Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Saturday, 23 June 2012 11:14

የልመና ክብር፤ የሥራ ውርደት የለውም

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

ህይወትን በአደራ ተቀብሎ በአደራ የመመለሻ ሙያ ነው ይላሉ - ባለሙያዎቹ ስለ አኒስተዚያ ሙያ ሲናገሩ፡፡ የማደንዘዣ ሰጪ ባለሙያ ወይም የሰመመን ሰጪ ባለሙያ የሚሉት ስያሜዎች ሙያውን የሚገልፁ ስላልሆኑ፤ ሙያውን የአንስቴዢያ ሙያ፣ ማህበራቸውን ደግሞ የአንስቴቲስቶች ማህበር ብለውታል፡፡ ከ300 በላይ አባላት ያሉት ማህበሩ፤ ትናንት አመታዊ ጉባኤውንና ስምንተኛ ዙር የሙያ ኮንፈረንሱን በግዮን ሆቴል ጀምሯል፡፡ በዚሁ ፕሮግራም ላይም፤ ለሙያው እድገት ከፍተኛ አስተዋፅኦ ላደረገው፤ እንዲሁም በድንገተኛ አደጋ ለተጎዱ ታማሚዎች ፈጥኖ በመድረስ የነፍስ አድን አገልግሎት በመስጠት ላይ ለሚገኘው የ”ጠብታ አምቡላንስ ፕሪ ሆስፒታል ሜዲካል ሰርቪስ” እውቅና ሰጥቷል፡፡ “በድንገተኛ አደጋ ወቅት በተለያዩ የህክምና ሙያዎች በመታገዝ ህመምተኛው በህይወት ወደ ሆስፒታል እንዲደርስ በማድረግ ረገድ ጠብታ አምቡላንስ ከፍተኛ አስተዋፅኦ እያደረገ ነው ይህንን ተግባር ከግምት ውስጥ በማስገባትና ድርጅቱ ለህብረተሰቡ እየሰጠ የሚገኘውን አገልግሎት በመገንዘብ፣ ማህበሩ ለድርጅቱ እውቅና ሰጥቶታል” (የኢትዮጵያ አንስቴቲስቶች ማህበር ፕሬዚዳንት አቶ ልዑል አየሁ የተናገሩት)፡፡

የጠብታ አምቡላንስ መሥራችና ባለቤት አቶ ክብረት አበበ፤ ለ17 አመታት በአንስቴዚያ ሙያ በጥቁር አንበሳና በተለያዩ ሆስፒታሎች ሲሰሩ ቆይተው ነው፤ የዛሬ ሶስት አመት ፈጥኖ ደራሽ ህይወት አድን የአምቡላንስ አገልግሎት የጀመሩት። በስራ አለም የገጠሟቸውን ሁኔታዎች ከህይወት ፍልስፍና ጋር በማስተሳሰር ለአዲስ አድማስ በሰጡት ቃለምልልስ፤ በስዊዲን የወሰዱትን የቢዝነስ ፈጠራ ስልጠናና የካናዳ የአምቡላንስ አገልግሎትን እየጠቀሱ፤ የሁሉም ነገር ቁልፍ የስራ ክብር ነው ይላሉ።

ለስልጠና ወደ ስዊድን ሄደህ ነበር፡፡ እንዴት ነበር?

የስዊድን አለማቀፍ ተራድኦ ድርጅት (OSIDA) ለግል የቢዝነስ ዘርፍ የሚሰጠው ድጋፍ አለ፡፡ ከአምስት የቢዝነስ ዘርፎች አንድ አንድ ለመምረጥ ነው የፈለጉት፡፡ በግብርና፣ በህክምና፣ በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ፣ በማኑፋክቸሪንግና በኤሌክትሮኒክስ ዘርፎች የውድድር ማስታወቂያ አወጡ፡፡ ማስታወቂያው በንግድ ምክር ቤት በኩል ለአባላት ይሰራጫል - በኢሜይል፡፡ የመወዳደሪያ ሃሳቦችህን ገልፀህ ደብዳቤ ታስገባለህ፡፡ ከማዋዳደሪያ ነጥቦች መካከል አንዱ፤ የቢዝነስ ትርፋማነት ነው፡፡ በቢዝነስ አለም፣ ትርፋማ የሆነ ስራ ነው እያደገ ሊቀጥል የሚችለው፡፡

እንግዲህ፤ ጠብታ የአምቡላንስና የቅድመ ሆስፒታል አገልግሎት ጥሩ እየሰራ ስለቆየ፤ በዚሁ ውድድር ለመሳተፍ አስቤ ፕሮፖዛል አስገባሁ፡፡ ከወር በኋላ ለሁለተኛው ዙር ውድድር እንዳለፍኩ ተነገረኝ፡፡ በርካታ ድርጅቶች ነበሩ፡፡ አምስት ድርጅቶችን ለመምረጥ፤ ከስዊድንም ባለሙያዎች መጥተው፤ መከራከሪያ እንድናቀርብ ተጋበዝን፡ በተለይ በኛ ቢዝነስ ላይ የተነሳው ትልቁ ጥያቄ የትርፋማነት ጉዳይ ነው፡፡

