Saturday, 25 January 2020 11:43

በደቡብ ኦሮሚያ ጉጂና ሶማሌ ክልል የኮሌራ ወረርሽኝ ተከስቷል

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(3 votes)

   24 ሰዎች በወረርሽኙ መሞታቸው ተገልጿል

               ከታህሳስ መጨረሻ ጀምሮ በደቡብ በሶማሌና በኦሮሚያ ክልል ጉጂ ዞን የኮሌራ በሽታ ወረርሽኝ መከሰቱን ዩኒሴፍ ያስታወቀ ሲሆን እስካሁን በበሽታው 24 ሰዎች መሞታቸው ተገልጿል፡፡
በሪፖርቱ በተጠቀሱት የደቡብ፣ ሶማሌ ክልል ሸበሌ ዞንና በኦሮሚያ ክልል ጉጂ ዞን ባለፉት ሳምንታት ውስጥ 1045 ያህል የኮሌራ ህመምተኞች መመዝገባቸውን ለማወቅ ተችሏል፡፡
ከፍተኛ የወረርሽኝ መጠን በተመዘገበው በደቡብ ክልል ማለትም በደቡብ ኦሞና ጎፋ ዞን ሲሆን 970 ሰዎች በበሽታው መያዛቸውንና በእነዚህ አካባቢዎች 18 ያህል ሕይወታቸው ማለፉ ተመልክቷል፡፡
በአካባቢዎቹ የተከሰተውን ድንገተኛ የኮሌራ ወረርሽኝ ለመቆጣጠር የአካባቢው አስተዳደሮችና የጤና አካላት፣ ጊዜያዊ የአደጋ መከላከል ኮሚቴ አዋቅረው እየተንቀሳቀሱ መሆኑንና በዚህ እርብርብ ላይም የአለም ጤና ድርጅትና የአለም ህጻናት አድንን ጨምሮ የተለያዩ አለማቀፍ ተቋማት እየተሳተፉ መሆኑ ተጠቁሟል - በሪፖርቱ፡፡
የኮሌራ ወረርሽኝ በአካባቢዎቹ መከሰቱን ተከትሎ፣ ወደ ሌሎች አካባቢዎች አድማሱን እንዳያሰፋ ከወዲሁ ለመከላከል የየክልሎቹ ጤና ቢሮዎችና መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች የቅድመ መከላከል ተግባር እያከናወኑ ነው ተብሏል፡፡
ባለፈው የፈረንጆች አመት (2019) ከቤንሻንጉል ጉሙዝና ከጋምቤላ ክልል ውጪ ባሉት ሁሉም የአገሪቱ አካባቢዎች ከ2074 በላይ የኮሌራ በሽታ ተጠቂዎች መመዝገባቸውንም ሪፖርቱ አስታውቋል፡፡
በኢትዮጵያ ኮሌራ ፈተና እየሆነ የመጣው በማህበረሰብ አቀፍ የንጽሕናና ጤና አጠባበቅ ላይ በጥንካሬ ባለመሰራቱ መሆኑንም ሪፖርቱ አትቷል፡፡


Read 14275 times