የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮችና ጠቅላይ ም/ቤት በአዋጅ ተቋቁሞ፣ ህጋዊ ሰውነት እንዲኖረው የሚያስችለው አዋጅ፤ በሚኒስትሮች ም/ቤት ፀድቆ ወደ ፓርላማው ተልኳል፡፡ የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ም/ቤት ህጋዊ ሰውነት እንዲኖረው ከ60 አመታት በላይ ለመንግስት ጥያቄ ሲቀርብበት የነበረ ጉዳይ መሆኑን ለሚኒስትሮች ም/ቤት በቀረበው ጥያቄ ላይ ተመልክቷል፡፡
ም/ቤቱ እስከ ዛሬ እንደ ማንኛውም መንግስታዊ ያልሆነ ድርጅት ተመዝግቦ የሚገኝ የነበረ ሲሆን የሚኒስትሮች ም/ቤት ውሣኔ፣ ይህን ሽሮ መጅሊሱ ራሱን ችሎ በአዋጅ የተቋቋመ ተቋም እንዲሆን ያስችለዋል ብለዋል - የህግ ባለሙያዎች
ም/ቤቱ ራሱን በቻለ አዋጅ የተቋቋመ ሲሆን፤ በቀጣይ ከሌሎች ሃይማኖቶች የሚነሱ ጥያቄዎችን አንድ ላይ ለማስተናገድ ግን ተጨማሪ ህጎች እየተዘጋጁ መሆኑ ተገልጿል፡፡ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ውሳኔው ለፓርላማ ቀርቦ ይፀድቃል ተብሎ ይጠበቃል፡፡