Print this page
Monday, 13 January 2020 00:00

ቀጣዩ ምርጫና የፖለቲካ ድርጅቶች አሠላለፍ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(0 votes)

  6ኛው አገር አቀፍ ምርጫ በተያዘለት የጊዜ ቀነ-ገደብ መካሄዱ እንደማይቀር ብሔራዊ የምርጫ ቦርድ አስታውቋል፡፡ ምርጫው የሚካሄድ ከሆነ፣ከወዲሁ ምን ዓይነት ዝግጅቶች ማድረግ ያስፈልጋል? የፖለቲካ ፓርቲዎች አሠላለፍ ምን ይመስላል? ምርጫው በሰላም እንዲጠናቀቅ ከመንግስት፣ ከፓርቲዎችና ከህዝብ ምን ይጠበቃል? በሚሉና ከምርጫ ጋር በተያያዙ ጉዳዮች ዙሪያ የፖለቲካ ተንታኙ አቶ ሙሼ ሰሙ፣ ከአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሴ ጋር ተከታዩን ቆይታ አድርገዋል፡፡


            በቀጣይ ምርጫ የፖለቲካ ድርጅቶች አሠላለፍ  ምን ይመስላል?
የተፈጠረውን መልካም እድል ተጠቅመው ወደ ሀገር ውስጥ የገቡ በርካታ የፖለቲካ ድርጅቶች ናቸው፡፡ በእነዚህ ፓርቲዎች መካከል አንዳንድ ስትራቴጂያዊ የሆኑ ጥምረቶችና ውህደቶች እያየን ነው፡፡ ነገር ግን ብዙዎቹ ዘንድ መሠረታዊ የሆነ የርዕዮተ አለም ወይም የፖለቲካ አጀንዳ የለም፡፡ ህዝቡን በየትኛው የርዕዮት አለም አጀንዳ ወዴት ለመውሰድ እየተሞከረ እንደሆነም አይታወቅም፡፡ ስለ ልማት፣ ኢኮኖሚ፣ ዲሞክራሲና ሰብአዊ መብቶች ሁሉን አቀፍ በሆነ መልኩ የሚነሳ ነገር የለም፡፡ ሁሉም የየራሱን ብሔር ይዞ፣ በዚያ ዙሪያ ንትርክ በመፍጠር ተጠምዶ ነው እያየን ያለነው፡፡ አንዴ በሰንደቅ አላማ፣ ሌላ ጊዜ በቋንቋ፣ አንዳንዴ በሃይማኖት ዙሪያ ሽኩቻ እየተደረገ ነው ያለው:: አንዳንዶቹ ለምርጫ በሚመጥን ደረጃ ግልጽ የወጣ ርዕዮተ አለምም ሆነ አሠራር ይዘው አልመጡም - ከ“ብልጽግና” ፓርቲ በስተቀር፡፡ የ“ብልጽግና” ፓርቲን መደገፍና አለመደገፍ ሌላ ጉዳይ ነው፤ ነገር ግን ግልጽ ነገር ይዞ የቀረበው ይሄ ፓርቲ ነው፡፡ ምርጫውን ብናሸንፍ ሀገሪቱን የምንመራው በዚህ ርዕዮተ አለም፤ በዚህ የፖለቲካ አጀንዳ ነው ብለው የቀረቡት እነሱ ናቸው፡፡ ከዚያ በተረፈ ግን በተደራጀና ወጥ በሆነ መልኩ የሚታይ  ነገር የለም፡፡ በተደራጀና ወጥ በሆነ መልኩ ከፖለቲካ ርዕዮተ አለምም ከማህበራዊ ጉዳዮችም አንፃር ምንም ነገር የለም፡፡ ዝም ብሎ አዲስ አበባ የኛ ናት  አይደለችም፣ ቋንቋ ብሔራዊ ይሁን አይሁን፣ ባንዲራው ኮከብ ይኑረው አይኑረው፣ ክልል ልሁን አትሆንም ወዘተ -- የሚል ንትርክ ነው ስንሰማ የከረምነው፡፡ እስካሁን ምንም የጠራ ነገር አላየንም፡፡  
ሁሉም ፓርቲዎች በዚህ ዓይነት ውዝግብ ውስጥ ናቸው ብሎ መደምደም  ይቻላል?
