Saturday, 25 January 2020 12:58

ኢትዮጵያ ድንቅና ረቂቅ ፍልስፍና አላት

Written by  ወልደጊዮርጊስ ይሁኔ
Rate this item
(1 Vote)

   የሀገራችን የቀደሙት ሰዎች ጠያቂና መርማሪ እንደነበሩ፡-ተደላድሎና ተመቻችቶ በተቀመጠው ስርዓት ውስጥ የዛገና የሚራገፍ ነገር የሚያይ የአእምሮ ችሎታና የተፈጥሮ ተሰጥኦ ያላቸው ታላላቅ ሰዎች ዘንድ የሚመጡ ሀሳቦች ናቸው፡፡ በሀገራችን እንደዚህ ያሉ ታላላቅ ሰዎች ነበሩ፡፡
ከእነዚህ ሰዎች ውስጥ ለምሳሌ ያህል የተወሰኑትን ማንሳት ተገቢ ነው፡፡ ፕሮፌሰር ጌታቸው ኃይሌ ‹‹ ሐተታ ዘርአ ያዕቆብ ( ወርቄ )›› በሚል በ2006 ዓ.ም ባሳተሙት መጽሐፍ፤የዘርዓ ያዕቆብ (የወርቄን) ጥያቄዎችና ከምልከታዎቹ መካከል ሃይማኖታዊና ስነ ምግባራዊ የሆኑትን ስናይ፣ አታመንዝር ከሚለው ከሙሴ አስርቱ ትዕዛዛት ውስጥ ‹‹ሙሴ የግብረ ስጋ ግንኙነት እርኩስ መሆኑን መናገሩ የፈጣሪን ግሩም ስራ ያበላሸዋል፡፡›› ይላል፡፡ ቀጥሎ ደግሞ ‹‹ ክርስቲያኖች ምንኩስና ከጋብቻ ይሻላል ማለታቸው የፈጣሪን ጥበብ ይሽራል፡፡ የሰው  ሀሳብ እንዴት የእግዚሃብሄርን ስራ ሊያሻሽል ይችላልን?›› በማለት ይሞግታል፡፡ ስለ ክርስትና ሃይማኖት አስተምህሮትና ስለ ስነ ምግባር ሲያነሳ ደግሞ ‹‹የክርስቲያኖች ሃይማኖት በወንጌል ዘመን ግዜ እንደተደነገገችው ቢሆን ክፉ አይደለችም፤ ምክንያቱም ሰዎችን እርስ በርስ በፍቅር እንዲኖሩና መልካሙን ሁሉ እንዲሰሩ ታዛቸዋለች፡፡ በዚህ ዘመን ግን ያገራችን ሰዎች የወንጌልን ፍቅር ወደ ጥል፣ ወደ ጨቋኝነት ወደ እባብ መርዝ አዞሩት፡፡ ሃይማኖታቸውን ከመሰረቱ ንደው፣ ከንቱ ነገር ያስተምራሉ፡፡ አመጻ እየሰሩ በውሸት ክርስቲያን ይባላሉ፡፡›› ብሎ በመጠየቅ፣ የክርስቲያኖች አስተምህሮት ችግር እንዳለበትና መስተካከል እንደሚገባው ተናግሯል፡፡ ከፍ ሲልም የክርስትና አስተምሮት የሚጠይቃቸውን ሀቀኝነት፣ እውነተኛነት፣ ከዓመጻ ንጹህ በመሆን እንዲተገብሩት ያሳስባል፡፡
ፕሮፌሰር ጌታቸው ኃይሌ፣ በ2007 ዓ.ም ላይ ‹‹ ደቂቀ እስጢፋኖስ ›› በሚል ርዕስ ባሳተሙት መጽሐፍ፣ ስለ ህይወት ታሪኩ ሲጽፉ ፣ ሲወለድ ስሙ ‹ ኃድገ አንበሳ › እንደተባለ፤ ቄስ ትምህርት ቤት ገብቶ መማር ሲጀምር በጭምታው፣ ጠያቂ በመሆኑ፣ በመልስ አሰጣጡ፣ በትምህርቱ ባለው ጉጉትና ባጠቃላይ በስራው ውበት የተነሳ ካህናቱ ስሙን ‹ እስጢፋኖስ › አሉት፤ በማለት በመግቢያቸው ላይ አስቀምጠዋል፡፡
