Saturday, 18 January 2020 13:36

ባህልና ታሪክን ያማከለ የቱሪስት መዳረሻ (በጐንደር)

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(0 votes)

    - “ህይወት በአብያተ መንግስት” ፕሮጀክት በአባጅፋርና በአፄ ዮሐንስ ቤተመንግስት ይተገበራል
        - “ህይወት በአብያተ መንግስት” የጐብኚውን የቆይታ ጊዜ ያራዝማል
        - በኪነጥበብ የተኮራረፈ ህዝብ ፣ እንዲታረቅና ፍቅራችን እንዲመለስ እተጋለሁ


            ዘንድሮ የጥምቀት በዓል በዩኔስኮ መመዝገቡን ተከትሎ፣ ጐንደር ክብረ - በዓሉን በተለየ ዝግጅትና ድምቀት ለማክበር ሽርጉድ ስትል ነው የሰነበተችው፡፡ በዓሉን ወደ 1ሚ. በላይ ህዝብ ይታደመዋል ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን የጥምቀት እንግዶች በቅርቡ ለጉብኝት የተዘጋጀውን የ “ህይወት በአብያተ መንግስትን” ክዋኔ ይጐበኛሉ፡፡ ለመሆኑ የባህል ማዕከሉ ምን አሰናድቷል? ማዕከሉ እስከዛሬ የሚጠበቅበትን ያህል ሰርቷል? የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ ናፍቆት ዮሴፍ፤ በቅርቡ የጐንደር የባህል ማዕከል ዋና ዳይሬክተር ሆነው ከተሾሙት አቶ ገብረማርያም ይርጋ ጋር ባደረገችው ቆይታ የማዕከሉን አጠቃላይ እንቅስቃሴና የወደፊት ራዕይ አስመልክቶ ቃለምልልስ አድርጋለች፡፡


              ቀደም ሲል በጐንደር ዩኒቨርስቲ የሙዚቃ ጥበባት ትምህርት ክፍል ያስተምሩ እንደነበር ሰምቻለሁ፡፡ እስኪ በጐንደር ዩኒቨርስቲ ስለነበረዎት ቆይታና ለጐንደር ባህል ማዕከል ዳይሬክተርነት የተመረጡበትን ሂደት ያጫውቱኝ?
እንዳልሽው በጐንደር ዩኒቨርስቲ የሙዚቃ ጥበባት ትምህርት ክፍል እሰራ ነበር፡፡ በዩኒቨርስቲው የሙዚቃ ጥበባት ትምህርት የተመሰረተው በ2009 ዓ.ም ነው፡፡ መስራቹም እኔ ነኝ፡፡ በ2008 ዓ.ም የቴአትር ጥበባት ትምህርት ክፍል ሲመሰረት፣ የትምህርት ክፍሉ ባልደረባ ሆኜ  አስተምር ነበር፡፡ ከዚህ ጐን ለጐን የሙዚቃ ጥበባትን ሥርዓተ ትምህርት ዲዛይን በማድረግ፣ ከእኛ በፊት የትምህርት ክፍሉን ጀምረው ከነበሩት ከእነ አዲስ አበባ፣ መቀሌና ጅማ ዩኒቨርስቲዎች ልምዶችንና ተሞክሮዎችን በመቀመር ስርዓተ ትምህርቱ እንዲቀረጽ በማድረግና ወርክሾፖችን በማዘጋጀት የመጀመሪያው የትምህርት ክፍሉ መስራች ልሆን ችያለሁ፡፡ አስተምርም ነበር፡፡
የትምህርት ዝግጅትዎ ከሙዚቃ ጋር ግንኙነት አለው?
