Saturday, 28 December 2019 13:58

የ2019 የአለማችን አክራሞት - በወፍ በረር

Written by 
Rate this item
(5 votes)

 ሊጠናቀቅ የሶስት ቀናት ዕድሜ ብቻ በቀረው የፈረንጆች አመት 2019 አለማችን ብዙ ክፉና ደጎችን አስተናግዳለች፡፡ እጅግ አሳዛኝና አስደንጋጭ ነገሮች በተፈጸሙበት፣ በርካታ በጎና አስደሳች ነገሮች በተሰሙበት፣ ብዙዎችን ጭንቀትና ፍርሃት ውስጥ የከተቱ በርካታ ፖለቲካዊ፣ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ክስተቶች በተስተናገዱበት የተገባደደው የፈረንጆች አመት 2019፤ የአለማችን መገናኛ ብዙሃን ትኩረት ሰጥተው ከዘገቧቸው አንኳር ጉዳዮች መካከል የተወሰኑትን መራርጠን እነሆ ብለናል፡፡
የተቃውሞና የአመጽ ማዕበል
የተገባደደው የፈረንጆች አመት 2019 ሰበብ ምክንያቱም ሆነ አላማና ግቡ ይለያይ እንጂ ከአፍሪካ እስከ እስያ፣ ከአውሮፓ እስከ መካከለኛው ምስራቅና አሜሪካ አለማችን በያቅጣጫው በተቃውሞ ስትናጥ የከረመችበት የተቃውሞና የአመጽ አመት ነበር፡፡ ከሊባኖስ እስከ ባርሴሎና፣ ከእንግሊዝ እስከ ጣሊያን፤ አለማችን ዙሪያ ገባውን በተቃውሞ እሳት ስትለበለብ ነው አመቱን የገፋችው፡፡
ቦሊቪያውያን በቅርቡ በተካሄደው ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ፤ “የህዝብን ድምጽ አጭበርብረው አሸናፊነታቸውን አውጀዋል” ያሏቸውን ፕሬዚደንት ኢቮ ሞራሌስ፤ ለመቃወም እሳት ለብሰው እሳት ጎርሰው፣ አደባባይ በመውጣት ከፖሊስ ሲተናነቁና በተቃውሞ ማዕበል አገሪቱን ሲያጥለቀልቋት ከርመዋል፡፡
በቺሊ ባለፈው ጥቅምት ወር የትራንስፖርት ዋጋ ጭማሪ መደረጉን ተከትሎ፣ ጉዳዩ ያስቆጣቸው የአገሪቱ ዜጎች፤ የመዲናዋን ሳንቲያጎ ጎዳናዎች በማጥለቅለቅ ተቃውሞ ከማሰማት አልፈው መደብሮችን መዝረፍና አውቶብሶችን ማቃጠላቸውን ተያያዙት፡፡
 የህዝቡ ቁጣ ያሳሰበው የአገሪቱ መንግስትም ነገሩ ከቁጥጥር ውጭ ከመሆኑ በፊት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በማጽደቅ ሁኔታዎችን ለማረጋጋት ደፋ ቀና ሲል ከርሟል፡፡
የኢኳዶር መንግስት ለአስርት አመታት ያህል በነዳጅ ዋጋ ላይ ሲያደርግ የዘለቀውን ድጎማ ማንሳቱን ተከትሎ፣ የአገሪቱ ዜጎች በተቃውሞ ጎዳናዎችን ያጥለቀለቁትም ሆነ በሆንግ ኮንግ በታሪኳ አይታው በማታውቀው ማብቂያ የሌለው፣ ለወራት የዘለቀ ተቃውሞ የታመሰችው በዚሁ የ2019 አመት ነው፡፡
የአለማችን አገራት በተቃውሞ የሚታመሱበት ሰበብ እየቅል ቢሆንም፣ በተደጋጋሚ ለተቃውሞ ምክንያት ሆነዋል ብሎ ሮይተርስ ከጠቀሳቸው ዋነኛ ጉዳዮች መካከል አንዱ ነው - ኢኮኖሚ፡፡ ኢኳዶር፣ ቤሩት፣ ሃይቲና ኢራቅን ጨምሮ በአመቱ በበርካታ አገራት የተቀሰቀሱት ተቃውሞዎች፤ ዜጎችን ባስቆጡ የመንግስታት ኢኮኖሚያዊ እርምጃዎች ሳቢያ መሆኑን ሮይተርስ ዘግቧል፡፡
