Print this page
Tuesday, 28 January 2020 00:00

አሜሪካ በ4 የአፍሪካ አገራት ላይ የጉዞ ዕገዳ ልትጥል ነው

Written by 
Rate this item
(4 votes)

  የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ በተወሰኑ አገራት ላይ አዲስ የጉዞ ዕገዳ እንደሚጣል ባለፈው ረቡዕ በይፋ ማስታወቃቸውን የዘገበው ሮይተርስ፤ የጉዞ ዕገዳው ከሚጣልባቸው ሰባት አገራት መካከል አራቱ የአፍሪካ አገራት ኤርትራ፣ ናይጀሪያ፣ ሱዳንና ታንዛኒያ እንደሚሆኑ የአሜሪካ መገናኛ ብዙኀን መናገራቸውን አመልክቷል፡፡
በተለያዩ የአለማችን አገራት ላይ ቀደም ብለው አወዛጋቢውን የጉዞ ዕገዳ የጣሉት ዶናልድ ትራምፕ፣ በስዊዘርላንድ ዴቮስ በመካሄድ ላይ በሚገኘው የአለም የኢኮኖሚ መድረክ ስብሰባ ላይ ከዎልስትሪት ጆርናል ጋር ባደረጉት ቃለመጠይቅ፤ በተወሰኑ አገራት ላይ የጉዞ ዕገዳው እንደሚጣል እንጂ በየትኞቹ አገራት ላይ እንደሚጣል በግልጽ ባይናገሩም፣ መገናኛ ብዙሃን ግን ከአራቱ የአፍሪካ አገራት በተጨማሪ ቤላሩስ፣ ካይሬጊስታንና ማይንማር የጉዞ ዕገዳው እንደሚጣልባቸው መዘገባቸው ተነግሯል፡፡
በቅርቡ ይጸድቃል ተብሎ የሚጠበቀው አዲሱ የጉዞ ዕገዳ ረቂቅ ሕግ፣ የአገራቱን ዜጎች በሙሉ ወደ አሜሪካ እንዳይገቡ የሚያግድ እንዳልሆነ የጠቆመው ዘገባው፤ የጉዞ ዕገዳው በአንዳንዶቹ አገራት በተወሰኑ የቪዛ አይነቶችና በመንግስት ባለስልጣናት ላይ ብቻ ተግባራዊ እንደሚደረግ መነገሩንም አመልክቷል፡፡
ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ በምርጫ ቅስቀሳቸው ሲናገሩ እንደነበረው ሁሉ፣ ስልጣን በያዙ ማግስት በኢራን፣ ሶማሊያ፣ ሶርያና የመን ላይ የጣሉት የጉዞ እገዳ ከብዙ ክርክር በኋላ መጽደቁና በአወዛጋቢነቱ መዝለቁ ይታወሳል፡፡

Read 12082 times
Administrator

Latest from Administrator