አዎ! የመጀመሪያ ዲግሪዬን ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ፣ ያሬድ ሙዚቃ ት/ቤት ነው ያገኘሁት:: ሁለተኛ ዲግሪዬን ደግሞ ከባህርዳር ዩኒቨርስቲ በፎክሎር ተከታትያለሁ፡፡ እንደነገርኩሽ በጐንደር ዩኒቨርስቲ በስራ ላይ እያለሁ አዲሱ የከተማ መስተዳድር አመራሮች፣ (በጐንደር ዩኒቨርስቲ ያስተምሩ የነበሩ ወጣቶች ናቸው፡፡) በኔ የትምህርት ዘርፍ ለከተማውና ለአካባቢው የበኩሌን አስተዋጽኦ እንዳደርግ ጋብዙኝ፡፡ እኔም ጥያቄ ሲፈጥሩብኝ የቆዩ ጉዳዮች፣ የሚያስቆጩኝ የጉያችን እውነቶች በውጭ ሆኜ ከምብሰለሰል በጐንደር ባህልና ኪነ-ጥበባት ላይ የበኩሌን ሚና ለመጫወት ፈለግሁ፡፡ የከተማው ተቀዳሚ ም/ከንቲባ ኢ/ር ማስተዋልና ምክትል ከንቲባው አቶ በሪሁን ያቀረቡልኝን ጥሪ፣ ተቀብዬ፣ ባህል ማዕከሉን መምራት ጀመርኩኝ፡፡ ይኸው ስራ ከጀመርኩ 1 ወር ተኩል አልፎኛል፡፡
ጐንደር ካላት እድሜ፣ ሰፊ ባህልና ቅርስ አንፃር፣ ባህል ማዕከሉ የሚጠበቅበትን አልሰራም የሚሉ ወቀሳዎች ይሰነዘሩበታል፡፡ እርስዎ በወቀሳው ይስማማሉ?  ምን አዲስ ለውጥና አሰራር ይዘው ነው ወደ ማዕከሉ የመጡት?
ጥሩ ጥያቄ ነው! እንግዲህ ባህል ማዕከሉ የሚጠበቅበትን ርቀት ያህል ተጉዟል ማለት አይቻልም፡፡ በነገራችን ላይ የጐንደር ባህል ማዕከል፣ በ2009 ዓ.ም ጥር ወር ላይ ነው የተቋቋመው፡፡ ያቋቋመውም የጐንደር ከተማ አስተዳደር ምክር ቤት ነው፡፡ ስራ አስኪያጅና ምክትል ስራ አስኪያጅ ያሉት ሆኖ፣ በውስጡ የተለያዩ አደረጃጀቶች አሉት፡፡ የጐንደር ፋሲለደስ የኪነት ቡድንን፣ የጐንደር ሲኒማን፣ ወደፊት የሚቋቋመውን ቴአትርና የጐንደር ሙዚየምን በውስጡ ይይዛል ተብሎ ነው የሚታሰበው፡፡  አሁን ላይ በማዕከሉ የጐንደር ፋሲለደስ የኪነት ቡድን፣ ጐንደር ሲኒማ ቤትና ሰራተኞቹ ናቸው በውስጡ ያሉት፡፡ የቴአትር ቡድንም የለውም፤ የጐንደር ሙዚየምም የለውም፡፡ በተለያየ የስነ ጽሑፍ አደረጃጀት ውስጥ የሚኖሩ ክፍሎች አልተደራጁም፡፡ እነዚህ ባልተሟሉበት ሁኔታ በቂ ስራ ተሰርቷል ማለት አይቻልም እንጂ ከላይ የገለጽኳቸው ክፍሎች እንዲደራጁ ጥረት ሲደረግ እንደነበርና የተኬደበትም ርቀት እንዳለ አውቃለሁ፡፡ ስለዚህ ክፍተቶች እንዳሉ በማመን፣ ክፍተቶቹ እንዴት ነው የሚታከሙት? እንደ ባለሙያስ ምን አስተዋጽኦ አድርጌ ክፍተቶቹን ልሙላ? ብዬ ነው… ወደዚህ ቦታ የመጣሁት፡፡
እነዚህን ክፍተቶች ለመሙላት ምቹ ሁኔታዎች አሉ?