በእርግጥ ድርጅታችን ትርፋማ ነው፡፡ ግን ትርፉ በሚሊዮኖች የሚቆጠር አይደለም፡፡ ትርፉ ለምን ትንሽ ሆነ? በውድድሩ ለማለፍ መከራከሪያህ ምንድነው አሉኝ፡፡ የኔ ምላሽ፤ “የሰው ህይወት እያተረፍን ነው” የሚል ነበር፡፡ የአንድ ሰው ህይወት ማትረፍ፤ በገንዘብ ሲተመን ስንት ይሆናል? ተመኑ ስንት እንደሆነ ከነገራችሁኝ፤ ስንት ሰው ሆስፒታል እንዳደረስን ስለማውቅ በጠቅላላው ምን ያህል ትርፍ እንዳገኘን እነግራችኋለሁ አልኳቸው፡፡ በየትኛው መስክ ማንኛውም ስራ ሲከናወን፤ አላማው የሰውን ህይወት ማለምለም ነው፡፡ ከሰው ህይወት የላቀ ነገር ምን አለ? በአምቡላንስ እጦት እና በኦክስጅን እጥረት የሰው ህይወት እንዳይጠፋ እየሰራን ነው፡፡ ይሄ ትልቅ ትርፍ ነው፡፡

መከራከሪያህ ፍሬ ነገር አለው፡፡ ግን የእነሱ መመዘኛም ትክክለኛ ነው፡፡ በአምቡላንስ አገልግሎት የብዙ ሰዎችን ህይወት ማትረፍ የምትችለው፣ የድርጅቱ ትርፋማነት ሲያድግና ስራው ሲስፋፋ ነው። አይደለም?

አዎ፣ ትክክል ነው፡፡ የቢዝነስ ትርፋማነት ከሌለ፤ የጀመርከው ስራ በአጭር ይቀራል፡፡ ትርፋማነት በእርግጥ የስኬት መመዘኛ መሆኑ ተገቢ ነው፡፡ ነገር ግን፤ የተለያዩ የቢዝነስ አይነቶች፤ የተለያየ የአከፋፈል አሰራር ያስፈልጋቸዋል፡፡ ለምሳሌ ለአምቡላንስ እና ለደራሽ ህክምና፣ በጣም ተስማሚ የሆነው የክፍያ ስርዓት የኢንሹራንስ አሰራር ነው፡፡ የሚጠበቅብህን አገልግሎት ትሰጣለህ፡፡ ክፍያውን ከኢንሹራንስ ትቀበላለህ፡፡ እንዲህ አይነት አሰራር ገና አለመስፋፋቱ፤ የአገልግሎቱን ትርፋማነት ይጎዳል፡፡፡ ቢሆንም ግን የኢንሹራንስ አሰራር እስኪስፋፋ ድረስ የአምቡላንስ አገልግሎት ሳንጀምር መቆየት አለብን? ይሄ አልተሟላም፤ ያ አልተሟላም እያልን ከማማረር፤ የቻልነውን ያህል እየሞከርን መስራት አለብን፡፡

ከስራ ውጭስ ምን አይነት ህይወት ሊኖርህ ይችላል? አንድ ምሳሌ ልንገርህ፡ በአሜሪካ የኢትዮጵያውያን ማህበር በኩል ለስልጠና ወደ ካናዳ ሄጄ ነበር፡፡ አንዳንድ ሰዎች፤ በዚያው ትቀራለህ ወይስ ትመለሳለህ ብለውኝ ነበር፡፡ እኔ እዚያ መቅረት የሚባል ሃሳብ አልመጣልኝም፡፡ የስልጠናው ማብቂያ ላይ፤ ዘና ለማለት በጣም ውብ የሆነ ቦታ ወሰዱኝ፡፡

የባህር ዳርቻ ነው፡፡ ውበቱን ለመግለፅ ያስቸግረኛል፡፡ በፊልም ወይም በፎቶ ብታየው እንኳ፤ እውነተኛ ነው ብለህ ለማመን ያቅትሃል፡፡ ባህርዬን የምታውቅ አንዲት ሴት፤ “እዚህ ውብ ስፍራ ውስጥ መኖር ትችላለህ” ብትባልስ አለችኝ፡፡ የአካባቢው ውበት ምንም አይወጣለትም፡፡ ግን እዚያ ቦታ መኖር አልችልም፡፡ ምን እሰራለሁ? ወንድሜ፤ የአካባቢው ነዋሪዎችኮ የሥራ ዘመናቸውን ጨርሰው፤ በፀጥታ ዘና ብለው የሚኖሩ አዛውንቶች ናቸው፡፡ አንተ እዚያ ሄደህ ያለስራ ኑር ብትባል ከሳምንት በላይ መቆየት አትችልም፡፡ ይጨንቅሃል፣ የህይወት ትርጉም ይጠፋብሃል፡፡

በውጭ አገራት፤ በርካታ ኢትዮጵያውያንን አግኝቻለሁ፡፡ “ሙሉ ደስተኛ ነኝ” ያለኝ ሰው አላገኘሁም፡፡ እውነት ለመናገር፣ ኢትዮጵያውያን እድሉን ሲያገኙ ጎበዞች ናቸው፡፡