በአወዛጋቢ የስራ ፈቃድ አዋጅ ተጀምሮ ሌሎች ጥያቄዎችን እያግተለተለ ላለፉት አምስት ወራት የዘለቀውን የሆንግ ኮንግ ተቃውሞ ጨምሮ በተለያዩ አገራት ዜጎችን ለተቃውሞ ያስወጣ ሌላኛው ምክንያት ተብሎ የተጠቀሰው ደግሞ የፖለቲካዊ ነጻነት ወይም የሉአላዊነት ጥያቄ ነው፡፡ የስፔን መዲና ባርሴሎናን ጎዳናዎች በመቶ ሺዎች በሚጠጉ ካታሎናውያን ያጥለቀለቀው የጋለ የተቃውሞ ሰልፍም ለአመታት ከዘለቀ የመገንጠልና ራሱን የቻለ ሉአላዊ አገር የመፍጠር ጥያቄ ጋር የተያያዘ መሆኑን ነው ሮይተርስ ያስነበበው፡፡ መንግስት በሙስና ተጨማልቋል፤ ሹመት በዝምድናና በውግንና ሆኗል፤ ባለስልጣናት ከዜጎች በሚዘርፉት ሃብት የግል ካዝናዎቻቸውን እየሞሉ ነው የሚሉና መሰል የሙስና ምሬት የወለዷቸው ተቃውሞዎች ከተቀሰቀሱባቸው አገራት መካከልም ሊባኖስ፣ ኢራቅና ግብጽ እንደሚገኙበትም ቢቢሲ ዘግቧል፡፡
በአመቱ በተለያዩ የአለማችን አገራት በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ተቃዋሚዎችን አደባባይ ያስወጣው ሌላኛው የተቃውሞ ሰበብ ደግሞ የአየር ንብረት ለውጥ ነው፡፡ መንግስታት ለአየር ንብረት ለውጥ በቂ ትኩረት እንዲሰጡ የሚጠይቁ በርካታ ተቃዋሚዎች፤ ከአሜሪካ እስከ እንግሊዝ፣ ከጀርመን እስከ ስፔን፣ ከኦስትሪያ እስከ ፈረንሳይና ኒውዚላንድ ጎዳናዎችን ያጥለቀለቁትም በዚሁ አመት ነበር፡፡
አፍሪካ
የተገባደደው አመት 2019 አፍሪካ ከአወዛጋቢ ምርጫዎች እስከ አሰቃቂ የስደት አደጋዎች፣ ከተፈጥሮ አደጋዎች እስከ ፖለቲካና ኢኮኖሚ ቀውሶች በርካታ ጉልህ ክስተቶችን ያስተናገደችበት ነበር፡፡ ከሶስት አስርት አመታት በላይ ሱዳንን አንቀጥቅጠው የገዙት ኦማር አልበሽር፤ መሬት በሚያንቀጠቅጥ ህዝባዊ ተቃውሞ ከመንበረ ስልጣናቸው ወርደው ወደ እር ቤት የተሸኙበት፤ የዚምባቡዌው መሪ ሮበርት ሙጋቤ፤ ከስልጣን ወርደው ወደ መቃብር የተሸኙበት ታሪካዊ አመት ነበር - 2019፡፡
የደቡብ አፍሪካውን የመጤ ጠልነት ጥቃት ጨምሮ አፍሪካ በአመቱ ካስተናገደቻቸው አሳዛኝ ክስተቶች መካከልም፣ በወርሃ መጋቢት በሞዛምቢክ የተከሰተውና ብዙዎችን ለሞትና ለመፈናቀል የዳረገው ሳይክሎን ኢዳይ የተባለው ጎርፍ እንዲሁም በዚምባቡዌና በማላዊ የተከሰቱት አደገኛ የተፈጥሮ አደጋዎች የሚጠቀሱ ሲሆን፣ በምስራቃዊ አፍሪካ ከፍተኛ ዝናብ 2.8 ሚሊዮን ያህል ሰዎችን ተጎጂ ማድረጉ ይነገራል፡፡
ከሁለት አስርት አመታት በላይ ተኳርፈው የኖሩትን ኢትዮጵያና ኤርትራ ባልተገመተ ሁኔታ ወደ ሰላም ያመጡት ጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ አህመድ የኖቤል የሰላም ተሸላሚ በሆኑበትና አገራችን ሳተላይት ያመጠቀችበትን አዲስ ታሪክ የጻፈችበት የ2019 አመት፣ አፍሪካ ካስተናገደቻቸው ሌሎች በጎ ክስተቶች መካከል የሚጠቀሰው ጉዳይም በምዕራብ አፍሪካ አገራት በሺህዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን ለሞት ለዳረገው የኢቦላ ቫይረስ መድሃኒት የመገኘቱ የምስራች አንዱ ነበር፡፡