እኔ ወደዚህ ስመጣ፣ ምንድን ነው ልሰራ የምችለው ብዬ፣ ስትራቴጂ ይዤ ነው የመጣሁት:: አሁን ላይ ባህል ማዕከሉ ያለበት ቁመና ምን ይመስላል? ወደፊትስ ምን ያስፈልገዋል? እኔ በምን ያህል ጊዜ ውስጥ ስራ ሰርቼ፣ ማዕከሉን ወደሚጠበቀው ቁመና አመጣዋለሁ? የሚለውን መሪ እቅድ ይዤ ነው የመጣሁት፡፡
ምቹ ሁኔታን በተመለከተ አሁን የከተማ አስተዳደሩ በወጣት አመራሮች ስለተተካ፣ ተግባብቶ በመስራቱ በኩል ችግር ይኖራል ብዬ አላምንም፡፡ ሌላው የግለሰብም አቅም ለውጥ ያመጣል ብዬ አምናለሁ፡፡ ተነሳሽነት ካለ ብዙ ነገር መለወጥ ይቻላል፡፡ እያንዳንዱ ሰው ወደዚህ ምድር የሚመጣው በምክንያት ነው፡፡ ዞሮ ዞሮ ስራ ሲሰራ ችግሮችና ተግዳሮቶች ዜሮ ይሆናሉ፤ ይጠፋሉ ማለት አይደለም፡፡ ነገር ግን ለችግሮች መፍትሔ እየሰጡ፣ ልብን ቀና አድርጐ በተነሳሽነት መስራት ለውጥ ያመጣል:: እኔም በዚህ አስተሳሰብ ውስጥ ሆኜ ነው ስራ የጀመርኩት፡፡  የአንድን ማህበረሰብ እድገትና ለውጥ ስናስብ፣ ባህሉን ታሪኩን መሰረት ማድረግ አስፈላጊ ነው፡፡ ባህልና ታሪክን መሰረት ያላደረገ ሥራ ለውጥ ያመጣል ብዬ አላምንም፡፡
ማዕከላችሁ  “ሕይወት በአብያተ መንግስት” የተሰኘ ፋሲለደስ ላይ ነፍስ የመዝራት ፕሮጀክት  መተግበር ጀምሯል፡፡ ፕሮጀክቱ በብዙዎች አድናቆትን አትርፏል፡፡ እንዴት ታሰበ?
እኔ ገና በማዕከሉ ሥራ እንደጀመርኩ ለቱሪዝም ኢትዮጵያ ዳይሬክተር ለአቶ ስለሺ ስልክ ደወልኩ፡፡ ባህልና ታሪክ ለቱሪዝም መሰረት ነው፡፡ ስለዚህ ምንድን ነው አብረን ልንሰራ የምንችለው በሚል ነው አደዋወሌ:: “ህይወት በአብያተ መንግስት”ን ከዚህ በፊት ሰዎች እንዲህ አስቤ እንዲህ ሞክሬው ሳይሳካ ቀርቶ ይላሉ፡፡ ከቱሪዝም ኢትዮጵያ ጋር ስንነጋገር ግን ይሄ ነገር የራሱ ቅርጽና ፕሮጀክት ያስፈልገዋል፤ ይተግባር ወደሚል ስምምነት ደረስን፡፡    
ግን የ “ህይወት በአብያተ መንግስት” ሃሳብ አፍላቂ ማን ነበር?
