Print this page
Saturday, 25 January 2020 12:35

በ1 ቢ. ዶላር ሙስና የተከሰሰችው የአንጎላው መሪ ልጅ ለፕሬዚዳንትነት እወዳደራለሁ አለች

Written by 
Rate this item
(2 votes)

      የብሩንዲው መሪ ከግማሽ ሚሊዮን ዶላር በላይ እንዲሸለሙ ፓርላማ ወሰነ

              የአፍሪካ ቁጥር አንድ ሴት ቢሊየነር የሆነችውና በ1 ቢሊዮን ዶላር ያህል የሙስናና የገንዘብ ማጭበርበር ክስ የተመሰረተባት የቀድሞው የአንጎላ መሪ ልጅ ኤልሳቤል ዶስ ሳንቶስ በስደት ከምትገኝበት እንግሊዝ በሰጠችው ቃለ መጠይቅ፤ ለፕሬዚዳንትነት ለመወዳደር እንደምትፈልግ መናገሯን ኦልአፍሪካን ኒውስ ዘግቧል፡፡
የቀድሞውን የአንጎላ ፕሬዚዳንት የአባቷን ጆሴ ኤድዋርዶ ዶስ ሳንቶስ ስልጣን መከታ በማድረግ፣ የአልማዝና የነዳጅ ዘይትን ጨምሮ በተለያዩ ዘርፎች በህገ ወጥ መንገድ ንግድ በማከናወንና የድሃ አንጎላውያንን ሃብት በመመዝበር የአፍሪካ ቁጥር አንድ ሴት ቢሊየነር እንደሆነች የሚነገርላት ኤልሳቤል፤ የቀረቡባትን ክሶች በሙሉ በማጣጣል ራሷን ነጻ ለማውጣት ከመሞከር ባለፈ በቀጣይ የአገሪቱ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ እወዳደራለሁ ማለቷ ብዙዎችን እያነጋገረ እንደሚገኝ ዘገባው አመልክቷል፡፡
ሃብቷ እንዳይንቀሳቀስ ያገደው የአንጎላ መንግስት ኤልሳቤጥን አሳልፎ እንዲሰጠው ለፖርቹጋል መንግስት ጥያቄ ማቅረቡ የተነገረ ሲሆን የአገሪቱ ጠቅላይ አቃቤ ሕግም ባለሃብቷ ወደ አንጎላ ተመልሳ ለቀረበባት ክስ መልስ የማትሰጥ ከሆነ እሷን ጨምሮ በሙስና በተጠረጠሩና በውጭ አገራት በሚገኙ ስድስት ግለሰቦች ላይ የእስር ማዛዣ እንደሚወጣባቸው ማስታወቃቸውንም ከትናንት በስቲያ ቢቢሲ ዘግቧል፡፡ ከ2.2 ቢሊዮን ዶላር በላይ የተጣራ ሃብት እንዳፈራች የሚነገርላትና በእንግሊዝ የስደት ኑሮን በመግፋት ላይ የምትገኘው ኤልሳቤል፤ በአገሯ ከዘረጋችው የቢዝነስ መረብ የምትሰበስበውን ረብጣ ዶላር በመጠቀም በማዕከላዊ ለንደን ፈርጠም ያሉ የቢዝነስ ተቋማትን እንደገነባች ይነገርላታል።
በሌላ ዜና ደግሞ፣ የብሩንዲ ፓርላማ በመጪው ግንቦት ወር ስልጣናቸውን ይለቃሉ ተብለው የሚጠበቁት የአገሪቱ ፕሬዚዳንት ፔሪ ንኩሩንዚዛ፣ 530 ሺህ ዶላር እንዲሸለሙ የቀረበውን ረቂቅ የውሳኔ ሃሳብ በአብላጫ ድምጽ እንዳጸደቀው ተዘግቧል፡፡ እ.ኤ.አ በ2005 ወደ ስልጣን የመጡትና ህገ-መንግስቱን በማሻሻል ለሶስት የስልጣን ዘመናት አገሪቱን ያስተዳደሩት ንኩሩንዚዛ፤ ከገንዘብ ሽልማቱ በተጨማሪ ስልጣን ከለቀቁ በኋላ እጅግ ዘመናዊ የመኖሪያ ቤት እንዲሰጣቸውና ዕድሜ ዘመናቸውን ሙሉ ደመወዝ እንዲከፈላቸው የወሰነው ፓርላማው፣ ከዚህ በተጨማሪም በስራ ላይ ያለ ምክትል ፕሬዚዳንት የሚያገኛቸውን ጥቅማጥቅሞች እንዲያገኙ መወሰኑንም ቢቢሲ ባወጣው ዘገባ አስነብቧል፡፡
ንኩሩንዚዛ “ታላቁ መሪ” እየተባሉ ይጠሩ ዘንድ የደነገገውና 100 አባላት ካሉት የአገሪቱ ፓርላማ፣ ከሁለት ተቃውሞ በስተቀር በሙሉ ድጋፍ የጸደቀው ህጉ፤ እነዚህ ጥቅማጥቅሞች በዲሞክራሲያዊ ምርጫ አሸንፈው ስልጣን ለያዙ ቀደምት የአገሪቱ መሪዎችም ሆነ በቀጣይ ስልጣን ለሚይዙ የአገሪቱ ፕሬዚዳንቶች እንዲከበር የሚያደርግ መሆኑ ተነግሯል፡፡
ንኩሩንዚዛ እ.ኤ.አ በ2018 በህገወጥ መንገድ ህገ መንግስቱን በማሻሻል እ.ኤ.አ እስከ 2034 በስልጣን ላይ መቆየት የሚያስችላቸውን ምቹ ሁኔታ ማመቻቸታቸውን ተከትሎ፣ በአገሪቱ ከፍተኛ ተቃውሞ መቀስቀሱንና በርካቶች ለሞትና ለእስራት መዳረጋቸውን ያስታወሰው ዘገባው፤ እሳቸው ግን በግንቦት ወር በሚካሄደው ቀጣዩ ምርጫ ላለመወዳደር መወሰናቸውን ሲናገሩ እንደቆዩ ገልጧል፡፡

Read 1520 times
Administrator

Latest from Administrator