ምርጫ
2019 ዩክሬን፣ እንግሊዝ፣ ፖላንድ፣ ኢራቅ፣ አፍጋኒስታን እና ሲሪላንካን ጨምሮ በአለም ዙሪያ የሚገኙ በርካታ አገራት ምርጫ ያከናወኑበት አመት እንደነበር ያስታወሰው ዘጋርዲያን በበኩሉ፣ መንግስት ለመመስረት የሚያስችል ድምጽ በመታጣቱ ለሶስተኛ ጊዜ ምርጫ ለመመስረት የተዘጋጀችውን እስራኤል ምርጫ በተለየ ሁኔታ ጠቅሶታል፡፡
በአመቱ ናይጀሪያ፣ ቦትሱዋና፣ ሴኔጋል፣ ናሚቢያ፣ ሞዛምቢክና ጊኒ ቢሳኡን ጨምሮ በበርካታ የአፍሪካ አገራት ምርጫ የተከናወነ ሲሆን፣ እንደተለመደው አብዛኞቹ አገራት ምርጫን ተከትሎ በሚፈጠር ብጥብጥና ተቃውሞ በርካታ ዜጎቻቸውን በሞት ያጡበት እንደነበር ቢቢሲ አስታውሷል፡፡
ስደት
ተመድ ባለፉት አስር አመታት የ23 በመቶ ጭማሪ ያሳየው የአለማችን ስደተኞች ቁጥር፣ በፈረንጆች አመት 2019 በመላው አለም የስደት ህይወትን በመግፋት ላይ የሚገኙ ሰዎች ቁጥር 272 ሚሊዮን መድረሱን ያስታወቀውም ባለፈው ወር ባወጣው አለማቀፍ የስደት ሁኔታ አመላካች ሪፖርቱ ነበር፡፡
በፈረንጆች አመት 2019 በአውሮፓ 82 ሚሊዮን፣ በሰሜን አሜሪካ 59 ሚሊዮን በሰሜን አሜሪካና ምዕራብ እስያ አገራት ደግሞ በተመሳሳይ 49 ሚሊዮን ያህል ሰዎች የስደት ህይወትን በመግፋት ላይ እንደሚገኙ የጠቆመው ተመድ፤  ከአለማችን 272 ሚሊዮን ስደተኞች መካከል ግማሽ ያህሉ በአስር አገራት ውስጥ እንደሚኖሩም ገልጧል፡፡
ብዙ ዜጎቿ የተሰደዱባት ቀዳሚዋ የአለማችን አገር ህንድ ናት ያለው ሪፖርቱ፤ 18 ሚሊዮን ህንዳውያን አገራቸውን ጥለው በመሰደድ በሌሎች አገራት ኑሯቸውን እየገፉ እንደሚገኙም አመልክቷል፡፡ ከአለማችን የህዝብ ቁጥር እድገት ይልቅ የአለማችን ስደተኞች ቁጥር እድገት ብልጫ እንዳለው የገለጸው ሪፖርቱ፣ በተገባደደው የፈረንጆች አመት በስደት ላይ ከሚገኙት 272 ሚሊዮን ስደተኞች መካከል 48 በመቶው ሴቶች መሆናቸውንም አስታውቋል፡፡
አለማቀፉ የስደተኞች ድርጅት ከቀናት በፊት ባወጣው አመታዊ ሪፖርት እንዳለው፣ በአመቱ በአለማችን የተለያዩ ክፍሎች 3 ሺህ 170 ያህል ስደተኞች ድንበር አቋርጠው የስደት ጉዞ በማድረግ ላይ እያሉ ለህልፈተ ህይወት ተዳርገዋል፡፡
በአመቱ በስደት ላይ ሳሉ ለሞት ከተዳረጉ ስደተኞች አመካከል ከፍተኛውን ቁጥር የሚይዙት ሜዲትራኒያን ባህርን አቋርጠው ወደተለያዩ የአውሮፓ አገራት ለመጓዝ ሲሞክሩ የነበሩ አፍሪካውያን ስደተኞች መሆናቸውንና በአመቱ በወር 10 ሺህ ያህል ስደተኞች ከአፍሪካ ቀንድ ወደ የመን ተሻግረዋል ተብሎ እንደሚታመንም ድርጅቱ አስታውሷል::
አስከፊ የተፈጥሮ አደጋዎች