ቀደም ብዬ እንደነገርኩሽ፤ ሰዎች ከዚህ ቀደም ስለ ጉዳዩ እንዲህ ላደርገው አስቤ፣ እንደዚህ ሞክሬ ሲሉ እሰማ ነበር፡፡ ነገር ግን የጐንደር የባህል ማዕከል ወጣቶችን በማሰባሰብና በማሰልጠን፣ አጠቃላይ ቤተ መንግስቱ ውስጥ ነገስታቱ ይኖሩ በነበሩ ጊዜ ይከወን የነበረ ወግና ሥርዓት ምን ይመስላል? ማን የት ይቆም ነበር? ነገስታቱ እንዴት ነበር እንግዳ የሚቀበሉት? አጋፋሪዎች፣ የጥበቃ ሰራተኞች፣ ደንገጡሮች፣ አዝማሪዎች  አንዴት ነበር የሚሰሩት? በቤተ መንግስት የአመጋገብ ስርዓቱ፣ አለባበሱ፣ የአዝማሪ ሚና፣ ምን ይመስል ነበር የሚለውን እንተግብር ብለን ከቱሪዝም ኢትዮጵያ ጋር ከተነጋገርን በኋላ፣ ነገሩን ማስኬድ የጀመርኩት እኔ ነኝ፡፡
ከላይ የገለጽኩልሽ ንድፈ ክዋኔ ምን ይመስል እንደነበር ስክሪፕት የፃፍኩት ኃይለማርያም ከሚባል ልጅ ጋር ነው፡፡ እዚህ ከተማ በቴአትር ቡድን ውስጥ የሚሰሩ እነ ግርማይ፣ እነ አሰግድ ከሚባሉ አስጐብኚዎችና ከታሪክም አንፃር ግንዛቤ ያላቸውን ወጣቶች ሰበሰብኩኝ:: በቃ ይሄ ይሄ በተግባር መሰራት አለበት አልኳቸው:: በወቅቱ ይደረጉ የነበሩ ነገሮችን እያነሳን እንወያያለን፤ ክርክርም አለ፡፡ “አይ አንተ ያልከው ትክክል አይደለም፤ በዛን ጊዜ እዚህ ቦታ እንዲህ ይደረግ እንደነበር እንዲህ አይነት መጽሐፍ ላይ አንብቤያለሁ ይላል አንዱ በክርክሩ ውሃ የሚያነሳውን ሃሳብ እየወሰድን፣ እያዳበርን ነው ስክሪፕቱን የፃፍነው፡፡ ነገር ግን ከዚህ ቀደም “ህይወት በአብያተ መንግስት” የሚለው ሃሳብ ታስቧል፡፡ እኛ ግን ደክመን አውጥተን አውርደን ተግብረነዋል፡፡ ዞሮ ዞሮ የፋሲል አብያተመንግስት፣ በዚያ ዘመን የነበረው ህይወት አሁን ላይ እንዲያንሰራራ ነው ያደረግነው፡፡ ይሄ ደግሞ ታሪክ ነው፡፡ ታሪኩ የህዝብ ሀብት ነው፡፡
ትልቅ ሃሳብ ነው፡፡ የመጀመሪያውን ትግበራ ለማየት የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትርና የኢትዮጵያ ቱሪዝም ድርጅት መስራች አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ ከእነባለቤታቸውና በርካታ ታዋቂ ሰዎች ታድመው ነበር፡፡ ግብረ መልሳቸው ምን ይመስላል?
