Saturday, 28 December 2019 13:23

‹‹አገራችን መስቀለኛውን መንገድ ተሻግራለች››

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(1 Vote)

   መንግስት ለጥላቻ ንግግር ብዙ ትዕግስት አሳይቷል

         ለውጡን ተከትሎ አፋኝ የሚባሉ ህጎች ማሻሻያ ተደርጎባቸዋል፡፡ አዳዲስ ህጎችም እየወጡ ነው፡፡ ከሰሞኑ በአዲሱ የፀረ ጥላቻና ሐሰተኛ መረጃ ረቂቅ ህግ ላይ ትችቶች ተሰንዝረዋል፡፡ የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሴ፣ በህግ ሪፎርሙ ላይ በከፊል የተሳተፉትንና በትኩረት የሚከታተሉትን የህግ ባለሙያ አቶ ወንድሜ ኢብሳን አነጋግሯቸዋል፡፡


              ከለውጡ ወዲህ የተለያዩ የቀድሞ ሕጎች የተሻሻሉ ሲሆን አዳዲስ ሕጎችም እየወጡ ነው፡፡ በህጐች ላይ እየተደረገ ያለውን ሪፎርም  እንዴት ያዩታል?
የቀድሞ ፀረ ሽብር አዋጅ ሲወጣ፣ ራሱ አዋጁ ሽብር ነበር፡፡ በመጨረሻ ላይ እንደውም አዋጁን ያወጡትን ራሣቸውን አሸብሯቸዋል:: በዚህ የሽብር አዋጅ የተነሣ በመላ ሀገሪቱ ከፍተኛ የሰብአዊ መብት ጥሰት ተፈጽሟል:: ሪፎርሙ ከመጣ ወዲህ ግን ይሄን ህግም ሆነ ሌሎች ህጐችን ለማሻሻል እየተደረገ ያለው ጥረት በእጅጉ ተስፋ የሚሰጥ ነው፡፡ አሁን በስልጣን ላይ ያለው ኢህአዴግ፤ ከቀድሞ ኢህአዴግ በ360 ድግሪ የተለየ ነው፡፡ አንደኛ እግዚአብሔርን የሚያወቅ መሪ ነው ድርጅቱን የተረከበው፡፡ በዶ/ር ዐቢይ የሚመራው አዲሱ የለውጥ ሃይል፤ ምድራዊ ህግን ብቻ ሳይሆን የተፈጥሮ ሃይልንና የህሊና ህግን ያከበረ ነው፡፡ ከዚህ አንፃር ለኔ በሚያከናውኗቸው ተግባራት እንድተማመንባቸው አድርጐኛል፡፡ ህግ እኮ ሰው ሰራሽ ነው፡፡ ዋናው የህሊና፣ የተፈጥሮ ህግ ነው፡፡ ጠ/ሚኒስትሩ በሹመት ንግግራቸው፤ የተፈጥሮ ህግን እንደሚያከብሩ ነው በግልጽ ያሳዩን፡፡ ይሄ በኢህአዴግ ቤት ያልተለመደ ነበር:: 30 ደቂቃ በፈጀው ንግግራቸው፣ ለ35 ጊዜያት ያህል የእምዬ ኢትዮጵያን ስም ከፍ አድርገው ጠርተዋል፡፡ ይሄ ለኔ፤ ጠ/ሚኒስትሩ ለተፈጥሮ ህግ ቀናኢ መሆናቸውን የምከራከርበት የሁልጊዜ ማስረጃዬ ነው፡፡
ሌላው ከጠቅላይ ሚኒስትሩ የመጀመሪያ ቀናት ንግግር መካከል ‹‹እኛ ነን ህዝብን ስናሸብር የቆየነው፤ ለዚህ ይቅርታ እንጠይቃለን›› ማለታቸው ህገመንግስቱን፣ የሰብአዊ መበትን፣ የተፈጥሮ ህግን ለማክበር ፍቃደኛነት እንዳላቸው መከራከሪያዬ ነው፡፡ በሌላ በኩል፤ ሰው ሠራሽ ህግንም እንደሚያከብሩ አረጋግጠውልናል:: በአጠቃላይ ይሄ አሁን በስልጣን ላይ ያለው ኢትዮጵያዊ ቡድን፤ የተፈጥሮ ህግን በሚገባ እንደሚያከብር አረጋግጧል፡፡ ይህንንም አቅመ ደካሞችን በመጐብኘትና