አንድ በጣም ጎበዝ የህፃናት ሃኪም ካናዳ ውስጥ አግኝቼው ምን አለኝ መሰለህ? የተከበረ ሃኪም ነው፡፡ ቤቱ፣ መኪናውና ኑሮው የተሟላ ነው፡፡ እዚህ ኢትዮጵያ ምን አይነት የአምቡላንስ አገልግሎት እንደጀመርን ስናገር ሰምቶ፤ በጣም እንደተሰማው ነገረኝ፡፡ የሚያስቀና ስራ እየሰራችሁ ነው አለኝና እንዴት አልኩት፡፡ “እኔ’ኮ እዚህ ሊታመሙ ያሰቡ፤ ገና ያልታመሙ ህፃናትን ነው የማክመው። እናንተ ግን ትልቅ ስራ ትሰራላችሁ” አለኝ፡፡

በአገራችን ብዙ እንቅፋቶች ቢኖሩም፤ ብዙ ያልተሟሉ ነገሮች ቢኖሩም፤ ለመስራት ከመሞከርና ከመጣጣር ወደ ኋላ ማለት የለብንም፡ ኢትዮጵያውያን ደግሞ አቅጣጫው ይጠፋብን እንደሆነ እንጂ አንዴ ከታየን ጎበዞች ነን፡፡ ይሄ.... የሰውን ተስፋ የሚያስቆርጡና የሚያዳክሙ ባህሎች ባይኖሩ ኖሮማ ትልቅ ለውጥ እናይ ነበር፡፡ የትም ቦታ ብትሄድ፣ “አይቻልም” የሚልህ ሰው አታጣም፡፡ “ባትሞክር ይሻላል”፣ “የማይሆን ነገር ነው” እያለ በየአቅጣጫው ይጫንሃል፡፡ ከሶስት አመት በፊት የአምቡላንስ አገልግሎት ለመጀመር ሃሳቤን ስናገር፤ 90 በመቶ ያህል “አይሳካልህም” ነበር የሚሉኝ፡ አንዳንዱ፤ እንዳትከስር በማሰብም ነው፡፡ እያንዳንዳችን የምናተኩርበት ነገር የተለያየ ስለሆነ፤ ሃሳብህን የማይቀበሉም ይኖራሉ፡፡

አንድ አጋጣሚ ልንገርህ፡፡ ሃኪም ነው፡፡ በስራ እንተዋወቃለን - ጥቁር አንበሳ  ሆስፒታል፡፡ እሱ የስራ ቦታ ቀይሮ ለተወሰነ ጊዜ ሳንገናኝ ቆይተን አንድ ቀን መንገድ ላይ ተገናኘን፡፡ ስለ ጤንነት ስለ ስራ ስንጠያየቅ፣ ከጥቁር አንበሳ እንደለቀቅኩና የአምቡላንስ አገልግሎት እየጀመርኩ መሆኔን ነገርኩት፡፡ ብዙም አልመሰጠውም፡፡ ብዙም ሳናወራ ተለያየን፡፡

ከዚያ በኋላ የተገናኘነው በስራ ነው፡፡ የነፍሰ ጡር የቀዶ ህክምና ላይ፤ ከአንድ የህክምና ተቋም ወደ ሌላ ማዛወር የሚያስፈልግበት አጣዳፊ ሁኔታ ተፈጠረ፡፡ በቀዶ ህክምና መሃል እንዲህ አይነት ነገር ሲፈጠር አስቸጋሪ ነው፡፡ የተሟላ አገልግሎት የሚሰጥ አምቡላንስ ያስፈልጋል፡፡ የኛ አምቡላንስ ተጠርቶ ታካሚዋን በፍጥነት አድርሰን፤ ህክምናዋም ተሳካ፡፡ በሌላ ጊዜ ከሃኪሙ ጋር ቁጭ ብለን ስናወራ፤ አንድ ነገር መናገር አለብኝ አለኝ፡፡ ምንድነው አልኩት፡፡ ያኔ የአምቡላንስ አገልግሎት እየጀመርኩ ነው ያልከኝ ጊዜ ታስታውሳለህ? በጣም ነበር ያዘንኩልህ! በቃ በማይሆን ሃሳብ ባክኖ ሊቀር ነው ብዬ የአእምሮህን ጤንነት እስከ መጠራጠር ደረጃ ደርሼ ነበር አለኝ፡ አሁን ግን ያንተ ስራ ከትልቅ ችግር አዳነኝ፤ ይሄን መናዘዝ ፈልጌ ነው አለኝ፡፡

አንድ ስራ ከታየህ፤ መሞከር አለብህ፡፡ ወላጆቼ ገንዘብ አልሰጡኝም፣ ጓደኞቼ አላገዙኝም፣ ወዳጆቼ አላበረታቱኝም … እና ሌሎችም ሰበቦች መደርደር የትም አያደርስም፡፡ ትልቅ ብርታት የሚሆንህ፤ የስራ ፍቅር ነው፡፡ ስራህን በጣም ከወደድክ፤ ብዙ ችግሮችን መቋቋም ትችላለህ፡፡ እንደ ችግርም ላታያቸው ትችላለህ፡፡