ያው አንቺም በቦታው ነበርሽ፡፡ ሁሉም ሰው ደስተኛ ነበር፡፡  ከበር ጀምሮ ጥበቃዎቹ እንዴት እንደሚቀበሉ፤ የንጉሱና የንግስቲቱ እንግዳ አቀባበል፣ የአጋፋሪው ሚና፣ ግብር ሲበላ የአዝማሪ ጨዋታው፣ የምግብና የመጠጡ መስተንግዶ ሁሉ ቀርቧል፡፡ ለዚህ ስራ ከቴአትር ቡድኖችና ከሌሎችም ክበባት ከ160 በላይ ወጣቶች ተሳትፈዋል፡፡ የስራ ዕድልም የፈጠረ ፕሮጀክት ነው፡፡ ሁሉም ደስተኞች ነበሩ:: ይህ አብያተ መንግስት ነፍስ እንዲዘራ ብዙ ደክመናል፡፡ የቱሪዝም ኢትዮጵያ ትብብርም የሚደነቅ ነው፡፡
የፋሲል አብያተ መንግስት በዓለም ቅርስነት የተመዘገበ ነው፡፡ ከፍተኛ ጥበቃ የሚደረግለት ነው፡፡ ሌላው ቀርቶ በዙሪያው ያሉ “ህድሞ” ቤቶች እንኳን “በፈር ዞን” ተብለው የተከለሉና እንዳይፈርሱ የተከለከሉ ናቸው፡፡ ከዚህ አንፃር “ህይወት በአብያተ መንግስት” ትግበራ ላይ ፈረሶች ይገባሉ፤ በርካታ ሰው ይመላለሳል:: ቅርሱ ላይ ጉዳት እንዳይደርስ ጥንቃቄ ያስፈልጋል የሚሉ ሰዎች ስጋታቸውን ሲገልፁ ሰምቻለሁ፡፡ በዚህ ረገድ ከባለሙያ ጋር ምክክር  ታደርጋላችሁ?
ከማንም በላይ ለቅርሱ እኛም እንሰስታለን እንጠነቀቃለን፡፡ በእያንዳንዱ ክዋኔ ቅርሱ እንዳይነካ እንዳይጐዳ ጥንቃቄ ይደረጋል፡፡ ከዚህ ሌላ በዩኒቨርሲቲውም በባህልና ቱሪዝሙም የቅርስና የባህል ባለሙያዎች እንዲያማያክሩን፣ ሙያዊ ድጋፍ በማድረግ አብረውን እንዲሰሩ እየጣርን ነው፡፡ ሀሳቡና ትግበራው ግን ይቀጥላል፡፡ ባዶውን የነበረውን ህይወት እየዘራንበት ነው፡፡ ለጐብኚ “እዚህ እዚህ እነ እከሌ እንዲህ ያደርጉ ነበር” ብለን እንደ ሶስተኛ ሰው ከምንነግራቸው፤ “እገሌ የሚባለው ንጉስ ይሄ ነበር” ብለን ከዋኒው ያንን ሲያደርግ ቢያዩት ስሜት ይሰጣል፤ ውስጣቸው ይቀራል፤ ንጉስ ሆኖ ከሚሰራውና ንግስት ሆና ከምትሰራው ጋር አብረው ፎቶ ይነሳሉ፡፡ የዛን ዘመን ታሪክ ሲተገበር ቀጥታ ያዩታል፡፡ ይሄ ሌላ ተጨማሪ የቱሪስት መዳረሻ ሃሳብ ነው፡፡ ስለዚህ ትልቅ ሃሳብ ነው፤ የህዝብ ሀብት ነው፡፡
“ህይወት በአብያተ መንግስት” ፕሮጀክት በጅማው “አባጅፋር” እና በመቀሌው “አፄ ዮሐንስ” ቤተ መንግስታት በቅርቡ እንደሚተገብር ከቱሪዝም ኢትዮጵያ ዳይሬክተር ሰምቻለሁ፡፡ ሌላ ተጨማሪ የቱሪስት መዳረሻ ይፈጠራል ማለት ነው?
ይሄ ተጨማሪ ቱሪስትን የሚስብ ትልቅ ክዋኔ ነው፡፡ እኛ ለእናንተ ያሳየናችሁ ጅምሩን ነው፡፡ እያደገ እያደገ ይሄዳል፡፡ ለምሳሌ ካራክተር ካስት ሲደረግ፤ የንጉስና የንግስት በተለይ እድሜ፣ ቁመናና መልክ ያን ጊዜ ከነበሩት ነገስታትና ንግስቶች ጋር ተመሳስለው በሚፈለገው መልኩ ይሆናል፤ ብዙ ነገሮች በተጠናከረ መልኩ ይሰራሉ፡፡
ይህንን ክዋኔ የጐንደር ከተማ ህዝብ የማየት ዕድል ገጥሞታል?