በመደገፍ እንዲሁም መልካምና በጐ ስራዎችን በተግባር እየሠራ አሳይቶናል፡፡ በተጨማሪም በመቶ ሺህ የሚጠጉ የህሊናና ፖለቲካ እስረኞችን አስለቅቋል፡፡ ሀገራቸው እንዳይገቡ ኢ-ሠብአዊ እገዳ ተጥሎባቸው የነበሩት ዜጎችን ወደ ሀገር ቤት እንዲመለሱ አድርጓል፡፡ እነዚህ ድርጊቶች ሁሉ በስልጣን ላይ ያለው መንግስት፤ ለተፈጥሮ ህግ ቀናኢ መሆኑን ያመላክተኛል፡፡ ስለዚህ ይሄ መንግስት የሚያወጣቸውንና የሚያዘጋጃቸውን ህጐች፤ በቀናነትና በሆደ ሰፊነት ነው የምመለከታቸው፡፡
በተለየ ባለፉት 10 አመታት ለበርካታ ፖለቲከኞች፣ ጋዜጠኞችና ግለሰቦች እስርና እንግልት፣ ለኢ-ሠብአዊ ድርጊቶች መፈፀም ምክንያት የሆነው የፀረ ሽብር ህግ ማሻሻያ ከዚህ በፊት ከነበረው ምን ያህል ተለውጧል?
ብዙ ነገሮች ተሻሽለዋል፡፡ ከቀናና በጐ እሣቤ የሚነሳ ነው፡፡ ዋናው ቁም ነገርም ይሄው አነሳሱ ነው፡፡ በእርግጥ በህግ ዝግጅቱ ወቅት እኔ በብዛት አልተሳተፍኩም፤ ነገር ግን ረቂቁን መጨረሻ ላይ በሚገባ አንብቤአለሁ፡፡ የተሻሻለውን ህግ እንከን የለሽ ነው ባልልም፤ ቀደም ብሎ ከነበረው ጋር የሰማይና የምድር ያህል የሚራራቅ ነው:: ቢያንስ የገዛ ዜጐቹን ክብር ስለመጠበቅ የሚጨነቅ ህግ ነው፡፡ የቀድሞው ግን ከዚህ በተቃራኒው ነበር፡፡
በነገራችን ላይ በዚህ የህግ ዝግጅት ላይ የታዘብኩት ነገር አለ፡፡ አንዳንድ ታዋቂዎች ነገር ግን አላዋቂዎች፣ አንዳንድ ዝነኞች ግን ነውረኞች በየቦታው እየገቡ፣ ከመጣው ጋር እየተገለባበጡ፣ በጥሩ ሁኔታ የተዘጋጀው የፀረ ሽብር ህግ ወደ ኋላ እንዲጓተትና ቶሎ እንዳይፀድቅ ማድረጋቸውን እረዳለሁ፡፡
የዚህ ሪፎርም አንዱ አስቸጋሪ ባህሪ፣ እንዲህ ያሉ ጐታች አካላትን በውስጡ ሰግስጐ መጓዙ ነው፡፡ ህጉ ግን በረቂቅ ደረጃ እንዳየሁት፣ በርካታ መሻሻሎችን የሚያመጣ እንደሆነ እተማመናለሁ፡፡ ይሄ ህግ ፈጥኖ ቢፀድቅና ወደ ተግባር ቢወርድ አሁን የምናየውን ቤተ እምነት ማቃጠል፣ ብሔርን ከብሔር ማጋጨት፣ ጥላቻ መቀስቀስ… የመሳሰሉትን የሚገራ ይሆን ነበር፡፡  የፀረ ሽብር ህጉ፣ ከበጐ አድራጐትና ማህበራት ህጉ… አንፃር እንዲዘገይ መደረጉ አግባብ አይደለም፡፡ ህጉ አሁን ያሉትን የቀውስና ሁከት ችግሮች ሊፈታ ይችል ነበር፡፡  እዚህ ላይ አንድ ማንሳት የምፈልገው ጉዳይ አለ፡፡ ይሄ አሁን በረቂቅ ደረጃ የተዘጋጀው የፀረ ሽብር ህግ፤ ከባህላዊ ህጐቻችን፣ ከሃይማኖት እሴቶቻችን አንፃር ተፈትሾ፣ አስፈላጊ ነገሮች ቢታከሉበት ደግሞ የበለጠ ቀናኢና ሀገር በቀል ሆኖ አስማሚ ህግ ይወጣዋል፡፡
እነዚህን የህግ ማሻሻያዎችና አዳዲስ ህጐች የማውጣት ሂደት በችኮላ፣ ያለ ጥናት የሚካሄድ ነው በማለት የሚተቹ  ወገኖች አሉ፡፡ እርስዎ በሂደቱ ላይ እንደተሳተፈ የህግ ባለሙያ ምን ይላሉ?
