Saturday, 18 January 2020 13:20

የዳዊት ጽጌ ‹‹የኔ ዜማ›› አዲስ አልበም ለአድማጭ ቀረበ

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(1 Vote)

 - ቴዲ አፍሮን ጨምሮ በርካታ የሙዚቃ ባለሙያዎች ተሳትፈውበታል
            - “ባላገሩ አይዶል” በሁለት ወራት ውስጥ ይጀመራል ተባለ

               ‹‹በባላገሩ አይዶል ውድድር›› አንደኛ በመውጣት ያሸነፈው ወጣት ድምፃዊ ዳዊት ጽጌ ‹‹የኔ ዜማ›› አልበም ከትላንት በስቲያ ሐሙስ ጀምሮ ለአድማጭ ቀረበ፡፡ ላለፉት አራት አመታት ከፍተኛ ጥረትና ድካም የተደረገበት አልበሙ፤ በባላገሩ ቴሌቪዥን ፕሮዲዩስ የተደረገ ሲሆን ‹‹ባላገሩ ቁጥር 4ን›› ጨምሮ 14 ዘፈኖችን ማካተቱንና 13 በሲዲው ላይ ሲካተቱ አንዱ ‹‹ሸክላ›› በሚባለው መተግበሪያ ላይ እንደሚገኝ ድምፃዊው፣ ፕሮዲዩሰሩ፣ ዳይሬክተሩ፣ ፕሮሞተሩና የግጥምና ዜማ ደራሲዎቹ ከትላንት በስቲያ በሸራተን ሆቴል ዳሽን አዳራሽ በጋራ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ አስታውቀዋል፡፡
በዚህ አልበም ይልማ ገብረአብ፣ ቴዎድሮስ ካሳሁን (ቴዲ አፍሮ)፣ አበበ ብርሃኔ፣ ናትናኤል ግርማቸው፣ አቤል ሙሉጌታ፣ ሰለሞን ሳህለ ትዕዛዙ፣ አብርሃም ወልዴና ሌሎችም እውቅ የሙዚቃ ባለሙያዎች በግጥምና ዜማ ሥራዎች ተሳትፈውበታል። በቅንብሩ ደግሞ አበጋዝ ክብረ ወርቅ፣ አቤል ጳውሎስ፣ ሚኪያስ ሀይሉ ሌሎችም የተጠበቡበት ሲሆን ዋና ማስትሪንጉ በአበጋዝ ክብረ ወርቅ መሰራቱም ተገልጿል፡፡
አልበሙ  ሰው የሚጠብቀውን ያህል በጥራት እንዲሰራ በርካታ ግጥሞችና ዜማዎች በመሰብሰብ፣ አመራረጡ ላይ በመጠንቀቅ፣ በቅንብሩ ጥራትና ከፍታ ላይ በመምከር ሥራ ተጠምደው መቆየታቸውን የገለፀው ፕሮዲዩሰሩ አብርሃም ወልዴ፣ ‹‹ምንም እንኳ አልበሙ አራት አመት ቢፈጅም ድምጻዊ ዳዊት ጽጌን ግን ብዙ አመት ለፍተንበታል›› ብሏል፡፡
ዘፈኖቹ በምን ጉዳዮች ላይ እንደሚያጠነጥኑም ሲያስረዳ፤ ዋናውን ድርሻ የያዘው የአገርና የኢትዮጵያዊነት ጉዳይ እንደሆነ ጠቅሶ፤ ‹‹አስመሪኖ›› የተሰኘው ዘፈን በኤርትራ ከፍተኛ የሙዚቃ ድርሻና እውቅና ለነበራቸው ነገር ግን በሕይወት ለሌሉ ኤርትራውያን ድምጻዊያን መታሰቢያ የተሰራ ሲሆን፣ በሲዲው ዘጠኝ ቁጥር ላይ የተቀመጠው የአርቲስት ጥላሁን ገሰሰ ዘፈን ሆኖ ሌላም ግጥምና ዜማ ተጨምሮበት ለአርቲስቱ መታሰቢያነት ሆኖ መሰራቱን የገለፀው ድምጻዊ ዳዊት ጽጌ ስለዚህ ዘፈን ሲናገር፣ ‹‹በባላገሩ አይዶል ተወዳድሬ ያሸነፍኩበት ዘፈን በመሆኑ ለታላቁ የሙዚቃ ሰው ጥላሁን ገሰሰ መታሰቢያ አድርጌዋለሁ›› ብሏል፡፡
ባላገሩ አይዶል መጀመሪያም ቃል የገባው አንደኛ ለሚወጣ አሸናፊ አልበም እስከ መሥራት ድጋፍ ማድረግ እንደነበር ያስታወሰው አብርሃም ወልዴ፤ በቃላቸው መሰረትም ዳዊት አልበም ለመስራት መብቃቱንም ተናግሯል፡፡
በቆሊያ ሲዲ የታተመው አልበሙ በ50 ብር ለገበያ የቀረበ ሲሆን፣ ‹‹አስመሪኖ›› እና ‹‹እቱቱ›› የተሰኙት ዘፈኖች ቪዲዮ ክሊፕ ቀረጻ ተጠናቅቆ በኤዲቲንግ ላይ መሆናቸውንና በቅርቡ ለእይታ እንደሚበቁ ተገልጿል፡፡ ከሲዲው በተጨማሪ ዘፈኖቹን እንደ ‹‹ሸክላ››፣ አማዞን፣ ሲዲቤቢ እና በመሳሰሉ የኢንተርኔት መገበያያዎች ላይ ማግኘት እንደሚቻልም ተገልጿል፡፡ የዳዊትን አልበም በማስተዋወቅ ሙሉ ሥራ ላይ የተሳተፈውና ከፍተኛ ድርሻ ያበረከተው ‹‹ኢምር አድቨርታዚንግ›› ከአብርሃም ወልዴም ሆነ ከድምፃዊ ዳዊት ጽጌ ከፍተኛ ምስጋና ተችሮታል፡፡
ዳዊትን የመሰለ ብቃት ያለው ድምፃዊ የተገኘው በባላገሩ አይዶል በመሆኑ ተቋርጦ የነበረው ይሄው አይዶል፤ በሁለት ወራት ውስጥ በድጋሚ እንደሚጀምርም አብርሃም ወልዶ ገልጾ የዳዊት ጽጌን ኦሪጂናል ሲዲ በመግዛት ለወጣቱ ድምፃዊ ያላችሁን አድናቆትና ክብር እንድትገልጹ ለኢትዮጵያዊያን በሙሉ ጥሪዬን አቀርባለሁ ብሏል - አብርሃም ወልዴ፡፡  

Read 11636 times