Saturday, 25 January 2020 11:34

ኦነግና ኦብነግን ጨምሮ 11 ፓርቲዎች እስከ ጥምር መንግሥት ምስረታ የሚያደርሳቸውን ስምምነት ተፈራረሙ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(0 votes)

   ኦነግና ኦብነግን ጨምሮ 11 የፖለቲካ ድርጅቶች በቀጣዩ ምርጫ በየአካባቢያቸው ካሸነፉ ጥምር መንግሥት ለመመስረት የሚያስችላቸውን ስምምነት ተፈራርመዋል፡፡
የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) እና የኦጋዴን ብሄራዊ ነፃነት ግንባር (ኦብነግ) ለረዥም ዓመታት በጋራ መግባባት ስምምነቶች እየተደጋገፉ የትጥቅ ትግል ሲያደርጉ መዝለቃቸውን ለአዲስ አድማስ የጠቆሙት የኦነግ ቃል አቀባይ አቶ ቀጄላ መርዳሳ፤ ይህን የትግል አጋርነታቸውን በምርጫውም ለመድገም ሌሎች ተመሳሳይ አላማ ያላቸውን 11  የፖለቲካ ድርጅቶች አካትተው ጥምር መንግሥት ለመመስረት የሚያስችላቸውን ስምምነት መፈራረማቸውን አስታውቀዋል፡፡
“ስምምነቱን የተፈራረምነው ተመሳሳይ አላማ ያለን ድርጅቶች ነን ያሉት አቶ ቀጄላ፤ በዋናነት በዚህ አገር ውስጥ በቅድሚያ ሰላምና እርቅ ማውረድ እንደሚገባ፣ የፖለቲካ ችግሮችን ለመፍታት በጋራ ለመስራት እንዲሁም ከምርጫ 2012 በፊትና በኋላ አገሪቱ ሰላም ሆና መቀጠል በምትችልበት ጉዳይ ላይ የጋራ መግባባት ላይ ደርሰው ስምምነት መፈፀማቸውን አስረድተዋል፡፡
ከምርጫው በፊትም ሆነ በኋላ ግጭቶች ቢከሰቱ በቅድሚያ ለድርድርና ውይይት ለመቀመጥና ግጭቶቹን ከማባባስ ለመቆጠብም ፓርቲዎቹ ቃል ኪዳን ማሰራቸውን አቶ ቀጄላ ገልፀዋል፡፡ ፓርቲዎቹ በተወዳደሩባቸው አካባቢዎች አሸናፊ ከሆኑም፣ ያገኙትን ድምጽ አዋጥተው የጋራ መንግሥት ለመመስረት መስማማታቸውን ነው ቃል አቀባዩ ያስረዱት፡፡
ስምምነቱን ከተፈራረሙት ፓርቲዎች መካከል የኦሮሞ ነፃነት ግንባር፣ የአገው ሸንጎ፣ የሞቻ ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ፣ የኦጋዴን ብሄራዊ ነፃነት ግንባር፣ የከፋ አረንጓዴ ፓርቲ፣ የቅማንት ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ፣ የአፋር ሕዝብ ፓርቲና ሌሎች በቤኒሻንጉል ጉሙዝ የሚንቀሳቀሱ ፓርቲዎች እንደሚገኙበት ለማወቅ ተችሏል፡፡
በመድረኩ ስብስብ ውስጥ ያሉ ሌሎች ፓርቲዎችም የዚህ ስምምነት አካል ለመሆን መስማማታቸውንና ማጠናቀቅ ያለባቸውን የእርስ በእርስ ግንኙነት ጉዳይ ከጨረሱ በኋላ የዚህ ስምምነት አካል እንደሚሆኑ አቶ ቀጄላ ጠቁመዋል፡፡ ሌሎች የፖለቲካ ድርጅቶችም የዚህ  ስምምነት አካል ለመሆን ፍላጎት ማሳየታቸውን ገልፀው፤ በማንኛውም ጊዜ የስምምነቱ አካል ለመሆን እንዲችሉ ሂደቱ ክፍት መደረጉን አስረድተዋል፡፡  

Read 1452 times