Saturday, 28 December 2019 13:38

ዐቢይ አህመድ - የኛው ዘመን ሊንከን!

Written by  ደረጀ በላይነህ
Rate this item
(2 votes)

  አብረሃም ሊንከን፤ በዘመኑ ብቻ ሳይሆን በዘመናችንም ከአሜሪካ ፕሬዚዳንቶች ሁሉ ከፍ ያለ ቦታ ያሰጠው የተለየ ማንነቱ ነበር:: ከልጅነቱ ጀምሮ የነበረው መልካም ጠባይ፣ ለሀቅ መቆም፣ ለሰዎች መራራት፣ ሰዎችን ማገዝ እንዲሁም በሥልጣን ዘመኑም ወደ ሕዝቡ ሕይወት ቀረብ ብሎ መኖሩ ነው፡፡
የገበሬ ልጅ የነበረው ሊንከን፤ ቤተሰቦቹ በግብርናው ሥራ እንኳን አልተሳካላቸውም፤ ስለዚህ ባብዛኛው ህይወቱን ያሸነፈው ገና ከልጅነቱ ጀምሮ ከኑሮ ጋር ግብግብ በመፍጠር ነው፡፡ የጉልበት ሥራ ሠርቷል፣ በጣውላ መሰንጠቂያ (Sow mill)  ተቀጥሯል፡፡ ከዚያ በኋላ ራሱን አስተምሮ ጠበቃ ሆኗል፡፡ ከዚያም በኋላ በጥረቱ የታላቋ ሀገር ፕሬዚዳንት ለመሆን በቅቷል፡፡
ሊንከን ህይወቱ ሲታይ ባለ ጥሩ ዕድል አይመስልም፤ ባብዛኛው በመከራ እሳት ውስጥ ያለፈና የነጠረ ወርቅ ነው፡፡ ከሁሉ የሚያሳዝነው ነው ደግሞ የሥልጣን ዘመኑ በታላቅ ነውጥና ጦርነት ውስጥ ያለፈ መሆኑ ነው፡፡ ይሁን እንጂ ሊንከን፣ ሁሉንም በትዕግሥትና በፍቅር አሳልፎ፣ አሜሪካንን ከመፈራረስ አድኗታል፡፡ ምናልባት በዚያ ጦርነት ውስጥ ሀገሪቱን የመራው ሌላ ሰው ቢሆን ኖሮ፣ ዛሬ አሜሪካ የተበታተነች ደካማ ሀገር ትሆን ነበር፡፡
በጦርነቱ ጊዜ ለሚደርስበተ ነቀፋና ትችት ጆሮውን ሳይሰጥ፣ በጽናትና በታማኝነት መቆሙ፣ ጀነራሎቹን በቅርብ መከታተሉና ማበረታታቱ፣ በተለይም በጦር አዛዥ በጄኔራል ግራንት ላይ የሚቀርበውን ትችት እየሰማ እንዳልሰማ በማለፉና በጩኸት ባለመናወጡ፣ አሜሪካን አሜሪካ አድርጓታል፡፡
ከጦርነቱ በኋላም ድሆችን ቀርቦ በማናገር፣ ለመበቃቀል የተዘጋጀውን ወገን በፍቅር በማርገብ፣ ይታወሳል፡፡ ከማህበረሰቡ ጋር ባለው ቀረቤታ፣ በጦርነቱ ልጆቻቸውን በሞት ለተነጠቁ እናቶች በግል ደብዳቤ በመፃፍ፣ የገፉትን በማቀፍ፣ የጠሉትን ይቅር በማለት አስደናቂ ማንነቱን ያሳየ ጀግና ነው -ሊንከን፡፡