በተወሰኑ ፓርቲዎች ዘንድ ያን ያህል ጉልህ ባይሆንም ጥረቶች ይታያሉ፡፡ ነገር ግን እነሱ ደግሞ ያን ያህል አቅሙ የላቸውም፤ ድጋፉንም አላሰባሰቡም፤ ተሰሚነታቸውን ገና ለማረጋገጥ እየታገሉ ያሉ ድርጅቶች ናቸው፡፡ በአጠቃላይ ግን ፓርቲዎቹ ራሣቸውን የአንድነት ሃይልና ፌደራሊስት የሚሉ ናቸው፡፡ ለእኔ የአንድነት ሃይል ነን የሚሉት ፌደራሊስት፣ በተቃራኒው ፌደራሊስት ነን የሚሉት ደግሞ የኮንፌደሬሽን ሃይሎች መስለው ነው የሚታዩኝ፡፡ የፌደራሊስት ሀይሎች የምላቸው፤ ኢትዮጵያ በፌደራል ስርአት ነው መተዳደር ያለባት፤ ነገር ግን ፌደሬሽኑ ቋንቋን ብቻ መሠረት ያደረገ ሳይሆን ሌሎች መስፈርቶች መካተት አለባቸው የሚሉ ናቸው፡፡ ሌሎቹ ደግሞ አሁንም ካለው በበለጠ ወደ ኮንፌደራሊስት የተጠጋ እንዲሆን የሚታገሉ ናቸው፡፡
አሁን እኮ በተጨባጭ ክልሎች ከማዕከላዊ መንግስት ቁጥጥር አፈንግጠው ነው ያሉት:: ኢትዮጵያ ፌደራሊስት ነች ይባላል እንጂ አሁን ኮንፌደራሊስት ሆናለች፡፡ እንደውም ካለፉት 27 አመታት በባሰ ደረጃ አሁን ነው ኮንፌደራሊስት የሆነችው፡፡ አንድ ክልል ውስጥ ፌደራል መንግስቱ ገብቶ ህግ ማስከበር፣ ስለ ልማት መነጋገር፣ ስርአት ማስያዝ፣ ሰብአዊና ዲሞክራሲያዊ መብቶችን ማስከበር የማይችልበት ደረጃ መድረሱን እያየን ነው:: በየትኛውም ክልል ቢሆን ይሄን ማድረግ አይቻልም፡፡ በጣም አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ነው ያለነው፡፡ ስለዚህ ለኔ አሁን ያለው የፖለቲካ አሠላለፍ ለፌደራሊዝም መጠናከር የሚታገሉ በአንድ ጐራ፣ በሌላ ጐራ ደግሞ ራሣቸውን ፌደራሊስት ሃይሎች ቢሉም ኢትዮጵያ ኮንፌደራሊስት እንድትሆን የሚታገሉ ሃይሎች ያሉበት ነው፡፡ ለምሣሌ፡- ትግራይ ፌደራሊስት ነኝ ይላል እንጂ በአሁኑ ወቅት ከመንግስት ቁጥጥር ውጪ የሆነ ክልል ነው:: ከዚህ በላይ የኮንፌደራሊስትነት መገለጫ ከየት ይመጣል፡፡ መንግስት በወንጀል የሚፈለጉ ሰዎችን በፈለገ ጊዜ ገብቶ መያዝ አልቻለም:: አሁን’ኮ ክልሎች ውስጥ የሚሠራውን ነገር የፌደራል መንግስቱ ማወቁን እጠራጠራለሁ:: ገንዘብ ተመድቦላቸዋል፤ ከዚያ በኋላ በክልላቸው ውስጥ ምን እየሠሩ እንደሆነ እንኳ የማይታወቅበት ሁኔታ ነው ያለው፡፡
በእርስዎ ዕይታ ተቋማትና ሀገረ መንግስቱ ምን ያህል ለምርጫ ዝግጁ ናቸው?