ጥቁር አንበሳ ስሰራ፤ ክፍያው ትንሽ ነው ብዬ ለማሰብ ብዙም ጊዜ አልነበረኝም፡፡ ስራዬን በጣም እወዳለሁ፡፡ በአንድ ሌሊት የሰባት እናቶች ቀዶ ህክምና ሲከናወን፤ ሰባቱም ላይ በሙያዬ የሰራሁበት ጊዜ አለ፡፡  ከባድ ስራ ነው፡፡ ግን ሙያዬን እወደዋለሁ፡፡ ህይወትን ማዳን ነው፤ ሰባት ቤተሰብ ውስጥ የስንት ሰዎች ኑሮ ውስጥ መግባት እንደሆነ አስበው፡፡ ስራዬ ላይ ብዘናጋ፣ ሙያዬ ላይ ለአፍታ ቸል ብል፤ የስንት ሰዎችን ህይወት እንደማበላሽ … ምን ያህል ለማሰብም እንደሚከብድ ይታይህ፡፡ ስራህን መውደድና የሙያህን ክብር ማወቅ የራስ አክብሮት እንዲኖርህ ያደርጋል፡፡ ራሱን የሚያከብር ሰው ደግሞ፤ ሌሎችን ሰዎች እንደራሱ ያያል፡፡ ህይወታቸውን ያከብራል፡፡ ህይወታቸውን ሲያከብር ደግሞ በሙያው በትጋት ይሰራል፡፡ እርስ በርሱ የተገናኘ ነገር ነው፡፡

የአንስቴዢያ ስራ ጫና ይበዛበታል የሚሉ አሉ፡፡ እኔ ግን ስራውን ስለምወደው፤ በሙያዬ የሚጠበቅብኝን ጠንቅቄ ስለማውቅ፤ ጫና አይሆንብኝም፡፡ ጥቁር አንበሳ እያለሁ፤ በትርፍ ጊዜዬ በአምስት ሆስፒታሎች እሰራ ነበር - ህይወቴን ለማሻሻል፡፡

ስራህን በፍቅር እስከ ሰራህ ድረስ፣ የጊዜ ጉዳይ እንጂ ገንዘብ መምጣቱ አይቀርም፡፡ አንተ ብቻ ስራህን አክብረህ ስራ፡፡ በእርግጥ ገንዘብ እንደ ጎርፍ አንዴ እንዲመጣ ከፈለግክ፣ እንደተመኘኸው ላይሆን ይችላል፡፡ እንደተመኘኸው ጎርፍ ሆኖ ቢመጣምኮ አይጠቅምህም፡፡ ጠራርጎህ ይሄዳል፡፡ እየሰራህ በዚያው መጠን ገንዘቡም በጠብታ ሲመጣ፤ ያቺ ህይወትን ትቀይራለች፡፡

ወደ ስዊዲኑ ወሬ ልመልስህና፣ ከዚያስ ምን ሆነ?

በአምስት ዘርፎች አምስት ሰዎች አለፍን፡፡ ከንግድ ም/ቤት ደግሞ ፕሬዚዳንቷ ወ/ሮ ሙሉ ሰለሞን፣ ዋና ፀሃፊው አቶ ጌታቸው ቢጋሳ፣ እንዲሁም የአርቢትሬሽን ሃላፊ አቶ አበበ .. በአጠቃላይ ከኢትዮጵያ ስምንት ሰዎች ሄድን፡፡ ከሌሎች 5 የምስራቅ አፍሪካ አገራትም እንዲሁ መጥተዋል፡፡ ስልጠናው የተጀመረው በስቶክሆልም ከተማ ነበር፡፡ ግንቦት አጋማሽ ላይ፡፡ ከዚያ በኋላ ደግሞ በሰሜን ስዊድን፡፡

ስራህን እንደገና በአዲስ አይን እንድታይ፣ ስራህን እንደገና በአዲስ መልክ እንድታከብር የሚያደርግ አስገራሚ ስልጠና ነበር፡፡ በአሜሪካና በአውሮፓ መኖር ባልመኝም፤ ጥላቻ የለብኝም፡፡ ጥሩ ነገራቸውን ካየሁ፤ ለመማር ዝግጁ ነኝ፡፡ እና ስልጠናውም፤ እነዚያ ፈረንጆች ለምን እንደሰለጠኑና እንደበለፀጉ እንዳስብ የሚያደርግ ሆነብኝ፡፡

ከዚሁ ሃሳብ ተነስቼ ደግሞ እኛስ እኔስ ብዬ እንደገና በስፋት እንዳስብ አድርጎኛል፡፡ ስትራቴጂክ ቢዝነስ ማኔጅመንት የሚል ነው ስልጠናው፡፡ በደፈናው ታታሪ ሆኖ መስራትና በደፈናው እቅድ በማውጣት መስራት ብቻውን በቂ አይደለም፡፡ ከምር አስፍቶ፣ ከምር አድቅቆ ማሰብ፤ ሃሳብን ከምር ከተግባር ጋር ማስተሳሰር … በቲዎሪ ብቻ ሳይሆን በተግባር፤ የስዊድን ምርጥ የቢዝነስ ሰዎች እንዴት እንደሚያስቡና እንዴት እንደሚሰሩ አየን፡፡ በጣም ያስደንቃል። አዲስ ሰው የመሆን ያህል ይሰማሃል፡፡ ከመቼ አገሬ ተመልሼ፤ ይሄን እውቀት ከመቼ ሰርቼበት ብለህ ትቸኩላለህ፡፡ የስልጠናው አስገራሚነት ከምን ይጀምራል መለሰህ?

