Saturday, 18 January 2020 13:23

“ዘንድሮ ማን ይታመናል?”

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(3 votes)

      “እኔ የምለው…እንግዲህ ጨዋታም አይደል…ይሄ ያለመተማመናችን ነገር የት ያደርሰን ይሆን!? አስቸጋሪ ነገር እኮ ነው፡፡ እናላችሁ… ምንም ጉዳይ ይነሳ፣ ምንም ነገር ይባል… አለ አይደል… የሆነ ነገር ሳንቀጥልለት መቀበል እያስቸገረን ነው፡፡--”
            
             እንኳን ለባህረ ጥምቀቱ አደረሳችሁ!
እንዴት ሰነበታችሁሳ!
እኔ ምለው… ይሄ የድሮ የጃን ሜዳ ‘አድቬንቸር’ አሁንም አለ እንዴ! ቀላል ‘አድቬንቸር’ ነበር እንዴ! አሀ…ልክ ነዋ፣ ስንቱ በጃን ሜዳ ሀርሞኒካ፣ በጃን ሜዳ ‘ስፒል’ ውሀ አጣጪውን አግኝቶ፣ ቤተሰብ መስርቶ የለም እንዴ! አሁን ነገር ተለውጦ “የጃን ሜዳን ውለታ ወሰደችው ቪትዝ…” አይነት ነገር ሊመስል! እኔ የምለው፣ ለጠቅላላ እውቀት ያህል…አሁን የመኪና ዋጋ ጣራ ሲነካ ቪትዝ ‘ትውልዳዊ ሀላፊነቷን’ ትቀጥላለች (ቂ…ቂ…ቂ…) ወይስ ቦታዋን የሚተኩ ‘እጩዎች’ ተዘጋጅተዋል?! (እነ እንትና፣ ያቺ ‘ታሪካዊ’ ሀርሞኒካችን ማንኛችሁ ሳጥን ውስጥ ነች? በሆነ የቲቪ ጣቢያ “በዚች ሀርሞኒካ፣ ስንት ልብ ተከካ!” የሚል ዘጋቢ ፊልም ለምን አንሰራባትምማ!)
ለክፉም፣ ለደጉም መልካምና በሀላፊነት የተሞላ የበዓል ሰሞን ይሁንልንማ!
እኔ የምለው…እንግዲህ ጨዋታም አይደል…ይሄ ያለመተማመናችን ነገር የት ያደርሰን ይሆን!? አስቸጋሪ ነገር እኮ ነው፡፡ እናላችሁ… ምንም ጉዳይ ይነሳ፣ ምንም ነገር ይባል… አለ አይደል… የሆነ ነገር ሳንቀጥልለት መቀበል እያስቸገረን ነው፡፡ የድሮዋ “ሦስቴ እንዴት ዋላችሁ፣ አንዱ ለነገር ነው” የምትለዋ ተረት አሁን… “አንዴ እንዴት ዋላችሁ፣ እሷው ለነገር ነች” ወደሚል ሳትለወጥ አልቀረችም፡፡ በፖለቲካ አለመተማመናችን ዛሬ፣ ዛሬ በአስደናቂ ሁኔታ ባሰበት እንጂ ትናንትም፣ ከትናንት ወዲያም የነበረ ነው፡፡ አንድም፣ ነገራችንን ሁሉ ‘ውሀ ቅዳ፣ ውሀ መልስ’ ያደረገው ይኸው ነው፡፡
እናላችሁ… ማንም ማንንም ያለ በቂ ምክንያት የሚጠራጠርበት ዘመን ላይ የደረስን ይመስላል:: እንበልና የሆነ ኮንዶሚኒየም የሚኖር ጓደኛ ይኖራል፡፡ ስሙኝማ…እንግዲህ ጨዋታም አይደል…የምር ግን ዘንድሮ ኮንዶሚኒየም የሚኖር ጓደኛ ወይም ዘመድ የሌለው ሰው…አለ አይደል… ጓደኛም፣ ዘመድም የሌለው ሊመስል ይችላል፡፡
ይሄ ነገር ግን የአዲስ አበባ ‘ቤቨርሊ ሂልስ’ ሰፈሮችን አይመለከትም፡፡ (ቂ…ቂ…ቂ…) እኔ ምለው..ይቺ ከተማ እኮ ዘወር፣ ዘወር ብለው ሲያዩዋት…አለ አይደል…አንዳንድ አካባቢዎች ከሆነ የኒው ዮርክ ወይም የፓሪስ ዲታዎች መንደር እንዳለ ነቅለው እዚህ የተከሏቸው ሊመስሉ ምንም አይቀራቸው!
