Saturday, 25 January 2020 12:17

ከ40 አመት በሁዋላ መውለድ የጤና ችግር ያስከትላል

Written by  ፀሐይ ተፈረደኝ ከኢሶግ
Rate this item
(3 votes)

 ባለፉት 30 አመታት ከ40 አመት በላይ በሆነው እድሜያቸው የሚወልዱ ሴቶች ቁጥር እየጨመረ መሆኑን ከሶስት አመት በፊት የወጣ አንድ ጥናት ያመለክታል፡፡ ለዚህ ቁጥር መጨመር እንደምክንያት የሚቆጠረውም የተለያዩ ባህላዊ እና ልማዳዊ ድርጊቶች ያመጡት ማህበራዊ ለውጥ ነው ተብሎ ይገመታል፡፡
Sharmila Deshpande – Jul 18, 2016 እንደገለጹት የሴቶች እድሜ ከገፋ በሁዋላ ልጅ የመውለድ ምክንያት ናቸው ተብለው ከሚገመቱት ውስጥ፤-
ትምህርትን ሳይጨርሱ እና ስራ ሳይይዙ ወይንም መተዳደሪያቸውን ሳያመቻቹ ኃላፊነት ውስጥ ላለመውደቅ፤
የሚገጥማቸውን ትዳር ጥገኛ ሆነው ልጅ ላለማሳደግ እራሳቸው የሚተማመኑበትን ገቢ መፍጠር እስኪችሉ ድረስ መቆየት፤
ምናልባት ስራ ቢኖራቸውም እንኩዋን ተደራጅተው ልጅ ለማሳደግ እርግጠኛ አቅም አለን ብለው እስከሚያምኑ ድረስ መቆየት፤
የቤተሰብ እቅድ አገልግሎትን በትክክል ማግኘትና መጠቀም የማይችሉ ከሆኑ ልጅ የመውለድ እድሉ እስኪያበቃ ድረስ ማለትም በግምት እስከ 49 አመት ድረስ እርግዝናን መቀበል እና ልጁን መውለድ ለመሳሰሉት ነገሮች ዝግጁ መሆን በስፋት የሚታዩ ናቸው፡፡
ከዚህ ውጭ በተለይም በገጠር አካባቢ በሚኖረው የህብረተሰብ ክፍል፤
ልጅን መውለድ ጸጋ ነው፤ልጅ የእራሱን እድል ይዞ ይመጣል፤
በስተእርጅና ልጅ መውለድ ቤት ጭር እንዳይል ያደርጋል፤
ቀደም ብለው የተወለዱት ልጆች በትዳር እና በመሳሰሉት ምክንያቶች ከእናት አባታቸው ስለሚለዩ በስተእርጅና የሚወለድ ልጅ ለእናት አባቱ ተላላኪና በቤት ውስጥ የጎደለውን በመሙላት ረዘም ላለ ጊዜ ያገለግላል፤
የሚባል ነገርም ስላለ እድሜ ከገፋ በሁዋላ መውለድ እንደስጋት የማይቆጠርበት አጋጣሚ ብዙ ነው፡፡ በእርግጥ ጥሩ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማድረግ፤ የተመጣጠነ ምግብ መመገብ የመሳሰሉት ሴቶች ከ40 አመት በላይ ባላቸው እድሜ ወጣት፤ ጤናማና አቅም ያላቸው ሊያስመስላቸው ስለሚችል ቢዘገዩም እንኩዋን ልጅ ለመውለድ ግን ብቁ ነን ብለው በራሳቸው እንዲተማመኑ ሊያደርጋቸው ይችላል፡፡
እ.ኤ.አ ከ1960ዎቹ ጀምሮ ያልተፈለገ እርግዝና መከላከያን በሚመለከት ያለው እውቀት እና የሚሰጠው አገልግሎት፤
የጋብቻ መፍረስ መጨመርና ዘግይቶ የማግባት ጉዳይም ዘግይቶ ለመውለድ በምክንያትነት ከሚጠቀሱ መካከል ናቸው፡፡    