የፀረ ሽብር ረቂቅ ህጉ፣ የበጐ አድራጐትና ማህበራት፣ የሚዲያ ረቂቅ ህግ በሚገባ የተጠኑና ከስረ መሠረታቸው የተሻሻሉ እንዳልሆኑ ለኔም ይሰማኛል፤ ነገር ግን ያደረጉት መሻሻል የሚናቅ አይደለም፡፡ በአሁኑ ወቅት ሰፊ ነፃነት ሠፍኗል፤ መገናኛ ብዙኃን ወደ አገር ውስጥ ገብተው፣ ዛሬም የነፃነት ታጋይነታቸውን የቀጠሉበትን ሁኔታ እየተመለከትን ነው፡፡ ያሻቸውን እንደ ልብ እያብጠለጠሉ ነው፡፡ ለሰላም ፀር የሆኑ ቅስቀሳዎችን እያደረጉ ሁሉ፤ ሀሳብን በነፃነት የመግለጽ ቀናኢነትን ለማሳየት ሲባል በቸልታ እየታለፉ ነው፡፡ እነዚህ ሁሉ የመጡት መንግስት በሰጠው ተስፋ ነው፡፡ እነዚህም ሕጎች ምንም እንኳ በቂ ጥናት ያልተደረገባቸው ቢሆንም፣ ከዚህ ቀናዒ ተስፋ የሚመነጩና የሚቀዱ በመሆናቸው ሲዘጋጁም በከፋ መንገድ አለመሆኑን ለመረዳት ችያለሁ፡፡ በነገራችን ላይ ዛሬ የሚዲያ ነፃነት ወይም ሀሳብን በነፃነት የመግለጽ መብት የሚተገበርበት መንገድ በጣም መስመሩን የሳተ ነው፡፡ አንዳንድ ሚዲያዎች እኮ በሕዝብ መካከል ጥላቻን፣ መጠራጠርንና አለመተማመንን የሚዘሩ ዘገባዎች እያቀረቡ ነው። የሰው አስክሬን ሲቃጠልና ሲቆራረጥ የሚያሳዩ ሚዲያዎች አሉ። በሚዲያ የሚቀርቡ ነገሮች እኮ አንድን ጉዳይ  የሚያባብሱ መሆን የለባቸውም። ይሄ ሁሉ የሕጎቹ መሻሻል የሰጠው የተለጠጠ ተስፋና አተያይ ውጤት ነው። በጥቅሉ የፀረ ሽብር ሕጉም ሆነ የሚዲያ ሕጉ በፍጥነት ፀድቀው በስራ ላይ መዋል  ይገባቸዋል፡፡
እኔ አንዳንዶች ዛሬም ኢትዮጵያ መስቀለኛ መንገድ ላይ ነች ሲሉ አልስማማም፡፡ ከመስቀለኛው መንገድ ወደተሻለው ጎዳና ትንሽ ፈቀቅ ብለናል፡፡ መገለጫዎቹም አንደኛ፤ ፊታችንን ወደ ተፈጥሯዊ ሕጎች (እግዚአብሄር) መልሰናል፡፡ ሁለተኛ፤ የሰው ሰራሽ ሕግንም እያከበርን ነው። ሦስተኛ፤ ዜጎች ስለ አገራቸው በነፃነት እየተወያዩ ነው። በእነዚህ ምክንያቶች አገራችን ከመስቀለኛው መንገድ ተሻግራለች ባይ ነኝ። እነዚህን እየተሻሻሉና አዲስ እየወጡ ያሉ ሕጎችንም የምመለከታቸው መስቀለኛውን መንገድ አሻጋሪ አድርጌ ነው። በቀጣይ የተሻሉና የተጠኑ ሕጎች ወጥተው ሊተገበሩ ይችላሉ ብዬ አስባለሁ፡፡ እስከዚያው ግን እነዚህን አሻጋሪ ሕጎች በአግባቡ ስራ ላይ አውለን ልንጠቀምባቸው ይገባል፡፡
ሌላው ከሰሞኑ በአለማቀፍ የሰብአዊ መብት ተሟጋቾች፣ ሀሳብን የመግለጽ ነፃነትን ያፍናል በሚል የተተቸው የፀረ ጥላቻና ሀሰተኛ መረጃ ረቂቅ ሕግ ነው፡፡ እርስዎ እንደ ባለሙያ ምን አስተያየት አለዎት?