አሁን የእኔ አሟሟት፣ አሟሟት ነው ወይ
የጂ ፕላስ ስሪን አልጋ፣ ተኝቼ ሳላይ
ነገር እኮ ነው፡፡ እናማ…ከውጪ ስናያቸው እንዲህ የጆርጅ ክሎኒ ቤት የመሰሉን ሁሉ ውስጣቸው ብንገባ… እንደው ሳስበው ነው… ከማተኮሳችን የተነሳ ውሀ በጎማ ተስቦ የሚቸለስብን ይመስለኛል፡፡ ታዲያላችሁ… በእነኚህ ሸላይ ሰፈሮች መሸት ሲል ብታልፉ ….“ስታዲየም አይደል፣ ይሄ ሁሉ መብራት ምን ሊያደርግላቸው ነው ያበሩት?” ማለታችሁ አይቀርም፡፡ ልክ ነዋ!... ከራሳችሁ ጋር ነዋ የምታመሳስሉት! ልጄ… ከአምስት አምፖል ሦስቱ ሲበራ የተገኘ ቀን፣ ሰማንያ ሁሉ ሊቀደድ ይችላል፡፡
“የውጪውን መብራት ብርሀን ለማድቤቱ ተጠቀሙ፣ ውስጥ ያለውን አታብሩ አላልኩም!” አይነት ጭቅጭቅ፡፡ ያውም በየሁለትና በየሶስት ወሩ… “ዋጋ ሊጨመር ነው”፣ “ክፍያው ጣራ ቀዶ ሊሄድ ነው” እየተባለ ለምንሳቀቅበት አገልግሎት፡፡ (ምን አለ… ቢያንስ፣ ቢያንስ በእድሜ የገፉ፣ አካል ጉዳተኞችና ሌሎች በተለያዩ ምክንያቶች ረጅም ሰዓት መቆም የማይችሉ ‘ደንበኞቻችሁ’፤ በስነ ስርአት ተቀምጠው የክፍያ ተራ የሚጠብቁበት ስርአት ማማቻቸት አቅቶ ነው!)
ከሁሉ በፊት… “ከእንግዲህ ቤታችሁ ቁጭ ብላችሁ መክፈል ትችላላችሁ” ሲባልለት የነበረ አገልግሎት ጭራሽ ገና ጎህ ሲቀድ ወረፋ መያዝ ተጀምሯል፡፡ ቤት ቁጭ ብለን መክፈሉ ቢቀርብን ቁጭ ብለን ወረፋ እንድንጠብቅ ብታደርጉን፣ እርግማናችን ሠላሳ ስድስት በመቶ ይቀንሳል:: ደግሞም አግዳሚ ወንበር ይበቃናል፡፡ አይ…ትንሹም፣ ትልቁም “የምናምን ሺህ ብር ቆዳ ወንበር ካልቀረበልኝ” ባይ ቢሆንብን ጊዜ ነው:: (ቂ…ቂ…ቂ…)   
እናላችሁ…በሸላዮቹ ሰፈር ስታልፉ ሌላ ምን ትዝ የሚል ነገር አለ መሰላችሁ…‘ፉድ!’ ልክ ነዋ…የምግብ ጠረጴዛውን ማማር ‘ፈርኒቸር’ ቤቶችን ወይም አንዳንድ የሀገራችን ፊልሞችን በማየት ልትጠረጥሩ ትችላላችሁ:: የ‘ፉዱን’ አይነት ግን በምን አንጀታችሁ ነው የምትጠረጥሩት! አሀ…ሆቴል ቤት ተጋብዛችሁ መጀመሪያ የገለበጣችሁት አንድ ጣባ ሾርባ፤ “ይሄ ‘አፕታይዘር’ ነው” የተባላችሁ ጊዜ “ጉድ! ጉድ!” ብላችሁ ሀገር ቤት ላሉት ዘመዶቻችሁ ሁሉ ስታወሩ  እኮ ነው የከረማችሁት!  እናማ… እዛ የጆርጅ ክሉኒ የሚመስለው ቤት ውስጥ ያሉ ሰዎች… “ምን እየተመገቡ ይሆን?!” ብትሉ አይገርምም፡፡ ምን እንደሆነ የማታውቁት ምግብ እኮ ይናፍቃችኋል፡፡ “የማያውቁት ሀገር አይናፍቅም” የሚለው ነገር ለሀብታም ምግብ ሲሆን አይሠራም፡፡ (ቂ…ቂ…ቂ…)