እስካሁን ጋዜጠኞችና አመራሮች ናቸው ያዩት፡፡ ምክንያቱም ለሙከራ ነው የታየው፡፡ ነገር ግን የከተማው ህዝብም ይህንን ትግበራ የሚያይበትን መርሃ ግብር አዘጋጅተናል፡፡ ጥምቀት ተቃርቧል፡፡ ከጥር 4-10 ቀን ባለው መርሃ ግብር ህዝቡ እንዲመለከተው ይደረጋል (ቃለ ምልልሱ ከሳምንት በፊት የተደረገ ነው)፡፡ ህዝቡ ካየው በኋላ አስተያየቶችን፣ ጥቆማዎችንና ምክሮችን በመቀበል ትግበራውን የማዳበር ስራ ለመስራት እንጠቀምበታለን፡፡ ከቱሪዝም ጋር ግንኙነት ካላቸው ሰዎች ጋር ቆይታ አድርገን ነበር፡፡ ከአለባበስና ከአጠቃላይ ሁኔታዎች አንፃር እንዴት አያችሁት? ምን ይስተካከል? ብለን ጠይቀን አስተያየት ሰብስበናል፡፡ ለጊዜው ባለን አቅም ነው እየከወንን ያለነው፡፡
ጥምቀት በዓለም ቅርስነት መመዝገቡን ተከትሎ፤ በዘንድሮ በዓል ከ1ሚሊዮን በላይ ሰዎች ጐንደር ላይ እንደሚታደሙ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ኢ/ር ማስተዋል ስዩም ነግረውኝ ነበር፡፡ “ህይወት በአብያተ መንግስት” ፕሮጀክት ደግሞ የተሰራው በእንግዶች እንዲጐበኝ ነው፡፡ ለዚህ ሁሉ ሰው ለማስጐብኘት ከጊዜና ከአቅም አንፃር ምን ያህል ዝግጁ ናችሁ?
“ህይወት በአብያተ መንግስት”ን ለእንግዶች ማስጐብኘት  ሲባል የጐብኚውን የቆይታ ጊዜ ማራዘም ነው እንጂ በአንዴ ያንን ሁሉ ህዝብ ማሳየት አይደለም፡፡ የቱሪስት የቆይታ ጊዜ መራዘሙ ለከተማው ህዝብ ያለው ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ በጣም ትልቅ ነው፡፡ ብዙ ሰው በአንዴ ማስጐብኘት ሳይሆን ቱሪስቱ ይህንን ለማየት ሲቆይ ምን ያህል ገቢ እናገኛለን? የሚለው ነው ዋና ትኩረታችን፡፡ ስለዚህ በርካታ ቁጥር ያለው ሰው ክዋኔውን የማየት ፍላጐት ሲኖረው መርሃ ግብር ተዘጋጅቶ፣ በወረፋና በቅደም ተከተል ይጐበኛል እንጂ ሁሉንም በአንዴ ለማስገባት አንችልም፤ ግንቡም አይችልም፡፡ በነገራችን ላይ አንደኛ፣ ሁለተኛና ሶስተኛ የሚባሉ ፓኬጆች ይኖሩታል፡፡ ጐብኚውም በመረጠው ፓኬጅ፣ ይመቸኛል ብሎ በያዘው ቀንና ሰዓት ተራውን ጠብቆ ይስተናገዳል፡፡ በአንዴ ስንት ሰው ብናስጐበኝ ቅርሱን አይጐዳውም የሚለው… ከባለሙያ ጋር እየተነጋገርን ነው የምንሰራው፡፡
የጐብኝት የታሪፍ ተመን ወጥቶለታል እንዴ?
