቅም አንሷት ከደረት ኪስ ወደ ምስጢር ኪስ እየዞረች ነው፣ በፕላስተር ተለጣጥፋ የተዥጎረጎረችውን ሁሉ ወደ ሰዉ መልሶ መላክ ምንድነው! ብዙ ቦታ እኮ የ“ተቀበል!” “አልቀበልም!” ችግር እየፈጠረች ነው፡፡ አሀ…በፊት እንዲህ የተለጣጠፉት በገቡበት እዛው ይቀሩ አልነበር እንዴ! እናማ… አሁን አይደለም አንድ ቦታ ሁለትና ሶስት ቦታ የተለጣጠፉት ሁሉ አላስፈላጊ ንትርክ ውስጥ እየከተቱን ነው፡፡
እንግዲህ የብርም ጉዳይ አይደል፣ የሆነ ነገር ትዝ ብሎኝ ነው፣..እነ እንትና የማትፈልጓት አንድ ሚሊዮን ካለቻችሁ አስገቡልንና በወር ‘ቴን ታውዘንዳችንን’ ለአፋችን እንበልማ:: እናንተስ ብትሆኑ ዝም ብሎ ‘ከሚቆለፍበት’ ለመንግስተ ሰማያት መከራከሪያ የሚሆን ሥራ ቢሠራበት አይሻልም! ለዚህ ጉዳይ የሚመጣው አይታወቅምና የ‘ቴሌግራም ቻነል’ የሚሉትን ልክፈት መሰለኝ፡፡ (ቴሌዎች ለብሮድባንድ በየወሩ “ሂሳቧን ቁጭ አድርግ” እያላችሁ አምስት ቀን ምናምን ማቋረጥ ግፍ አይሆንባችሁም!)
እኔ የምለው...እግረ መንገድ የሆነ ነገር ትዝ ብሎኝ ነው፡፡ ይሄ ተወስዶብናል የተባለውና በየጊዜው “አሁን ከያለበት ይመለሳል…” ስንባል የነበረው ፈራንካችን … እንዴት ነው ነገሩ! አሀ…እንቁልልጭ አይነት እንዳይሆንብን ነዋ! ሌሎች “አስመለሱ” “እያስመለሱ ነው” እየተባለም አይደል! ምናልባት የሚመጣ ከሆነም ለሁላችንም “ለአፋችሁ…” ተብሎ ምን፣ ምን ያህል ጣል ይደረግልን እንደሆነ ሀሳብ ለማቅረብ እንዲያመቸን ነው፡፡ ኑሮ እኮ በሀምሳ አራት ኪሎ ጫንቃ ላይ የሦስት መቶ ሀምሳ ኪሎ ሸክም ሆኗል፡፡
ስሙኝማ…ፍሬሽ ፍቅር ከያዘው ይሰውራችሁ! ወሬ ማውራት ሁሉ አትችሉማ፡፡ 
“ስማ፣ ና ፒያሳ እንሂድ፡፡ እቃ ታጋዛኛለህ፡፡”
“ምን ልትገዛ ፈልገህ ነው?”
“አንድ ቡቲክ ውስጥ ያየሁት አሪፍ ሰማያዊ ሸሚዝ አለ፡፡”
“ሰማያዊ! የእኔ ገርልፍሬንድ እኮ ሰማያዊ ትወዳለች፡፡”
ኸረ እባክህ ገና በአንድ ወርህ ሰው መግቢያ መውጫ አታሳጣ! እና እሷ ሰማያዊ ወደደች ጥቁር እኛ ምን ይኮነስረናል! እናላችሁ…ከዛ በኋላ በሁሉም ነገር ላይ “የእኔ ገርልፍሬንድ…”  ማለት፣ ምን አለፋችሁ ሀኪም ያዘዘለት ነው የሚመስለው፡፡ (ለምሳሌው “የእኔ ገርልፍሬንድ” የሚለው ጥቅም ላይ የዋለው የሆነ ስም ከተጠቀሰ አንዱ ተነስቶ “እኔን ለማለት ነው” ሊል ስለሚችል ለ‘ብልጥነት’ የተደረገ ነው፡፡ ዘንድሮ ያን ያህል ነው ያስጠላብን!)
ስሙኝማ… ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ፣ ስለ ፍቅር ነገር ከተነሳ…
ፎቅና መርሴዲስ ስሜት አይሰጡኝም
እኔን ፍቅር እንጂ ሀብት አያሞኘኝም
…እየተባለ የተዘፈነበት ጊዜ ነበር፡፡ አሁን “ቪትዝን ያላችሁ እስቲ እንያችሁ” ሊባል፡፡ ቂ…ቂ…ቂ…
እኔ የምለው… ይሄ ሥራ ላይ ሊውል ነው የተባለው ታሪፍና የቪትዝ ነገር እንዴት እንደሚሆን የሚነግርን አጣንሳ! አሀ… ስንት ጊዜ አጠራቅሞ ቪትዝ ሳልገዛላትማ 2012 አይወጣም” ሲል የነበረው አናቱ ላይ ሚሊየን ምናምን የሚል ወይም ወደዛ የሚጠጋ ቁጥር ሲጮህበት ያሳዝናላ!
ክፋቱ ደግሞ እንደፈለጉ ሞተር ቢስኪሌት የሚነዳበት ጊዜ አይደለም፡፡ ቂ…ቂ…ቂ…
እናላችሁ… በፍሬሽነቱ ደስ የሚለው ቆስጣ ብቻ ነው፡፡
“አዲስ ወጠ ሠሪ ዝንጅብል ታበዛለች፡፡”
ደህና ሰንብቱልኝማ!

Read 2223 times