ለሦስት ሳምንት የተዘጋጀው ፕሮግራም፤ አንዲት ነገር አንዲት ሰዓት ውልፊት ሳትል መካሄዱ … በስልጠናው ላይ ይካፈላሉ የተባሉ የስዊድን የቢዝነስ ሰዎች … አንዳቸውም ለአንዲት ደቂቃ ሳይዘገዩ ሁሉም በፕሮግራሙ መሰረት... ሲከናወን ስታይ፤ አስተሳሰብህን እንድትፈትሽ ያደርጋል፡፡ ከስልጠናው የምታገኘው እውቀትና አዲስ አቅጣጫ ደግሞ ሌላ ነገር ነው። ድሮምኮ ጫፍ ጫፉን ታስበዋለህ፤ በደፈናው ታስበዋለህ፡፡ ግን ጠብታ አምቡላንስ በ5 እና በ10 አመት የት እንደሚደርስ፤ በየት በየት በኩል እንደሚጓዝ አጥርተህ አድቅቀህ አንጥረህ ማሰብ፤ በፅሁፍ ማስፈር … ላይ ላዩን እንጂ እንዲህ ማሰብ በአገራችን አልተለመደም፡፡ ከስልጠናው በኋላ ግን ልብህ ይንጠለጠላል፡፡ የሦስት ሳምንቱ ስልጠና አለቀ፡፡ ግን ተከታይ ክፍሎች አሉት፡፡ በስልጠናው ባገኘነው እውቀት፤ የቢዝነስ ስትራቴጂያዊ እቅድ እናዘጋጃለን፡፡ ከአሰልጣኞቹ ጋር እንወያይበታለን፤ ወደ ተግባር እንዴት እንደምናሸጋግረው እናያለን፡፡ ስልጠና ብቻ ሳይሆን በቀላሉ የማይገባኝ የኮንሰልታንት አገልግሎትም እያገኛችሁ ነው?

የስራ ላይ ስልጠናና ክትትል ነው ማለት ይቻላል፡፡ ዛሬ የሆነ ፕሮጀክት አጠናቅቀን የምናቀርብበት ቀን ነው፡፡ ከዚያ በኢንተርኔት የቀጥታ ውይይትና ክርክር እናካሂዳለን፡፡ ከዚያ በኋላ እንደገና ሌላ አሳይመንት ይኖራል፡፡ በሩዋንዳ አንድ የማጠቃለያ ስልጠና፤ ከዚያ በአዲስ አበባ ሌላ የማጠቃለያ ስልጠና እያለ ይቀጥላል፡፡ በሙያዬ ተምሬያለሁ፤ በሶሻል ሳይንስ በዲግሪ ተምሬያለሁ፤ የአሁኑ ስልጠና ሌላ ህይወትን የሚቀይር አዲስ እይታ ከፍቶብኛል፡፡

በሌላ በኩል ስታየው ደግሞ ለካ፤ ሌላ ተአምር የለውም፡፡ አገር የሚለወጠው ስራ በሚፈጥሩ ሰዎች ነው፡፡ ስራ ክቡር ነው በሚሉ ሰዎች ነው አገር የሚቀየረው፡፡ አንድ የማምንበት አባባል አለኝ - የልመና ክብር፣ የስራ ውርደት የለውም፡፡ የሰው ሃቅ አለመፈለግ፤ የራስህን ነገር ደግሞ መፍጠርና መስራት ያስደስታል፡፡ ክብር አለው፡ያኔ ስትረዳዳ ስትተባበር በደስታና በክብር ነው፡፡

የምንለወጠው በስራ ነው፡፡ መንገድ ላይም ሆነ በየቤቱ እየሄደ የሚለምን ህጻንና አዋቂ፤ መላውን አለም እየዞረ የሚለምን አገርም ሆነ ባለስልጣን ያው ነው። አሁን በየቦታው የስራ ፍቅር የምታይባቸው ወጣቶች ናቸው የአገሪቱ ተስፋ፡፡ በቅጥሉ ስልጠናው ይህን ሃሳብ የያዘ ነው - የስራ ፍቅር፣ የስራ ክብር፡፡ ግን እንዲህ በደፈና ፍቅር ክብር ብሎ ማለፍ አይደለም፡፡ ሂሳብ ስናሰላ፣ በደፈናው ተደምሮ ይቀናነሳል ብለን አናልፍም አይደል? ሁሉንም ቃኝተን እያንዳንዱን ለቅመን እናሰላለን፡፡ የስራ ክቡርነትም ላይ እንደዚያ በረዥሙ መቃኘትና እያንዳንዱን ልቅም አድርጎ መስራት ያስፈልጋል፡፡ ብቻ በስልጠናው ላይ መካፈሌ ለኔ ትልቅ ዋጋ አለው፡፡

የሰሜን ዋልታ አጠገብ በበረዶ የተሸፈነ የማላውቀው አገር ላይ … አንድ ቀን ቁጭ ብዬ አሰብኩት፡፡ እንዴት እንዴት ብዬ ነው እዚህ ቦታ የተገኘሁት? እዚህ ስልጠና ውስጥ የገባሁት? ብዬ አሰብኩ፡፡ በዘመድ አዝማድ በኩል ነው? በወዳጅ በትውውቅ ነው? በገንዘብ በአማላጅ ነው? ይሄ ሁሉ አለመሆኑ እንዴት ደስ ይላል መሰለህ፡፡ በቅድሚያ ስራዬንና ሙያዬን አክብሬ በፍቅር መስራቴ፤ ከዚያም በጣም አስፈላጊ ሆኖ የታየኝን የአምቡላንስ አገልግሎት ለመጀመር አስቤ በተግባር የአቅሜን በመስራቴ … በዚህች መነሻነት ተወዳድር ነው እዚያ ቦታ ላይ የተገኘሁት፡፡ ትንሽም ብትሆን የራሴ ስራ ስለሆነች ኩራትና ደስታ ትሰጣለች፡፡

ስራ ክቡር የሚሆነውኮ ያለምክንያት አይደለም፡፡ ሁሉም የስራ ውጤት ፋይዳው ለሰው ነው፡፡ የሚመረተው ምግብና የሚገነባው ቤት ለሰው ነው፡፡ ለሰው ህይወት ክብር ሲኖርህ ስራን ታከብራለህ፡፡ እርሻም ሆነ ግንበኝነት ክቡር ናቸው፡፡ ሃኪምና ህክምና ክቡር የሚሆኑት ለምን መሰለህ? ታካሚው ሰው ክቡር ስለሆነ ነው ሃኪሙ የሚከበረው፡፡ ሃኪሙ፤ ታካሚዎችን የማያከብር ከሆነ ግን፤ ሙያውን ክብር ያሳጣዋል፡፡ በዚያው መጠን፤ ታካሚውም ሃኪሙን ማክበር አለበት፡፡ በደሞዝም ሆነ በክፍያ ሃኪሞችን መበደል ወይም አላግባብ ሃኪሞችን ማማረር፣ የሙያውን ክብር ይቀንሳል፤ የጤንነትንና የህይወትን ክብር ዝቅ ማድረግ ይሆናል፡፡ ዞሮ ዞሮ የራስህን ክብር ማዋረድ ነው፡፡ የስራ ፍቅር የሁሉም ነገር ቁልፍ ሆኖ እየታየኝ ስለሆነ ነው የምደጋግመው፡፡ ከውርደት መውጣትና ክብር ያለው ህይወት መኖር የምንችለው በስራ ከሆነ፤ ከስራ የበለጠ ምን ክቡር ነገር አለ? ልመና፣ ረሃብ፣ ድርቅ ... በእነዚህ ሁሉ ውርደት ደርሶብናል። ከሁሉም የባሰ ሆኖ የሚታየኝ ግን የስደት ውርደት ነው፡፡ ኢትዮጵያዊ እህታችን በሊባኖስ እንደዚያ ስትጎተት ያየሁ እለት፤ እንዴት እንዴት እንደሆንኩ ልነግርህ አልችልም፡፡ ወንድም እህቶቻችን እንዲህ አይነት ስቃይ እንዳይደርስባቸው ማድረግ የምንችለው፤ እዚሁ አገራችን ስራ ስንፈጥርና ክብር ያለው ህይወት የመመስረት እድል ስናመቻች ነው፡፡ አለበለዚያ ስደትንና ውርደትን ማስቆም አንችልም፡፡ ታዲያ በዚህ በኩል እኔ ምን ሰራሁ ብለን ራሳችንን መጠየቅ የለብንም? ደግሞ የስራ ፍቅር የሚታዩባቸው ወጣቶች ምን ያህል ተዓምር ሊሰሩ እንደሚችሉ አይታይህም? በቲቪ የሚተላለፈውን የቢዝነስ ሃሳብ ውድድር አይተኸዋል? ከቲቪ ፕሮግራሞች እንደሱ የወደድኩት የለም፡፡ ከምር ካሰብንበት ስንትና ስንት የስራ ሃሳቦች እንደሚፈጠሩ ስታይ በጣም ያስደስታል፡፡ መስራት ያለብን የስራ ብዛትኮ ተቆጥሮ አያልቅም፡፡

የራስህ አላማና የራስህ ደረጃ ሊኖርህ ይገባል (Purpose እና Standard)። የራስህ አላማና የራስህ ደረጃ ሲኖርህ፤ ለጉዞህ ሃይል ታገኛለህ፤ መንገድህን እንዳትስትም መለኪያ ይኖርሃል፡እንዲህ በህይወትና በስራ ዙሪያ የምንወያይ ጓደኛሞች አለን፡፡ በአገራችን በስፋት የሚታየው ችግር ምንድነው ብለን ስንነጋገር ነበር፡፡ የራስ አላማ፣ የራስ ደረጃ ከሌለ፤ መራመድ ይሳንሃል፤ አቅጣጫ ይጠፋሃል። አላማ ራዕይ ሲኖርህ፤ የየእለቱ ኑሮህ ትርጉም ይኖረዋል፡፡

ለምሳሌ ሁለት ሰዎች እኩል ገንዘብ ቢያገኙ፤ ሃሳባቸው እንደየ አላማቸው ይለያያል፡፡ አንተ የአምቡላንስ አገልግሎቱን እንዴት እንደምታሻሽልና እንደምታስፋፋ ልታስብ ትችላለህ፡፡ ሌላው ደግሞ ስለ ጃኩዚ ሊያስብ ይችላል፡፡ የራስ አላማ፣ የራስ ደረጃ ስትል ከዚህ ጋር ይገናኛል?

