Print this page
Saturday, 11 January 2020 14:46

ከምርጫው በሰላምና በጤና እንተርፋለን?

Written by  ዮሃንስ ሰ
Rate this item
(2 votes)

 የዘንድሮው ምርጫ፣ ‹‹ከውዝግብ የፀዳና እንከን አልባ›› እንዲሆንልን ብንመኝ፣ መልካም የቅንነት ምኞት ቢሆንም እንኳ፤ ሊሳካልን ይችላል ማለት አይደለም፡፡
“የዘንድሮ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ”፣ በአንዳች ተዓምር፣ ከድህነትና ከችግር መላቀቅ እንደማይችል ይገባን የለ? የዘንድሮው የፖለቲካ ምርጫም እንዲሁ፣ ከውዝግብና ከእንከን የማምለጥ እድል የለውም፡፡
ከሌላ ባለፀጋ ፕላኔት የሚመጣ ድንገተኛ ሃብት አይኖርም፡፡ “ቤት ያፈራው” ኢኮኖሚ ውስጥ ነው የምንኖረውም፡፡ ከአንዳች ተዓምረኛ ፕላኔት የተላከ ‹‹ስልጡን ፖለቲካ›› በአስቸኳይ ደርሶልናል ካልተባለ በቀር፣ የዘንድሮው ምርጫ፣ “ቤት ባፈራው የኋላ ቀርነት ፖለቲካ” ውስጥ ነው የሚካሄደው፡፡
ኢትዮጵያ ውስጥ፣ ለረዥም አመታት ሲስፋፉ የቆዩ ነባር የፖለቲካ ቅኝቶችንና ሃሳቦችን፣ ቀስ በቀስ ማሻሻል ቢቻልም፤ ‹‹ለዘንድሮ ምርጫ አስበው››፣ ድንገት በአክሮባት ፊታቸው አይዞርም፣ መልካቸው አይቀየርም፡፡
የአገራችን ፓርቲዎችና ፖለቲከኞችም፣ “ቤት ያፈራቸው” ናቸው፡፡ ከትናንት ዛሬ፣ የተሻሻሉ አሉ፡፡ የሚሻሻሉም ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ በአንድ ጀንበር፣ “የስልጡን ፖለቲካ” ፊታውራሪ እንዲሆኑልን መጠበቅ ግን፣ ሞኝነት ነው፡፡
ከምሁራንና ከጋዜጠኞች ጀምሮ፣ አብዛኛው ዜጋ እና መራጭም፤ እንደ እስካሁኑ የምናውቃቸው ያህል ናቸው፡፡ ከአምና ዘንድሮ፣ ይሄኛውና ያኛው ዘንድ፣ የመሻሻል ወይም የመበላሸት ለውጥ መኖሩ አይካድም፡፡ ነገር ግን፣ አንዳንድ ሰዎች የቱንም ያህል ቢሻሻሉ እንኳ፣ በተዓምረኛ ፍጥነትና “ትንግርት ነው” በሚያሰኝ ብዛት፣ አገር ምድሩ ሁሉ፣ በአስተዋይነትና በጥበብ ሊጥለቀለቅ ይችላል ማለት አይደለም፡፡
ትክክለኛ የስነምግባር መርሆችን የሚያውለበልብ፣ የህግ የበላይነት ስርዓትን የሚያከብር፣ የግለሰብ ነፃነት ላይ የተመሰረተ ስልጡን ፖለቲካን የሚያፈቅር ምሁርና ጋዜጠኛ፣ ዜጋና መራጭ፣ “ለዘንድሮ ምርጫ ሲባል”፣ ድንገት እልፍና ሚሊዮን እየሆነ አይፈጠርም፡፡
በአጭሩ፣ ምርጫው ከውዝግብ አያመልጥም፡፡
ሩብ ሚሊዮን ያህል የምርጫ አስፈፃሚዎችም እንዲሁ፣ በስነምግባር የፀኑ፣ በሙያ የበቁ የጠንካራ ስብዕና ባለቤቶች ከበዙበት፣ ከሌላ ፕላኔት የሚመጡ ሰዎች አይደሉም፡፡ ኢትዮጵያ፣ ለዘንድሮ ምርጫ፣ ሁሉም ነገር የተሟላላትና የተሳለጠባት አገር ትሆናለች ካልተባለ በቀር፣ ቤት ባፈራቸው ሰዎች የሚከናወነው ምርጫ፣ ከእንከን ሊያመልጥ ይችላል ብሎ መጠበቅ፣ የዋህነት ይሆናል፡፡