አባ እስጢፋኖስና ተከታዮቻቸው ሲያነሱት ስለነበሩ ጥያቄዎች ሲያትቱ፤ ‹‹ አባ እስጢፋኖስና ተከታዮቻቸው ስግደትን ከአምልኮት ጋር ስላያያዙት፣ ከሰው ጋር ሰላምታ ሲሰጣጡ እንኳን አንገታቸውን ሰበር አያደርጉም፡፡ ስግደት ለእግዚሐብሄር ( ለአብ፣ ለወልድ፣ ለመንፈስ ቅዱስ ) ካልሆነ በቀር ለሌላ አይገባም ይላሉ፡፡›› ( ጌታቸው፣ 29) በማለት ከገለጹ በኋላ ደግሞ ‹‹ የእስጢፋውያን ስቃይ መንስኤ የኤትዮጵያ መነኮሳትን ህይወት መንቀፋቸው ነው፡፡ ምንኩስናቸው ለስም እንጂ ህይወታቸው ካልመነኮሰ ሰው ህይወት አይለይም፡፡ ይኸ መለወጥ አለበት ባዮች ነበሩ፡፡›› አባ እስጢፋኖስ በወቅቱ ከነበሩ ካህናትና  በነገስታቱ ስለሚከሰሱበት ጉዳይ ደግሞ የሚከተለውን መልሰዋል፡-
‹‹ ‹ የሀገራችን ትምህርት ያልሆነ ታስተምራለህ › ሲሉ በጥል ተነሱብኝ፡፡ የዚች ሀገር ትምህርት ምንድን ነው / እንዴትም የሌላ ነው / በክርስቶስና በአንዲት ቤተክርስቲያን ከሆነው ሁሉ በቀር ሌላ አላውቅም፡፡›› (ጌታቸው፣ 55) አባ እስጢፋኖስ የተነሱት በአጼ ይስሀቅ ( 14 06 – 14 21) ዘመን ሲሆን ማርቲን ሉተር ጀርመን ላይ ተመሳሳይ የተሐድሶ ሐሳብ ይዞ ከመነሳቱ ከሰላሳና ከአርባ ዓመታት በፊት እንደነበር የታሪክ ድርሳናት ያስረዳሉ፡፡
ከላይ ካነሳኋቸው በተጨማሪ ግሩም ፍልስፍና (ልመና) ተነስቶ የምናገኘው በገድለ ክርስቶስ ሠምራ ድርሳን ላይ ሲሆን ተማጽኖዋና ልመናዋ ለሰው ልጆች ሰላም ነው፡፡ በገድሉ ላይ የተጻፈውን የሃይማኖት አስተማሪዎች ሲያስተምሩ የሰማሁትና ከሀገራችን የፍልስፍና ምሁራን የሰማሁት ቃል በቃል ባይሆንም ፍሬ ሀሳቡ እንዲህ የሚል ነው፡- ‹‹ ክርስቶስ ሠምራ ወደ እግዚሃብሄር ትሄዳለች፡፡ ከዛም እኔ አንድ ሀሳብ አለኝ፣ ይሄ ሰይጣን የሚባለው፣ ዲያብሎስ የሚባለው ካንተ ጋር ተጣልቶ ወደ ምድር መጣ፡፡ልጅህን ልከህ አስተማርከን፣ የሰው ልጅን ለማስተማር ብዙ መጽሐፈት ተጻፉ ግን አላዋጣም፡፡ ስለዚህ ይቅርታ አድርገህለት ወደ ሎሌነቱ ቢመለስ ሰላም እናገኛለን፡፡›› ብላ እንደጠየቀችው ነው፡፡ ይሄን እንድትል ያደረጋት ለሰው ልጆች ካላት ደግነት፣ ሰላም ከመፈለጓና ከቅድስትነቷ ስለመነጨ ነው፡፡ ጭንቀቷና ልመናዋ ለመላው የሰው ልጆች ሁሉ ነው፡፡
ስለ ነጻነት
ነጻነት እስትንፋስ ነው፡፡ ነጻነት ማለት በሌሎች ተገዢ (ተመሪ) አለመሆን ነው፡፡ የሚገኘው ደግሞ ለነጻነት ያለን ዋጋ ከፍተኛ ሲሆንና ከፍተኛ መስዋዕትነት ስንከፍል ብቻ ነው፡፡ የነጻነትን (Essence ) መሰረትና ትርጉም በውል የተረዱት አያቶቻችንና አባቶቻችን በተለያዩ ዘመናት የገጠማቸውን የውጭ ወራሪ ኃይል በጀግንነትና በቆራጥነት ተዋግተው፣ ነጻነታቸውን አስከብረው ቆይተዋል፡፡ ለአብነት ያህል ግብጽ በወረረችን ግዜ በ1875 እና በ 1876 በጉንደትና በጉራ ፤ ጣሊያንን ደግሞ በ1896 እና በ 1935 …  ተጠቃሽ ናቸው፡፡ ይሄን ሀሳብ የበለጠ የሚያጠናክረው  የሚከተለው ሀተታ ነው፡፡
