Saturday, 28 December 2019 13:44

ሰባት ጊዜ ሰባት

Written by  መሃመድ
Rate this item
(8 votes)

    ንግስት አዜብ በሳባውያን ህዝቦች በነገሰች በሰባተኛው አመት፣ ሰባተኛው ወር፣ ሰባተኛው ቀን፤ ሰባት ልጆች ያሉት የሰባ ሁለት አመቱ አዛውንት አሳ አጥማጅ፤ ስድስት ቀናት ሙሉ ባህሩ ላይ መረቡን ቢዘረጋም፤ አንድም አሳ ሳያጠምድ በለስ ሳይቀናው ሰንብቶ፣ በሰባተኛው ቀን እግዚአብሄር ጎበኘው፡፡ መረቡን ከባህር ሊያወጣ ሲጎትት በጣም ስለከበደው፣ በደከመ ክንዶቹ መጎተት ረዳት የሚጠይቅ ስራ ነበር፡፡ ቢሆንም ሰባቱ ወንድ ልጆቹ፤ ስንፍና ያጠቃቸው ስለሆኑ ዕድሉን እያማረረ መረቡን ጎተተ፡፡ መረቡ ከባህሩ ሲወጣ ይዞት የመጣው አሣ ሳይሆን ትልቅ የእንጨት ሳጥን ነው፡፡  
“.ያንተ ያለህ!” አለ አዛውንቱ፤በመደነቅ አፉንም አይኖቹንም በሰፊው ከፍቶ፡፡
አንድ ንጉስ የጣለው የተደበቀ ሃብት ይሆን? ምናልባት ሰባት ሺህ የወርቅ ዲናር የሚያወጣ!
ዞር ዞር ብሎ አካባቢውን ቃኘ፡፡ የሰው ዘር የለም፡፡ “አሁን ይህን ሳጥን ባህር ውስጥ መጣል ምን ሊባል ይችላል? ከንቱ ስራ እንዳልሆነ ግልፅ ነው፡፡ አንድ ሚስጥር መኖር አለበት፡፡ ለምሳሌ ሃብቱን መደበቅ ያሰበ አንድ ግለሰብ፤ ከዚህ ባህር ውጭ መደበቅያ ቦታ የት ሊያገኝ ይችላል? ጥልቅ ዋናተኛ ሊሆን ይችላል፡፡ በፈለገው ጊዜ ገብቶ ሊያወጣው የሚችል” ለራሱ አንሾካሸከ፡፡ ይህ ሽማግሌ አሣ አጥማጅ፤ በመንደሩ ሰዎች “ዕድለ ቢሱ አሣ አጥማጅ” በመባል የሚታወቅ ሲሆን ሁልጊዜ መረቡ ባዶ ሆኖ የሚመለስ ገደ ቢስ ነው፡፡ ሰውየው ያያት የቅድመ አያት እርግማን ቢኖርበት ነው፡፡ ሃብቱ ጥቂት፣ ዕድሉ ጠማማ የሆነው እያሉ፣ የመንደሩ ሰዎች ያንሾኮሹካሉ፡፡ ይህ እርግማን የሰባት ዘር ማንዘሩ- አያት ቅድም ቅም አያት፣ እንዥላት እንዝላት --- በሰሩት ስራ ተረግሞ ከሆነ፣ እርግማኑ ዛሬ ተሰብራል፡፡
    ሳጥኑን ከፈተ፡፡ ከአንድ ጠርሙስ በስተቀር ምንም የለም፡፡ ሽማግሌው አይኖቹ እንባ አቀረሩ፡፡ ይህንን ዘመን ሁሉ ቅዱስ መፅሐፍ ሲያነብ ለፈጣሪ ሲገዛ ቢኖርም --- አሁንም ፈጣሪ እሱን አያይም!? ጠርሙሱን አነሳና ተመለከተው፡፡ “የእስራኤል ንጉስ ሰለሞን፤ የዳዊት ልጅ” የሚል ፅሑፍ ባለበት ማህተም ታሽጓል፡፡ አተኩሮ ተመለከተው፡፡ ውስጡ ባዶ ነው፡፡  ማህተሙን ገንጥሎ ነቀለው፡፡ ከጠርሙሱ ለይ የተቀመጠበት ታንኳ ተንቀጠቀጠ፡፡ ባህሩ ተናወጠ፡፡ ሽማግሌው ደንግጦ ወደ ኋላ አፈገፈገ፡፡ ሃይለኛ ጢስ ከጠርሙሱ ወጣና ወደ ላይ ተቆለለ፡፡ ወዲያው የሰው ቅርፅ ያዘና አስፈሪ ፊት  ያለው አይኖቹ፣ እንደ እሳት የሚንቦገቦግ ፍጡር ቁልቁል ይመለከተው ጀመር፡፡