እዚህና እዚያ “እንከን አየሁ” ብሎ ለእሪታና ለውግዘት መሯሯጥ፣ አንድም አላዋቂነት ነው፡፡ አልያም፣ ግርግርና ጥፋት ለመፍጠር አንዳች ሰበብ የማግኘት ረሃብና የክፋት ጥም ነው፡፡ “ኢትዮጵያ፣ ዘንድሮውኑ ከድህነት አልተላቀቀችም” ብሎ አገሬውን በጩኸት ለመረበሽ፣ በግርግር ለመበጥበጥና በአመጽ ለማተራመስ ከመሞከር የተለየ አይደለም፡፡ ይልቅስ፣ ‹‹ምን ያህል ተሻሻለ?›› ብሎ መጠየቅ ይቻላል፡፡
የዘንድሮው ምርጫም፣ ከውዝግብና ከእንከን የማያመልጥ ቢሆንም፣ በተቻለ መጠን ሁሉ፣ ውዝግብንና እንከኖችን በሚቀንስ መንገድ፣ ወደ ክፉ ችግር እንዳይለወጡ በሚከላከል ዘዴ፣ ጥሩ የመሻሻል ስኬቶችን እንዲያሳይ ማድረግ ይቻላል፡፡
ዋናውና ትልቁ ስኬት፣ ምርጫው፣ ከሞላ ጐደል በሰላም ለውጤት ማድረስ ነው፡፡ ይሄ፣ ቀላል ስራ አይደለም፡፡ በጥቂት ሰው ወይም በሁለት ሦስት ተቋማት ብቻ የሚከናወንም አይደለም፡፡ ለምን ቢባል፤ የአገራችን ፖለቲካ፣ ከሥረ መሰረቱ፣ ለሰላማዊ ምርጫ አይመችም፡፡
ብሔር - ብሔረሰብ፣ ሃይማኖትና እምነት፣ ድሃና ሃብታም በሚሉ ሰበቦች የሚፈጠሩ ቀውሶችና ጥፋቶች ሁሉ፣ ከዚህ መሠረታዊ ችግር ጋር የተቆራኙ ናቸው፡፡
ይህንን ሰፊና መሠረታዊ ችግር ለመቃኘት፣ እንዲሁም የመፍትሔ እድሎችን ለማየት፣ ከአንድ ጥያቄ እንጀምር፡፡
ማንም ቢመረጥ፣ “አገራችንም ደህና”፣ “እኛም ጤና” እንሆናለን ወይ? የስልጡን ፖለቲካ ልክ፣ እዚህ ድረስ ነው፡፡
ምርጫ፣ የሞት ሽረት ፍጥጫ አይደለም - በስልጡን ፖለቲካ ውስጥ፡፡
የትኛውም ፓርቲ በ99% ጠቅልሎ ቢያሸንፍ፣ ወይም በጣት በሚቆጠር ድምፅ፣ በኢምንት ብልጫ ስልጣን ላይ ቢወጣ፣ የትኛውም ፖለቲከኛ በትንቅንቅ አልያም በሰፊ ልዩነት ቢመረጥ፣ በዜጐች ህይወትና ኑሮ ላይ፣ በአገር ህልውናና ሰላም ላይ፣ በህግና ስርዓት ላይ ያሰኘውን አይነትና ያሻውን ያህል ለውጥ መፍጠር የማይችል ከሆነ፣ ያኔ በሰለጠነ ፖለቲካ፣ “ሰላማዊ ምርጫ” የማካሄድ እድል ይኖራል፡፡
በሌላ አነጋገር፣ የፖለቲካ ምርጫ አልፋና ኦሜጋ መሆን የለበትም፡፡ ምርጫ ማለት፣ በየ5 አመቱ የሚመጣ የሞት ሽረት ፍልሚያ ካልሆነ ብቻ ነው፤ “ሰላማዊ ምርጫ” የሚሆንልን፡፡
በተቃራኒው፣ በምርጫ ያሸነፈ የትኛውም ፓርቲ ወይም ፖለቲከኛ፣ በሰዎች አእምሮና አካል፣ በሰዎች ሃሳብና ስራ፣ በሰዎች ኑሮና ሕይወት ላይ፣ እንዳሻው የመወሰንና የማዘዝ መንጃ ፈቃድ የሚያገኝ ከሆነ፣ ወይም የጌትነት ስልጣን የሚያገኝ ከመሰለንስ? ያኔ፣ የምርጫ ዓመት፣ የሞት ሽረት የፍልሚያ ቀጠሮ ይሆንብናል፡፡