በአኗኗሩም ሲለው በእግሩ የሚሄድ፣ ባልተገመተበት ቦታ የሚገኝ፣ በሥልጣኑ የማይኩራራ፣ በቤተ መንግሥቱ የአንድ ጥቁር ወታደር ሚስት ቢሮው አስገብቶ እንደ ጓደኛ በማውራት፣ ይባስ ብሎም ከቢሮው ወጥቶ በመሸኘት… ያልተለመደ መልካምነት ያሳየ ነበር:: ሊንከን “ጠላቶቼን ወዳጆቼ አደርጋቸዋለሁ” የሚል መርህ የነበረው መሪ ነው፡፡ በዚያ መርሁም እስታንተንን በፍቅር እንዴት አድርጐ ለሀገሩ ጥቅም እንዳዋላቸው ማየት ብቻ ይበቃል፡፡
እኔም የዚህ ጽሑፍ አቅራቢ፤ ይህንን ፕሬዚዳንት በዓለም ላይ በታሪክ ከማውቃቸው ሰዎች ሁሉ ይልቅ እወደዋለሁ፤ አከብረዋለሁ፡፡ ይህንን የፈጠረብኝ ደግሞ የሰራው ሥራ ነው፡፡ ለዚህም ምስክር የሚሆኑ ሰዎች አሉ፡፡ ለምሣሌ፡- ማርቲን ሉተር ኪንግ ስለ ፍቅርና ይቅርታ በፃፈው መፅሐፍ፤ አብረሃም ሊንከን በዓለማችን ላይ ካሉ ስድስት ታላላቅ ሰዎች አንዱ ነው ይለዋል፡፡ ስለ አሜሪካው ዋይት ሀውስ በተፃፈው መጽሐፍ ውስጥ እንዳነበብኩት ደግሞ ብዙ ፕሬዚዳንቶችና ሚስቶቻቸው ዋይት ሃውስን የሚናፍቁት፣ ያ መልካም ፕሬዚዳንታቸው ያሳለፈበት ቦታ ውስጥ ለማሳለፍ፣ ፍቅር ትዝታቸውን ለመቆስቆስ ነው፡፡
እኔም ሊንከንን ማንበብ፣ ሊንከን ማሰብ እወድዳለሁ፡፡ ስለዚህም በአንድ የግጥም መጽሐፌ፣ ሊንከንን አሥቤ ስንኞች ቋጥሬያለሁ:: በሬዲዮ ፋና ላይ የህይወቱን የመጨረሻ ቀን የሚያሳይና የሜሪ ቶድን ፍቅርና ፈተና የተመለከተ የሬዲዮ ድራማ ጽፌ አቅርቤያለሁ:: ከዚያ በተረፈ በተለያዩ ጋዜጦችና መጽሔቶች መጣጥፎችን እንድጽፍ ግድ ብሎኛል፡፡
ዛሬ ግን ወደ ሊንከን ህይወት የገባሁት፣ የኛውን ጠቅላይ ሚኒስትር አሥቤ ነው:: እኒህ ሰውዬ በተለይ ከልጅነታቸው ጀምሮ ህይወታቸውና ገጠመኛቸው ይመሳሰልብኛል፡፡
እኒህ ሰውዬ በራሳቸወ ጥረት፣ ባረገዙትና በፀነሱት ህልም ብርታት ራሳቸውን ያስተማሩ ናቸው፡፡ እንደ ሊንከንም ከገበሬ ቤተሰብ ነው የወጡት፡፡
እርህራሄያቸው ከሊንከን ጋር ያመሳስላቸዋል:: ሊንከን በጥብቅና ያገለገላቸው ሰዎች፣ የህይወት ታሪካቸውን ሲነግሩት፣ ገንዘቡን እስካለመቀበል ድረስ የሚሄድ፤ በዚህም ከሚስቱ ጋር ግጭት የሚገጥመው ሰው ነበር፡፡ ታማኝ ስለሆነም በወጣትነቱ የሰው ገንዘብ ለመመለስ ረዥም መንገድ በእግሩ ተጉዟል፡፡
