Saturday, 18 January 2020 13:02

የሚያብረቀርቅ ሁሉ ወርቅ አይደለም!

Written by 
Rate this item
(6 votes)

  ከዕለታት አንድ ቀን አንድ “እናትህ ልትሞት ነው” ተብሎ የተነገረው ወጣት በጣም ከመፍራቱ የተነሳ እቤቱ አካባቢ ወዳለ ተራራ ላይ ይወጣል፡፡ ከዚያም ሁሌ ጠዋት ጠዋት በተራራው አናት ብቅ እያለ፤
“ያች እናቴ ሞተች ወይ?”
“አልሞቱም፤ ገና እያጣጣሩ ነው” ይሉታል፡፡
“ከረመች በላታ!” ይላል፡፡
ሌላም ቀን ስለእናቱ ይሄንኑ ጥያቄ ይጠይቃል፡፡
“አልሞቱም ገና እያጣጣሩ ናቸው” ይሉታል
“ከረመች በላታ!” ይላል፡፡
አንድ ቀን ጠዋት የማይቀረው ሞት የእናቲቱን ነብስ ይዟት ሄደ፡፡
ያ ልጅ፤ “ያቺ እናቴ እንዴት ሆነች?” ሲል ይጠይቃል፤ እንደተለመደው፡፡
ሰውም ማረፏን ይነግረዋል፡፡
ልጁም አሁንም ራቅ ያለ ቦታ ሆኖ ሁኔታውን ይከታተላል፡፡ እድሩ የሚያደርገውን እየጠበቀ ነው፡፡
እድሩም ልጁ በችግር ምክንያት እናቱን ለመቅበር እንዳልቻለ ገብቶት ከዕድሩ የተጠራቀመ ገንዘብ ተወስዶ ቀን ሲሞላለት እንዲተካ ወሰነ፡፡
በዚህ መሠረትም ጃኖ ተገዝቶ በጃኖ ተከፍነው እናት ወደ ቀብር ሲወሰዱ፤ ልጁ የሚያሰላስለው የጃኖውን ዕዳ እንዴት እንደሚከፍል ነበር፡፡
ሲያለቅስም እንደሚከተለው እያለ ግጥም እየደረደረ ነበር፡-
“ለብሳ እማታውቀውን የሰው ጃኖ ለብሳ
ተመለሺስ ቢሏት በየት ተመልሳ
ፍሳሽ እናቴ ፍሰሽ
እኔን በእዳ ለውሰሽ!!”
***
ሁላችን የአገር ባለዕዳዎች ነን፡፡ እድሮች ችግሮቻችንን ለማቃለል የተሰናዱ ማህበራዊ የኢኮኖሚ አቅሞቻችን ናቸው፡፡ የተጐዳና ለሞት የተዳረገ ቢኖር በአገር ወግ ይቀብራሉ:: እህል ውሃ ያቃምሳሉ፡፡ ዘመድ የሞተበትን ሰው ያጽናናሉ፡፡ ለእንግዶች የሚቀመስ ያቀርባሉ፡፡ ማህበራዊ ድርና ማጉ መልኩንና ወዙን ሳይለቅ ህይወት ባህሉን እንደጠበቀች እንድትቀጥል፣ የተሻለውን ሁሉ ያደርጋሉ፡፡
የመተሳሰብ፣ የመረዳዳት፣ አንተ ትብስ እኔ የመባባል፣ ለችግሮች ሁሉ ቀድሞ የመድረስ ባህልና ልማድ፣ አገርን ከየትኛውም ድቀት ያድናል፡፡ ነገ ከነገ ወዲያ ብድር በምድር የምንባባልበት፣ ወንድም አለኝ፣ እህት አለኝ፣ ወገን አለኝ የምንልበት ጠንካራ የማህበረሰብ ትሥሥር እንዳለን ምንጊዜም አንረሳም፡፡ ዘመን ያበሰለው ባህልና ልማድ ዐይን ይከፍታል፡፡ ነገን በብሩህ መነጽር ያሳያል፡፡ ዛሬ ከእጃችን ሳያመልጥ እንጠቀምበት ዘንድ ያፀናናል፡፡ ያተባናል፡፡ ያጠነክረናል፡፡
የምናውቀውን ፀጋ ከነተስፋው እንድንገለገልበት ምንነቱን የመገንዘብ አስተውሎት ያስፈልገናል፡፡
እዚህ ላይ የአንድን ታዋቂ ገጣሚ የሮበርት ብራውንን አባባል ብንጠቅስ ስለዕውቀት ያለንን ብስለት ያጠነክርልናል፡-
“ደግሞ ማወቅ ማለት
ከውጪ ያለውን ሄዶ ከመፈለግ
ከውስጥ የበራውን እንዲወጣ ማድረግ”
የአገር የውስጥ ብርሃን ኃያል ነው፡፡ ነገ አዋቂና የነቁ የበቁ ልጆች እንዲኖሩን ዛሬ አስተሳሰባቸው የታነፀ፣ የተጠመቀና የተባረከ፤ ትውልድ መኮትኮት ያስፈልጋል፡፡ ብርሃን ስናሳየው ጨለማ የማያይ፣ ልምላሜን ስናሳየው በረሃ ውስጥ የማይቀር፣ አሸዋ የማይውጠው ባለመንፈስ ፀጋ ትውልድ እናፍራ፡፡ ዐይናችን ይከፈት፡፡ እጆቻችን ለሥራ ይዘርጉ፡፡ ከሌሎች የምንጠብቀውን ትልቁ ተስፋችን ነው ከማለት የራሳችን ትጋት ምን ያህል ቢጠናከር፣ እንዴትስ በወግ ቢያድግ የሁላችን ጠበል፣ የሁላችን ጥምቀት ይሆናል ብለን ልባችን ንፁህ ይሁን፡፡
የጥምቀት በዓል፣ ለክርስትና ዕምነት ተከታዮች የሞቀና የተባረከ ይሁን!
የደመቀና ያሸበረቀ የህይወት መንገድ ሁሉ የፍፃሜ መዳረሻችንን ያሳያል ብለን አናስብ:: ምክንያቱም “የሚያብረቀርቅ ሁሉ ወርቅ አይደለም”ና!

Read 13437 times