እኔ በመሰረቱ አሁን ያለውን ነገር ሁሉ በቀናነት ነው የምመለከተው፡፡ በተፈጥሮዬም ቀና ነገርን የበለጠ ለማሰብ ነው የምሞክረው፡፡ እኔ ከጨረቃ ላይ ክብሪት ጭሬ እሳት አገኛለሁ የሚል ተስፈኛ ሰው ነኝ፡፡ በዚህ የሪፎርም ቡድን የሚወጡ ሕጎችን በቀናነት እመለከታቸዋለሁ። አንድ ሰው የወጡትን ሕጎች በሙሉ በቀናነት ሳይሆን እንከን በመፈለግ የሚመለከታቸው ከሆነ፣ ከሁሉም ላይ ጉልህ እንከኖችን ማግኘቱ አይቀርም፡፡ ከዚህ አንጻር የፀረ ጥላቻና ሀሰተኛ መረጃ ሕጉ የተሟላና ሁሉንም የሚያስደስት ሊሆን አይችልም፡፡ ክፍተቶች አይኖሩትም ማለትም አይቻልም። ወሳኙ በስራ ላይ በሚውልበት ወቅት የሚኖረው አተረጓጎም ነው። ኢትዮጵያ ውስጥ የሕጎች አንዱ ችግር አተረጓጎም ነው። ስለዚህ ተርጓሚ አካላቱም በመጀመሪያ ቀናነትን ማሰብ አለባቸው፡፡ እንደዚያ ካልሆነ የትኛውንም ሕግ ጠምዝዞ ለእኩይ አላማ ማዋል ይቻላል፡፡
በአገራችን በግልፅ የጥላቻ ንግግር አለ፡፡ ይሄ በገሃድ የሚታይ ነው፡፡ ይሄ አይነቱ የጥላቻ ንግግር ደግሞ የሚጎዳው፣ መብቱን የሚጋፋው አካል አለ፡፡ ታዲያ የዚያ ሰው መብት በምን ይጠበቅ? ከዚህ አንጻር ነው ይሄን የፀረ ጥላቻ ሕግ መገንዘብ ያለብን፡፡ መንግስት ይሄን ሕግ ዜጎችን ለማጥቂያ ሊጠቀምበት ይችላል ወይ ከተባለ፣ አዎ ይችላል። ይሄን ሕግ ብቻ ሳይሆን ቀድሞ የወጣውን የወንጀለኛ መቅጫ ሕግንም በዚያ መንገድ ሊጠቀምበት ይችላል፡፡ እኔ የ‹‹መደመር›› መጽሐፍን ሳነብ፣ ጠ/ሚኒስትሩ አሉታዊ  ሰላምን ማለትም በሃይልና በጉልበት የሚመጣን ሰላም የማስፈን ፍላጎት እንደሌላቸው ተገንዝቤያለሁ፡፡ አሉታዊ ሰላምን የሚፀየፉና አዎንታዊ ሰላምን ለማምጣት የሚታገሉት መሪና ቡድናቸው፤ ይሄን ሕግ ቀናነት በጎደለው መንገድ ይተርጉሙታል ብዬ ማሰብ ይከብደኛል:: እስካሁን በማየው ሁኔታ፤ መንግስት ለጥላቻ ንግግር ሰፊ ትዕግስት አሳይቷል፡፡ ከዚህም በኋላ ይህን ቀናነት ይዞ እንደሚቀጥል ምንም ጥርጥር የለኝም፡፡
‹ሕጉ ለትርጉሞች የተጋለጠ ነው… ከዚህ አንፃር የፖለቲካ ማጥቂያ መሣሪያ ሊሆን ይችላል›› የሚሉ ወገኖች አሉ፡፡ የጠ/ሚኒስትሩን ቃል ብቻ ከመተማመን፣ ሕጉን አስተማማኝ ማድረግ አይቀልም?
