Saturday, 18 January 2020 13:06

ወጣቱ የፖለቲከኞች መጠቀሚያ እንዳይሆን!!

Written by  (ከአብዱራህማን አህመዲን፤ የቀድሞ የፓርላማ አባል)
Rate this item
(1 Vote)

  “ኃይል የተቀላቀለበት ፖለቲካ ከእንጭጭ አስተሳሰብና ከአውሬነት ባህሪ የሚመነጭ በመሆኑ ለሀገር እድገትና ለዜጎች ሰላማዊ ህይወት ጠንቅ ነው፡፡ ሀገራችንን ከዚህ ዓይነት ከንቱ የፖለቲካ ትርምስ በማውጣት ወደ ሰለጠነ የፖለቲካ ባህል ማሸጋገር ወቅቱ የሚጠይቀው፣ ይዋል ይዳር የማይባል ጉዳይ ነው፡፡”
           
           በዚህ ሳምንት በማቀርባት በዚች መጣጥፍ ትኩረት የማደርገው በወጣቶች ዙሪያ እንዲሆን አሰብኩ፡፡ ምክንያቴን ወደኋላ ላይ እነግራችኋለሁ፡፡ አንዳንድ ሰዎች ወጣቱን ትውልድ ሲወቅሱ እሰማለሁ፡፡ እነሱ እንዲሆን የሚፈልጉትን ሊሆን ባለመቻሉና እንዲያደርግ የሚፈልጉትን ሲያደርግ ባለመታየቱ ሲከሱት አደምጣለሁ፡፡ ግን ያልሰጡትን ከየት ያምጣው? ያላስተማሩትን ከየት ያግኘው? ወጣቶች በስነ-ምግባርና በሞራል ህግጋት ተኮትኩተው የሚያድጉበትን ሃይማኖታዊ ተቋማት፣ በኮሙኒስታዊ መንሽ እያበራዬ ያፈራረሳቸው ማን ነው? ቀዳሚው ትውልድ አይደለም እንዴ? በዚህ ረገድ ያለውን ጉድፍና ጥቀርሻ ለመጥረግ መስተዋቱን ወደ ራሳችን ማዞሩ መልካም ነው፡፡
በመሰረቱ ወጣትነት ኃጢያትም እርግማንም አይደለም፡፡ ወጣትነት እያንዳንዱ የሰው ልጅ በህይወት ዘመኑ የሚያልፍበት የእድሜ ደረጃ፣ የህይወት መሰላል፣ የእድገት እርከን ነው፡፡ ይህ የእድሜ እርከን በአንድ ማህበረሰብ ወይም በአንድ ሀገር የኢኮኖሚ፣ የፖለቲካና የማህበራዊ ጉዳይ ላይ ያለው ሚና የላቀ ነው፡፡ በዚህም ምክንያት የሀገራችን ወጣቶች በሀገራቸው ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ጉዳዮች ዙሪያ መጠነ ሰፊ ተሳትፎ ሲያደርጉ ነበር፣ አሁንም እያደረጉ ነው፡፡ ይህንን ማድረጋቸው የሚነቀፍም የሚኮነንም አይደለም፡፡ እንዲያውም እንዲህ ያለው ተሳትፎ እንደ ዜጋ ተገቢም አስፈላጊም ነው፡፡