የራስ ደረጃ ከሌለሀ እርካታ አይኖርህም፡፡ የ2008 ሞዴል ጃኩዚ ስታስብ፤ ከዚያ ሌሎች ሰዎች የ2010 ሞዴል ጃኩዚ ሲያስመጡ፤ እሱን አይተህ የ2011 እና የ2012 ሞዴል ስታስብ … ወይ ጃኩዚ ሳትገዛ ወይ በጃኩዚ ሳትረካ እድሜህ ያልቃል፡፡ ምክንያቱም ከሰው ባየኸው እየተመራህ እንጂ ከምር ራስህ የምትፈልገው ነገር ላይ አተኩረህ እየኖርክ አይደለም። ከምር የምትፈልገው ስታንዳርድ የቱ ነው? ከምር ጃኩዚ ከፈለግክ ችግር የለውም፡፡ ግን የጀመርከውና ለማስፋፋት ያቀድከው ስራ ላይ የምር ፍላጎት እያለህ፤ እሱን ትተህ በሌሎች ሰዎች ስታንዳርድ ከተመራህ ትባክናለህ፡፡ ከመባከን አልፎ፤ የአስተሳሰብ ጤንነት ሊያሳጣህም ይችላል፡ኑሮዬን አደላድያለሁ ብሎ ያስባል እንበል፡፡ ግን ጥሩ ኑሮ አደላድያለሁ ለማለት የቻለው በምን መመዘኛ ነው? የራስህ ደረጃ ከሌለህ፤ ከሌሎች ሰዎች ጋር ማነፃፀር ሊኖርብህ ነው፡፡ “እከሌን አታየውም ተቸግሯል፤ እከሊትን አታያትም ተጎድታለች፤ እኔ እሻላለሁ” ብለህ ልትረካ ነው፡፡ ያንተ እርካታ በሌሎች ሰዎች ስቃይ ላይ የተመሰረተ ይሆናል፡፡ ይሄ ጤናማ አስተሳሰብ አይደለም፡፡ እርካታ እንዲሰማህ ሌሎች ሰዎች መቸገር አለባቸው ማለት ነው፡፡ ከበለጡህ ደግሞ ያበሳጭሃል ማለት ነው፡፡

ምን ያህል የታመመ አስተሳሰብ እንደሆነ እየው። የራስህ ስታንዳርድ ካለህ ግን፤ ያን ደረጃ ማሟላት ላይ ነው የምታተኩረው፡፡ ከሰዎች ጋር የንፅፅር ጣጣ ውስጥ አትገባም፡፡ ያኔ ሰዎች ተቸግረው ማየት አትወድም፡፡ ሲሳካላቸው ስታይ ደግሞ ያስደስትሃል፡፡ እንዲያውም በአርአያነት ታደንቃቸዋለህ፡፡ የራሳቸውን ደረጃ ያሟሉ ሰዎችን ስታይ፤ አንተም ለራስህ ስታንዳርድ እንድትጣጣር ያነቃቁሃል፡፡ ሮል ሞዴል ናቸው። በምዕራብ አገራት የሞዴል ነገር ጎልቶ የሚታየው በዚህ ምክንያት ሊሆን ይችላል፡፡ በኛ አገር ግን፤ ሞዴል ሲባል ቶሎ ወደ አእምሯችን የሚመጣው የመልክ የቁንጅና ሞዴል ነው፡፡ የስብእና ሞዴል አይታየንም፡፡ የስብእና ሞዴል ያስፈልገናል፡፡

የካናዳው ስልጠናስ እንዴት ነበር?

የካናዳው ስልጠና፤ በደራሽ ህክምና (በድንገተኛ ህክምና) ዙሪያ ላይ ነው፡፡ በዚያ ስልጠና ምክንያት፤ አሁን የድንገተኛ ህክምና ባለሙያዎችን የማሰልጠን ብቃት አግኝተናል፡፡ እውቅና ያለው (Certified) ስልጠና እንሰጣለን፡፡

የካናዳው ስልጠናም አይን ከፋች ነበር፡፡ በዩኒቨርሲቲው ሆስፒታል ውስጥ ከተሰጠው ስልጠና በተጨማሪ፣ ድንገተኛ የአምቡላንስ ጥሪና አገልግሎት እንዴት እንደሚሰሩ ለ15 ቀን ስልጠና ወስጃለሁ፡፡ በተግባር 15 የአምቡላንስ ጥሪዎች ላይ ተካፍያለሁ፡፡

በ911 የስልክ ቁጥር የአምቡላንስ ጥሪ ይመጣል፡፡ በጥሪውና በአምቡላንሱ ጩኸት መካከል ያለው ልዩነት የቅፅበት ያህል ነው፡፡ በ5 ደቂቃ፣ ቢበዛ በ7 ደቂቃ በቦታው ከተፍ ይላል፡፡ ፈጥኖ ደራሽ የህይወት አድን ህክምና በመስጠት፣ በፍጥነት ወደ ሆስፒታል የሚያደርሱበት አሰራር ይገርማል፡፡ እዚህ አገራችን ውስጥም የአምቡላንስ አገልግሎታችንን ወደዚያ ደረጃ ማድረስ አለብን፡፡ ደግሞ በርትተን ከጣርን አያቅተንም፡፡