ጠ/ሚኒስትሩን ወይም ቡድናቸውን እንተማመን አይደለም ያልኩት፡፡ ነገር ግን ጠ/ሚኒስትሩ በፃፉትና የለውጡ ፍኖተ ካርታ ነው በተባለው ‹‹መደመር›› መጽሐፍ ላይ በግልጽ የተፈጥሮ  ሕግን፣ ሰው ሰራሽ ሕግን፣ የወንጀል ሕግን በመንተራስ የተቀመጡ ሀሳቦችን የተመለከተ ሰው፤ እኔ ያለኝን ቀና እይታ መጋራቱ አይቀርም፡፡ ሕጎቹም ወጥተው የሚተገበሩት በዚህ ፍኖተ ካርታ ማዕቀፍ ውስጥ እንደመሆኑ፣ የጸረ ጥላቻ ንግግር አዋጁም ከዚህ ጋር የተስማማ እንደሚሆን አልጠራጠርም፡፡ ረቂቁን ስመለከተውም ያን ያህል የከፋና ለትርጉም የተጋለጠ የሕግ ክፍተት የለውም፡፡ ነገር ግን እንከን የለሽ ደግሞ አይደለም፡፡ አሁን ላይ የሕግ አተረጓጎም ማሻሻያ ለማድረግ ሰፊ ጥረት ሲደረግ እመለከታለሁ፡፡ ነገር ግን የበለጠ ወደ ታች ለመውረድና አጥጋቢ ደረጃ ለመድረስ ጊዜ እንደሚፈልግ ደግሞ እገነዘባለሁ። ከዚህ አንፃር ይሄ ሕግ የወጣው ለጥቃት ነው ብሎ አጨልሞ ማየት ተገቢ አይደለም። መንግሥት ባለፉት 27 ዓመታት የተጓዘበትን መንገድ መድገም  ቢፈልግ እኮ የፀረ ሽብር ሕጉን አለማሻሻል ይበቃዋል፡፡
የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ተቋማት ስጋት ከምን የመነጨ ነው?
ከዚህ ቀደም ኢትዮጵያ ውስጥ ከነበረው ሁኔታ አንጻር ስጋት ቢያድርባቸው የሚደንቅ አይደለም፡፡  ግን ደግሞ ያለውን ነገር ከኛ በላይ ሊገነዘቡት አይችሉም፡፡ የአሁኑ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን ኮሚሽነር ዶ/ር ዳንኤል በቀለ እኮ በአካልና በሕይወት ጭምር ለሰብአዊ መብት መረጋገጥ ዋጋ የከፈለ ሰው ነው፡፡ ይሄ ሰው ባለበት ሁኔታ የወጣው ይህ ሕግ፤ ለፖለቲካ ማጥቂያነት ቢውል ምን ሊፈጠር እንደሚችል መገመት ቀላል ነው፡፡ ዶ/ር ዳንኤል በሰብዓዊ መብት ጉዳይ ለሰከንድ የሚደራደር ሰው እንዳልሆነ የተመሰከረለት ነው፡፡ ስለዚህ  ሕጉ ወዳልተፈለገ መንገድ ሊተረጎም የሚችልበት እድል የለም ባልልም፣ እንደ ቀድሞው በዝምታ የሚመለከት አካል ግን የለም ባይ ነኝ፡፡ መንግስት ህጎችን ለፖለቲካ ማጥቂያ ሊጠቀም ይችላል ተብሎ የሚፈራው በምርጫ ወቅት ነው። በአሁን ሰዓት ምርጫውን የሚያስተዳድሩት  ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ ደግሞ በሕግና በሰብአዊ ጉዳይ ቀልድ የማያውቁ መሆናቸውን ያስመሰከሩ ናቸው፡፡ ስለዚህ ሕጉ በብዙ ቁጥጥርና አይን ስር ያለ ነው። ከዚህ አንጻር ነው እኔ ብዙም ስጋት የለኝም የምለው፡፡
ከስድስት ወራት በኋላ አገራዊ ምርጫ እንደሚካሄድ ይጠበቃል፡፡ ምርጫ ቦርድ ምርጫውን ለማስፈፀም ያለውን አቅም እንዴት ያዩታል?