ሰውየው… “አሳማዎች ሁሉ እኩል ናችው፣ አንዳንድ አሳማዎች ግን የበለጠ እኩል ናቸው” አለ እንደሚባለው “አንዳንድ ምሳዎችና እራቶች የበለጠ እኩል ናቸው” የሚል ‘ፉድ ፊሎሶፊ’ የሚያራምድና ‘ምናምን ፋርም’ የሚል መጽሀፍ ይጻፍልንማ! ታዲያላችሁ… “እነሱ ምን ይመገቡ ይሆን?” እያላችሁ የራሳችሁ ‘ፉድ’ አእምሯችሁ ውስጥ እንደ ተከታታይ ፊልም ያለማቋረጥ ይመላለሳል፡፡ ‘ሩጫውን ሳይጨርስ’ በ“በቃኝ፣ ሰው ጠመደኝ” እንደተሰናበተው ዛራና ቻንድራ አይነት ነገር፡፡
እናማ… ለመጀመሪያ ጊዜ (ቂ…ቂ…ቂ…) ሰኞ እለት ምሳ ተብላ ቀርባ የነበረች ምስር፤ ቅዳሜ እለት እራት ተብላ ለሰባተኛ ጊዜ እየቀረበች… በአእምሯችሁ የሀብታም አጥር አልፋችሁ የሆነ ‘‘ፉድ ፋንታሲ’ ነገር ውስጥ ብትገቡ ምን ይገርማል! እንደውም ድስቱ ላይ የተረፈችው ምስር “ልክ እንዳስቀመጧት” የምትባል ሳትሆን… አለ አይደል… ተራፊ ምስሮች በ‘ቡድንና የቡድን አባቶች’ አይነት ሰብሰብ እያሉ እንደ ፓስታል ፉርኖ አይነት ነገርም መስለዋል፡፡ ‘ሶስ’ የበዛበት ፓስታል ፉርኖ፡፡ ቂ…ቂ…ቂ…
እናላችሁ…ከፍ ብለን የጠቀስነውን የኮንዶሚኒየም ጓደኛችሁን …“ስማ ጎረቤትህ ያለውን ሰውዬ ታውቀዋለህ?” ብላችሁ ትጠይቁታላችሁ፡፡
“እንደውም…”
“ጭራሽ አይተኸው አታውቅም?”
“ከገባ ወደ ሁለት ዓመቱ ገደማ ነው፡፡ ምን ይምሰል ምን አይቼው አላውቅም፡፡”
“ለነገሩ አይገርምም፣ ወይ ሥራ ይበዛበት ይሆናል…ወይ ብዙም ከሰው መቀላቀል አይፈልግ ይሆናል” ትላላችሁ፡፡
“አይመስለኝም፡፡ የማይታየው የሆነ የሚደብቀው ነገር ቢኖረው ነው፡፡ ዘንድሮ ማን ይታመናል?”
እናማ… “ዘንድሮ ማን ይታመናል?” የሚለው ነገር፣ ለማህበራዊ ኑሮ አስቸጋሪ ነው፡፡
ስሙኝማ…ድሮ ትምህርት ቤት በየክፍሉ ‘ክርክር’ የሚባል ነገር ነበር፡፡ እናማ… በሶስተኛ ሲ ክፍል ክርክር…
“አንተ ስኳር ጣፋጭ ነው ትላለህ፣ አንተ ደግሞ ስኳር መራራ ነው ትላለህ” ይባላል:: አለቀ፡፡ ሌላ ምንም የሚቀጠል፣ የሚቆረጥ ምናምን ብሎ ነገር አልነበረም፡፡ እናማ… “ስኳር መራራ ነው” ብሎ ሽንጡን ገትሮ መከራከር ነው፡፡
እንደ ዘንድሮ ነገራችን ግን… “አንተ ስኳር መራራ ነው ብለህ ተከራከር” የተባለ ሰው ‘እውቀት’ በአንድ ጊዜ ነው የሚገለጽለት፡፡ “ለእኔ ስኳር መራራ ነው ብለህ ተከራከር ያለኝ ከጀርባ የሆነ ነገር ቢኖረው ነው” አይነት ነገር ነው የሚለው፡፡ አለመተማማናችን ጥግ ነው ደረሰው፡፡ ለነገሩማ… ጠዋት ቀይ የሆነው ነገር አመሻሽ ላይ አረንጓዴ እየሆነብን… “ችግሩ ከዓይኖቼ ነው ወይስ የእውነት ቀይ የነበረው ሳይነኩት ወደ አረንጓዴ እየተለወጠ ነው?” እያስባለን፤ አለመተማመናችን ቢበዛም ያን ያህል ላይገርም ይችላል፡፡
እንዲህም ሆኖ ግን… “ዘንድሮ ማን ይታመናል?” የሚለው አስተሳሰብ አሳማኝ መሰረት በሌለው ጥርጣሬ፣ ከአንድ ማእድ እንዳንቋደስ እያደረገን ነው፡፡
በድጋሚ…መልካም የበዓል ሰሞን ይሁንላችሁ!
ደህና ሰንብቱልኝማ!

Read 2052 times