የክልሉ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ነው ታሪፍ የሚተምነው፡፡ እኛ አንተምንም፡፡ ፍላጐት ነው የምናቀርበው፡፡  ፍላጐታችንንም አሳውቀናል፡፡ የታሪፉን ጉዳይ፣ የክልሉ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ያሳውቀናል ብለን ነው የምንጠብቀው፡፡
እርስዎ በኃላፊነት ላይ እያሉ፣ ባህል ማዕከሉ የት ደርሶ ማየት ይፈልጋሉ?
የማዕከሉ ራዕይ ማህበረሰቡን ያሳተፈ፣ ኪናዊና ባህላዊ እንቅስቃሴዎችን በማጐልበት፣ የጐንደር ባህል ማዕከልን ከሌሎች የባህል ማዕከላት ተወዳዳሪና ሳቢ ማድረግ ሲሆን ተልዕኮው የጐንደርን ቱባ ባህል ጠብቆ መከወንና ከትውልድ ወደ ትውልድ እንዲተላለፍ ማስቻል ነው፡፡ ይሄ እንዳለ ሆኖ ዋና ግቡ፣ በኪነጥበብ ተጠቃሚ መሆን ነው፡፡ እኔ ኪነ-ጥበብን የሆነ ጉዳይ ማሟያ ሆና ነው የማያት:: በሙዚቃ፣ በቴአትርም ሆነ በሌላው… ለሆነ ጉዳይ ማስፈፀሚያ፤ ለዚያውም ክብር በሌለው መልኩ ሲከወን አያለሁ፡፡ የሆነ ነገር ሲሆን “ኑ ድምፃዊያን እንዲህ አድርጐ” “እንደዚህ ሁኑ” ይባላል፡፡ እኔ ይሄንን ለማስቀረትና ኪነ-ጥበብ ትልቅ ክብር ተሰጥቷት የቀድሞው ግርማ ሞገስ ኖሯት፣ የጐንደርን ከፍታ የሚያሳይ ራሱን የቻለ የሙዚቃ መንደር፣ የፊልም መንደር፣ እንዲኖር ነው የምፈልገው፡፡ የአዝማሪ መንደር ሁሉ እንዲኖር እሻለሁ፡፡ ጐንደር የእነ ይርጋ ዱባለ፣ ታማኝ በየነ፣ እንዬ ታከለ፣ ፍቅር አዲስና ሌሎችም አርቲስቶች መፍለቂያ ናትና… በየዘርፉ እነዚህን የሚተኩ ወጣቶች ተፈጥረው ማየት ነው ግቤ፡፡ ባህል ማዕከሉ በዚህ በኩል ትልቅ ቦታ ደርሶ ማየት እፈልጋለሁ፡፡
በኪነ-ጥበብ የተኮራረፈ ህዝብ ታርቆ፣ ፍቅራችን ተመልሶ ለማየት በትጋት እሰራለሁ “ጊዮን በጐ አድራጐት” ከተባለ ድርጅት ጋር “ደም በደም አይደርቅም” የሚል ፕሮጀክት ጀምረናል፡፡ ወጣቶች በኪነ-ጥበብ እያዋዙ ጐንደርና አካባቢው ወረዳዎች ላይ የአዕምሮ ልማት ስራ እየሰራን ነው፡፡
ይሄ የቂምና የበቀል አሰራር ቆሞ ጐንደር የሀገር መሰረት ሆና በመጣችበት መንገድ እንድታድግ፣ ለኪነ-ጥበብና ባህል ማደግ አጥብቀን መስራት አለብን፡፡ በመጨረሻም ሰዎች የጥምቀትን በዓል በጐንደር እንዲያሳልፉ እየጋበዝኩ፤ ሁሉም ሙሉ ሁሉም ዝግጁ መሆኑን ለመግለጽ እወዳለሁ፡፡ “ሠላምና አብሮነት በጐንደር ጥምቀት” በሚለው የዘንድሮ የጥምቀት በዓል መሪ ቃል እሰናበታለሁ፡፡
መልካም በዓል!!


Read 1688 times