Saturday, 18 January 2020 12:58

ከምርጫ በኋላ ህይወት መቀጠል አለበት!

Written by  ኤልያስ
Rate this item
(6 votes)

 • “ለፖለቲከኞች ድምፃችንን እንጂ ነፍሳችንን አንሰጥም”
          • እንኳ በምርጫ - በጦርነትም መሞት ቀርቷል!
           
        ወዳጆቼ፤ ከዛሬ ጀምሮ በምርጫ ዙሪያ ትንሽ ትንሽ ማውጋት መጀመር ያለብን ይመስለኛል፡፡  ለምን መሰላችሁ? ሰሞኑን አንዳንድ ተቃዋሚዎች የምርጫ ቅስቀሳ ጀምረዋል፡፡ እናም ቶሎ ቶሎ  ደንብና መመሪያዎች… እንዲሁም ማኒፌስቶ ማዘጋጀት ያስፈልጉናል፡፡ (ለኛ ለመራጮች!) አያችሁ… ፖለቲከኞቹ ብቻ ሳይሆኑ እኛም መራጮቹ፤ መረጃና ዕውቀት ላይ ተመስርተን ነው ድምጽ መስጠት ያለብን፡፡
በዘንድሮ ምርጫ፣ የአንድም ዜጋ ህይወት መጥፋት የለበትም!!  ፖለቲከኞቻችን ምርጫ አሸንፈው ስልጣን  እንዲይዙ ወይም ቤተ መንግስት እንዲገቡልን እንሻለን፡፡ ነገር ግን (ያውም ፊሽካ ላይነፋ!) እንደ ድሮው ህይወታችንን አንሰጥም፡፡ ድምጻችንን እንጂ!  (ከንቱ መስዋዕትነት ነው!)
ወዳጆቼ፤ እስከ ዛሬ ብዙ ብዙ ተሸውደናል:: በምርጫ ማግስት፣ ተቃዋሚዎችና መንግስት ከምርጫ መጭበርበር ጋር ተያይዞ በሚፈጥሩት ውዝግብ፣ ስንቱ ነው  ህይወቱን ያጣው፡፡ ስንቱ ነው ዘብጥያ የተወረወረው፡፡ ስንቱ ነው ለስደት የተዳረገው፡፡ ስንቱ ነው የአካል ጉዳት የደረሰበት፡፡ ተቃዋሚዎችም ሆኑ መንግስት (በተለይ የትላንቱ!) ለሥልጣናቸው እንጂ ለዜጎች ህይወት ደንታ እንደሌላቸው አሳምረን እናውቃለን፡፡ ለዚያ እኮ ነው… ምርጫ ተጭበረበረ፣ እያሉ ደጋፊዎቻቸውን  አደባባይ ሲጠሩ ምንም የማይሰማቸው፡፡ (መንግስት እንደሚገድል እያወቁ እኮ ነው!)
