Tuesday, 24 December 2019 00:00

ዶናልድ ትራምፕ እንዲከሰሱ ውሳኔ ተላልፎባቸዋል

Written by 
Rate this item
(3 votes)

    የአሜሪካ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት፤ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ስልጣናቸውን ያላግባብ በመጠቀምና የምክር ቤቱን ስራ በማደናቀፍ እንዲከሰሱና ከስልጣናቸው እንዲወርዱ ባለፈው ረቡዕ በአብላጫ ድምጽ መወሰኑን ተከትሎ፣ ትራምፕ በአገሪቱ ታሪክ ሴኔት ፊት ቀርበው ክሳቸውን እንዲከላከሉ የተወሰነባቸው ሶስተኛው ፕሬዚዳንት ሆነዋል፡፡
ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ፣ የዩክሬን አቻቸው ቭላድሚር ዘለንስኪን በቀድሞው የአሜሪካ ምክትል ፕሬዚዳንትና በምርጫ ተቀናቃኛቸው ጆ ባይደን እና በልጃቸው ላይ የሙስና ምርመራ እንዲያደርጉ በመደለልና ጫና በማድረግ ስልጣንን ያለአግባብ በመጠቀም፤ እንዲሁም ከዚህ ጋር በተያያዘ ለሚደረግባቸው ምርመራ መረጃዎችን ባለመስጠትና የምክር ቤቱን ስራ በማደናቀፍ እንዲከሰሱ በቀረበባቸው የውሳኔ ሃሳብ ዙሪያ፣ ለአስር ሰዓታት ያህል ክርክር ያደረጉት የምክር ቤቱ አባላት፣ በስተመጨረሻም ፕሬዚዳንቱ  እንዲከሰሱና ሴኔት ፊት ቀርበው የቀረቡባቸውን ክሶች እንዲከላከሉ በአብላጫ ድምጽ መወሰናቸውን ሮይተርስ ዘግቧል::
ዩክሬን በቀጣዩ የአሜሪካ ምርጫ ዴሞክራቶችን ለመወከል እየተፎካከሩ ባሉት ጆ ባይደን ላይ ምርመራ እንድታደርግ ጫና ማሳደር በሚል የቀረበው ክስ፤ በ230 የኮንግረሱ አባላት ድጋፍና በ197 ተቃውሞ፣ የቀረበባቸውን ክስ ለማጣራት በተጀመረው ጥረት ምስክሮች ቃላቸውን እንዳይሰጡ በመከላከልና መረጃ በመከልከል የምክር ቤቱን ስራ ማደናቀፍ የሚለው ክስ ደግሞ በ229 ድጋፍና በ198 ተቃውሞ ሁለቱም በአብላጫ ድምጽ መወሰናቸውን ዘገባው አመልክቷል፡፡
የኮንግረሱ አባላት በአፈ ጉባኤዋ ናንሲ ፔሎሲ አነሳሽነት በቀረቡት ሁለት ክሶች ላይ የሚያደርጉትን የድምጽ ስነስርዓት ሚቺጋን ውስጥ የምረጡኝ ቅስቀሳ እያደረጉ፣ በቴሌቪዥን በቀጥታ የተከታተሉት ዶናልድ ትራምፕ፣ የቀረበባቸውን ክስ የአክራሪ ግራ ዘመሞች ነጭ ቅጥፈትና በሪፐብሊካን ላይ የተሰነዘረ ጥቃት ሲሉ እንዳጣጣሉት ተነግሯል፡፡
ሴኔቱ ከሳምንታት በኋላ በጉዳዩ ዙሪያ መክሮ ውሳኔ ያሳልፋል ተብሎ እንደሚጠበቅ የጠቆመው ዘገባው፤ ፕሬዚዳንት ትራምፕ ስልጣናቸውን የሚለቅቁት ከሴኔቱ አባላት ሁለት ሶስተኛው የድጋፍ ድምጽ ከሰጡበት ብቻ እንደሆነና ያም ሆኖ ግን  ሴኔቱ ሪፐብሊካን የሚበዙበት እንደመሆኑ በፕሬዚዳንቱ ላይ ውሳኔው የመተላለፉ ዕድል አነስተኛ እንደሆነ መነገሩን አመልክቷል፡፡
ኮንግረሱ ውሳኔውን ማስተላለፉን ቀጥሎ ዋይት ሃውስ ባወጣው መግለጫ፣ ሴኔቱ በትራምፕ ላይ የቀረበውን ክስ ውድቅ እንደሚያደርገውና በነጻ እንደሚያሰናብታቸው ሳይታለም የተፈታ ነው ማለቱን ዘገባው አክሎ ገልጧል፡፡
ዋይት ሃውስ እርግጠኛ እንደሆነውና ብዙዎች እንደገመቱት ሳይሆን ቀርቶ፣፣ ሴኔቱ ፕሬዚዳንት ትራምፕ ከስልጣን እንዲሰናበቱ ውሳኔ የሚያስተላልፍ ከሆነ፣ ምክትላቸው ማይክ ፔንስ መንበረ ስልጣኑን ተረክበው እስከ መጪው የ2021 የአሜሪካ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ፤ አገሪቱን ማስተዳደር እንደሚቀጥሉ ተነግሯል፡፡
በአሜሪካ ፕሬዚዳንቶች ታሪክ በመሰል የኮንግረስ ውሳኔ ሴነት ፊት ቀርበው ክስ እንዲመሰረትባቸው የተወሰነባቸው ሁለት የአገሪቱ መሪዎች አንድሪው ጆንሰንና ቢል ክሊንተን እንደነበሩ ያስታወሰው ዘገባው፣ ያም ሆኖ ግን ሁለቱም ከስልጣን እንዲለቅቁ እንዳልተወሰነባቸው አክሎ ገልጧል፡፡



Read 8588 times