ዶክተር ዐቢይ አህመድም፤ ልጅነታቸው ላይ ያየሁት ቀለም ይሄ ነው፡፡ ለድሆች ያዝናሉ፣ ለድሆች ይራራሉ፤ ስለ ድሆች ይጠይቃሉ፡፡ ስለዚሁ ጉዳይ መጀመሪያ ወደ ትግሉ ሲቀላቀሉ፣ የብርጌድ አዛዥ ሆነው የመጡት ኮማንደር ግዲ አብዱ ብዙ ይመሠክራሉ፡፡ “ለሰው ልጆች የነበረው ርህራሄና ቀና አመለካከት በጣም ይገርማል፣ ድሆችን፣ ችግረኞችን ሲያይ ወዲያው ፊቱ ይቀያየራል፡፡ የሚገርም ልጅ ነበር” ይላሉ:: በወታደራዊው ዓለም የነበሩት ጓደኞቻቸውም ይህንኑ ሃሳብ ይደግሙታል፡፡ በራሱ ተራ፣ የነርሱን ሥራ ሸፍኖ እነርሱ ከተማ እንዲሄዱ ይፈቅድላቸው ነበር፡፡ እንደ አለቃ ሳይሆን እንደ ጓደኛ ነበርን ይላሉ፡፡
ሊንከን ህይወቱ እንዲህ ነበር፡፡ ፕሬዚዳንት ከሆነ በኋላም አንድ ቢሮ አብረው ይሰሩ የነበረ ጠበቃ ጓደኛው ጋር ሄዶ፣ “ሥልጣኔን እርሳው፣ እንደ ቀድሞው እንጫወት” ብሎ ቀለል ባለ መንገድ ቀርቦታል፡፡
በዚህ ደግሞ የኛው ጠቅላይ ሚኒስትር የሚብሱ ይመስለኛል፡፡ ከተለያዩ ሀገራት እሥር ቤት የተፈቱ ወጣቶችን አቅፈው ፎቶግራፍ የሚነሱ፣ ከከተማም ሲወጡ ሀገሬውን ሁሉ ካልጨበጥኩ ብለው እጃቸውን የሚዘረጉ ናቸው፡፡
በኢትዮጵያ ታሪክ ባልተለመደ ሁኔታ ለህዝብ ራሳቸውን ቅርብ ያደረጉና ቀና መንፈስ ያላቸው ሲሆኑ ከሃይል ይልቅ በፍቅር የሚያምኑ ናቸው፡፡ ከጦርነት ይልቅ በእርቅ፣ ከበቀል ይልቅ በይቅርታ ማሸነፍ የሚፈልጉ መሆናቸውን ባለፉት ሁለት ዓመታት አሳይተውናል፡፡
እንደ አጋጣሚ ሆኖ የሥልጣን ዘመናቸው የሊንከን ዐይነት ነው፡፡ ሀገሪቱ ለሃያ ሰባት ዓመታት ጥላቻና መለያየት የተዘራባትና በተከፋፈሉ ልቦች የታነቀች ስለነበረች ይህቺን የተበታተነች ሀገር በአንድነት መም ውስጥ ማስኬድ ቀላል አይደለም፡፡ አንዱን ወገን የሚያስደስተው ሌላውን ሲያስከፋው፣ ሁሉም ወደየ ራሱ ሃሳብና ምኞት ሲጐትታቸው የከፈሉት ዋጋ  በእጅጉ የሚያሳዝንና ግራ የሚያጋባ ነው፡፡ ይሁንና ሰውየው በታጠቁት የፍቅር አቅም፣ ያንን ሁሉ ጥላቻና ክፋት በትዕግስት አሳልፈዋል፡፡
የቀደሙትና ዐይን አውጣዎቹ የወያኔ መሪዎች፤ ከሀገሪቷ ገፍፈው ባጨቁት ገንዘብና በሎሌዎቻቸው እየተጠቀሙ በየሥፍራው የለኮሱትን እሣት በተመሳሳይ የመበቃቀልና የመገዳደል መንገድ ሳይሆን በትዕግስትና በርጋታ ያለፉበት መንገድ የሚገርምና የሊንከንን ዘመን የሚያስታውስ ነው፡፡