“ምንድን ነህ?” ጠየቀ፤ ሽማግሌው እየተርበደበደ፡፡
“የማትረባ ጭቃ ፍጡር.. እስከዛሬ ከተፈጠሩት ሃይለኛ አጋንንቶች አንዱ”
“ምን ታደርጋለህ ጠርሙሱ ውስጥ?”
 “ያንተው ቢጤ ጠቢብ ነኝ ባይ ሰለሞን፤ በቤቱ አስሮኝ! አይ እናንተ ሰዎች… አጋንንቶች እያላችሁ ትሰድቡናላችሁ… ነገር ግን እርስ በእርሳችሁ በመተት ስትተባተቡ፣ የኛን እግር ትልሳላችሁ… ብጢያችሁን ለመግደል ለኛ ትሰግዳላችሁ… ቱፍ” ብሎ ተፋና፤ “ያንተው የእግዚአብሄር ሰው ተብዬው ሰለሞን እውነተኛ የእግዚአብሄር ሰው ቢሆን… አንድን ፍጡር ሰባት መቶ አመት ጠርሙስ ውስጥ ያሽጋል?”
“ሰባት መቶ አመት?”
“አዎና” ጥርሱን አፏጨ፤ “እኔ ሰባት መቶ አመት መከራዬን ሳይ --- እሱ ግን ከሰባት መቶ ሚስቶቹ ጋር ይምነሸነሻል” አለ ጥርሱን እያፏጨ፡፡
“ለምን አትመጣም ነበር?”
“በማህተሙ አሰረኝ… ከሰባቱ ማህተሞች አንዱ አልጨረሰም፡፡”
“እና እኔ ምን አጠፋሁ?”
“የቃል ጉዳይ ነው፤ እኛና እናንተ ጠላቶች ነን፡፡ ሰብ (ሰው ማለት) አራቱ ባህሪያት፡- ስጋ፣ አፈር፣ ውሃ ንፋስና   ከሶስቱ ባህሪያት ነፍስ - ሰባት! ፈጣሪ ለናንተ ብቻ ምን ስለሆናችሁ፣ አሁን ለመሞት ተዘጋጀ?!”
 “ምን አጠፋን?”
ጂኒው የበለጠ ሳቅ ሳቀና “የመጀመሪያው መቶ አመት ከዚህ ባህር አውጣኝ፤ ዕድሜ ልኬን ባርያ እሆናለሁ ቃሌ ነበር፡፡ በሁለተኛው መቶ አመት የአልማዝ ተራራ እሰጠዋለሁ፡፡ በሶስተኛው መቶ አመት የወርቅ ተራራ፡፡ በአራተኛው መቶ አመት የብር፡፡ በአምስተኛው የመዳብ፡፡ በስድስተኛው የነሃስ፡፡ በሰባተኛው ግን እገድለዋለሁ አልኩኝ፡፡  ይኸው በሰባት መቶኛ አመት አንተ አመጣኸኝ፡፡ ስለዚህ ልገድልህ ነው”
ሽማግሌው አይምሮውን ማሰራት ጀመረ፤ “አንተ ውሸታም ነህ” ባህሩ ተናወጠ፡፡ ጂኒው በቁጣ ጮኽ፡፡ ፊቱን ከሽማግሌው ፊት በስንዝር ርቀት አስጠግቶ፤ “መጥፎ ብሆንም ውሸታም አይደለሁም “
“እንዴት እንዳንተ ያለ ግዙፍ ፍጥረት-- እዚህ ጠባብ ጠርሙስ ውስጥ ሊገባ ይችላል?”
“አላመንከኝም”
“የማይመስል ነገር ነው”
“አሳይሃለሁ “
ጂኒው ተኮማትሮ ተነሳና ጠርሙሱ ውስጥ ገባ፡፡
“አየኸኝ?” አለ ጠርሙሱ ውስጥ ተወትፎ፡፡
አሣ አጥማጁ ማህተሙን አነሳና የጠርሙሱን አፍ ደፈነው፡፡ ጂኒው ጠርሙሱ ውስጥ ተወትፎ አይኖቹን አቁለጨለጨ፡፡ አሣ አጥማጁ ከት ብሎ እየሳቀ፤ “ለሚቀጥሉት ሰባት መቶ አመታት ማን እንዲሚያወጣህ አያለሁ” እያለ ሳጥኑ ውስጥ ከቶት፣ ቁልቁል ግብአት ባህሩን ፈፀመለት፡፡

Read 3788 times