እንዲህ አይነት ምርጫ፣ ያለ ጥረት ሃብት፣ ያለ ብቃት ሽልማት ለማግኘት የምንሻማበት ግጥሚያ ሆኖ ይታየናል፡፡ በሌሎች ኪሳራና ጉዳት፣ በሌሎች መስዋዕትነትና ውርደት… በዝርፊያ፣ በግፊያ፣ በግድያ… ሃብትና ክብር የሚሰጠን ገዢ እንዲመረጥ እንጋደላለን፡፡ ለሌሎች የሚያስፈራ፣ ለኛ የሚያደላ አምባገነን፣ በዚህም ተባለ በዚያ፣ ስልጣን እንዲይዝ እንፋለማለን፡፡
በሌላ በኩል ደግሞ፣ ለሌሎች የሚያደላ፣ እኛን የሚጠላ፣ እንዳሻው ስራችንን ማደናቀፍና መገደብ፣ ወይም ማገድና መዝጋት የሚችል፤ በስንት ዓመት ጥረት ያፈራናትን ንብረትና ያጠራቀምናትን ጥሪት በአንዲት አንቀጽ መውረስና ለሌሎች መስጠት የማይገደው፣ ከልካይ የሌለው፣ እኛን የሚያስፈራራ፣ ሌሎችን የሚያበላ አምባገነን፣ ስልጣን ላይ እንዳይወጣ፣ በስጋትና በጭንቀት እንፋለማለን፡፡
ይሄኛው አምባገነን ካሸነፈ፣ አየርባየር “አለፈለን”፡፡
ያኛው አምባገነን ካሸነፈ፣ ባንድ ጀንበር “አለቀልን”፡፡
እንዲህ የሚያሰኝ ፖለቲካ፣  የሰላምና የጤና ምልክት አይደለም፡፡ በዚህ መሃል የሚደረግ ምርጫም፣ “ከመኖር ወይም ካለመኖር ጥያቄ” ጋር የምንጋፈጥበት አደገኛ ግጥሚያ ሆኖ ያርፈዋል፡፡
የተቀናቃኝ ፓርቲዎች ፉክክር ማለት፣ የመተናነቅና የመጠፋፋት “ፉከራ” ይሆናል:: የፖለቲከኞች የምርጫ ውድድር ማለት፣ ውረድ እንውረድ የሚባባሉበት፣ ጦር ወድረው የሚፋለሙበት ግጥሚያ ይሆናል፡፡
በሃሰትና በአሉባልታ፣ በስድብና በውንጀላ ብዛት፣ አንዱ ሌላኛውን ለማዋረድ የሚሽቀዳደሙበት ወራዳ ትዕይንት ይሆናል -የምርጫ ውድድር፡፡
እርስ በርስ ገዝግዞ የመገንደስ፣ ከርክሮ የመቀንጠስ ዘመቻ ይሆናል - የፓርቲዎች ክርክር፡፡  
በአጭሩ፣ በኋላ ቀር ፖለቲካ ውስጥ፣ ተቀናቃኝ ፖለቲከኞችና ተፎካካሪ ፓርቲዎች የሚወዳደሩበት ምርጫ፤ የማዋረድና የውርደት፣ የመተናነቅና የመጠፋፋት ፉከራ ይሆንና፣ እልፍ የውዝግብ ሰበቦች ይፈለፈላሉ፡፡ የሽምግልና ግልግልም ጭምር፣ የግርግር አጋጣሚዎችን በእልፍ ለማራባት ይውላል፡፡
እለት ተእለት በሁከት መሃል ብዙ ጉዳት ይደርሳል? አዎ፣ ህይወት ይቀጠፋል፣ አካል ይጎድላል፤ ንብረት ይዘረፋል፣ ኑሮ ይናጋል፤ ይነቀላል፡፡ ነገር ግን፣ ይህንን እንደ ችግር የማይቆጥሩ፣ የክፋት ፊታውራሪዎች ሞልተዋል:: ግርግር ፈጥረው ጉዳት ሲደርስ፣ “እሰየው” ይላሉ፡፡ ተጨማሪ ሁከት ለመቀስቀስ የሚጠቅም ተጨማሪ ሰበብ ይሆንላቸዋል፡፡
ከዚያማ፣ ጭፍን ስሜትን እያነሳሱ፣ የእሮሮ ምሬትን ተመርኩዘው ክፉ ጥላቻንና የጥቃት ዛቻን እየነዙ፣ በአጭር ጊዜ፣ ወደ እልቂት ዘመቻ ለመሸጋገር ብዙ ድካም አይጠይቃቸውም:: ቁልቁል ለመንሸራተት የተመቻቸ ፖለቲካ፣ እንጦሮስ ከመውረድ ማን ያስቆመዋል?