‹‹ኢትዮጵያ ባለፉት 4000 ዓመታት ሮማውያንን፣ ግብጽን፣ አረቦችንና ሌሎችንም በጦርነት ድባቅ እየመታች ነጻነታችንንና ለሁሉም ጥቁር ህዝቦች የነጻነትና የድል አድራጊነት ዐርማ በመሆንዋ እንኮራለን፡፡›› (ፍቅሬ፣ 232)
‹‹ ነጻነት ሁለት ዘይቤ አለው፡፡ አንደኛ መንፈስ ሊታዘዝለት የሚገባው ሕግ ያለው፣ አስገዳጅነት ከገዛ ባህሪዩ ጋር የማይስማማ ሆኖ፣ ከሱ ውጭ ከሆነ ተቆጣጣሪ ነጻ መሆን፡፡ ሁለተኛው ደግሞ ከውስጣዊ የፍትወትና (የዝቅጠኛ ) ስሜት ባርነት ነጻ መሆን ነው፡፡›› ( እጓለ፣ 119) በማለት ከውጫዊ ተቆጣጣሪ ገዢ ኃይል መውጣት እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል፡፡
አባቶቻችን ከሶስት ሺህ ዘመናት በላይ በጀግንነታቸው ነጻነታቸውን አስጠብቀው ኖረዋል፡፡ ጀግንነታቸውና ድላቸው ከነጻነት መንፈስ ብቻ የመጣ ሳይሆን የአንድነት መንፈሳቸውም ጠንካራ ስለነበር ነው፡፡ ከቀድሞ አያቶቻቸው የወረሱት የትልቅነት ጠባይን የሚያሳዩት የመልካም ምግባር፣ እውነትን የመውደድ፣ የወዳጅን ፍቅር ከገንዘብ ፍቅር በላይ አድርጎ መመልከት፣እርስ በርስ የመከባበር፣ የመስዋዕትነትና አምላክን የመፍራትን ጠባዮች ይዘው ስለነበር ነው፡፡ እንደ አንድ ህዝብ አስበን ስንሰራ ምንም የሚደፍረንና የማንወጣው ችግር እንደሌለ የአባቶቻችን አኩሪና ድንቅ ታሪክ ህያው ምስክር ነው፡፡
ስለ ሕግ
ከሕግ አንጻር የቀደመውን ስርዓት ለማየት ስንሞክር ፣ ቀድሞ በአዕምሯችን የሚመጣው ፍትሀ ነገስት ነው፡፡  ፍትሐ ነገስት ሁለት ክፍሎች አሉት፡፡ ስጋዊና መንፈሳዊ ይባላሉ፡፡ መንፈሳዊው ክፍል የሃይማኖት ጉዳዮችን ሲደነግግ፤ ስጋዊው ደግሞ የዓለማዊውን ጉዳይ ይመለከታል፡፡ ይህም ምሉዕነቱን ያሳያል፡፡
የበልሃ ለበልሃ የህግ ስርዓት፣ ሌላኛው ድንቅ የሕግ ስርዓታችን ነበር፡፡ ከአሁኑ ዘመናዊ የሕግ ስርዓት (due process of law) ጋር ይመሳሰላል፡፡ በዚህ የህግ ስርዓት፣ ተከሳሽና ከሳሽ ከዳኛ ፊት ተመልካች ባለበት ይቀርባሉ፡፡ ከሳሽ ክሱን ያቀርባል፡፡ ተከሳሽም ስለ ክሱ ምላሽ እንዲሰጥ ግዜ ይሰጠውና ምላሹን ያቀርባል፡፡ ቃላቸው እውነት ለመሆኑ በመሃላ ያረጋግጣሉ፡፡ ከዚህ ሂደት ቀጥሎ ዳኞች ነገሩን ይመረምሩና ፍርድ ይሰጣሉ፡፡ የሚደንቀው ነገር የከሳሽና የተከሳሽ ጥያቄና መልሱ የሚደረገው በግጥም መልክ መሆኑ ነው፡፡ ግጥም የሚያነሱትን ሀሳብና ጭብጥ ጎልቶ እንዲወጣ ያስችላቸዋል፡፡ ምክንያቱም ግጥም በተፈጥሮው የእምቅነትና የቁጥብነት ባህሪ ስላለው ነው፡፡