ብዙ ጊዜ የግድያ ሙከራ ተደርጐባቸው እንኳን ገዳዮቻቸውን ለመግደል ጠመንጃ ባለማንሳታቸው፣ እኛ ጥቃት የማንወደው ኢትዮጵያውያን፤ ያገር ያለህ ብለን ጮኸናል፡፡ ሰውየው ግን የሚያምኑት አምላክ ያዋጣቸው ክኒን ትዕግሥቱን ሰጥቷቸው፣ ይኸው እዚህ ደርሰዋል፡፡ ብዙ ሀገሪቱ ያበቃላት የመሠሉባቸው ቀናትን አሳልፈናል፡፡ የሀገሪቱ ወታደራዊ ኤታማዦር ሹም፣ የአማራ ክልል ፕሬዚዳንትና ሌሎችም ባለሥልጣናት ተገድለው ሀገሪቱ ደም የለበሰችበትንና መገናኛ ብዙሃን በሬሣ ሣጥኖች ቀለም የታዩበትን ጊዜም እናስታውሳለን፡፡
አጋጣሚውን ለመጠቀም የሞከሩ የሥልጣን ጥመኛ ቡድኖች፣ ከየጐጡ ብቅ እያሉ በለውጡና በመሪው ላይ ምላሳቸውን ሲያወጡ “ምላሳችሁ ይቆረጣል!” ብለው አልዛቱም፤ ይልቅስ “ኢትዮጵያ አትፈርስም!” እያሉ የተስፋ ድምጽ አሰሙ፡፡
በዚህ ጊዜ በእጅጉ በእግዚአብሔር ላይ የፀና እምነት ካላቸው ሰዎች በስተቀር ብዙዎች ተፍረክርከው ነበር፡፡ ግን ደግሞ “የኢትዮጵያ አምላክ ከወጀቡና ከማዕበሉ በላይ የሆነ ተዓምር አለው” ብለው ለፀሎት የተንበረከኩና የፀኑ ነበሩ፡፡
የሊንከን አሜሪካም ምጥ እንዲሁ ነበር፡፡ አንዳንዶቹ “የሚያድነን አምላክ ያድነናል” ሲሉ፤ ሌሎቹ በየጐጣቸው ተሠልፈው ነበር፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ ይዘው ወንጌል የሰበኩ፣ የሃዋርያው ጳውሎስን ጥቅስ ይዘው “ማንም በክርስቶስ ቢሆን አዲስ ፍጥረት ነው” ብለው ጥቅስ የጠቀሱ፣ ጠመንጃ ይዘው ወንድሞቻቸውን ለመግደል ተሠልፈዋል፡፡ ይሁንና የፍቅርና የእውነት አምላክ፣ የሙጢኝ ያሉትን ፀሎት ሰምቶ አሜሪካንን ታድጓታል፡፡
የኛው ጠቅላይ ሚኒስትር አንዳንዴ ለኦሮሞ የቆሙ፣ ድብቅ ሴራ ያላቸው፣ አንዳንዴ ደግሞ የኦሮሞን ሕዝብ ዕድል ያስነጠቁ ተደርገው ታይተዋል፡፡ በአዲስ አበባ ከተማ ጉዳይ እርሳቸውና ከንቲባ ታከለ ኡማ የገቡበት አጣብቂኝ የሚያሳዝን ነበር፡፡ የሰውን ልብ ከፈጣሪ በቀር የሚያነብበው ስለሌለ ለውጡ በብዙ ጥርጣሬና ሥጋት የተሞላ ነበር፡፡ ይሁንና ይህንንም ዶክተር ዐቢይ በትዕግስትና በእምነት አልፈውታል፡፡ ምናልባት አንዳንዶቻችን እንደምንሰጋው፤ ሰውየው “በቃኝ ሥልጣኔን ተቀበሉኝ!” ቢሉን ኖሮ ምን ይውጠን እንደነበረ አላውቅም፡፡ በእኔ እምነት ግን ይህንንም እንዳይሉ ፅናት የሚሰጣቸው፤ እኛም ተስፋችን አድርገን የምንለምነው እግዚአብሔር ነው፡፡