ከየትኛው ነን - የሁለት ግቢዎች ልዩነት፡፡
አንድ ግቢ ውስጥ፣ አንዱ የሌላውን ቤት ለመውረስም ሆነ ለመዝረፍ ሳይመኙና ሳይቃጡ፣ ተከባብረው፣ እንደየዝንባሌያቸውም ተቀራርበውና ተዋድደው የሚኖሩ ጐረቤታሞችን አስቧቸው፡፡
ግድ የለም፣ እስከ መዋደድ ባይደርሱ እንኳ፣ ችግር የለውም፡፡
የሚገበያዩት ነገር ባይኖር፣ ወይም በዋጋ ባይስማሙም ጭምር፣ አያሰጋም፡፡ ለክፉ የሚሰጥ ጉዳይ አይሆንባቸውም፡፡
ሌላው ሁሉ ይቅር፡፡ አንዱ የሌላውን ህይወትና ኑሮ ካልደፈሩ፣ ይህችን “የመብት መከበሪያ” ቀይ መስመር ካልጣሱ፣ በየፊናቸው “በነፃነት” የየራሳቸውን ህይወት በእውቀት መምራት፣ ሰርተው ኑሯቸውን ማስተዳደር ይችላሉ፡፡ ሰላም ነው፡፡ ይህን በማገናዘብ የምናገኘው አንድ ቁም ነገር አለ፡፡
በእውቀትና በጥረት ንብረት ማምረትን፣ እንዲሁም የሰውን ብቃት አይቶ ማድነቅን የሚያስተምር፣ ጭፍንነትን የሚያስቀር፣ የሌላ ሰው ንብረት መመኘትንና የምቀኝነት ክፋትን የሚፀየፍ ትክክለኛ የስነምግባር መርህ፣ ዋናው የስልጡን ፖለቲካ ስረመሰረት ነው፡፡ ‹‹ይህንን እንፈልጋለን ወይ?›› የሚል ነው የመጀመሪያው ጥያቄ፡፡
በትክክለኛ የስነምግባር መርህ ላይ የተሰመረተ፣ የእያንዳንዱን ሰው መብትንና ነፃነትን የሚያስከብር ‹‹ህጋዊ ስርዓት››፣ ማለትም የሀሰት ውንጀላን፣ ዝርፊያንና ግድያን ፍፁም የሚከለክልና የሚቀጣ፣ በዚህም አማካኝነት በሰዎች ዘንድ ለግብይትና ለትብብር፣ ለቅንነትና ለፍቅር የሚመች ‹‹የነፃነት ሰላምን›› የሚያሰፍን ህጋዊ ስርዓት እንፈልጋለን ወይ? ይሄ ሁለተኛው ጥያቄ ነው፡፡
ይህንን የምንፈልግ ከሆነ፤ የመንግስት ስራ፤ ‹‹ለህግ ተገዢ በሆነ መንገድ ህግን ማስከበር ብቻ›› ይሁን እንላለን፡፡ መንግስት ያሻውን ነገር መስራት አይችልም ማለት ነው፡፡ የትኛውም ፓርቲና ፖለቲከኛ ቢመረጥ፣ ከሞላ ጐደል ‹‹ህግን ከማክበርና ከማስከበር›› ውጭ፣ እንዳሻው አይሆንም፡፡ በተቀራኒው፤ ሁለተኛውን ግቢ እንመልከት፡፡
የግቢው ጐረቤታሞች፣ “ወይ እኔ ወይ  አንተ”፣ “ወይ ትዘርፋለህ፣ ወይ እዘርፋለሁ”፣ “ወይ ያልፍልሃል ወይ ያልፍልኛል”፣ “ወይ ያልቅልሃል፣ ወይ ያልቅልኛል” ቢባባሉ፣ እንዴት በሰላም መኖር ይችላሉ? ለጥፋት ተመቻችተዋልኮ፡፡