2019 የአየር ንብረት ለውጥ ያስከተላቸው በርካታ የተፈጥሮ አደጋዎች በተለያዩ የአለማችን አገራት በርካቶችን ለሞትና ለመፈናቀል አደጋ የዳረገበት አመት እንደነበር መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ በአመቱ 10 የተፈጥሮ አደጋዎችን አስተናግዳ 1 ቢሊዮን ዶላር የሚገመት ጉዳት የደረሰባት አሜሪካን ጨምሮ በተፈጥሮ አደጋዎች ሳቢያ በርካታ አገራት ኢኮኖሚያቸው ክፉኛ መጎዳቱን የጠቆመው የአለም የሜትሪዮሎጂ ኤጀንሲ፣ ለአብነትም በሞዛምቢክ የተከሰተውንና በቢሊዮኖች የሚቆጠር ዶላር ጉዳት ያደረሰውን የጎርፍ አደጋ ያስታውሳል፡፡
መስከረም ወር ላይ ባህማስን የመታው ሃሪኬን ዶሪያን፣ በነሃሴ ወር ቻይና ውስጥ ተከስቶ 72 ሰዎችን ለሞት የዳረገው ታይፎን ሌኪማ፣ በጥቅምት ወር ላይ በጃፓን ተከስቶ 80 ሰዎችን የገደለው ታይፎን ሃግቢስ፣ በሰኔ 90 ህንዳውያንንና ከ160 በላይ ጃፓናውያንን ለሞት የዳረጉት የሃይለኛ ሙቀት ክስተቶች፣ 900 የአፍሪካ አገራት ዜጎችን ለሞት የዳረገው ሳይክሎን ኢዳይ እንዲሁም በ14 የአፍሪካ አገራት 45 ሚሊዮን ሰዎችን ለተረጂነት የዳረገው ድርቅ አለማችን ካስተናገደቻቸው በርካታ የተፈጥሮ አደጋዎች መካከል የሚጠቀሱ ናቸው፡፡
የትራምፕ መከሰስ
አመቱ እየተገባደደ ባለበት የመጨረሻው ወር ላይ ከተከሰቱና የመገናኛ ብዙሃንን ቀልብ ከሳቡ የአመቱ ጉልህ አለማቀፋዊ ክስተቶች ተርታ የሚሰለፈው ሌላው ጉዳይ ደግሞ የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ መከሰስ ነው:: የአሜሪካ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት፤ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ስልጣናቸውን ያላግባብ በመጠቀምና የምክር ቤቱን ስራ በማደናቀፍ እንዲከሰሱና ከስልጣናቸው እንዲወርዱ በአብላጫ ድምጽ መወሰኑን ተከትሎ ነበር፣ ትራምፕ በአገሪቱ ታሪክ ሴኔት ፊት ቀርበው ክሳቸውን እንዲከላከሉ የተወሰነባቸው ሶስተኛው ፕሬዚዳንት ሆነው በታሪክ መዝገብ ላይ የሰፈሩት፡፡
ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ፣ የዩክሬን አቻቸው ቭላድሚር ዘለንስኪን በቀድሞው የአሜሪካ ምክትል ፕሬዚዳንትና በምርጫ ተቀናቃኛቸው ጆ ባይደን እና በልጃቸው ላይ የሙስና ምርመራ እንዲያደርጉ በመደለልና ጫና በማድረግ ስልጣንን ያለአግባብ በመጠቀም፤ እንዲሁም ከዚህ ጋር በተያያዘ ለሚደረግባቸው ምርመራ መረጃዎችን ባለመስጠትና የምክር ቤቱን ስራ በማደናቀፍ እንዲከሰሱ በቀረበባቸው የውሳኔ ሃሳብ ዙሪያ፣ ለአስር ሰዓታት ያህል ከተደረገ ክርክር በኋላ ነበር፣ የምክር ቤቱ አባላት ፕሬዚዳንቱ  እንዲከሰሱና ሴኔት ፊት ቀርበው የቀረቡባቸውን ክሶች እንዲከላከሉ በአብላጫ ድምጽ የወሰኑት፡፡