ተቃዋሚዎች “ድምጽህ ተዘረፈ” ብለው ህዝብን አደባባይ ይጠራሉ፤ መንግስት ደግሞ ልዩ የአድማ በታኝ ፖሊስ መድቦ የወጣውን ሁሉ ይቀነድበዋል፡፡ (ደመ ከልብ ሆኖ ይቀራል!) ይሄ በጦቢያ ብቻ ሳይሆን በመላው አፍሪካ ተመሳሳይ ነው፡፡ የአፍሪካ ምርጫ ምሱ፤ የህዝብ ደም ነው የሚመስለው፡፡ (የአሜሪካ ምርጫ ምሱ፤ ዲሞክራሲ ነው!) እናላችሁ -- ምርጫ ይካሄዳል፣ የምርጫ ውጤት በተሰማ ማግስት፤ እነዚያ ድምጽ የሰጡ ዜጎች በገፍ አደባባይ ይወጡና በመንግስት የጸጥታ ሃይል ‹ዲሊት› ይደረጋሉ:: በሁለቱ የሥልጣን ሽኩቻ ታዲያ በቅጡ ያልኖረ ምስኪን ድሃ ህይወቱን ያጣል፡፡ በአጭር ይቀጫል!! ከምርጫ በኋላ  ቀውስ፣ እስር፣ ስደት፣ ሞት፣… ፈጽሞ መፍቀድ የለብንም፡፡  
ሌላው ደግሞ ምን መሰላችሁ? ፖለቲከኞች ምርጫውን የሞት ሽረት ጉዳይ ሲያደርጉት… በጄ አለማለት ነው ነው (ዜጐችን ለመስዋዕትነት እያዘጋጁ ነው!) እናም… ዘንድሮ የሚደረገውን ምርጫ መቁጠር ያለብን… እንደ “ፖለቲከኞች አይዶል” ነው:: “የፓርቲዎች አይዶል” ልትሉትም ትችላለችሁ:: እንደ ተሰጥኦ ውድድርም፤ ፉክክር የጦፈበትና አዝናኝ ሊሆን ይገባል፡፡
ፍርሃትና ጭንቀት ሊፈጥርብን አይገባም:: ይህን የፖለቲከኞች አይዶል የሚዳኙት ደግሞ “ህዝብ” በሚል የወል ስም የሚጠሩ… በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ዜጐች ናቸው፡፡ እኒህ ዳኞች በምርጫ ቅስቀሳ ወቅት ፖለቲከኞች ወይም የፖለቲካ ፓርቲዎች በሚያቀርቡት  ፖሊሲዎች፣ የሥራ ፈጠራ ዕቅድ፣ ርዕዮተ ዓለም (አብዮታዊ ዲሞክራሲ፣ ካፒታሊዝም፣ መደመር፣ ሶሻሊዝም፣ ብሔርተኝነት ወዘተ… እንደማለት…)  የድህነት ቅነሳ ስትራቴጂ፤ የኑሮ ዋስትና ትልም፣ ወዘተ ላይ ተመስርተው ለመረጡት ድምጽ ይሰጣሉ፡፡  አሸናፊዎችን ይመርጣሉ፡፡ በወል ሳይሆን ማለት ነው!  በምርጫ ካርዳቸው፡፡ በምርጫ ካርዳቸው! አሸናፊዎች ሥልጣን ይሸለማሉ:: ሽልማቱ ሙሉ አገር የማስተዳደር ሥልጣን ሊሆን ይችላል፡፡ (የፌደራል መንግስት ወይም ገዢ ፓርቲ በመሆን!) የተወሰኑ ከተሞችን አሸንፎ ማስተዳደርም ሊሆን ይችላል፡፡ (በ97 ቅንጅት አዲስ አበባን እንዳሸነፈው!) የተወሰኑ ወረዳዎችን ማስተዳደርም ይሆናል፡፡ እንደየተወዳደሩበት ዘርፍ ማለት ነው፡፡