እንዲያው፤ “ልዩታችሁን በሃይል ለመፍታት ከመሞከር ይልቅ፣ በዲሞክራሲያዊ መንገድና በነፃ ምርጫ መፎካከር ትችላላችሁ” የሚል ምክር ብንሰጣቸው አስቡት፡፡ በምርጫ ያሸነፈ፣ “ያልፍለታል፣ ያሰኘውን ይፈጽማል”፣ የተሸነፈ ደግሞ፣ “ያልቅለታል፣ ይራቆታል”፡፡
እንዲህ አይነት ምርጫ፣ ከመነሻው ጤናማ አይደለም፡፡
በሕይወት ተወራርዶ ለመጠፋፋት፣ ወይም ኑሮን አስይዞ ለመበላላት የሚደረግ ቁማር፣ ከጤና ሊነሳ፣ ወደ ፍሬ ሊያደርስ አይችልም:: በተሳከረ ሃሳብ፣ በከሰረ አቅጣጫና በረከሰ ጉራንጉር ወደ ጥፋትና ክፋት የሚያወርድ ነው:: በአጣናና በሜንጫ ቀርቶ፣ በእጣ እና በምርጫ መበላላት ወይም መጠፋፋት፣ በምን ተዓምር ትልቅ ስኬት ሊሆንልን ይችላል?
በዱላና በጠመንጃ ከመጠፋፋት ተቆጥበን፣ በሃይልና በአመጽ ከመበላላት ታቅበን፣ “መብትንና ነፃነትን” አክብረን ለመጨፋጨፍ፣ ‹‹በሰላማዊና በዲሞክራሲያዊ ምርጫ›› ለመበላላት እንስማማ ተባብለን ብንፈራረምና ብንማማል ምን ዋጋ አለው? ውሎ በማያድር መከባበር፣ ከዛሬ ወደ ነገ በማይዘልቅ ሰላም፣ የትንቅንቅና የእልቂት ቀጠሮ መያዝ፣… እንዴት “ስኬታማ ፖለቲካ” ይባላል?  እንዲያው፣ ምርጫው፣ በሰላም ተጀምሮ ያለ እንከን በሰላም ቢጠናቀቅ እንኳ፤ በጭራሽ “የስኬት” ጠብታም ሆነ ሽታ አይኖረውም፡፡
እንዲህ አይነት የቁማር ፖለቲካ፣ ከሰላም ጋር አብሮ ሊሰነብት አይችልም፡፡
ለዚህም ነው፤ “ዲሞክራሲ” ወይም “ምርጫ” የሚሉ መፈክሮችን በቁንጽል የሚያራግቡ አገራት፣ የፖለቲካ ምርጫ የማካሄድ ሙከራቸው፣ አገርን የሚያቃውስ አስፈሪ አደጋ የሚሆንባቸው፡፡ በመጀመሪያው ምርጫ፣ አገር ይረበሻል፡፡ ዘገየ ከተባለ ደግሞ፣ በሁለተኛው ወይም በተከታዩ ምርጫ፣ አገር ይበጠበጣል፡፡ የብዙዎች ህይወት ይጠፋል፡፡ ንብረት ይዘረፋል፣ በቃጠሎ ይወድማል፡፡
ከዚያ ሁሉ ጥፋት በኋላስ? ከድሮው የባሰና ህግ የማይገዛው አምባገነን፣ አገር ምድሩን ሰጥ ለጥ አድርጐ ይገዛል፡፡ አልያም በየሰፈሩ የሚፈለፈሉ እልፍ ጥቃቅንና ጨካኝ የመንደር አምባገነኖች፣ አገሪቱን እያተራመሱ የምድር ሲኦል ያደርጓታል፡፡
ምን ለማለት ፈልጌ ነው? የፖለቲካ ምርጫ፣ በምኞት ብቻ ሰላማዊና ስኬታማ ሊሆን አይችልም ለማለት ፈልጌ ነው፡፡ በቅድሚያ የአገሬው ፖለቲካ ጤናማ መሆን አለበት፡፡
በአንድ በኩል፣ ለትክክለኛ የስነምግባር መርሆች ተገዢ መሆን አለበት - ፖለቲካው:: ቢያንስ ቢያንስ፣ ስነምግባር ላይ በግላጭ ከማመጽ የመቆጠብ ጨዋነት ሊኖር ይገባል:: በተቃራኒው፣ ውሸት እያናፈሱ የማሳመን፣ አሉባልታ እየነዙ የማምታታት፣ ሽንገላ እየደረደሩ የማስመሰል ፖለቲካ፣ ለምርጫ አይመችም፡፡
