Saturday, 25 January 2020 13:05

በሃሳብ መንገድ ላይ

Written by  ተመስገን
Rate this item
(0 votes)

  “ሰው የተገለጠ እንጂ ተነቦ ያለቀ መጽሐፍ አይደለም”
                      
            ሰውየው ከመጠጥ ቤት ወጥቶ ወደ ቤቱ  ሲሄድ ጨለማን ተገን ያደረጉ ሁለት ዘራፊዎች ጠብቀው፡-
“የያዝከውን ሁሉ በሰላም ታስረክባለህ…ወይስ?” ቢሉት…
“ችግር የለም፤ ያለውን ውሰዱ” አላቸው፡፡
“አውጣና መሬት ላይ ቁጭ አድርግ” አሉት፡፡
“እሽ” ብሏቸው ገንዘቡን፣ ስልኩን፣ ላይተሩን አውጥቶ ቁጭ አደረገ፡፡
“ሌላስ? ”
እያቅማማ ዝም አለ፡፡
“የደበቅኸው ነገር አለ አውጣ!” እያሉ አምባረቁበት፡፡ አወጣ፡፡ እየተደነቃቀፉ ፈረጠጡ፡፡
ወዳጄ፡- በሰው ኪስና በሰው አእምሮ ምን እንዳለ ማን ያውቃል?
ሴትየዋ ከታላቁ በርናንድ ሻው ጋር ልትግባባ ባለመቻሏ ተበሳጭታ…
“ያንተ ሚስት ብሆን ቡናህ ውስጥ መርዝ እጨምር ነበር” ብትለው…
“ጭልጥ አደርገው ነበር” አላት ተብሎ ይወራል፡፡ “ያንቺ ባል ከምሆን ብሞት ይሻለኛል” ማለቱ ነው፡፡
…በሰው ኪስና በሰው ጭንቅላት ምን እንዳለ ማን ያውቃል?...
***
“አልታየኝ አለ ያገሬ ሰማይ
እንዲህ ሆዴ ቆርጦ ርቄአለሁ ወይ?”… ተብሎ ይዘፈናል፡፡ ሰው ከኖረባት፣ ካደገበት ቀዬ ርቆ ሲቆይ፣ ሲፈናቀል፣ ሲሰደድ… የነበረበትን ይናፍቃል፡፡ ናፍቆት አእምሮን ይፈታተናል፡፡ በተለይ ደግሞ ናፍቂው አሁን ላይ የሚገኝበት ሁኔታ ካልተመቸው፣ ኑሮ ከኮሰኮሰው ድብርቱ ይብሳል፡፡ “ኖስታልጂክ” ይሆናል፡፡
ወዳጄ፡- በዘመን የለውጥ ጉዞ ምክንያት በአካልም፣ በአእምሮም ተቀይረናል፡፡ አሁንም፣ ወደፊትም መቀየራችን ይቀጥላል፡፡ ያለ ማቋረጥ በልምድ የዳበረው የዛሬው “እኛነት”፤ ከትናንቱ “እኛ” ይለያል፡፡ የነገው ደግሞ ከዛሬው፡፡
“…መቼም አንክዳት ይቺን “መራራ” እውነት
ከርጅና እስክንደርስ አልፎብን ልጅነት”
…እንዳለው ገጣሚ፤ የለውጥ ህግን አለመረዳት ጊዜን ለማቆም እንደ መሞከር ይቆጠራል፡፡
ወዳጄ፡- በህመም ወይም በብልሽት ምክንያት ካልሆነ ወደ ወፍጮ ቋት ወይም ወደ ዳይጄስቲቭ ትራክ የገባ እህል ወይም ምግብ ሳይፈጭ ወይም ሳይልም እንደነበረ ቆይቶ አይወጣም፡፡ በዓይነትም በመጠንም ዕድሜ ሲጨምር፣ ቦታ ሲቀየር ትተናቸው የመጣናቸው ነገሮች ሁሉ የኛኑ ያህል ይቀየራሉ፡፡ ቀለል ስናደርገው ወንዙ እንጂ ውሃው ሌላ ነው፡፡
ወዳጄ፡- የናፍቆት ሃያልነት ሲነሳ፣ በብዙ መጽሐፍት ላይ የሚጠቀስ አባባል አለ፤ መጀመሪያ በስፓኒሽ የተፃፈ፡፡ ትዝ ከሚሉኝ ውስጥ (ካልተሳሳትኩ) የሎሬት ጃቪር ሮድሪገዝ ድንቅ የግጥም መጽሐፍ ዋና ጭብጥ (Central theme) ያደረገው እሱኑ ነው ናፍቆትን፡፡ እንዲሁም “Journey to Ixalan” የተባለውን ዝነኛ መጽሐፍ ጨምሮ በካርሎስ ካስቴናዳ ስራዎች ውስጥ እየደጋገመ “ቦግ” ይልልናል፡፡ ይኸው የናፍቆት ህመም፡፡
ስፓኒሹ ወደ እንግሊዝኛ ሲመለስ:-