በነገራችን ላይ… ብዙዎቻችን በተለምዶ የፖለቲከኞችን አይዶል (ምርጫን) ዳኛነት የሚሰጠው ምርጫ ቦርድ ሊመስለን ይችላል፡፡ ግን አይደለም፡፡ ቦርዱ አሸናፊውንና ተሸናፊውን የመወሰን ሥልጣን የለውም - በመርህ ደረጃ ማለቴ ነው፡፡ የውጤት ነጥብም አይሰጥም፡፡ አሸናፊውን የመወሰን ሥልጣን (የውድድር ዳኝነት ማለት ነው!) የተሰጠው ለህዝቡ ብቻ ነው፡፡ (ለእኛ ማለት ነው!) አዎ የምርጫው ዳኛ እኛ ነን - (ህዝብ)፡፡ ምርጫ ቦርድስ?...  ልትሉኝ ትችላላችሁ፡፡
 ምርጫውን ከሀ እስከ ፐ የሚያዘጋጅና የሚመራው እሱ ነው፡፡  የዳኝነት ሚና ግን የለውም:: መቼም ህዝቡ የሰጠውን ነጥብ (ድምጽ) መቁጠር ዳኛ አያሰኝም…አይደል!፡፡ (ቆጣሪ እንጂ!) እሱ ነው፡፡
ወዳጆቼ፡- እኔ የማወራው ባለፉት ዓመታት በአገራችን ስለተካሄዱ… ቀውስና ጥፋቶችን  ያስከተሉ የሃሰት (fake) ምርጫዎች አይደለም፡፡ የማወራው… በማጭበርበር ውዝግብ ስለሚጠናቀቁ ምርጫዎችም አይደለም፡፡ የማወራው… ህዝቡም ሆነ ፓርቲዎች እምነታቸውን ያልጣሉበት አወዛጋቢ የምርጫ ቦርድ  ስለሚያካሂዳቸው ምርጫዎች እንዳልሆነም እወቁልኝ፡፡ የማወራው… እስከ ዛሬ በተግባር ከምናውቃቸው የ “ኢህአዴግ ነፍሴ” ምርጫዎች በእጅጉ የተለየ ስለሆነ ምርጫ ነው:: እኔ የማወራው… ብዙዎች በተስፋና በስጋት እየጠበቁት ስላለው መጪው የነሐሴ ወር ምርጫ ነው፡፡ የማወራው… በቀድሞ የተቃዋሚ ፓርቲ መሪና የሰብአዊ መብት ታጋይ፣ በዳኛ ብርቱካን ሚደቅሳ፤ ዘንድሮ ስለሚካሄደው  ሰልጠን ያለ ምርጫ ነው፡፡ የማወራው… ጠ/ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ደጋግመው “ነፃ፣ -ፍትሃዊና ዲሞክራሲያዊ እንደሚሆን ቃል ስለገቡለት ምርጫ ነው፡፡ የማወራው… ገዢው ፓርቲ በታሪኩ ለመጀመሪያ ጊዜ “ተቃዋሚዎች ቢያሸንፉ ሥልጣኔን በደስታ አስረክባለሁ” ሲል የቅድምያ ቃል ስለሰጠበት  የ2012 ምርጫ ነው፡፡ እኔ የማወራው… በምርጫ መቃረቢያ ላይ ፖለቲከኞችና ጋዜጠኞች እንደማይታሰሩና እንደማይዋከቡ ተስፋ ስለተጣለበት አገራዊ ምርጫ ነው፡፡  የማወራው… “የምርጫው ሂደት ነፃና ፍትሃዊ እስከሆነ ድረስ ባናሸንፍም እንኳን እንደ ትልቅ ድል እንቆጥረዋለን” የሚሉ ተቃዋሚ ፓርቲዎች (በጣት የሚቆጠሩ ቢሆኑም!) በተፈጠሩበት ታሪካዊ ወቅት ላይ ስለሚካሄደው የጦቢያችን ምርጫ ነው፡፡
ወዳጆቼ፡- ይሄን ምርጫ ነው እንግዲህ የፖለቲከኞች ወይም የፓርቲዎች አይዶል የምለው… እንጂማ ከዚህ ቀደም የተካሄዱትን አምስት አገራዊ ምርጫዎች ፈጽሞ አይደለም፡፡ (እንዴት ይሆናል? ተወዳዳሪውም… ዳኛውም …ቆጣሪውም ተቆጣጣሪውም አወዳዳሪውም…አንድ አካል የሆነበት ምርጫማ እንዴት ተብሎ አይዶል ሊሆን ይችላል፡፡ (ፌክ ምርጫ እንጂ!)