የአገራችን ፖለቲካ ግን ከዚህም በእጅጉ የባሰ ነው፡፡ በተረብ፣ በብሽሽቅና በስድብ በኩል ተሻግሮ፣ የሃሰት ውንጀላ፣ ጭፍን ጥላቻና የፀብ ዛቻ የበዛበት ፖለቲካ ነው የነገሰብን:: ብሔርና ብሔረሰብ ፣ ሃይማኖትና እምነት፣ ድሀና ሃብታም በሚሉ ሰበቦች በጐራ ማቧደን፣ ለጥፋት መቀስቀስና ለእልቂት ማዝመት፣ እንደ “ሃራም” ሳይሆን እንደ “ሃላል” የሚቆጠር ከሆነ፣ ፖለቲካው፣ ስነምግባር ላይ ያመፀ፣ አገርንና ዜጐችን የሚጠፉ ክፉ በሽታ ሆኗል ማለት ነው::
ከፖለቲካ በላይ ልቀው የሚከበሩ ትክክለኛ የስነምግባር መርሆች ሲኖሩ ግን፣ የአገሬው ፖለቲካ ጤናማ ሊሆን ይችላል - ፖለቲካው የስነምግባር ተገዢ ሲሆን)፡፡
በሌላ በኩል ደግሞ፣ የፖለቲካ ምርጫ፣ ክንውኑም ሆነ ውጤቱ፣ መራጮችም ሆኑ አሸናፊ ፓርቲዎችና ፖለቲከኞች ሁሉ፣ ለህግ የበላይነት ተገዢ መሆን አለባቸው፡፡ አንድ ግለሰብም ሆነ 50 ሚሊዮን መራጮች፣ ህግን የማክበር፣ የሰውን ንብረት ከመንካት የመታቀብ፣ የሰውን ሕይወት ከማጥቃት፣ (በአጠቃላይ ወንጀል ከመፈፀም) የመቆጠብ ግዴታ አለባቸው፡፡
አንዲት ነጠላ የድምጽ ብልጫ አግኝቶ ስልጣን የያዘ ፖለቲከኛ፣ አልያም በ99% የድጋፍ ድምጽ ያሸነፈ ፓርቲ፣ ሁሉም፣ ለህግ ተገዢ መሆን ይኖርባቸዋል፡፡
ይህም ብቻ አይደለም፡፡ በጠባብም ሆነ በሰፊ ልዩነት ተመርጠው ስልጣን ይዘዋልና፣ ህግን የማክበር ብቻ ሳይሆን የማስከበር፣ ወንጀልን ያለመፈፀም ብቻ ሳይሆን የመከላከል፣ የሰው ንብረትንና ሕይወትን ያለማጥቃት ብቻ ሳይሆን ከጥቃት የመጠበቅ የህግ ግዴታ አለባቸው፡፡ “በምርጫ አሸንፈናል፤ ተመርጠናል” በማለት፣ ያሻቸውን ነገር መፈፀም አይችሉም - የህግ የበላይነት በሰፈነበት ስልጡን ፖለቲካ ውስጥ፡፡
የፖለቲካ ምርጫ፣ እንዲህ ከህግ የበላይነት ስር የሚካሄድና ለህግ ተገዢ ሲሆን፣ ፖለቲካው ጤናማ፣ ምርጫውም ሰላማዊ ይሆናል፡፡
በእርግጥ፣ ይሄ ለዘንድሮ ምርጫ ብቻ ሳይሆን፣ ወደፊት ለበርካታ አመታትም፣ ብዙ ጥረትን የሚጠይቅ ዘላቂ መፍትሄ ነው፡፡ ነገር ግን፣ ዘንድሮ፣ ከምርጫው በሰላምና በጤና ለመትረፍ የሚጠቅሙ ተጨማሪና ጊዜያዊ መፍትሄዎችንም ማፈላለግ ይኖርብናል፡፡ የአገራችን ምርጫ ለአደጋ የተጋለጠ መሆኑን አይተናልና፡፡

Read 1800 times