በአለማችን ሳይንስ በፈጠረው እድል ሰዎች በተፈጥሮአቸው ልጅ መውለድ እንኩዋን ባይችሉ በላቦራቶሪ ውስጥ ዘርና እንቁላልን በማዳቀል፤ ወይንም ከሌሎች እንቁላል በመውሰድ፤ በመሳሰሉት ልጅ እንዲያገኙ ሁኔታዎች የተመቻቹላቸው ብዙ ናቸው፡፡ በአለማችን እውቅ በሆኑ ስራዎች ላይ የተሰማሩና ሀብት ያላቸው የተለያዩ ሴቶች (Mariah Carey, Janet Jackson, Madonna,) እና ሌሎችም እድሜያቸው ከ40 አመት በላይ ከሆኑ በሁዋላ ልጅ መውለድ የቻሉ ሲሆን በእርግዝናቸው ወቅት ሲደረግላቸው የነበረው ክትትል ግን እጅግ በጣም ውድ እና ብዙ ገንዘብ ያስወጣቸው መሆኑን ጥናቱ አሳይቶአል፡፡
ምንም እንኩዋን በተለያዩ እንቅስቃሴዎችና እንክብካቤ ምክንያት በቁመና ሲታዩ ወጣት ቢመስሉም እድሜ ግን መቁጠሩን ስለማይተው እንቁላሎች ማርጀታቸውን አያቋርጡም፡፡ የሴቶች የመራባት አቅም እድሜ 30 ከሞላ በሁዋላ እየቀነሰ እንደሚመጣና በተለይም እድሜ 40 ከደረሰ የሚኖረው የማርገዝ እድል 5 ከመቶ ብቻ እንደሚሆን ሳይንስ ያረጋግጣል፡፡ በእርግጥ በዘመናዊ መንገድ በተለያዩ ዘዴዎች የሚሰጡ የማርገዝ እድሎች በ40 ወይንም ከዚያም በላይ በሚኖረው እድሜ ሊሆን እንደሚችልና እናትም ደህንነትዋን ጠብቃ እናትነትዋን እንድትቀጥል አስተማማኝ ሊሆን ይችላል፡፡
‹‹በዕድሜ የገፉ እናቶች፣ መጸነስ፣ እርግዝናና ወሊድ ከ35 ዓመት በኋላ›› የተሰኘው መጽሐፍ ተባባሪ አዘጋጅ ዶ/ር ጁሊያ ቤሪማን እንደምትለው ሴቶች በሰላሳዎቹ የዕድሜ ክልል ውስጥ ሆነው የሚያጋጥሟቸው እርግዝናዎች የታሰበባቸውና ተፈላጊ የሆኑ ናቸው፡፡ በዚህ ደረጃ ያሉ ሴቶች በኑሯቸው የሚፈልጉትን ያገኙና ደስተኛ መሆናቸውንም ትጠቅሳለች፡፡ በዚህ ዕድሜ እየገፋ በሚመጣበት ወቅት የሚፈጠር እርግዝና ሊያስከትል የሚችለውን ችግር በተመለከተ እነኝህ ሴቶች ከእርግዝናው በፊት ከወጣቶቹ ይልቅ እንደ ሪህ፣ የደም ግፊት፣ ስኳር በመሳሰሉ በሽታዎች የተጠቁ ሊሆኑ መቻላቸው አንዱ ነው፡፡ ከዚህ ሌላ በእርግዝና ወቅት እንደ ስኳርና ከፍተኛ ደም ግፊት ባሉ በሽታዎች የመጠቃት ዕድላቸው ከፍተኛ ነው፡፡
ዕድሜያቸው ገፍቶ የሚወልዱ ሴቶች በተለይ የመጀመሪያ ልጆቻቸው በስኳር በሽታ የመያዛቸው አጋጣሚ ከፍ ያለ መሆኑን ጥናቶች ይጠቁማሉ፡፡
በተጨማሪም ሴቶች ዕድሜያቸው በጨመረ ቁጥር በተለይም ከሰላሳዎቹ የዕድሜ ክልል የመጀመሪያ ዓመታት ካለፉ በኋላ የሰውነታቸው ቅልጥፍና እየቀነሰ በእርግዝና ወቅት ሊያጋጥሙ ለሚችሉ ችግሮችም የበለጠ ተጋላጭ እየሆኑ ይሄዳሉ:: በብሪቲሽ ሜዲካል ጆርናል ጽሑፍ እንደሚለው 40 ዓመት ካለፋቸው በኋላ የሚወልዱ እናቶች ከወጣቶቹ 14 እጥፍ በቀዶ ጥገና ብቻ ለመገላገል የሚያስገድድ ሁኔታ ውስጥ ይገባሉ፡፡
በተፈጥሮ መንገድ ከ40 አመት በላይ ከሆኑ በሁዋላ ልጅ ለመውለድ መዘጋጀት ብዙ የጤና እውክታዎችን ሊያስከትል እንደሚችል አስቀድሞ ማሰብ ይገባል፡፡ Sharmila Deshpande – on Jul 18, 2016 እንዳስነበበው፡፡