`I am so far away from the sky where I was born. Immense nostaligia invades my thoughts. Now that I am so alone and sad like a leaf in the wind. Sometimes I want to weep, sometimes I want to lough with longing”…የሚል ትርጉም አለው፡፡ ጥያቄያችን፡- የምንናውቃቸው ነገሮች በርግጥ አሉ ወይስ የሉም? ካሉ እንዴት ሆነው? ከሌሉ ወዴት ሄደው? የሚል ነው፡፡ እኔ እስከሚገባኝ ድረስ የነበሩት ሁሉ እንደነበሩ ሆነው አሁን አይገኙም፡፡ አሁን ያሉት “እነሱ” ሌሎች ናቸው፡፡ ለምሳሌ የልጅነት አእምሮዬን ይዤ ዛሬ ላይ ብለርስ ወይም ዛሬ ባለኝ የአእምሮ ብስለት ወደ ትናንተ ብመለስ ትናንትና ዛሬን አላውቃቸውም፡፡ Hallucination (ቅዠት) ይሆናሉ፡፡ ምክንያቱም፡-
“ያ ጊዜ ጥሩ ነበር፤ ያ ጊዜ መጥፎ ነው” ማለት “ዕውነት” የሚሆነው፣ ያኔ በነበረን የአእምሮ ዕድገትና ባሳለፍነው ኑሮ “ልክ” ተመዝኖ ሲመጠን ነው፡፡ በሌላ አነጋገር “ናፍቆት” የምንለው ትናንትን ወደ ዛሬ አምጥቶ መመልከት፣ ያደረ ሃሳብን ደግሞ ማሰብ፣ ትዝታ ወይም ሚሞሪ ማለት ነው፡፡ ሊያስታውሱት እንጂ እንደገና ሊኖሩት የማይችሉት …ሃሳብ!!
ወዴጄ፡- አእምሮ የሚበለጽግበት ዋና ቁም ነገር ልምድ ነው፡፡ ልምድን ሰርዞ (delete አድርጐ) ትናንትን እንደ አዲስ መኖር አይቻልም፡፡ ሰዓታችንን ወደ ሃዋሳ ጠምዘን ወይም ወደፊት አስቀድመን ብንሞላው፣ ጊዜን ከትክክለኛ ጉዞው አያዛንፈውም፡፡ የሚዛነፈው አስተሳሰባችን ነው፡፡
ብሩክ የሺጥላ የሚባል ጐበዝ ልጅ አለ:: ሰዓሊ፡፡ አንድ ጊዜ ከኢቲቪ ጋር ያደረገውን ቃለ ምልልስ ሰምቼ ደንቆኛል፡፡ ብሩክ በልጅነቱ ከጓደኞቹ ጋር “አኩኩሉ” በመጫወት ስላሳለፈው ጊዜ ሲናገር፤ “እኔና የምወዳት ልጅ ብቻችንን ለመቆየት ስለምንፈልግ፣ ጓደኛችን “አኩኩሉ!” እያለ ሲጮህ እየደጋገምን “አልነጋም” እንል ነበር፡፡ ላለመለያየት፡፡ እነዛን የደስታ ወቅቶች (Happy moments) መቼም አልረሳቸውም፡፡ እስካሁን ባይነጋ ደስ ይለኛል” ብሎ ነበር፡፡
ሁላችንም በነሱ ቦታ ብንሆን እንደዛ ነን:: ዛሬ ልጅቱ ብትመጣ ወይም እሱ ቢሄድ የበፊቱ ዓይነት ደስታ አይገኝም፡፡ በልጅነት የፍቅር ቤት “ልብ” ነው፡፡ አእምሮና ምክንያት አልተዳበሉትም፡፡ ጥላሁን ገሠሠ፡-
“ያሳለፍነው ጊዜ ደስታን ያየንበት
አሁን ተመልሶ ቢኖር ምን አለበት”…
ብሎ ያንጐራጐረው ትዝታን እንጂ “መሆንን” መኖር እንደማይቻል ስለገባው ይመስለኛል:: መሐሙድም “ፍቅር እንደገና አይገኝምና” በማለት አግዞታል፡፡ ወዳጄ፤ በሌላው አእምሮና ኪስ ምን እንዳለ ማን ያውቃል?
“ሰው የተገለጠ ገጽ እንጂ ተነቦ ያለቀ መጽሐፍ አይደለም” ይላሉ አንዳንድ ሊቃውንት፡፡ ታላቁ ኸርማን ሄስም እንደ ኤግዚስተንሺያሊስቶቹ፡-
“…Man is an onion made up of a hundred layers, a texture made from many threads.” ይለናል፡፡ አንዱ ቅርፊት ሲነሳ ሌላው ከስር ብቅ ይላል፤ እሱ ሲገለጥ ደግሞ ሌላ፤ እንደ ሽንኩርቱ!!
***
ወደ መጀመሪያ ቀልዳችን ስንመለስ፡- ዘራፊዎች “አውጣና” አስቀምጥ” ብለው ሲያንባርቁ፣ ሰውየው በመጨረሻ ያወጣው ምን መሰላችሁ? ሽጉጥ! ሽጉጥ ነበር፡፡ ለዚህ ነው የፈረጠጡት፡፡
ወዳጄ፡- በሌላው አእምሮና ኪስ ምን እንዳለ ታውቃለህ?
…መቼም “ናፍቆት” አትለኝም?!
ሠላም!!

Read 1670 times