ይሄ አሁንም በጥያቄ ውስጥ ያለ ጉዳይ ነው:: ሀገሪቱ በሽግግር ውስጥ ነው ያለችው፡፡ ይሄ ሽግግር ደግሞ ብዙ ነገሮችን አደበላልቋል:: በዜጐች መሃል መተማመንን አጥፍቷል፡፡ በህዝቦች መሃል መተማመን የለም፡፡ በክልሎች ውስጥ ተንቀሳቅሶ መስራት አይቻልም፡፡ እንደኔ እይታ ግን፤ በጣም ምስቅልቅል ሁኔታ ሊፈጥር የሚችለው ምርጫውን አለማካሄድ ነው፡፡ ዋጋ ቢያስከፍልም ህጋዊ መሠረት የያዘን መንግስት ለማቆም ምርጫ ማድረግ ጠቃሚ ጉዳይ ነው:: ምርጫን አለማካሄድ ግን ወደ በለጠ ግጭትና ትርምስ የሚመራ ሁኔታን ይፈጥራል፡፡ የምርጫ አለመካሄድን ምክንያት አድርገው ሀገሪቱን ለማፍረስ አሰፍስፈው የሚጠብቁ ሃይሎች አሉ:: መንግስት ሀገሪቱን መምራት አልቻለም ብለው የራሳቸውን ክልላዊ መንግስት ለመመስረት ወይም ደግሞ በጉልበት ስልጣንን ለመንጠቅ የተዘጋጁ አሉ፡፡ ለእነዚህ ሃይሎች በር መክፈት አያስፈልግም፡፡ በሩን መዝጋት የሚቻለው ደግሞ ዋጋ የሚያስከፍል ቢሆንም፣ ቀጣዩን ምርጫ በማካሄድ ነው፡፡ የሚጠናከሩትን ተቋማት አጠናክሮ ወደ ምርጫ መግባት ያስፈልጋል፡፡  
ምርጫው ቢካሄድ ከጉዳቱ ጠቀሜታው ነው የሚያመዝነው፡፡ አንደኛ፤ ሰው ጊዜውንና ትኩረቱን ለምርጫ ጉዳይ ይሰጣል:: ውይይቶችን፣ ክርክሮችን ቅስቀሳዎችን፣ አማራጭ ሃሳቦችን ይሰማል፤ ይቀሰቅሳል፤ እጩ ይሆናል፤ ታዛቢ ይሆናል፤ በዚህ ሁሉ ሂደት ህዝብ ይሳተፋል፡፡ ይህ ተሳትፎ ደግሞ በህዝብ መካከል ያለውን ትስስር ይበልጥ ያጐለብተዋል፤ ያጠናክረዋል፤ መጥፎ ግንዛቤዎችን ይሸረሽራል:: ምርጫው ባይካሄድ ግን ሀገሪቱን ወደማያባራ ብጥብጥና ግጭት ውስጥ ይከታታል፤ ምክንያቱም የምርጫው ያለመካሄድ  አሁን ያለውን መንግስት ህጋዊነት ያሳጣዋል፡፡ ከዚያ በኋላ ሁሉም ነገር በጉልበት ነው የሚሆነው:: በነገራችን ላይ ምርጫው ዲሞክራሲያዊና ከእንከን የፀዳ ይሆናል ተብሎ አይታሰብም፡፡ እንዲህ ያለ ምርጫ በታሪካችንም አድርገን አናውቅም፡፡ በታሪካችን እርስ በእርስ የተማመንበትን ምርጫ አድርገን አናውቅም፡፡
እርስዎ ከምርጫው በፊት ሊደረጉ ይገባሉ የሚሏቸው ነገሮች  ምንድን ናቸው?