ከስልጠናው ጋር በተያያዘ፤ በአስቸጋሪ የወሊድ ጊዜ ለህፃናት የሚካሄድ የህክምና እገዛ ላይም ስልጠና ወስጃለሁ፡፡ ያንን እዚህ ለስራ ባልደረቦቼ አከፍላለሁ - የአንስቴዢያ ባለሙያዎች ማህበር ሙያዊ ኮንፈረንስ ላይ ማለት ነው፡፡

የማህበራችሁ ሙያዊ ኮንፈረንስ ላይ፤ ለጠብታ አምቡላንስ እውቅና ተሰጥቷል፡፡

እንደነገርከኝ የዛሬ 3 ዓመት በተካሄደ ኮንፈረንስ ላይ ነበር፤ የጠብታ አምቡላንስ ለመጀመር መዘጋጀትህን የገለፅከው አምቡላንሶቹ ገና አልገቡም ነበር፡፡ ባለቤቴ ስጋት ቢገባትም፤ መኖሪያ ቤታችንን ሸጠን ጠብታ አምቡላንስ እንድናቋቁም ተስማምተን አምቡላንሶቹን ለማስመጣት ከፍለን ነበር፡፡ ግን ገና አልገቡም ነበር፡፡ የአምቡላንስ አገልግሎት ፈቃድ ማግኘት አለማግኘታችንም እርግጠኞች አልነበርንም፡፡ ቢሆንም ወደ ኋላ አላልንም፡፡ እና በኮንፈረንሱ ላይ ሃሳቤን ሳቀርብ፤ የተለያዩ ሃሳቦች ተነስተው ነበር፡፡ ከብዙዎቹ የሙያ ባልደረቦቼ ጋር ሙያዊ ጥያቄዎች ተነስተው ተወያየን፡፡ “የማይሆን ነገር ነው” ያሉም ነበሩ፡

አሁን ሦስት አመት ሆነው?

አዎ፤ የአምቡላንስ ቁጥር ጨምረናል፡፡ በሦስት አመት ውስጥ ለ10ሺ ታማሚዎች የአምቡላንስ አገልግሎት ሰጥተናል። ከእነዚህም መካከል ከ6 ሺ በላይ የሚሆኑት አፋጣኝ ኦክስጅን የሚያስፈልጋቸው ነበሩ፡፡ እንደምታስታውሰው እውቁ ድምፃዊ ጥላሁን ገሰሰ፤ የኦክስጅን አቅርቦት ያለው የአምቡላንስ አገልግሎት ያስፈልገው ነበር፡፡ በተሟላ የአምቡላንስ አገልግሎት እጥረት ሳቢያ ጉዳት መድረስ የለበትም፡፡ የአምቡላንስ አገልግሎት በአእምሮዬ ውስጥ ሲብሰለሰል ቆይቶ እንዴት ወደ ውሳኔ እንደተሸጋገርኩ አልረሳውም፡፡ ለስራ የምገባበት ሰዓት ነበር፡፡ ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ነው፡፡

አንድ ወጣት ክንዱ ላይ አደጋ ደርሶበት፣ ዋናው የደም ቧንቧ ተጎድቶ ብዙ ደም እየፈሰሰው ነበር፡፡ በመኪና ውስጥ አስገብተው ነው ወደ ሆስፒታል ያመጡት፡፡ ካርድ እንዲያወጡ ተነግሯቸው ይሯሯጣሉ፡፡ ጉዳት የደረሰበት ወጣት ግን እዚያው መኪና ውስጥ ተጋድሟል፡፡ አይንቀሳቀስም፡፡ ሁኔታው ስላሳሰበኝ ተጠግቼ አየሁ፡ እጁ ተዘርግቷል፡፡ ደሙ ይፈሳል፡፡ ሰውነቱ ውስጥ የነበረ ደም በሙሉ መኪናው ላይ ፈሷል ማለት ይቻላል፡፡ በፍጥነት መከናወን ካለባቸው የነፍስ አድን ስራዎች መካከል አንዱ፤ የደም መፍሰስን ማስቆም ነው፡፡

ወደ ሆስፒታል ያመጡት ሰዎች ይህን አላወቁም፡፡ ደም እንዳይፈስ ማሰርና መያዝ ያስፈልግ ነበር፡፡ ልጁ ሃኪም ጋ ሳይደርስ እዚያ መኪና ውስጥ ህይወቱ አለፈ፡፡ እንዲህ አይነት አሳዛኝ ነገር ማየት ምን ያህል ውስጥን እንደሚረብሽ ... በተለይ፤ በቀላል የነፍስ አድን ህክምና ጤናማ መሆን ይችል የነበረ ህይወት በአጭር ሲቀጭ ማየት ቁጭቱ ከአእምሮህ ሊወጣ አይችልም። የአቅሜን ያህል የጠብታ ያህል ለመስራት መወሰን ነበረብኝ።

 

 

 

 

Read 6601 times Last modified on Saturday, 23 June 2012 11:17