አሁን በቅርቡ የተፈጠረው የአቶ ለማ መገርሣ ጉዳይ ደግሞ ከሁሉም የከፋና የሚያሳዝን ነበር::
ምንም እንኳ አቶ ለማ፤ ጊዜው አይደለም ያሉት የፓርቲዎቹ ውህደት ጉዳይ እንደመለያያ ሃሳብ ቢታይም፣ ሌሎችና እኛ የማናውቃቸው ነገሮች ሊኖሩ እንደሚችሉ እንገምታለን፡፡
ቢሆንም የሁለቱን መሪዎቻችንን ጥምረት ስናይ፣ በዶክተር ዐቢይ በኩል የሚፈስሱት የፍቅር ቃላትና ምስክርነቶች ግን ሰውየው፤ እንደ ሊንከን ሰዎችን በፍቅር የመያዝ አቅምና ተፈጥሮ እንዳላቸው የሚጠቁም ነው፡፡
ለምሣሌ በአደባባይ “ቀድሞ በግልጽ አለቃዬ የነበረ፣ አሁን ደግሞ በጓድ አለቃ የሆነው ለማ መገርሣ” በማለት በእጅጉ የሚገርም ዕውቅና በመስጠት በኢትዮጵያውያን ያልተለመደ ትህትናቸውን አሳይተዋታል፡፡ አሁን በቅርቡም፣ የተሸለሙትን ሜዳሊያ በአደባባይ በአንገታቸው በማጥለቅ፣ “የድህነት ጓደኛዬ” ብለው፣ ውለታ ያለመርሣታቸውንና ቅንነታቸውን አስመስክረዋል፡፡
አሁንም ፀቡ ተፈጠረ፣ በተባለበት ጊዜ አንዳች ክፉ ቃል ከአፋቸው አልወጣም፡፡ ብዙ የሀገሬ ሰዎች ቸኩለው ለመሳደብ አፋቸውን ሲያላቅቁ፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ግን በዚያው በፍቅር መንገዳቸው ቀጥለዋል፡፡ ዛሬም “ድራማ ተሠራብን!” የሚሉ ሰነፎች፣ “እንዴት አንድ ባለሥልጣን ድራማ ለመሥራት ብሎ ታሪኩን ያጠለሻል?” ብለው እንኳ ማሰብ እንዳቃታቸው እያሰብኩ፣ እኔ ሲነድደኝ ሰውየው እየሳቁ መንገዳቸው ይጠበጥባሉ፡፡ በዚህ ሁሉ ነውጥ ውስጥ ሥራቸውን ይሠራሉ፡፡ የጀመሯቸውን ፕሮጀክቶች ይቀጥላሉ፡፡ አብረሃም ሊንከንም በአሜሪካ ታሪክ የሠራው ይህንኑ ነበር፡፡ እስከዛሬ ድረስ ታሪኩ የደመቀውና የጣፈጠው ለዚህ ነው፡፡ የእኛ ጠቅላይ ሚኒስትርም የእኛ ሊንከን ሆነው በታሪካችንና በትውልድ ሁሉ ፊት እንደ ህያው ጀግና የሚወሩ እንደሚሆኑ ጥርጥር የለኝም፡፡ ውሾቹ እየጮኹ ግመሎቹ ጉዟቸውን ይቀጥላሉ ያሉት ዐረቦች አይደሉ? እኔም እንደዚያው እላለሁ፡፡ ኢትዮጵያ አትፈርስም፣ የለውጡ ግስጋሴ አይቆምም፡፡ ማንም የኢትዮጵያን ጉዞ አያቆመውም፤ አንድነቱን አይበትነውም፤ የሚጠብቀን አይተኛም፤ አያንቀላፋም፡፡    

Read 1764 times