ያው ብዙዎች እንደሚሉት ብሔራዊ መግባባትና እርቅ ያስፈልገናል፡፡ ሰፋ ያሉ መድረኮች እየተዘጋጁ እርስ በእርስ የምንግባባበትና መሟሟቅ የምናደርግበትን ገንቢ ሥራ ብንሰራ ጥሩ ነው፡፡ ሰው እየተገናኘ ሲወያይ ከጥላቻና እርስ በእርስ ከመጠራጠር እንዲወጣ እድል ይሰጠዋል፤ መብትና ግዴታውን ለይቶ እንዲያውቅ ይረዳዋል፡፡ የጋራ ጥቅምና የተናጠል ጥቅምን ለይቶ እንዲያውቅ ያግዘዋል፡፡ ስለዚህ ወደ መግባባትና እርቅ የሚያደርሱ ውይይቶች በየደረጃው መደረግ አለባቸው፡፡ ሁለተኛ፤ የምርጫ ቦርድ ቅድመ ዝግጅት ወሳኝ ነው፡፡  ምን ያህል ምርጫውን ለማስተዳደር፣ የሚመጡትን ችግሮች ለመቀነስ ስልት ነድፏል የሚለው ጥያቄ መመለስ አለበት:: ዛሬ ኢትዮጵያ 120 ሚሊዮን ሕዝብ ያላት አገር ሆናለች፡፡ ምርጫ ቦርድ ሲፈጠር ደግሞ 54 ሚሊዮን ሕዝብ ነው የነበራት፡፡ በአቅምም፣ በሰው ሃይልም፣ በፋይናንስም የሚመጣጠን ነገር መኖር አለበት፡፡ ምርጫ ቦርድን በተለያዩ ኮሚቴዎች ማጠናከር ያስፈልጋል፡፡ የአደጋ ጊዜ ትንተና (Risk analisis) የሚሰሩ ባለሙያዎችን ያካተተ ኮሚቴ ማዋቀር ይገባል፡፡ ምርጫ ቦርድ ብቻውን ምርጫውን ይወጣዋል የሚል እምነት በግሌ የለኝም፡፡ ስለዚህ የተለያዩ ኮሚቴዎች በሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት አማካይነት መቋቋም ይኖርባቸዋል፡፡  
የዚህ ምርጫ ሌላው ገጽታ፣ አንዳንድ በብሔር ወይም በክልል የተደራጁ ፓርቲዎች “ክልላችን የኛ ስለሆነ ከኛ ውጪ ማንም አያሸንፍም” የሚል መቶ በመቶ መተማመን ውስጥ ገብተዋል፡፡ ያ መተማመን ደግሞ በምርጫ መሸነፍ ሲከሰት ምስቅልቅል ሁኔታን ይፈጥራል፡፡ ለእንደዚህ አይነት ችግሮች ቅድመ ዝግጅት የሚያደርግ ኮሚቴ ከምርጫ ቦርድ ውጪ ከወዲሁ መዘጋጀት አለበት፡፡ አደጋዎችን ከወዲሁ እያጠና… ይሄ ቢፈጠር ይሄን አደርጋለሁ፣ ይሄ መሰራት አለበት የሚል ሕጋዊ ሀይል ያስፈልጋል፡፡ ምርጫ ቦርድ በራሱ በሂደቱ በጣም ውጥረት ውስጥ ነው የሚሆነው፡፡ ስለዚህ ይሄን መሰል ኮሚቴ ማቋቋም ችግሩን ለመቀነስ በእጅጉ አጋዥ ነው፡፡ ሌላው ክልሎች የፌደራሉ ሥርዓት አካል መሆናቸውንና የፌደራል መንግሥቱ ሕጋዊ ጉዳዮችን የመፍታት ስልጣን እንዳለው እንዲያምኑ ማድረግ ያስፈልጋል:: ምክንያቱም ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎችን እያባረሩና አባሎቻቸውን እየገደሉ ሊቀጥሉ  አይችሉም፡፡ ይሄን ችግር እንዲፈቱ ከወዲሁ መወያየት አለባቸው፡፡ ተወያይተው ችግሩን በመፍታት፣ መተማመን በመፍጠር፣ መግባባት ላይ መድረሳቸውን ማረጋገጥ ይገባቸዋል፡፡  
በምርጫው ማን ሊያሸንፍ እንደሚችል መገመት የሚቻል  ይመስልዎታል?