ሴኔቱ የተገባደደውን አመት ሸኝቶ ከሳምንታት በኋላ ዳግም ተገናኝቶ በጉዳዩ ዙሪያ በመምከር ውሳኔ ያሳልፋል ተብሎ የሚጠበቅ ቢሆንም፣  ትራምፕ ስልጣናቸውን የሚለቅቁት ከሴኔቱ አባላት ሁለት ሶስተኛው የድጋፍ ድምጽ ከሰጡበት ብቻ ነው፡፡  ሴኔቱ ሪፐብሊካን የሚበዙበት እንደመሆኑ ግን በፕሬዚዳንቱ ላይ ውሳኔው የመተላለፉ ዕድል አነስተኛ እንደሆነ የሚናገሩ ብዙዎች ናቸው::  ብዙዎች እንደገመቱት ሳይሆን ቀርቶ፣ ሴኔቱ ፕሬዚዳንት ትራምፕ ከስልጣን እንዲሰናበቱ ውሳኔ የሚያስተላልፍ ከሆነ፣ ምክትላቸው ማይክ ፔንስ በመጪው አዲስ አመት ስልጣኑን ተረክበው እስከ ቀጣዩ 2021 የአሜሪካ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ አገሪቱን ያስተዳድራሉ ተብሏል፡፡
በሞት የተለዩ ዝነኞች
ከፖለቲካው መስክ የዚምባቡዌው የቀድሞ ፕሬዚዳንት ሮበርት ሙጋቤ፣ የቀድሞው የፈረንሳይ ፕሬዚዳንት ዣክ ሲራክ እና የግብጹ አቻቸው ሞሃመድ ሙርሲ ከዚህ አለም በሞት የተለዩበት 2019፣ አለማችን በተለይ በመዝናኛው መስክ ስማቸውን በደማቁ ለማስጻፍ የቻሉ በዛ ያሉ ዝነኞችን በሞት ያጣችበት አመት እንደነበር ዘገባዎች ያመለክታሉ፡፡
የአሜሪካን ትልቁ የክብር ሽልማት የፕሬዚደንቱ የነጻነት ሜዳይ የተቀበሉትና የኖቤል የስነጽሁፍ ተሸላሚዋ አሜሪካዊት ደራሲ ቶኒ ሞሪሰን ባለፈው ነሃሴ ነበር በተወለዱ በ88 አመታቸው ከዚህ አለም በሞት የተለዩት፡፡
አለማቀፍ ዝናን ያተረፈው ኤርትራዊው ራፐር ኒፕሲ ሃስል ባልታወቁ ሰዎች በተተኮሰበት ጥይት በ33 አመቱ ከዚህ አለም በሞት በተለየበት፣ በተገባደደው የፈረንጆች አመት 2019 ይህቺን አለም በሞት ከተለዩት ሌሎች የአለማችን ዝነኞች መካከል የሚጠቀሰው ደግሞ በአውሮፕላን አደጋ ለሞት የተዳረገው አርጀንቲናዊው የእግር ኳስ ተጫዋች ኢሚሊያኖ ሳላ ነው፡፡
በአመቱ ከዚህ አለም በሞት ከተለዩ ሌሎች ስመጥር የአለማችን ሰዎች መካከልም ታዋቂው ፈረንሳዊ የሙዚቃ ቀማሪና የጃዝ ፒያኒስት ሚሼል ሌግራንድ፣ የቀድሞው የጃፓን ጠቅላይ ሚኒስትር ያሱሺሮ ናካሶኔ፣ የአይሲሱ መሪ አቡበከር አል ባግዳዲ፣   የቀድሞ የህንድ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሱሻማ ስዋራጅ፣ የቀድሞው የአርጀንቲና ፕሬዚዳንት ፈርናንዶ ዲ ላ ሩኣ ይገኙበታል፡፡
ሌሎች ጉልህ ክስተቶች
የጋዜጠኛ ጀማል ካሾጊ ግድያ፣ ቦሪስ ጆንሰንን በጠቅላይ ሚኒስትርነት የመረጠውን የእንግሊዝ መንግስት አመቱን ሙሉ ወጥሮ ይዞት የዘለቀውና ከጫፍ የደረሰ የሚመስለው የአገሪቱ ከአውሮፓ ህብረት አባልነት የመውጣት ዕቅድ፣ የኢራን የአንግሊዝን የነዳጅ ታንከር መቆጣጠሯ፣ ተካርሮ የቀጠለው የአሜሪካና የቻይና የንግድ ጦርነት፣ ንብረትነቱ የኢትዮጵያ አየር መንገድ የሆነው የቦይንግ አውሮፕላን መከስከስ፣ የአሸባሪው ቡድን አይሲስ መሪ አቡበከር አልባግዳዲ መገደሉ፣ የሜሲ ለ6ኛ ጊዜ የባሎንዶር የወርቅ ኳስ ተሸላሚ መሆን እና የአማዞን ጫካ ቃጠሎም በአመቱ አለማችን ካስተናገዳቻቸውና የመገናኛ ብዙሃንን ትኩረት ስበው ከከረሙ ሌሎች በርካታ ጉልህ ክስተቶች መካከል የሚጠቀሱ ናቸው፡፡


Read 12143 times