ዕድሜያቸው ከገፋ የሚፀንሱ ሴቶች ከሚያጋጥሙዋቸው የጤና እውክታዎች መካከል ሶስቱ የሚከተሉት ናቸው፡፡
ውርጃ፣ ወይንም የጽንስ መቋረጥ
ከማህፀን ውጪ የሚፈጠር እርግዝና እና
ሕይወት የሌለው ልጅ መገላገል ናቸው፡፡
ከዚህም በተጨማሪ ዕድሜያቸው የገፋ ሴቶች የአካል ጉድለት ያለበት ልጅ የመውለዳቸው አጋጣሚ ከፍ ያለ ነው፡፡ ሌላው ዕድሜ ገፍቶ መውለድ ለሴቶች የሚያመጣው ችግር በመጨረሻው የእርግዝና ወቅት በማህጸን ውስጥ የሚከሰት የጽንስ ሞት ነው፡፡
የደም ግፊትና የልብ ሕመም፤ በእርግዝና ጊዜ የሚከሰት የደም ግፊት Preeclampsia፤ የስኩዋር ሕመም፤ የእንግዴ ልጅ ከቦታው መላቀቅ፤ መንትያ ልጆችን መጸነስ፤ በቀዶ ሕክምና ልጅን መውለድ፤ የጽንስ መሞትና ለእናቶችም ሕይወት አደገኛ መሆን፤ ልጅ ያለቀኑ እንዲወለድ መሆን፤ ተፈጥሮአዊ ችግር ያለበትን ልጅ መውለድ የመሳሰሉት ችግሮች ይከሰታሉ፡፡
ከላይ ከተጠቀሱት ችግሮች በተጨማሪ ሴቶች እድሜያቸው ከገፋ በሁዋላ ልጅ ሲያረግዙ ለተረገዙት ልጆችም የጤና ችግር መከሰቱ አይቀርም:: ጥናቶች እንደሚጠቁሙት እድሜያቸው 40 አመት የሆኑት እርጉዝ ሴቶች ወጣት ከሆኑት ሴቶች በበለጠ (2.9 ከመቶ) የሚሆኑ ሕጻናትን በችግር የሚገላገሉ ናቸው::  
እድሜያቸው 40 ከሆነ በሁዋላ የሚያረግዙ ሴቶች በእርግዝናው ወቅት አቅም የማይኖራቸውና የእርግዝና ጊዜውን በትክክል ማጠናቀቅ ሊያቅታቸው ይችላል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ በ40 አመት የሚከሰት እርግዝና የሴትየዋን ነጻነት የሚጋፋ፤ ቀደም ሲል የነበረውን ሕይወትን የመምራት አቅምን የሚፈታተን፤ በራስ የመተማመን አቅምን የሚያሳጣ ሲሆን በተለይም የሚወለደውን ልጅ ተቀብሎ የማሳደግን ኃላፊነት በመወጣት በኩል ምቹ ያልሆኑ ስሜቶችን ሊፈጥር ይችላል፡
እድሜ 40 አመት ከደረሰ በሁዋላ ልጅ የመውለድን ችግር ይህን ያህል ካነበብን አሁን ደግሞ ዕድሜ ከገፋ በኋላ የሚፈጠሩና በሰላም የሚቋጩ እርግዝናዎች ውጤቶችን በሚመለከት የቀረቡትን የጥናት ውጤቶች በአጭሩ እንመልከት:: የመጀመሪያው ነጥብ ዕድሜ ከገፋ በኋላ መንታና ሦስት ልጆች ባንዴ የመገላገል ዕድሉ ሰፋ ያለ እንደሆነ ተጠቅሷል፡፡ ዕድሜያቸው ከፍ ብሎ የሚወልዱ ሴቶች በአብዛኛው በግራ እጃቸው የሚጠቀሙ ግራኝ ልጆች የመውለዳቸው አጋጣሚ ከፍ ያለ ነው:: በብሪታንያ በአሁኑ ወቅት ከጠቅላላው ሕዝብ 13 በመቶ ወንዶችና 11 በመቶ ሴቶች ግራኞች ናቸው፡፡ ይህ አሃዝ ቀደም ብሎ ከነበረውና በአንፃራዊ መልኩ ሴቶች በወጣትነት ዕድሜያቸው ይወልዱ በነበረበት ዘመን ለምሳሌ በ1910-3 በመቶ ብቻ ማለትም አነስተኛ እንደነበር ተጠቁሟል፡፡

Read 35213 times