ወዳጆቼ፡- አንድ ነገር ልብ እንድትሉልኝ እሻለሁ::
እኔና እናንተ መጪውን ምርጫ… ከዚህ ቀደሙ የተለየ ማድረግ እንችላለን፡፡ ምርጫው በኛ ቁጥጥር ሥር እንጂ በፖለቲከኞች ቁጥጥር ሥር ፈጽሞ ሊሆን አይገባም፡፡ እስከ ዛሬ ነገር የተበላሸው ሁሉን ነገር ለፖለቲከኞች አስረክበን በመቀመጣችን ነው:: እናላችሁ… ድምጽ የምንሰጠው በጭፍን ድጋፍ አይደለም፡፡ ‹‹ያንተ ወገን ወይም ዘር ነኝ›› ስላሉም አይደለም (ኢትዮጵያዊ ሁሉ ወገናችን - ዘራችን ነው!) እናም… ምርጫውን የተለየ እናደርገዋለን! (ሞትና ቀውስ የማያስከትል ምርጫ ማለት እኮ ነው!) አያችሁ…ምርጫውን ፈጽሞ የሞት ሽረት ጉዳይ ማድረግ የለብንም፡፡ ምርጫውን መቁጠር ያለብን እንደ “አይዶል” ነው - ፓርቲዎች የፖለቲካ ተሰጥኦዋቸውን አሳይተው እንደሚያሸንፉበትና እንደሚሸነፉበት ውድድር! አራት ነጥብ፡፡ ከዚያ በላይ አይደለም! ዜጐች የሚሞቱበትና የሚሰደዱበት፣ በአገሪቱ ላይ ተጨማሪ ቀውስና ጥፋት የሚየስከትል፣ እንደ 97 ወደ ኋላ የምንሸራተትበት… እንዲሆን ፈጽሞ መፍቀድ የለብንም፡፡ ከአይዶል ውድድር በኋላ (ማንም ያሸንፍ ማንም!) የሰው ህይወት ጠፍቶና ቀውስ ተፈጥሮ (በፍፁም!) እንኳን በኛ አገር አይዶል ይቅርና… ሚሊዮን ዶላር በሚያሸልመው የአሜሪካን አይዶልም ቢሆን ቀውስ ተፈጥሮ አያውቅም፡፡ ስኬትና ድል፤ ዕድገትና ብልጽግና እንጂ! ሁሌም ምርጫውን የሞት ሽረት ጉዳይ የሚያደርጉት ፖለቲከኞች ናቸው - ሥልጣን ለመያዝና ቤተ መንግስት ለመግባት ሲሉ የማያደርጉት ነገር የለም:: ይዋሻሉ፣ ታሪክ እንደ ተረት ይፈበረካሉ፣ ከፋፋይ ትርክቶችን ያስተጋባሉ:: የተበድለሃል - ተጨቁነሃል የኋላ ታሪክ ይሰብካሉ፣ ያለፈውን አገዛዝ ይረግማሉ - ይወቅሳሉ፡፡ ህዝብን በዘርና በሃይማኖት ያቧድናሉ ብዙ ብዙ ይቦተልካሉ:: እኒህን ሁሉ አድርገው በምርጫው ካላሸነፉ ታዲያ “ተጭበረበረ” ብለው አመጽ በመጥራት ለህዝቡ ሞት ይደግሳሉ:: እነሱ ቤተመንግስት ስላልገቡ ዜጐች የህይወት መስዋዕትነት ይከፍላሉ፡፡ ይታሰራሉ፡፡ ለስደት ይዳረጋሉ፡፡ ህይወቱ ይመሳቀላል፡፡
ወዳጆቼ፤ የዘንድሮው ምርጫ የሞትና የውድቀት ድግሰ ሳይሆን አዝናኝ አይዶል ነው መሆን ያለበት፡፡
ከምርጫው በኋላም ህይወት መቀጠል አለበት (ያውም ከቀድሞው የላቀና የተሻለ ህይወት!)፡፡ ወደድንም ጠላንም… በዚህ ጉዳይ ላይ መተማመን ይኖርብናል፡፡ ስምምነት ላይ መድረስም ይገባናል፡፡
እውነቴን ነው የምላችሁ…ከምርጫው በኋላ ህይወት ሳይሸራረፍና ሳይቀናነስ መቀጠል አለበት:: ከምርጫው በኋላ ህይወት በተሻለ መንገድ እንደሚቀጥል ሳናረጋግጥ የነሐሴው ምርጫ ፈጽሞ መካሄድ የለበትም፡፡ (ጽኑ አቋም ነው!)