መሪዎቻችን ሆኑ ህዝቡ ህግ አዋቂና ህግ አክባሪ ነበሩ፡፡ የቅርብ ታሪካችን ብንመለከት፤ ይህንን እውነታ እንረዳለን፡፡ አጼ ምኒልክ የዓለም የእስረኞች አያያዝ ህግ ከመውጣቱ በፊት በንጹህ ህሊናቸው በመመራት ቀድመው ተግብረውት እናገኛለን፡፡ አጼ ምኒልክ ከአድዋ ጦርነት በኋላ የኢጣሊያ ቁስለኞች፤ ከኢትዮጵያዊያን ቁስለኞች ጋር እንዲታከሙ አድርገዋል፡፡
ይህን ሀሳብ የሚደግፈው ደግሞ ‹‹ዐጼ ምኒልክ እና የኢትዮጵያ አንድነት›› በሚል ርዕስ በተክለ ጻዲቅ መኩሪያ ተጽፎ በ1983 ዓ.ም ላይ በኩራዝ አሳታሚ ድርጅት የታተመው መጽሐፍ ላይ የተጠቀሰው ሀተታ ነው፤‹‹ ንጉሰ ነገስቱ የተማረኩት ኢጣሊያኖች በአንድ ሰው ትዕቢት - በግድ ተይዘው የመጡ ወታደሮች መሆናቸውን ያውቃሉና እንደ ሹመታቸው፣ ሹማምንቱን፣ ወታደሩን እንደ ማዕረጉ በሚገባ አድርገው፣ ልብስ የሌለውን ልብስ አልብሰው፣ የቆሰለውንም ከሞት የተረፉትንም ሐኪሞች ሰብስበው እያስታመሙ አስቀምጠዋል፡፡››
ከጦርነቱ መሪዎች አንዷ ንግስት ጣይቱ ነበረች፡፡ እሳቸው ከጦርነቱ በኋላ ስለነበራቸው የእስረኞች ሁኔታ ደግሞ ‹‹እቴጌ ጣይቱ ለኢጣሊያኖች ያደረጉላቸው ርህራሄ፣ እናታቸውም ቢኖሩ፣ እቴጌ እንደ ሠሩላቸው ርህራሄና በጎነት የሚሰሩላቸው አይመስለኝም፡፡›› (ተክለ ጻድቅ፣ 496) በማለት በወቅቱ ከነበሩት የሀገር ቤትና የውጭ ሰዎች የሰሙትን ጽፈዋል፡፡
ፕሮፌሰር ፍቅሬ ቶሎሳ በ ሐምሌ 2008 ዓ.ም ‹‹ የኦሮሞ እና የአማራ እውነተኛው የዘር ሐረግ ›› በሚል ርዕስ ባሳተሙት መጽሐፍ ላይ ስለ አጼ ምኒልክ ፍርድ አዋቂነት የሚከተለውን ብለዋል፡- ‹‹አጼ ምኒልክ ካዎ ጦና አልቀበላቸው ስላለ ወግተው አሸነፉት ግን መልሰው የወላይታ ንጉስነት ስልጣኑ ላይ አስቀመጡት፡፡ የምኒልክ ይቅር ባይነት፣ ትእግስትና መሐሪነት ብዙውን ግዜ አጸፋውን አስገኝቶላቸዋል፡፡
በአሁኑ ዘመን በሰለጠነው ዓለም እንደ ግለሰብም ሆነ እንደ ህዝብ የስልጣኔ መገለጫዎች ከሚባሉት ፍሬ ነገሮች (Elements) መካከል ለሰው ልጅ ያለን ክብር ፣ ሰብዓዊነት፣ የስነ ምግባር ደረጃ፣ ስለ ውበት ያለን አድናቆት፣ የስነ ጽሁፍ ደረጃ፣ መቻቻል፣ የነጻነት እሳቤ፣ ብዝሓነትን ተቀብሎ ማክበርና ማስተናገድ  እንዲሁም ሰላማዊ የአኗኗር ስርዓት ይገኙበታል፡፡ እነዚህ ሁሉ እሴቶች የነበሩንና አሁንም ጨርሰው ያልጠፉት፣ አያቶቻችንና አባቶቻችን ጥልቅ የመንፈሳዊነት ስሜት ስለነበራቸው ነው፡፡ ውጤቱም በማህበራዊ የስልጣኔ መመዘኛ (cultural civilizations) ከፍተኛ ደረጃ ላይ እንድንደርስ አድርጎን ነበር፡፡

Read 1451 times