እውነቱን ለመናገር፣ ከትግራይ ክልል በስተቀር መቶ በመቶ ለማሸነፍ ብቃቱም ዝግጅቱም ያለው ድርጅት አለ ብዬ አላምንም፡፡ ኦፌኮ፣ ኦነግ፣ ብልፅግና ሌላውም በየክልላቸው ይሄ አይነቱ አቅም አላቸው ብዬ አላምንም:: ስለዚህ ሊኖረን የሚችለው መንግስት ብዙ አይነት መልክ ያለው ነው፡፡ ምናልባት የቀደመ ጠንካራ አደረጃጀትም የተሻለ ዝግጅትም ያለው ብልጽግና ፓርቲ ምርጫውን በፌደራል ደረጃ ሊያሸንፍ ይችላል፡፡ ሌሎቹ በየክልላቸው ያለውን ወንበር ይከፋፈሉታል፡፡ ሂደቱ የሚመራው በተንኮል ካልሆነ፣ ከምርጫው ውጤት የሚገኘው ም/ቤት ጤናማ ሊሆን ይችላል፡፡ የተለያዩ ሃይሎች የሚፋጩበት ም/ቤት ሊኖረን ይችላል፡፡ ይሄ ደግሞ በአንድም ሆነ በሌላ መልኩ ለኢትዮጵያ ሕዝብ ጠቃሚ ነው፡፡
የሕወኃትና የብልጽግና ፓርቲ  አለመግባባት በአገሪቱ ላይ  የሚፈጥረው ችግር ይኖራል?
እኔ ይሄን የማየው ከመርህ አኳያ ነው:: ሕግን ከማክበርና ካለማክበር አንጻር ነው ማየት የምፈልገው፡፡ ሁለቱም ለሕግ ተገዥ መሆን አለባቸው፡፡ ሁለቱም ሕግን አክብረው በሕጋዊ መንገድ የሚለያዩ ከሆነ የሚፈጠር ችግር አይኖርም፡፡ አንዳቸው ግን ይሄን አጋጣሚ ተጠቅሜ፣ በሕዝብ ላይ ግርግር እፈጥራለሁ የሚሉ ከሆነ ችግር ያጋጥመናል፡፡ ግን ችግሩ አገሪቷን የማፍረስ አቅም አይኖረውም፡፡ የሚያሸንፈው አሸንፎ አገሪቱ ትቀጥላለች እንጂ በዚህ የሚፈጠረው ችግር አገር ያፈርሳል የሚል እምነት የለኝም፡፡ የፓርቲ መጣመር፣ መዋሃድና መፍረስ ጉዳይ ተፈጥሯዊ ነው፤ ከዚህ የተለየ ሆኖ አይታየኝም፡፡ ነገር ግን ይሄን ተፈጥሯዊ ሂደት በሃይል ለማስተዳደር ከተሞከረ ነው ችግር የሚፈጠረው፡፡ ችግሩ ሲፈጠር ደግሞ ዋጋ የሚከፍሉት ፓርቲዎቹ ሳይሆኑ ሕዝብ ነው፡፡ ስለዚህ ሕዝቡ ነው ጥንቃቄ ማድረግ ያለበት፡፡ ነገሩን በአግባቡም መገንዘብ አለበት:: ይሄ የፓርቲዎች ጉዳይ ነው ብሎ ለነሱ መተው ይገባዋል፡፡ አሁንም እነዚህ ሃይሎች በሕጋዊ መንገድ ሕግ አክብረው ነው መለያየት ያለባቸው፡፡
ከዚህ ውጪ ችግር እፈጥራለሁ የሚል ለራሱም አይሆንም፤ ግን አገር የማፍረስ አቅም ፈጽሞ አይኖረውም፡፡ ያለፈ ታሪክን ወደፊት አምጥቶ ሂሳብ ለማወራረድ ከመሞከር መጠንቀቅ አለባቸው፡፡ ሂሳብ እናወራርዳለን ብለው ያልሆነ ነገር ውስጥ ከገቡ ግን ሕዝብ ሁሉንም ነው ጠራርጎ የሚበላቸው፡፡ ሕዝብ የፖለቲካ ፓርቲ አሽከር አይደለም፤ ፓርቲ ነው የሕዝብ አሽከር፡፡ ፓርቲዎች ሥርዓት ካልያዙ፣ ህዝቡ በሚቀጣቸው መንገድ ይቀጣቸዋል፡፡    


Read 3157 times