ዜጐች የሚሞቱ ከሆነ፣ ጋዜጠኞችና ፖለቲከኞች ወህኒ ከታጐሩ ወይም ከተሰደዱ ፍርሃትና ስጋት ከተፈጠረ፣ የተስፋ ጭላንጭል ከተዳፈነ፣ ቀውስና ሁከት ከተከሰተ…ለምንድን ነው ምርጫ የሚደረገው? ለሞትና ኪሳራ? ለስደትና አፈና?! ለቀውስና ዕልቂት?! ፈጽሞ አይሞከርም! ከምሬ ነው የምላችሁ…ለተጨማሪ የዜጐች ሞትና ፖለቲካዊ ቀውስ…  ምርጫው  ፈጽሞ መካሄድ የለበትም:: እስቲ በዘንድሮ ምርጫ እንኳን… በብልጣብልጥ ፖለቲከኞች ከመሸወድ ራሳችንን እንታደግ፡፡ (ሞትና ዕልቂት ይብቃን!) ምርጫው ፈጽሞ በዜጐች የህይወት መስዋዕትነት መካሄድ የለበትም፡፡
 ምርጫው ፈጽሞ የሞትና ሽረት ጉዳይ መሆን የለበትም፡፡ የምርጫው ሂደትም ሆነ ውጤት ምንም ይሁን ምንም ዜጐች እንዲሞቱ ጨርሶ መፍቀድ አይገባም፡፡ በምርጫው ገዢው ፓርቲ ብልጽግና ያሸንፍ ወይም ተቃዋሚው የእነ ጀዋር ኦፌኮ ወይም ሌላ… ዜጐች ከቀድሞው የበለጠና የተሻለ መኖር እንጂ ፈጽሞ መሞት አይገባቸውም፡፡ (ድምጽ በሰጡ!)፡፡
መራጭ ወዳጆቼ፡- ከምርጫው በኋላም ህይወት መቀጠል አለበት፡፡ ህይወት መጨመር..ህይወት መሻሻል… ህይወት መላቅ… እንጂ ህይወት መቀነስ…ህይወት መጥፋት… ህይወት መኮሰስ… ህይወት መጨለም… ፈፅሞ የለበትም፡፡
ይሄውላችሁ ምርጫው በተቀመጠለት የጊዜ ሰሌዳ ካልተደረገ… ሞተን እንገኛለን የሚሉ ፖለቲከኞችና ፓርቲዎችን አትመኗቸው (ምን ቸገራቸው እነሱ ሞተው አያውቁ!) ምርጫው ከተራዘመ አገር ይፈርሳል ባዮችንም ነገሬ ብላችሁ አታዳምጧቸው (ሀገር ሲያፈርሱ እኮ ነው የኖሩት!) እውነቱን ልንገራችሁ አይደል በዜጐች ህይወት ለመቆመር ለተዘጋጁ ፖለቲከኞች ህይወት አንገብርም፡፡ ለምርጫው ድምፃችንን እንጂ ደማችንን አንሰጥም (ደም የምንሰጠው ለቀይ መስቀል ነው!) ለፖለቲከኞች ሥልጣን ድምፃችን እንጂ ህይወታችንን አንሰጥም፡፡ (ህይወታችንን የምንሰጠው ለእናት አገራችን ብቻ ነው - እንደ አባቶቻችን!)
እናላችሁ… ስልጣን የተጠሙ ፖለቲከኞች ህይወት አንገብርም፡፡ ለምርጫው ድምፃችንን እንጂ ደማችንን አንሰጥም! (ደም የምንሰጠው ለቀይ መስቀል ነው!)


Read 3628 times