አሁን ያለው የምርጫ ቦርድ ከዚህ ቀደም እንደነበረው ከገዥው ፓርቲና ከካድሬ የተውጣጣ አይደለም፡፡ የሕግ ባለሙያዎች፣ የሰብአዊ መብት ተሟጋቾች፣ የዩኒቨርሲቲ ምሁራን የተሰበሰቡበት ነው፡፡ የኢትዮጵያን የምርጫ ችግር በአግባቡ የተረዱ ሰዎች ተካተውበታል፡፡ በእነዚህ ሰዎች ላይ አለመተማመን የጤንነት አይደለም፡፡ በምርጫ ቦርድ በኩል ጥሩ ተቋማዊ ዝግጅት እንዳለ እገነዘባለሁ፡፡ እነዚህ ሰዎች ራሳቸውን በማይገባ ሂደት ውስጥ ያስገባሉ ብዬ አላስብም፡፡ በፍትህ ተቋማት ረገድም የመጨረሻ ውሳኔ ሰጪ የሆነው ፍ/ቤት የሚመራው፣ ለፍትህ ዋጋ በከፈሉና በሚከፍሉ፣ ተአማኒነት ባላቸውና ለፍትህ ቀና በሆኑ ግለሰብ ነው፡፡ ስለዚህ በተቋማት በኩል ቀሪ ነገሮች ቢኖሩም፤ እኔ ያን ያህል አያሰጋኝም:: ዋናው የሕግና የሰላም ጉዳይ ደግሞ በሕዝቡ የሚወሰን ነው የሚሆነው፡፡ በቀሪ ጊዜያትም ጥሩ የሕግ ዝግጅት ማድረግ ይቻላል፡፡ የትኛውም ምርጫ ዋጋ ያስከፍላል፤ ግን የሚከፈለውን ዋጋ በእጅጉ ለመቀነስ መረባረብ ያስፈልጋል፡፡
በምን ዓይነት መንገድ?
አንደኛ፤ ከወዲሁ የሕግ ማስከበር ልምምዶች መኖር አለባቸው፡፡ ለምሳሌ በሀገሪቱ ለሚፈጠሩ ቀውሶች፣ ሁከቶች፣ የቤተ እምነቶች መቃጠል፣ የሰው ሕይወት መጥፋት… አስተማማኝ ሕዝብ ሊያምነው፣ ሊተማመንበት የሚችል የሕግ ማስከበር መጀመር አለበት፡፡ ሰዎች ተከሰው ችሎት ሲቆሙ፣ ቅጣት ሲጣልባቸው ወዘተ አስተማሪ በሆነ መልኩ ማሳየት ያስፈልጋል፡፡ ‹‹ይሄን ያህል ተጠርጣሪዎች ታሰሩ›› ከሚለው ዜና ባለፈ እያንዳንዱ ችሎት በመገናኛ ብዙሃን ለሕዝብ ቢተላለፍ፣ ጠንካራ የሕግ ማስከበር ልምምድና መተማመን ውስጥ እንድንገባ ያደርገናል፡፡ ይሄ ለምርጫው ውጤታማነት እጅግ ጠቃሚ ነው፡፡ በአሜሪካ እኮ በአሁኑ ወቅት ፕሬዚዳንቱ እየተከሰሱ ነው፣ በእስራኤልም ጠ/ሚኒስትሩ ብዙ ክስ ይጠብቃቸዋል፡፡ እነዚህ ክሶች ከፍትህ አላማቸው ባሻገር በሚዲያ ሲቀርቡ አስተማሪነታቸው ይጎላል።
ሁለተኛ፤ የተሻሻሉ ሕጎችንና አዳዲስ ሕጎችን ወደ ተግባር የማስገባት ሂደትን ማፋጠን ይገባል:: ይሄ ሲደረግም ጥንቃቄ ሊለየውም አይገባም፡፡ ፖሊስ ከወዲሁ ሰብዓዊነት የተሞላበት ጠንካራ የሕግ ማስከበር ተግባርን መለማመድ አለበት፡፡

Read 2131 times