ብዙዎቻችን እንደምንገነዘበው፤ በሀገራችን ረጅም የመንግስትነት ታሪካችን ውስጥ ሰላማዊ የስልጣን ሽግግር በተግባር የታየበት ሁኔታ አልነበረም፡፡ ይልቁንም በየዘመኑ የተነሱ የስልጣን ተፋላሚዎችና የፖለቲካ ኃይሎች በተለይም ወጣቱን ትውልድ በጀሌነት በማሰለፍ ባልተቋረጡ ጦርነቶች በመማገድ ህልቆ መሳፍርት የሌለው አምራችና ተመራማሪ ዜጋ በዱር በገደል ወድቆ እንዲቀር ምክንያት ሆነዋል፡፡ ይህ ሁኔታ ዛሬም በተለያዩ ስልቶች እንደቀጠለ ነው፡፡ ይህ የታሪካችን መጥፎ ገጽታ ደግሞ ለአጠቃላይ ማህበራዊ፣ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ህይወታችን ኋላ ቀር መሆንና እንደ ግመል ሽንት ወደ ኋላ የመመለስ ጉዞ ዋና ተጠቃሽ ምክንያት ከመሆን አልፎ፤ ዛሬም በሀገራችን ስር ሰዶ ለሚገኘው ስልጣንን በኃይል የመንጠቅ ፍላጎት፣ የጥላቻ ፖለቲካና የመናናቅ ዝንባሌ መሰረት መሆኑን መገንዘብ ይቻላል:: እንዲህ ዓይነቱ ፋይዳ ቢስ ሁኔታ እርምት ወይም መሻሻል ሳይደረግበት፣ ከትውልድ ወደ ትውልድ መሸጋገሩ አላንስ ብሎ አዲሱ የስልጣን አያያዝ መንገድ ወደ ተረኛነት ደረጃ የመሸጋገሩ አስተሳሰብና ልባዊ ፍላጎት አሳሳቢ ብቻ ሳይሆን አስፈሪ መሆኑን ማመዛዘን የሚችል ኅሊና ያለው ሁሉ የሚገነዘበው ሀቅ ነው፡፡
ይህ ሁኔታ አንድ ስፍራ ላይ እንዲቆም ካልተደረገ፣ ነገ ኢትዮጵያ የምትባል ሀገር የመኖሯ ሁኔታ ዋስትና የለውም፡፡ በጠመንጃ ኃይልና በጎሳ ፖለቲካ አማካይነት ስልጣንን ጨብጦ የነበረው ህወሓት መራሹ ኢህአዴግ ዳግም ላይመለስ የተንኮታኮተ ቢሆንም፤ ለ25 ዓመታት የዘረጋው የአሰራር ስርዓትና በሰዎች አእምሮ ውስጥ የጠቀጠቀው የዘረኝነት መንፈስ በአንድ ጊዜ ከነሰንኮፉ ይነቀላል ብሎ ማሰብ አስቸጋሪ ነው፡፡
የኃይል፣ የጥላቻ፣ የአድሎና የመድሎ፣ የመናናቅና የኩርፊያ ፖለቲካ አጠቃላይ ጉዞ ወደ ሽኩቻ፣ ከፍ ሲልም ወደ ግድያና ግብግብ የሚያመራ አውዳሚ መንገድ በመሆኑ፣ ህሊና ያለው ዜጋ ሁሉ ሊያወግዘው የሚገባ ነው፡፡ ማውገዝ ብቻ ሳይሆን የኃይልና የጥላቻ ፖለቲካ ወደ ሰላማዊ መቻቻልና መደማመጥ የተሞላበት የውይይትና የክርክር ፖለቲካ እንዲቀየር ግፊት ሊደረግ ይገባል፡፡ አበው “ሳይቃጠል በቅጠል” እንዲሉ ያንቆረዘዘው የጎሣ ፖለቲካና የተረገዘው ቂም ሳይወለድና ሁሉንም ጠርጎ ሳይወስድ ገደብ ሊበጅለት ይገባል፡፡
ኃይል የተቀላቀለበት ፖለቲካ ከእንጭጭ አስተሳሰብና ከአውሬነት ባህሪ የሚመነጭ በመሆኑ ለሀገር እድገትና ለዜጎች ሰላማዊ ህይወት ጠንቅ ነው፡፡ ሀገራችንን ከዚህ ዓይነት ከንቱ የፖለቲካ ትርምስ በማውጣት ወደ ሰለጠነ የፖለቲካ ባህል ማሸጋገር ወቅቱ የሚጠይቀው፣ ይዋል ይዳር የማይባል ጉዳይ ነው፡፡ ብዙዎች እንደሚስማሙት፤ ስልጣን ርስተ-ጉልት አይደለም፡፡ ስልጣን በምርጫ ስርዓት ህዝብ ይሆነኛል ላለው የፖለቲካ ፓርቲ የሚሰጠው፤ አይሆነኝም ላለው የሚነፍገው፣ በጊዜ የተገደበ የአደራ ኃላፊነት መሆኑም ልብ ሊባል ይገባል:: ከዚሁ ጋር አያይዘን መገንዘብ የሚገባን ቁም ነገር፤ የፖለቲካ ኃይሎች የህዝብን ስልጣን በአደራ ለመያዝ ጥረት የማድረጋቸውን ያህል የስልጣን ጊዜያቸውን ሲያጠናቅቁና ይበቃችኋል አስረክቡ ሲባሉ፣ ሽንፈታቸውን ተቀብለው በፀጋ የማስረከብ ባህልንም ሊያዳብሩ ይገባል፡፡
ወደፊት ለመሄድ ወደ ኋላ ማፈግፈግ አስፈላጊ ነው፡፡ ይህም ማለት ስለ መጪው ጊዜ ለመናገር ስላለፈው ማስታወስ ተገቢ ነው፡፡ ዛሬ ላይ ሆነን ትናንትን ማስታወስ፣ ለዛሬ ትልማችንና ለነገ ግባችን መነሻ መሰረት መሆኑ የሚያከራክር አይደለም፡፡ እንዲህ ያለው አስተውሎት የታከለበት አካሄድ አስፈላጊም ጠቃሚም ነው:: ከዚህ አኳያ የሀገራችን ወጣቶች ላለፉት 60 ዓመታት፣ የፖለቲከኞች ጠመንጃ ያዥና ተዋጊ፣ ካድሬና መፈክር አስተጋቢ፣ በየሰልፉ ባንዲራና ባነር ተሸካሚ በመሆን መጠቀሚያ እንደነበሩ መናገር ሊካድ የማይችል ሀቅ ነው፡፡ በዚህም ሂደት በተለይም በ1960ዎቹ በነበረው ያልሰከነ የፖለቲካ ቱማታ ይህቺ ሀገር ምንጊዜም ልትተካው ያልቻለቺውን ትውልድ አጥታለች፡፡ በዚህም ምክንያት ሀገርም ህዝብም የከፋ ኪሣራ ደርሶባቸዋል፡፡ እስከ አሁን ድረስ ሊስተካከል ያልቻለ ክፍተትም ተፈጥሯል፡፡
ይህንን ሁኔታ ያነሳሁት ያለ ምክንያት አይደለም፡፡ እንደሚታወቀው ይህ ዓመት የምርጫ ዓመት ነው፡፡ ይህ ዓመት ለኢትዮጵያና ለኢትዮጵያውያን ፈተና ነው፡፡ ከሀገሪቱ ህዝብ ውስጥ 60 በመቶ የሚሆነው እድሜው ከ30 ዓመት በታች የሆነ ወጣት ነው፡፡ በምርጫው ሂደት በመራጭነትም በምርጫ ቀስቃሺነትም በምርጫ ታዛቢነትም የሚሳተፉት በዋናነት ወጣቶች እንደሚሆኑ የሚጠበቅ ነው፡፡ የሀገሪቱ ፖለቲከኞች እነዚህን የለውጥ ኃይል የሆኑ ወጣቶችን ለፖለቲካ መጠቀሚያነት የሚፈልጓቸው መሆኑም ጥርጥር የለውም:: “ይህ ዓመት ለኢትዮጵያና ለኢትዮጵያውያን ፈተና ነው” ያልኩት በዚህ ምክንያት ነው፡፡ ይህንን ፈተና በብልሃት ለማለፍ ጥረት ማድረግ የእያንዳንዱ ዜጋ ኃላፊነት ነው፡፡ በተለይም ወጣቶች ካለፉ ትውልዶች ስህተቶች በመማር የፖለቲከኞች መጠቀሚያ ላለመሆን ብርቱ ጥንቃቄ ማድረግ ይገባቸዋል፡፡
 ጸሐፊውን Email: This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it. ማግኘት ይቻላል፡፡

Read 1154 times